>
5:01 pm - Monday November 30, 7654

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት [ክፍል ፪- አቻምየለህ ታምሩ)

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት

[ክፍል ፪]

አቻምየለህ ታምሩ

* … እኔም በጽሑፌ ኦሮሞ ኢትዮጵያን መውረሩን ያቀረብሁትን የዛሬውን የኦሮሞ ትውልድ ሳይሆን ከገዳ ሜልባህ ዘመን ጀምሮ እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ድረስ ያለውን  በሉባዎች የተመራውን የኦሮሞ የገዢ መደብ ኢትዮጵያን የወረረበትን የታሪክ ዘመን ነው። 
——
በዚህ ዘመን ኦሮሞ ኢትዮጵያን እንደወረረ  “ምኒልክ ወደ ኦሮሚያ ሲመጣ በአህያ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ፈረስ ላይ መቀመጥ የት ያውቅበትና ነው?  ምኒልክ የተቀመጠበት ፈረስ [ጊዮርጊስ ያለው ሀውልት] ገላን አካባቢ ከሚኖር ሲዳ ደበሌ ከተባለ ገበሬ የተሠረቀው ነው” መባሉን ተከትሎ “ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት” በሚል ርዕስ የጋሞውን መነኩሴ አባ ባሕርይን በመጥቀስ  ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ የለመደው ኢትዮጵያን መውረር በጀመረ በአርባ አመቱ እንደነበር ጽፌ ነበር።  ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ ከመለማመዱ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የዳግማዊ ምኒልክ ቅድመ አያቶች የጥንቶቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት የተዋቡ፣ ቄንጠኛና እንደ መስከረም ፀሐይ ከሚያንጸባርቅ ወርቅ በተሰራ ኮርቻ የሚጫኑ ፈረሶችን ይጋልቡ እንደነበር ብዙ የታሪክ መረጃዎችን በመጥቀስ መጻፌ ብዙ ውርጅብኝና ዘለፋዎችን አስከትሎብኛል። አበው “ማይምነት ለድፍረት፤ የገንዘብ ፍቅር ለክሕደት ያመቻል” እንዲሉ በፌስቡክ ያተምኩትን በማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ ከሁሉ በላይ ያበሳጨው  የታሪክ ንባብ የሌላቸውንና ቀለብ እየተሰፈረላቸው አማራን ሌት ተቀን ለማጥፋት ለሚሰሩ ድርጅቶች ምንደኛ ሆነው የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ነው።
ሀጫሉ ከኦሮሞ ሕዝብ ዳግማዊ ምኒልክ ከ150 ዓመት በፊት የሰረቀው አንድ ፈረስ የፈጠረበት የጥቃት እና የሐዘን ስሜት አልወጣለት ብሎ በቁጭት ሲናገር በጃዋር ቴለቭዥን ተመልክተነዋል። በዓፄ አምደ ጽዮን ዘመን በተጻፈው በሥርዓተ መንግሥቱ ላይ ከተዘረዘሩት 500 ገደማ የአማራ እና የጋፋት አማራ ሕዝብ አፅመ ርስት አውራጃዎች፣ ወረዳዎች እና ንኡስ ወረዳዎች ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑትን በኦሮሞ ወረራ ምክንያት የተነቀለው አማራ ግን ርስታችን ይመለስ፣ ለደረሰብን ጉዳት ካሳ ይከፈለን ብሎ እስከአሁን ድረስ አልጠየቀም። በወረራ የፈለሰብን ዐፅመ ርስታችን ይመለስልን፣ ለደረሰብንም ጉዳት ካሳ ይከፈለን ብሎ መጠየቅ ቀርቶ የአገር ባለውለታ መሪዎችን ታሪክ እና ዝና ለማጉደፍ ከአዕምሯቸው አንቅተው፣ ከአፋቸው አውጥተው የሚናገሩትን ለምን ተቻችሁ እየተባልን ያልተሰደብነው ስድብ የለም። “እናቱ ገብያ የሄደችበት ልጅ እና እናቱ የሞተችበት ልጅ እኩል ያለቅሳሉ” የሚለው ስነቃል ከ300 በላይ አፅመ ርስት ወረዳዎቹና አውራጃዎቹ በግፍ ተነቅሎ በሚያለቅሰው የአማራ ሕዝብ እና በዳግማዊ ምኒልክ አንድ ፈረስ ተዘርፎበት በሚያለቅሰው ሀጫሉ መካከል ያለውን ልዩነት ይገልጸዋል። ከሁሉም በለይ ሁል ጊዜ የሚያስደንቀኝ፣ ሊገባኝም ያልቻለው  ምኒልክን እና የአማራን ሕዝብ ፈጽሞ እየጠሉ የአማራውን ሕዝብ አጽመ ርስት እስከነፍሳቸው የሚወዱት ለምን እንደሆነ ነው። “ወንድ እወዳለሁ ጭኔ ያመኛል” ማለት ይህ ነው።
በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ታሪክና ዝና ላይ የነገድ ድርጅት መሪዎች እና ተገንጣዮች ያልፈጠሩትና ያልጻፉት የፈጠራ ክስ የለም። ንጉሡን ሰፊና ነጻ አገር መሰረተብን፣ ቅኝ ገዛን ከሚሉት ጀምሮ የፈንጣጣ በሽታን የሚያመጣውን ጀርም በመጠቀም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ማምረቻ ቤተ ምርምር ነበረው እስከሚለው የፈጠራ ታሪክ ሰምተናል። በዚህ ተደንቀን ሳንጨርስ በቅርቡ በዘመቻ መልክ በንጉሡ ታሪክ ላይ ሌላ የፈጠራ ክስ በሱሌማን ደደፎና በሀጫሉ ሁንዴሳ ሰማን። ሱሌማን በአምባሳደርነት እወክለዋለሁ የሚለውን አገር ሰርቶ ባሥረከበው መሪ ላይ የጻፈው የመንግሥትነት ስልጣኔ ታሪክ ባላቸው የዓለም አገሮች ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም። አምባሳደሮች በጥንቃቄ በተመረጡ ቃላት ሀሳባቸውን የሚገልጹ፣ ጭምትና ቁጥቦች፣ የአገራቸውን መልካም ገጽታ የሚያሳውቁና ሕዝባቸውን በእኩልነት የሚያገለግሉ ናቸው። የኛው ሱሌማን ግን የአገሩ መሪ የነበረን ታላቅ ባለታሪክ “የዱር አውሬ” ብሎት አረፈው። ቀጥሎ ንጉሡ የፈረስ ሌባ ነው ተባለ። “ሐሰተኛ ያወራውን ፈረሰኛ አይመልሰውም” እንዲሉ እንደዚህ አይነት የፈጠራ ክሶች በጊዜው በእውነተኛ ታሪክ ካልታረቁ ጉዳታቸው ከፍተኛ መሆኑን ባለፉት 50 ዓመታት ካሳለፍነው ፍዳና መከራ በላይ አስረጂ ሊኖር አይችልም።  በመሆኑም እነሱም ፈጠራቸውን ይቀጥላሉ እኛም ማጋለጡን እንቀጥላለን። “እውነት የተናገረና ወተት የለመነ አይወደድም” እንዲሉ ያ  ሁሉ ውርጅብኝ የወረደብን እውነቱን በመጻፋችን ነው።
ይህ ጽሑፍ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ላይ ለተነሡት የፈጠራ ክሶች የሰጠሁትን ምላሽ መነሻ በማድረግ ኢያስፔድ ተስፋየ የተባለ ሰው ለጻፈው ፈገግና ዘና የሚያደርግ ጽሑፍ መልስ እንዲሆን የጻፍኩት ነው። ወደዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ግን ስለኢያስፔድ ተስፋየ  ትንሽ ልበል። ኢያስፔድ በአሁኑ ጊዜ OMN በተባለው የጃዋር  መሐመድ ቴሌቭዥን ጣቢያ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ የኦሮሞ ብሔርተኛ  ነው። OMN በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያሰራጨው የጅምላ ጭፍጨፋ ቅስቀሳ የርዋንዳን የዘር ፍጀት አነሳስቶ ያስፈጸመውን Radio Télévision Libre des Milles Collines (RTLM) ያስንቃል። ኢያስፔድ ኢትዮጵያንና የአማራን ሕዝብ በመጥላት ጣሊያናዊውን ፋሽስት ግራዚያኒን የሚያስንቀው የአገር በቀሉ ጥቁር ግራዚያኒ የዋለልኝ መኮነን አድናቂ ነው። ኦነግ ዋለልኝ መኮነን ሌሎች ኢትዮጵያውያን በአማራ ሕዝብ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሆ ብለው እንዲነሱ በሚቀሰቅሰው ፅሑፉ መነሻ የተቋቋመ፤  በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ማካሄድን ፖለቲካው ያደረገ  የጽለምትና  የደም ድርጅት ነው። የዋለልኝ ጽሑፍ ኦነግ በ1982 ዓ.ም. በዘራቸው ምክንያት ከራያ፣ ከዋለልኝ የትውልድ ቦታ ከቦረና እና ከሌሎችም የወሎ አካባቢዎች ደርግ አገራችህ ነው ብሎ ወለጋ ባሰፈራቸው የአማራ ተወላጆች ላይ ለተፈጸመው የማይረሳ ጭፍጨፋ መነሻ ጠንቅ ነው። ለመስማት እንኳ በሚሰቀጥጥ እኳኋን ገላው ተቆራርጦ የተገደለው የኢያስፔድ አባትም የሞቱ ምክንያት የዋለልኝ ጽሑፍ የፈጠረው ጠንቅ ነው።
