>
5:13 pm - Thursday April 19, 0525

ግልፅ ደብዳቤ ለ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር (ሙክታሮቪች) 

ግልፅ ደብዳቤ ለ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር

 

(ሙክታሮቪች) 

ይድረስ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር
ውድ አምባሳደር እንደምን ከርመዋል። እኔ አልሃምዱሊላህ ደህና ነኝ።
ትናንትና የግብፁ አልሲሲ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርን ክቡር ራማፖሳ ስለአባይ ግድብ አንስተውላቸው፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳትፈርም ውሃ በግድቡ መያዝ እንዳትጀምር ጫና እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ሰማሁና ይህን ደብዳቤ ልፅፍሎት ተነሳሳሁ።
ውድ አምባሳደር
ለግብፅ የዲፕሎማሲ ወከባ ብዙም ሳይጨነቁ የሚከተለውን ቢያደርጉ ለኢትዮጵያ ሀገረዎ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ተግባር እንደፈፀሙ ይቆጠራል።
እሱም፣
ለፕሬዝዳንት ራማፖሳ እነዚህን ሁለት ፎቶዎች በፍሬም አሰርተው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ሰውታ እንዴት ለደቡብ አፍሪካ ትግል በወሳኝ ጊዜ ለኔልሰን ማንዴላ ስልጠና በመስጠት እንደቆመች በደብዳቤ ሊያስታውሷቸው ይገባል።
በተለይም ማንም የአለም ሀገራት የደቡብ አፍሪካን ጭቆና ችላ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ ፓስፖርት አዘጋጅታ፣ የትጥቅ ስልጠና ሰጥታ የደቡብ አፍሪካን ትግል ስታግዝ እንደነበረ የኔልሰን ማንዴላን መፅሃፍ አጣቅሰው የሀገራችንን ውለታ በሚገባ አጉልተው ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ውለታ እንዳለባት ሊያሳስቧቸው ይገባል።
 እንዲሁም ኢትዮጵያ ሀገራችን የአፍሪካ ሀገሮችን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ የታገለችውን ትግል በማስታወስ ዛሬ ራማፖሳ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የአፍሪካ ህብረት ጃንሆይ የመሰረቱት ድርጅት መሆኑን አስገንዘበው፣ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስርዓት እንድትላቀቅ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ታሪክን አጣቅሰው በመተንተን የኢትዮጵያን ባለውለታነት በአፅኖት አስረግጠው መንገር ይኖርቦታል።
ውድ አምባሳደር
 የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ ባልፈረመችበት በቅኝ ግዛት ዘመን ውል ተገድዳ በሀብቷ ከደህነት እንዳትላቀቅ የሚደረግባትን ጫና በዝምታም ሆነ በምናገባኝ ዳተኝነት ከግብፅ ወገን አብረው ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፅሙ የሚያሳስብ አሳማኝ ደብዳቤ ሊፅፉላቸው ይገባል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ አገዛዝ ምን ያህል እንደተጎዱ በማስታወስ፣ የቅኝ ግዛትን መጥፎ ትዝታ ግብፅ እየቀሰቀሰች እንደሆነ በማስረዳት፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ስትቆም እና ብሄራዊ ጥቅሟን መስዋዕት በማድረግ ለአፍሪካ ነፃነት እንደሞገተችው ሁሉ፣ የአፍሪካ ሀገራትም በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ታሪካዊ ሀላፊነት ራማፖሳ ስላለባቸው ይህን ሀላፊነት እንዲወጡ ሊያሳሱባቸው ይገባል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ግድቧን ከሞሙላት ማንም ምድራዊ ሀይል የማያግዳት በመሆኑ ግድቡ ሲጠናቀቅ በወዳጅነት ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙ ሀገራትን ኢትዮጵያ በፍፁም የማትረሳ መሆኑን በአፅኖት በመግለፅ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ የዋለችው ውለታ ዛሬ ራማፖሳ እንደማይረሱት እና በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በምትፈልጋቸው ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ልትነግሯቸው ይገባል።
ውድ አምባሳደር
የሀገራችን አምባሳደሮች ለየተወከሉበት ሀገራት ስለግድቡ በከፍተኛ ደረጃ ሽንጣቸውን ገትረው መከራከር ቀዳሚ ተግባራቸው በመሆኑ እርስዎ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በዚህ ቀዳሚ ሚናዎን መጫወት ይኖርበታል እላለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።
ከሰላምታ ጋር
ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ
የማይነበብ ፊርማ
ግልባጭ
ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት
ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ለኢትዮጵያ ሕዝብ
Filed in: Amharic