>

የአገር ቤት ጨዋታ ታደለ ገድሌ ጸጋዬ (ዶ/ር)

የአገር ቤት ጨዋታ

ታደለ ገድሌ ጸጋዬ (ዶ/ር)

እኛ ጨስ ጫኔ ብለንሃል…!!!
በ1950ዎቹና 60ዎቹ ላይ አባ መልስ እጅጉና አባ ቼሬ አስረሴ የተባሉ የሀገር ሽማግሌዎች አራውጭኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ ይኖሩ ነበር፡፡ አራውጭኝ ጊዮርጊስ የሚገኘው በደብረ ማርቆስ አውራጃ (በቀድሞው አጠራር) በደጀን ወረዳ፣ ከደጀን ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል ወርዶ በሚገኘው ቆላማ ቦታ ላይ ነው፡፡ አባ መልስና አባ ቼሬ በአገር የታወቁ ሽማግሌዎች ስለሆኑ አገሩ ላይ ሠርግ ሲደገስም ሆነ ተዝካር ሲወጣ አይነተኛ መራቂዎች እነርሱ ናቸው፡፡ በአካባቢው ባህል መሠረት አንድ ሰው ተዝካር ሲጠራ፤ “በዚህን ቀን ቅጠል፡ይርገፍብህ”ይባላል፡፡ለሠርግ፡ደግሞ“በዚህ ቀን የአዱኛዬ ተካፋይ እንድትሆን፣ የባሕር ዕቃም ይዘህ እንድትመጣ” በሚል ጥሪ ይደረጋል፡፡
የባሕር ዕቃ ማለት የጠላ መጠጫ ብርጭቆ ወይንም ብርሌ ለማለት ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይም ወሳኞች ናቸው፡፡ በተለይም አባ መልስ ከልጃቸው ከቄስ አየለ መልስ የሰሙትን ይዘው እሑድ እሑድ ተአምረ ማርያም ከተነበበ በኋላ ወንጌል ለማስተማር ይዳዳቸው ነበር፡፡ ጥቁርና ረጅም፣ ቀጭንና ሽበታም የነበሩት አባ መልስ፣ ነጭ ጭራቸውን እየነሰነሱ፤ “እናንተ ሰዎች አዋርያው ጣቢሎስ በመጀመሪያ አሂዛብ ነበር፡፡ በኋላም እዚጊሐር መረጠው ወደደው፡፡ ጦለቱም ቅድመ እዝጊሐር ደረሰለት እና እንደጣቢሎስ እንድንመረጥ ደግ ሥራ እንሥራ” ይላሉ፡፡ አዋርያ የሚሉት ሐዋርያ፣ ጣቢሎስ የሚሉት ደግሞ ጳውሎስ ለማለት ነው፡፡አባ መልስ በጣም የዋህ ሲሆኑ አባቼሬ ደግሞ ብልጥ ናቸው፡፡ አባ መልስ በአንድ ወቅት አህያ ማነቂያ ከተባለው ቦታ በሬ ሳር ሲያበሉ፣ በሬው ወደ ገደል አፋፍ እየተጠጋ ሳር ሲነጭ በርቀት ላይ ሆነው “ወይኖ ተው ተመለስ ገደል ትገባለህ?” ይሉታል፡፡ “ወይኖ” የበሬያቸው ስም ነው፡፡ ነገር ግን ወይኖ የእርሳቸውን ምክር አልሰማ ብሎ ወደ ገደሉ እየተጠጋ ሳር ሲነጭ ዥው ብሎ ገደል ይገባና ይሞታል፡፡