የኢያስፔድ አባት ተስፋየ ታደሰ የትውልድ ስፍራ፣ ከዋለልኝ መኮነን የትውልድ ስፍራ ከሆነው ወሎ ቦረና ሳይንት ነው። ለኢያስፔድ አባት በግፍ ታርዶ መገደል ምክንያት የሆነው ዳግማዊ ምኒልክ ቅኝ ገዥ አይደሉም፣ አንድ ጋት እንኳ የኦሮሞ አፅመ ርስት አልወሰዱም የሚለው አቋሙ ነው። ይህን የተስፋየ ታደሰን አቋም ለማወቅ የሚሻ ቢኖር በባለቤትነት ያስተዳድራቸው የነበሩ  የመስትዋት መጽሔትና የሉባር ጋዜጣ ኅትመቶችን ያንብብ። አንዳንድ ሰዎች የኢያስፔድ ነገር “አባቱን ገድሎ ለአማቱ ይነጭ፣ አማቱን ጋርዶ እናቱን ያስፈጭ” የሚለውን ያስታውሰናል ይላሉ። ይህን የሚሉት ኢያስፔድ ለOMN ተቀጥሮ በመስራት በፈጠረባቸው አግራሞት ምክንያት ነው። ለኔ ግን የኢያስፔድ ምክንያት ሌላ ነው። ኢያስፔድ ለጃዋር ቴሌቭዥን እንደሚሰራ ስሠማ በሰዎች ተስፋ እንዳደርግ አድርጎኛል። ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት እንደኢያስፔድ ተስፋየ ያሉ ሰዎች ናቸው። “ማን ይሙት ጠላት፣ ማን ይኑር አባት” እንዲሉ ኢያስፔድ የአባቱ ገዳዮች  ረግፈው፣ አባቱ በሕይዎት ቢኖር እንደሚመርጥ እርግጠኛ ነኝ። ኢያስፔድ የኦሮሞ ብሔርተኛ ቢሆንም ራሱን እንደ አማራ እንደሚቆጥር የሰማያዊ ፓርቲ አመራር በነበረበት ወቅት  ባልደረቦቹ የነበሩ ሰዎች ነግረውኛል። ኢያስፔድ “ሞኝ በአባቱ ሞት ይጨፍራል” የሚባለውን አባባል እየሰማ እንዳደገ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን ለአባቱ ሞት ጠንቅ የሆነ መነሻ ጽሑፍ የጻፈውን ትምህርቱን ያልጨረሰው ዋለልኝን አብነት አደረገ፤ የዋለልኝን ጽሑፍ መነሻ አድርጎ ለተመሰረተው፣ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን አገራችሁ ነው ተብለው በመንግሥት ትእዛዝ ወለጋ የሰፈሩትን የወሎ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ቤት ውስጥ በማስገባት በመትረየስ ለጨፈጨ ድርጀት ለኦነግ በልሳንነት ለሚያገለግለው ለOMN ተቀጥሮ ይሰራል። ይህ በእውነቱ ዳግማዊ ምኒልክንን  የሚያስንቅ “የታላቅነትና የቸርነት” መንገድ ነው።
ኢያስፔድ  የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ “ተመራምሮ” የደረሰበትን ድንቅ ግኝት ለኔ ጽሑፍ በሰጠው ምላሽ አበርክቶልናል። ይህ የሚያስመሰግን ስራ ነው። ኢያስፔድ በስሙ የለጠፈውን የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶች እና ምሁራን ለአለፉት 50 ዓመት የጻፉት እና በተለያየ መድረክ የተናገሩት ስለሆነ አዲስ አይደለም። የፖለቲካ ማንነት በሰውነት የደም ጥራት የሚወሰን ስላልሆነ ከቦረናው አማራ ከተስፋየ ታደሰ የተወለደው ኢያስፔድም የኢትዮጵያም ሆነ የአማራ ፖለቲከኛ ሳይሆን የኦሮሞ ብሔርተኛ መሆንን መርጧል። “ጠላትን ሲረቱ በወንድም በእኅቱ” እንዲሉ ኦነግን የመሰረቱት ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ጠንቅ የሆነውን “የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ” የተሰኘውን ቅርሻት ጽፈው በዋለልኝ ስም እንዳሳተሙት የኦነግ መስራቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ዲማ ነገዎ በቅርቡ የዋለልኝን 50ኛ የሙት ዓመት ለመዘከር ጸረ አማራዎች በተሰበሰቡበት መድረክ ምስክርነቱን ሰጥቷል። “ሞኝ እንደነገሩት በቅሎ እንዳሰገሩት” ሆኖ ኢያስፔድም ሳያቅማማ የሚያስገምተውን የኦነግ ጽሑፍ በስሙ ለጠፈው።
