>

አሁንም ቢሆን ያልጠሩ ነገሮች አሉ!  (የሕግ ባለሙያ ሞገስ ዘውዱ)

አሁንም ቢሆን ያልጠሩ ነገሮች አሉ! 

የሕግ ባለሙያ ሞገስ ዘውዱ

ኢትዮጵያ፣ ግብፅናሱዳን ለጊዜዉ የዉሀ ሙሌቱ እንዲቆም መስማማታቸዉን ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለምን እዚህ ዉሳኔ ላይ እንደደረሰ ለህዝቡ ማብራሪያ መስጠት ይጠበቅበታል።
ምክንያቱም በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በተደራዳሪዎች በኩል ሲነገር የነበረዉ ከዚህ ዉሳኔ በተቃራኒ ነዉ። በተለይ በዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ ሲሰጥ የነበረዉ መግለጫ ኢትዮጵያ የምትፈልገዉን ለማድረግ ፍንክች እንደማትል ነበር።
ለህዝቡ ሲነገር የነበረዉ የጡዘት ሰበካ አሁን ከተወሰነዉ ዉሳኔ ጋር የሚቃረን ነዉ። ተደራዳሪዎቹ ለጊዜዉም ቢሆን ለምን ለማዘግየት እንደተስማሙ ለህዝቡ ሰፊና አሳማኝ ገለፃ ካላደረጉ ሌላ አንድምታ ይዞ ይመጣል።
የግብፅን የሚዲያ ዘመቻና ፕሮፓጋንዳ ሊመጥን የሚችል የተደራጀና የሚገዳደራቸዉ ዘመቻ (Counter Propaganda) በእኛ በኩል አለመደረጉ ያሳዝናል። ግብፆች  የዉሀ ሙሌቱን ለጊዜዉ የማሸጋገርን ዉሳኔ ልክ እንደ ዘላቂ ድል አድርገዉ እየነዙት ነዉ።
፩: ሲጀመር ኢትዮጵያ ግድቡን ከ2 ሳምንታት በፊት የመሙላት እቅድ የላትም። ስለዚህ ግድቡን ለመሙላት ከታቀደው ቀን በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ መሞከር መጀሪያውን ክፍት ነበር አሁን ምንም እንደ አዲስ የሚወራ ጉዳይ አይደለም፣
፪: እድሜ ልኳን ስትጓተትና ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍቃደኛ ያልሆነኝ ግብጽ በምን ተአምር ነው አሁን በአጭር ግዜ ውስጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሙከራ የሚደረገው? የማንስ ጫና ከጀርባ አለ? ፪ ሳምንት reasonable period ነው ወይ? ስምምነት ቢደረግ እንኳን ሲሮጡ የታጠቁት ዓይነት ነገር ነው የሚሆነው።
፫: በግብጽ የፖለቲካ ባህርይ (state nature) እና የለየለት ስግብግብነት አንጻር ሲታይ እሷን የበለጠ የሚጠቅም ከሆነ ብቻ ነው ስምምነቱን የምትፈርም።
፬: በድርድሩ ሂደት ግብጽ መቀበል እንጂ የምትሰጠው ነገር ስለሌላት ምንም ጫና የለባትም። ስለሆነም ተጣድፈን የማይሆን ስምምነት ልንፈርም የምንችለው እኛ ነው።
፭: ስምምነቱን ለውሃ ሙሌታ እንደ ቅድመ-ሁኔታ ማስቀመጥ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ከጥያቄ ውስጥ ያስገባል (it compromises the inherent sovereignty of Ethiopia over its natural right )። ይሄ አካሄድ ደግሞ ለወደፊቱ ፕሮጀክቶች ማሰሪያ (precedent) ሆኖ በማገልገል እጃችንን ያስራል። ስለዚህ የዚህ ስምምነት ውጤት የውሃ ሙሌቱን የተናጠል መብት አሳልፎ መስጠት ነው።
፮: የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መያዙ complementary jurisdiction ቢኖረውም ግብጽ መጀመሪያውን ድርጅቱን ንቃ እንደ መሄዷ መጠንና በድርጅቱ ጥርስ አልባነት ተሞክሮ ከጫና ነጻ ሆኖ አስፈላጊውን ጫና ያሳድራል ብሎ ማመን ይከብዳል፣
፯: ግድቡ እራሱ ለውሃ ሙሌት ዝግጁ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። ምናልባት ለዚህ ትንሽ የሳምንታት  ግዜ ለምግዛትም  የታሰበ ሊሆን ይችላል እና
፰: ስምምነት ባይኖርስ የሚለውም በመግለጫው እንደተቀመጠው ቀላል መልስ የለውም። ሲጀመር የተጠቀሙት ቋንቋ “all the three countries reached a consensus to make an agreement” ነው። ይሄ የሚያሳየው ስምምነቱ ላይ  መድረስ እንደሚቻል ነው። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ያወሩትን ይንገሩንና እንፍረድ። ያለስምምነት ቀኑ ከደረሰ ኢትዮጵያ ግድቡን ትሞላለች ማለት ለግብጽ ምን የተለየ ጥቅም ኖሮት ነው ወደ ድርድር የምትመለሰው? መልሱ ሁለት ነው:- ወይ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ እርግጠኛ ናቸው(ከላት እንደተቀመጠው) ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ሙሌቱን ታራዝማለች።
ስለሆነም ግድቡን ከስምምነት ጋር ማገናኘት ግዴታና አስፈላጊም አይደለም። ስምምነት ላይ ለመድረስ ከተፈለገ ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩት ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች መጥራት አለባቸው!
Filed in: Amharic