በአገሬው ባህል ከብት የሞተበት፣ ሰው የሞተበትን ያህል ስለሚታይ ሰው ሊያጽናናቸው ወደቤታቸው እየሄደ “ርጥባኑን ያውርድልዎ” ሲላቸው፣ “ተውት አትዘኑ፡፡ ተው ወይኖ ገደል ትገባለህ ተመለስ ብዬ መክሬው ነበር፡፡ አልሰማኝ ብሎ ነው ገደል የገባው ተውት፣ ተውት’ ይሉ ነበር፡፡ አባ መልስ በሕይወታቸው የዘንጋዳ እንጀራ በልተው አያውቁም፡፡ አንድ ወቅት ክፉ ቀን መጣና እህል ጠፍቶ “የዘንጋዳ እንጀራ አልበላም” ብለው ሰባት ቀን ሰነበቱ ይባላል፡፡ በሰባተኛው ቀን ሚስታቸው እማማ ሰገዱ፣ ከዘመዶቿ ጤፍ ተበድራና ተለቅታ ቀን እንዲገፋ ከዘንጋዳው ጋር ለማስፈጨት ፈልጋ፤ “አባ መልስ! ዘንጋዳውን ከጤፉ ጋር ላስፈጨው?” ትላለች፡፡“ወዴት ወደ ህል ጠጋ ጠጋ! ነግሬሻለሁ፡፡ ጤፉን ብቻ አስፈጪው፡፡” አሉ ይባላል፡፡ አካባቢው የዝንጀሮ አገር ስለሆነ በአዝመራ ወቅት ዝንጀሮ የማይጠብቅ ገበሬ የለም፡፡ በዚያው አካባቢ ለዝንጅሮ ሁለት ስም አለው፡- አንደኛው “ሌባው”፣ ሁለተኛው “ማቲው” ይባላል፡፡ ሌባው ከጓደኞቹ እየተለየ በቆሎ ዘንጋዳና ማሽላ የሚሠርቀው ሲሆን ማቲው ደግሞ በጅምላ የሚጓዘው የዝንጀሮ መንጋ ነው፡፡
ዝንጀሮ ወረራ በማድረግ ላይ መሆኑን የተረዳች አንዲት ሴት፣ አባ መልስን ከመንገድ ላይ ቆመው አገኘቻቸውና “አባ መልስ ሌባው ነው ማቲው በዚህ በኩል ያለፈው?” ትላለች፡፡ “አይ ሞኚት፤ የዝንጀሮ ሌባ እንጂ ሠራተኛ አለው እንዴ?” ብለው አሳቋት፡፡ አባ መልስ በአንድ ቅዳሜ ደጀን ገበያ ሄደው ሲመለሱ ይጉል ከተባለው ቦታ ወደሚገኘው ወደ ልጃቸው ማማው መልስ ቤት ይሄዳሉ፡፡ የልጃቸው ሚስት ደግሞ አለቅጥ ብልጥና ቅሬ ናት፡፡“አስናቁ ተሎ በይ እኽል ውኃ ስጭኝ፡፡ ገበያ ውዬ ርቦኛል” ይሏታል፡፡ ሴትዮይቱ ደግሞ ሁሉም ነገር ከቤቷ እያለ የንፉግነት ባሕርይዋ አልለቃት ብሎ፤
“አይ አባቴ! እንጀራም፣ ወጥም የለም፡፡ በሞቴ እንጨት ለቃቅሜ ልምጣና እንጀራ ጋግሬ ወጥ ሠርቼ በልተው ይሔዳሉ?” ትላለች፡፡ አባ መልስም ንፉግነቷን ስለሚያውቁ፤ “በይ ተይው አስናቁ አፍሽ ቅቤ ነው፡፡ እንደበላሁ፣ እንደጠጣሁ እቆጥረዋለሁ፡፡” ብለው ወደቤታቸው ወደ አጋዥ ወረዱ ይባላል፡፡በአገሩ ደንብ መሠረት በድግስ ወቅት ሽማግሌና ካህን የሚያበላ ወይም የሚጋብዝ ሰው የተከበረና ሚስቱም ባለሙያ የሆነች መሆን አለባት፡፡ ሽማግሌና ካህን ፊት የተመረጠ ጠላና እንጀራ፣ ወጥ ነው የሚቀርበው፡፡ እናም በአንድ ወቅት በአካባቢው ሠርግ፣ ተደገሰና አንድ ባለአፍላ (ባለጊዜ፣ ሀብታም) ሽማግሌውን አቆልቋይ ይዞ እንዲያበላ ይደረጋል፡፡ (አቆልቋይ 30 ሰው ያህል የሚይዝ አንድ የዳስ ረድፍ ነው፡፡) በአጋጣሚ ግን ጠላው ቅራሪ፣ እንጀራና ወጡም የማይጥም ይሆንባቸዋል ለአባ ቼሬ፡፡በመጨረሻ ምንም ሳይመርቁ ተነሥተው ወደቤታቸው ሊሔዱ ሲል የሰውየው ሚስት (ደጋሿ)፤