በኢያስፔድ ስም በወጣው ጽሑፍ የተዘረዘረው ቅራቅንቦ የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ካሳተሟቸው የተረት መጽሐፍት የተለቃቀሙ ናቸው። ስለዚህ የምተቸው ኢያስፔድን ሳይሆን በኢያስፔድ ስም የወጣውን የኦነግ ጽሑፍ  መሆኑን አንባቢ  ልብ እንዲል ማሳሰብ እሻለሁ። ነገር ግን አማራውን ከብዙ ሽህ ዓመታት በፊት ጀምሮ ይኖርበት ከነበረው ከአጽመ ርስቱ ሲያፈናቅል፣ ሲገድል እና ሲያስገድል ለነበረውና አሁንም ለሚያስገድለው፣ ለሚያፈናቅለው ለኦነግ ለማገልገል ስለመረጠ ኢያስፔድም በጽሑፉ ላይ ለሰፈረው ሁሉ ኃላፊነት አለበት። ዋለልኝንም ሆነ ኢያስፔድን አማራም ሆነ ጸረ አማራ የሚያደርጋቸው ተግባራቸው ነው። አማራን በሚመለከት በተግባር በዋለልኝ፣ በኢያስፔድ እና በግራዚያኒ መካከል ከቆዳ ቀለም በስተቀር ምንም ልዩነት የለም። “መመራመር ያገባል ከባሕር” እንዲሉ መልስ በማዘጋጅበት ጊዜ ብዙ ነገር ስላገኘሁ ጽሑፌ ትንሽ  ዘለግ ያለው ነው። ስለሆነም ይህንን ጽሑፍ ማንበብ የጀመራችሁ ወገኖቼ  በጥሞና ጊዜ ወስዳችሁ እንድታነቡት እጠይቃችኋለሁ። ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁት በኢያስፔድ የወጣው ጽሑፉ ትችት የሚያስፈልገው ሆኖ ሳይሆን ያው “ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም”፤ “ሐሰቱ ስለበዛ እውነቱ ሆነ ዋዛ”  እንደሚባለው ብዙ የዋሆች እውነት ሊመስላቸው ስለሚችል እውነተኛን ነገር እንዲያውቁ  በማሰበ የተደረገ ነው።
ኢያስፔድ ሊያስተጋባ የሞከረው የኦነጋውያን  የመጀመሪያው ትርክት “አቻምየለህ በዚህ ፅሁፉ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ፅሁፎቹ ውስጥ ዋነኛ ችግሩ የምንጭ አጠቃቀሙ ነው። ያልተባለውን የተባለ በሚያስመስል መልኩ ከአውዱ ገንጥሎ እና አፋቶ የሚያመጣቸውን ምንጮች ከዚህ ቀደም ያነበበ ወይም የጠቀሰውን ምንጭ ተከትሎ ሄዶ የመረመረ ሰው ምን እያልኩ እንዳለሁ በሚገባ ይገባዋል” ሲል የምጽፈውን አለማንበቡን፤ ቢያነበውም ያነበበውን አለመረዳቱን  ያሳመቀበት በኔ ላይ የተሰነዘረው ክሱ ነው። ሲጀመር ሥርዓት የተላበሰ አስተሳሰብ ያለው ሰው የምንጭ አጠቃቀም ችግር አለ የሚለውንና ከአውዱ ተገንጥሎና ተፋቶ ቀረበ የሚለውን በማስረጃ  አስደግፎ ጭብጡን ያቀርባል እንጂ ሾላ በድፍን የግራ ፖለቲከኞችን የተለመደ ጥላሸት የመቀባት አካሄድን አይመርጥም። ስለዚህ ቀደም ብዬ የጠቀስሁት የኢያስፔድ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ጌቶቹ ኦነጋውያን ሲሉት የሰማውን ነገር ያሳመረና ለመታመን የሚበቃ መስሎት ደገመው እንጂ እንዳች ቁምነገር የለበትም።
