>

ፖለቲካችንን ከዘውገኝነት ነፃ ማውጣት ካልቻልን ፤ ”እኔ ከሌሎች የተለየሁና የተሻልኩ ነኝ“ መባባሉ የሕዝብና የአገር መጥፊያ ሊሆን ይችላል! (ዶር ታደሰ ብሩ ከርሴሞ)

ፖለቲካችንን ከዘውገኝነት ነፃ ማውጣት ካልቻልን ፤ ”እኔ ከሌሎች የተለየሁና የተሻልኩ ነኝ“ መባባሉ የሕዝብና የአገር መጥፊያ ሊሆን ይችላል …!!!

በዶር ታደሰ ብሩ ከርሴሞ

 

* ትናንሽ ልዩነቶችን ማጉላት እና የዘውግ ፓለቲካ 

የስነልቦና ተመራማሪው ስግመንድ ፍሬይድ “ትናንሽ ልዩነቶንች” በማጉላት ”እኔ ከሌሎች የተለየሁና የተሻልኩ ነኝ“ ማለት እና እነዚህ ትናንሽ ልዩነቶችን በመለጠጥ ቅራኔ ውስጥ መግባት Narcissism of Minor Differences ብሎ ጠራው።
Narcissus (ናርሲሰስ) ከራሱ ጋር ፍቅር የያዘው፤ ስለ ራሱ ያለው የተጋነነ እምነት መጥፊያው የሆነ የግሪክ አፈታሪክ ገፀ-ባህሪይ ነው። ናርሲሰስ ሌሎች ሰዎችና አማልዕክት እሱን የመውደድ ግዴታ ያለባቸው ይመስለው ስለነበር ለፍቅር እንኳን ያልተመቸ ገፀ-ባህርይ ነው።  በዚህ የአፈታሪክ ገፀ-ባህሪ መነሻነት ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ናርስሲዝም (narcissism) ተባለ።
Narcissism of Minor (Small) Differences ጎልቶ ከሚታይባቸው ቦታዎች ቀዳሚው የዘውግ (ethinic) ፓለቲካ ነው። የዘውግ ፓለቲከኛ የራሱን ዘውግ ከሌላው የሚለየውን ድንበር ለማበጀት፤ የሱ ዘውግ አባላት ከሌሎች የተሻሉ አስተዋይ፣ ቻይ፣ ታታሪ፣ ጀግና፣ ሩህሩህ ሆኖም ያለአግባብ እየተጠቁ ያለ ተበዳዮች አድርጎ ለማቅረብ Narcissism of Minor Differences ይጠቀማል። ጥቂት ምሳሌዎችን ላንሳ
1. ሁቱና ቲትሲዎች አንድ ቋንቋ ይናገራሉ፤ ሁለቱም ክርስቲያኖች ናቸው። ለዘመናት ሲጋቡ ስለኖሩ የክልሶች ቁጥር ቀላል አይደለም።  በቁመትና በቆዳ ፍካታቸው ያለውን ትንሽ ልዩነት በመጠቀም አንድ ሩዋንዳዊ  ሁቱ ይሁን ቱትሲ መሆኑ መገመት ቢቻልም መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እርግጠኛ ለመሆን ብሔር የሚገልጽ ማስረጃ ያስፈልጋል ወይም ራሱን መጠየቅ ይገባል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል የዚህንም ያህል መቀራረብ ቢኖርም  እአአ በ1994 በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ 800 000 ሰዎችን የፈጀ እልቂት ተፈጽሟል፤ ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ  እስከ 2003 ድረስ በጠቅላላው 5 ሚሊዮን ያህል ሰው ሕይወቱን አጥቷል።
2. በቆጵሮስ  (Cyprus) ደሴት  ውስጥ በሚኖሩ የግሪክ-ቆጽሮሳዊያን እና የቱርክ-ቆጽሮሳዊያን መካከል ያለው መመሳሰል የገረመው የቅራኔዎች ተመራማሪ የደሴቲቱ ነዋሪ የሆነ ረዳቱን “በምንድነው ማን ከየትኛው ወገን እንደሆነ የምትለዩት?” ብሎ ይጠይቀዋል። “ወንድሜ ብዙ ዓመት ስንፋጅ ስለቆየን እንተዋወቃለን፤ አንድ ቆጵሮሳዊ ሲጋራ ሲለኩስ በሚያጨሰው ሲጋራ የማን ወገን እንደሆነ ይታወቃል” አለው።