“አባቴ ይመርቁኝ እንጂ?” ትላለች፡፡“አይ አንቺ ምንሽ ይመረቃል” ብለው ጋቢያቸውን እየጐተቱ ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በነጋታው ደግሞ እዚያው አካባቢ የተዝካር ድግስ ኖሮ ተጠርተው ወደ ዳስ ሲገቡ፣ ያ ትላንትና የማይረባ ድግስ ያቀረበው እዚያም እተዝካሩ ላይ ሌማት (አቆልቆይ) ይዞ/ኖሮ የዳስ ባላ ተደግፎ ያገኙታል፡፡ አባቼሬም፤ “አንተዬ ትላንትና እኛን ገደልክ፤ ዛሬ ደግሞ ማንን ለመግደል ነው እዚህ ቆመህ የምታደባ” አሉት፡፡ እነዚህ ሁለት ሽማግሌዎች በ1958 የጥቅምት ወር ላይ አራውጭው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደጀሰላም ፊት ለፊት ከቅጽረ ግቢው ውጭ በሚገኝና ረጅም እድሜ በአስቆጠረ የወርካ ዛፍ ሥር የጽጌ ድግስ ሲበሉ፣ ጫኔ የተባለ ዲያቆን ልብሱን ግራና ቀኝ በመስቀለኛ መልክ አጣፍቶ አጨበጨበና፤ የሕዝቡን ሁካታና ጨዋታ ፀጥ አሰኘው፡፡ ከዚያም፣ “ስማኝ አገሬ ከ30 ዓመት በላይ በዲቁና ሳገለግልህ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ቅስና ተቀብለህ በቅስና አገልግለን፤ እነ ቄስ ከበደና እነ ቄስ አዳነ እያረጁ ናቸውና ቅስና ተቀብለህ እነርሱን ተክተህ አገልግለን ብትለኝ ከቄሰ ገበዙ ከአደራው አረጌ 3 ነጭ ሽልንግ እየተቀበልኩ ደ/ማርቆስ ሦስት ጊዜ ሙሉ ብመላለስም በፈተና ዜሮ በልተሃል እያሉ አባ ማርቆስ የቅስና ማዕረግ ሊሰጡኝ አልቻሉምና አገሬ ምን አርግ ትለኛለህ” አለ፡፡
ከመኻል አባ መልስ ብድግ አሉ፤ “አሄሄ እኒህ አባ ማርቆስ ምን ይከፉ ሰው ናቸው አያ? ማ ይሙት ማኔን ጨስ ብለው ቢልኩልን ምን ነበረበት? ስማ ማኔ አባ ማርቆስ ቢከለክሉህም እኛ ከዛሬ ጀምሮ ጨስ ማኔ ብለንሃል፡፡ ይቀበለው እግዚሐር፤ አቡነ በሰማያት እያልክ ማሳረግ ትችላለህ፡፡” ብለው የቅስና ማዕረግ ሰጡት፡፡ በአካባቢው ያልተማረውና ፊደል ያልቆጠረው ሕዝብ፤ ቄስ ለማለት ጨስ፣ ባቄላ ለማለት በጨላ ይላል፡፡ እናም ጨስ ማኔ የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አባ ቼሬም ብድግ አሉና፤ “መልስ! ልክ ነህ፤ አሁኑኑ በእኔ ይጀመር ይፍቱኝ አባቴ” ብለው የማኔን እጅ ሳሙት፡፡ ጨስ ማኔም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፈራ ተባ እያለ፣ አቡነ ዘበሰማያት እየሰጠ  ያሳርግ ጀመር፡፡ ይሁን እንጂ የጨስ ማኔ ትምህርት እንኳን ለቅስና ማዕረግ ይቅርና ለዲቁናም በቂ ስለአልነበረ፣ ፈታኙ አሳልፎ የጐጃም ሊቀ ጳጳስ ወደነበሩት ወደ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘንድ ሊያቀርበውና የቅስና ማዕረግ ሊያሰጠው አልቻለም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ወርካ ኪዳነምሕረት በተባለች ቤተክርስቲያን ቄስ ታረቀኝ እና አባ ኃይሌ አወቀ የተባሉ ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ ቄስ ታረቀኝ ቅዳሴ ሲቀድሱ አዘውትረው የሚመርጧት የቅዳሴ ዓይነት “ናኩተከ” የተባለችውን ኖሯል፡፡ “ናኩተከ” በጣም አጭርና ብዙ የማታስቸግር የቅዳሴ ዓይነት ናት፡፡ ኃይሌ ዐወቀ ደግሞ ሁልጊዜ ቆሞ ስለሚያስቀድስ “ነአኩተከ”ን በጨዋ አንደበቱ በቃሉ ሳይቀር ይዟታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ኃይሌ አወቀና ቄስ ታረቀኝ ይጣላሉ፡፡ አባ ኃይሌ በኃይል ሲመጡበት ኃይለኛ ነውና “አንት የናኩተክ ቄስ፣ ሰባኪ” ብሎ ይሳደባል ቄስ ታረቀኝን፡፡ ቄስ ታረቀኝ”፤ “ልባርጉልኝ ሰደበኝ” ብሎ ወደ ወረዳው ሊቀካህናት ጽ/ቤት በመሄድ ከሰሰና መጥሪያ ያመጣበታል፡፡ አባ ኃይሌም ወደ ሊቀ ካህናቱ ዘንድ በቀጠሮ ይሄዳል፡፡ ሊቀ ካህናቱም፤ “አባ ኃይሌ ቄስ ታረቀኝን የናኩተከ ቄስ፣ ሰባኪ ብለው ሰድበውታል?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ እርሱም፤
“ስድብ ውሸት፣ መናገሬ ግን እውነት ነው፡፡ አሁንስ ቢሆን የናኩተከ ቄስ ማለት ናኩተከን የሚቀድስ ማለት አይደለም ወይ? ሰባኪስ ማለት የሚያስተምር ለሕዝቡ ትምህርት የሚያስተላልፍ አይደለም ወይ?” ብሎ አባ ኃይሌ ይጠይቃል፡፡ ቄስ ታረቀኝ ደግሞ፤ “የለም የለም የናኩተከ ቄስ ያለኝ ዘልቀህ ያልተማርክ ነህ ሲለኝ ነው፡፡ ሰባኪም ያለኝ አጭበርባሪ አታላይ ማለቱ ነው፡፡ ሲል “ውሸት፤ ናኩተከም፤ ቅዳሴ ነው፤ ሰባኪም አስተማሪ ነው” ይላል ጨዋው አባ ኃይሌ፡፡ ሊቀ ካህናቱም “አባ ኃይሌ ትክክል ናቸው፡፡ ምንም አልተሳሳቱ” ብሎ፣ ክሱን ሠርዞ፣ አባ ኃይሌን አስክሶና ሁለቱንም አስታርቆ ወደ ሀገራቸው ወርካ ኪዳነምሕረት መለሳቸው ይባላል፡፡
Filed in: Amharic