እኔ በጻፍሑት ጽሑፍ ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ የለመደው ኢትዮጵያን መውረር በጀመረ በ40 ዓመቱ ነው በሚል ያቀረብሁትን  የታሪክ እውነት  የነገሩን ብቸኛው ቀዳሚ የኦሮሞ ታሪክ የጽሑፍ ምንጭ የሆኑት አባ ባሕርይ በዜናሁ ለጋላ ክፍል ዘጠኝ ላይ  መሆኑን ጠቅሼ ይህንንም  ታሪክ  የኦሮሞ ብሐርተኛው ፕሮፈሰር  መሐመድ ሐሰን በመደገፍ እንደጻፈ “The oromo and the Christian kingdom of Ethiopia 1300- 1700” በሚል ያሳተመውን  መጽሐፉ ገጽ 173 ላይ ጠቅሼ ያቀረብሁትን እያስፔድ ነጭ ውሸት ነው ይለዋል። ሆኖም ግን  እኔ የጠቀስሁትን የመሐመድ ሐሰን ጽሑፍ “አንባቢ እንዲፈርድ እንደወረደ በቀጥታ ላስቀምጥላችሁ” ብሎ የጠቀሰው የመሐመድ ሐሰን ጽሑፍ እኔ የጻፍሑትን የሚደግፍ እንጂ እሱ እንዳለው ነጭ ውሸት አይደለም።
 እንዴውን ኢያስፔድ የመሐመድን ጽሑፍ ሲጠቅስ መሐመድ የተቸውን የአሊ ማዙሪን አስተያየት የተነሳለትን አላማ ስለማይደግፍ ሊያቀርበው አልፈለገም። የመሐመድን ጽሑፍ እንደወረደ ላቅርብላችሁ ብሎ አንባቢዎችን ካስተዋወቀ በኋላ የመሐመድ ሐሰን ጽሑፍ   “. . . Ali Mazuri asserts that it was the Oromo use of horses in battle that eventually convinced Ethiopians of the military use of horses. This is historically inaccurate as horses had been used in warfare for centuries among the Amharas, the Tigrayans, . . . . population in Ethiopia”  ሲል ያቀረበውን  “Ali Mazuri asserts that it was the Oromo use of horses in battle that eventually convinced Ethiopians of the military use of horses” የሚለውን ብቻ ቆርጦ በማቅረብ “This is historically inaccurate as horses had been used in warfare for centuries among the Amharas, the Tigrayans, . . . . population in Ethiopia” በሚል  መሐመድ ሐሰን  በAli Mazuri ላይ ያቀረበውን ትችት ይዘለዋል። እያስፔድ ቆርጦ እየቀጠለ ይህንን ሲያደርግና  መሐመድ ሐሰን የAli Mazuriን ሐሳብ ደግፎ እንደጻፈ አድርጎ ሲያቀረብ አማራ ከኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ እንደተማረ ያሳይልኛል ያለውን ፍላጎቱን ማቅረቡን እንጂ መሐመድ ሐሰን በግልጽ የተቃወመውንና  የነቀፈውን ሀሳብ ደግፎ እንዳቀረበ አድርጎ ማቅረቡ አላሳሰበውም።
ጮሌው ኢያስፔድ ሌላኛው ለመተቸት የተንጠራራው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንም “ Greater Ethiopia: The Evolution of a Multiethnic Society”  በሚል የጻፉትንና ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ የለመደው ኢትዮጵያን መውረር በጀመረ በ40 ዓመቱ መሆኑን ለመደገፍ የጠቅስሁትን ምንጭ ነው። ኢያስፔድ የፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንን ጥናት ሊነቅፍ የሞከረው  እኔ ያልጠቀስሁትን መጽሐፍ በማውሳት <<wax and gold የተሰኘውን ስራ አዲስ መግቢያ (preface) ፅፎለት በድጋሚ ባሳተመበት ወቅትም እሱ ራሱ bias እንዳለበት አምኗል። እንዲህ ሲል “The motive which lies behind any scholar’s effort to characterize an exotic culture is ultimately aesthetic. I freely admit to having been seduced by the charm of traditional Amhara life.”>> በማለት ነበር።