3. ሰርቦች፣ ኮራቶች እና ቦስኒያዎች አንድ ቋንቋ ይናገራሉ። በአለባበሳቸው፣ በሙዚቃዎቻቸው፣  በባህል ምግቦቻቸው ጉልህ ልዩነት የለም። በ200 ዓመታት በፊት የነበሩ ቅም አያቶቻቸው በሀይማኖትም ይሁን በባህል ተለያይተው ነበር ይሆናል። በዩጎስላቪያ ጊዜ ለነበሩ ወጣቶች ልዩነቶቹ ከታሪክ ያለፈ ትርጉም አልነበራቸውም። ቀዝቃዛው ጦርነት ሲያበቃ ግን እነዚያ ሊረሱ የደረሱ ልዩነቶ ገዝፈው ለእልቂትና ለዩጎዝላቪያ መበታተን ምክንያት ሆኑ። ሚካኤል ኢግናቴቭ (Michael Ignatieff) አንድ ሰርብ  የነገሩትን በጽሁፉ አስቀምጧል “ኮራቶች ከኛ የተሻሉ ይመስላቸዋል፤ ራሳቸውን ምርጥ አውሮፓውያን አድርገው ይመለከታሉ።  ግን አንድ ነገር ልንገርህ፣ ሁላችንም የባልካን … ነን”
4. ሶማሊያ ከአፍሪቃ አገሮች ሁሉ በብዙ ነገሮች የታደለች ናት። 3,333 ኪሜትሮች የባህር ጠረፍ አላት፤ ይህ በአህጉሩ ትልቁ የአንድ አገር የባህር ጠረፍ ነው። የባህር ክልሏ፤ በማዕድንና በአሳ ሀብት የበለፀገ ነው። ዜግነት (citizenship)  እና ዘውግ (ethnicity) አንድ የሆነበት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ሶማሊያ ናት። መቶ በመቶ ማለት በሚቻል ሁኔታ ሁሉም የሶማሊያ ዜጋ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው። ለጠብ ምክንያት የሌላት አፍሪካዊት አገር ማናት ተብለን ብንጠየቅ በጭንቅላታችን መምጣት ያለባት አገር ሶማሊያ ነች። ምድር ላይ ያለው ሀቅ ግን ሁላችንም የምናውቀው ነው።  ለምን ይህ ሊሆን ቻለ? መልሱ Narcissism of Minor Differences ነው። የሶማሊያ ልሂቃን የጎሳ ልዩነትን በመጠን በላይ አግዝፈው ለእልቂት የሚያበቃ ምክንያት አደረጉት። አንድን ሶማሊን በማየት ብቻ ጎሳውን ማወቅ አይቻልም፤ ራሱን መጠየቅ ያስፈልጋል። ታድያ የሞት አደጋ የሚያስከትልበት ቢሆን እንኳን አብዛኛው ሶማሊ ጎሳውን አይደብቅም። ለምን ይህ ሆነ? መልሱ አሁን Narcissism of Minor Differences ነው። በብዙ አገሮች ትርጉም የማይሰጠው ጎሳ ሶማሊያ ውስጥ እጅግ … እጅግ  ወሳኝ ነገር ተደረገ።
ለኔ የንባቦቼ ሁሉ ማጠንጠኛዬ ኢትዮጵያዬ ነች። የኢትዮጵያ “ሶሻሊስት መንግሥት” ከኤርትራና ትግራይ አማጺያን ጋር ባደረገው ውጊያ የተሳተፈ በጊዜው የሶብየት ኅብረት ወታደራዊ መኮንን የነበረ ዩክሬናዊ በኢትዮጵያ ቆይታው ስለነበረው ጥሩም መጥፎም ትዝታዎች አውርቶኛል። ከመጥፎ ትዝታዎቹ ዋነኛው ጠላትንና ወዳጅን መለየት በማይችልበት ውጊያ መሳተፉ ነው። “በምንም የማይለዩ ሰዎች እርስ በርስ ሲዋጉ አንዱን ወገን ረድቶ የጠቡ አካል መሆን ያሳፍራል፣ ያሳምማል።  …  ለእኛ የሚሊተሪ ዩኒፎርም የለበሰ እትዮጵያዊ ወዳጅ፤ ቁምጣ የለበሰና ጎፈሬያም ኢትዮጵያዊ ደግሞ ጠላት ነበር፤ ይህ ሁሌ ያሳፍረኛል” ነበር ያለኝ።  ይህን ከነገረኝ ጥቂት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ገጥሞት የሰቀጠጠው የወንድማማቾች ጦርነት እሱም አገር ተከሰተ። እኔ ደግሞ ዛሬ ያለበት ሁኔታ እሱ በነበረት ወቅት ከነበረው ሁኔታ ጋር እያወዳደርኩ ሊመጣ የሚችለው አደጋ ያስፈራኛል።
ዛሬ ትናንሽ ልዩነቶችን በማስፋት ሥራ ላይ የተጠመዱ ብዙ ሰዎች አሉን።  በአሮሞ፣ በአማራ፣ በትግሬ፣ በጉራጌ … መካከል ስላሉ ልዩነቶች  አግዝፈው  የሚናገሩና የሚጽፉ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እነሱ የኔ የሚሉት ወገን ምርጥነት የሚነግሩን “ምሁራን” መብዛታቸው  እጅግ ያሳስበኛል።
በአሮሞ ውስጥ በሜጫ፣ በቱለማ፣ በጉጂ፣ በቦረና፣ ፣ በከረዩ ..  በአማራ ውስጥ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ   …..  በጉራጌ ውስጥ በቸሀ፣ በቀቤና፣ በመስቃን፣ በማረቆ … መካከል ስላሉ ልዩነቶች  አግዝፈው  የሚናገሩ ሰዎች መብዛት  እጅግ ያሳስበኛል።  ደቡብ ክልል “በክላስተር” “መጠርነፍ”  Narcissism of Minor Differences ያባብሳል የሚል ስጋት አለኝ።  የዘውግ ፓለቲካን ከ Narcissism of Minor Differences መለየት ከባድ ነው። ፓለቲካችንን ከዘውግ ፓለቲካነት ነፃ ማውጣት ካልቻልን Narcissism of Minor Differences የብዙ ሕዝብና የአገር መጥፊያ ሊሆን ይችላል።
ማጣቀሻዎች 
Blok, Anton (1998) The Narcissism of Minor Differences. European Journal of Social Theory 1 (1):33-56
Brubaker, Rogers (2004) Ethnicity Without Groups. Cambridge, Mass.: Harvard University Press
Ignatieff, Michael (1999) ’Nationalism and the narcissism of minor differences’ in Ronald Beiner, ed,. Theorizing Nationalism. State University of New York Press: 99-102
Freud, Sigmund (1917) The Taboo of Virginity. Standard Edition, Hogarth Press, London 1953: 11: 191:208
Freud, Sigmund (1921) Group psychology and the analysis of the ego. Standard Edition, 18 Hogarth Press, London 1953: 18:67-144
Freud, Sigmund (1930) Civilization and its Discontents. Standard Edition, Hogarth Press, London 1953: 21: 191-208
Volkan, Vamik D. (1986) The Narcissism of Minor Differences in the Psychological Gap Between Opposing Nations. Psychoanalytic Inquiry, 6:175-191
Filed in: Amharic