ሲጀምር ፕሮፈሰር ዶናልድ ሌቪን በሰምና ወርቅ መጽፋቸው ከገጽ ix -x  የጻፉትና ኢያስፔድ በከፊል የጠቀሰውን መግቢያ የጻፉት ኢያስፔድ እንደሚለው biased ሆነው እንደነበር ለመናገር ሳይሆን እኔ ያልጠቀስሁትን መጽሐፍ ለመጻፍ ለምን እንደተነሱ ለማስረዳት ነበር።  ሲቀጥል ኢያስፔድ እንደነገረን ፕሮፈሰሩ biased ሆኜ ነበር ብለው የጻፉት አንዳች ነገር የለም። ኢያስፔድ ፕሮፈሰሩ ያላሉትን፤ ይልቁንም ጥናታቸውን ለማድረግ ገፊ የሆናቸውን መነሻ ያብራሩበትን መግቢያ ቀንጭቦና አዛብቶ በማቅረብ  ነው እንግዲህ እኔ ላልጠቀስሁት መጽሐፍ ማጣጣያ አድርጎ ያቀረበው። ሲሰልስ ኢያስፔድ ላሕራ ስሚዝ ተቸችው ያለውን የፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪንን  መጽሐፍና ጥናት አንዱንም በስም ሳይጠቅስ ነው ፕሮፈሰሩ አማራን አድንቀው የጻፉ ስለመሰለው ብቻ ነቅፎ የጻፈው። ኢያስፔድ ፕሮፈሰር ዶናልድ ሌቪንን ለመተቸው የተነሳው መጽሐፋቸን አንብቦ የሚተቸው ሀሳብ ስላገኘበት ሳይሆን ፕሮፈሰሩ የአማራን ባሕል በማድነቅ እንደጻፉ ከኦነጋውያን ስለሰማ ለምን አማራ ተደነቀ ብሎ ተበሳጭቶ ነው።
ባጭሩ ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ የለመደው ኢትዮጵያን በወረረ በአርባ አመቱ መሆኑን የሚያሳይ ብቸኛ ቀዳሚ የጽሑፍ ማስራጃ የዘመኑ የዐይን ምስከር አባ ባሕርይ የጻፉት ዜናሁ ለጋላ ብቻ ነው። መሐመድ ሐሰንም ሆነ ዶናልድ ሌቪን ይህንን ደግፈው እንጂ ተቃውመው አልጻፉም።  ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን  ኦሮሞ ከምችሌ ገዳ  ማለትም ኢትዮጵያን ከመውረሩ ከአርባ ዓመታት በፊት ፈረስ ይጋልብ እንደነበር ጽፏል የሚል ካለ መሐመድ  ሐሰን  ያቀረበውን ማስረጃ ያቅርብ።
ቀጣዩን ትችት በዝርዝር ከማቅረቤ በፊት የመለስ ዜናዊ አማካሪ የነበረው የሲ.አይ.ኤው ፓል ሄንዝ ስለኦነግ አና በአጠቃላይ የኦሮሞ ፖለቲካ ሰለተመሰረተበት የውሸት ታሪክ የጻፈውን ላስቀድም። ፓል ሄንዝ የአሜሪካ ተወላጅ ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ብዙ የጥናት ጽሑፍ አሳትሟል። ደርግ ወደስልጣን ከመምጣቱ በፊት እና ከወደቀ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሩ ወደጅ እንደነበር ጽፏል። ፓል ሄንዝ የመለስ ዜናዊ አማካሪ እና የቅርብ ወዳጅ ነበር። ኦነጋውያንን  ገና ጫቃ እያሉ ጀምሮ ያውቃቸው ነበር። እንደአውሮፓውያን አቆጣጠረ በሀምሌ 30 ቀን 1992 ለመለስ ዜናዊ በጻፈለት ረጅም ደብዳቤ ስለኦነጋውያን ተረት ተረት የሚቀጥለውን ጽፎ ነበር፤
“The OLF tries to represent the Oromo as victimized by Menelik and never given justice for their sufferings. They are entitled to their own view of their history, but they cannot require other Ethiopian peoples to accept it. Much of their history is selective mythology. They forget that in historical terms, the Oromo are one of the newest [underlined in the original] peoples in Ethiopia. Europeans in North America and whites in South Africa have occupied their territories longer than the Oromo in most regions of Ethiopia.”
ትርጉም፤ 
“ኦነግ ኦሮሞን በምኒልክ የተጠቃና ለደረሰበትም ጥቃት ፍትህ ያላገኘ አስመስሎ ለማቅረብ ይጥራል። ስለታሪካቸው የራሳቸውን አመለካከት ሊኖረቻው መብታቸው ነው፤ ነገር ግን ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እንዲቀበሉት መጠየቅ አይችሉም።  አብዛኛዎቹ ታሪካቸው የተመረጠ ተረት ነው። በታሪክ በነባርነት አንጻር ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ነገዶች ሁሉ በጣም አዲስ መጤ (ገብ)  ሕዝብ መሆኑን ረስተውታል። አውሮፓውያን ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ነጮች ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡበት ጊዜ ኦሮሞዎች በአብዛኛው የኢትዮጵያ አውርጃዎች ከሰፈሩበት ጊዜ ይረዝማል።”
 የኦሮሞ የታሪክ ምሁራን እና የነገድ ድርጅት መሬዎች ተረት ተረት እየፈጠሩ ታሪክ ነው እያሉ እንድንቀበላቸው የሚፈልጉበት ዋናው ምክንያት ከላይ ፓል ሄንዝ በገለጸው ምክንያት ነው። ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር ነበር፣ ኦሮሞ ነባር ሕዝብ ነው እያሉ የሌለ ልብ ወለድ የሚፈጥሩበት ምክንያት ሕዝባችን የሚሉት የሰፈረበት ምድር የሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለይም የአማራው ሕዝብ አጽመ ርስት ስለሆነባቸው ነው። ኦነጋውያን እውነተኛ፣ የታመነ፣ የተጨበጠ ታሪክ ባይሆንም  ኦሮሞ ነባር መሆኑን ያረጋግጥልናል ብለው የሚያስቡትን ማንኛውንም ቅራቅንቦ እንደ ታሪክ ማስረጃ  ከመቀበል  ወደኋላ አይሉም።
ፕሮፌሠር ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ “በራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባ” በሚል ርዕስ  በቅርቡ ያሳተመው አስደማሚ የታሪክ እና የሕግ ሰነድ የብሔር ድርጅት መሪዎች በተለይም ኦነጋውያን ለ50 ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የፈጸሙትን ሀጢያት ስፋቱን እና ጥልቀቱን በግልጽ ያሳያል። “የበራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባ”ን 6ኛውን ምዕራፍ ያነበበ ሰው የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፌሠር መሐመድ ሐሰን የዶክትሬት ዲግሬውን ለሰጠው ለለንደን ዩንቨርሲቲ ለተቋሙ ክብር ሲል ቢመልሰው ጥሩ ነበር ያሰኛል። “መልሕቅ ባሕር ውስጥ በተወረወረ ተዘፈዘፈ እንጅ መች ዋና ተማረ” እንዲሉ መሐመድ ሐሰን ለንደን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ወጣ እንጅ ምንም አልተማረም። ኦሮሞ ከ16ኛው ምዕተ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ መኖሩን ለማረጋገጥ ባደረገው መጋጋጥ 379 ገጽ ርዝመት ያለው ባዶ የቃላት ኳኳቴ መጽሐፍ ጽፏል። መሐመድ ሐሰን ያባከነው ወረቀት እና ቀለም ያሳዝነኛል። ሰላሌና ጅማ የሚባሉ በታሪክ ያልነበሩ የኦሮሞ ጎሳዎች ከመፍጠር አልፎ ዓምደ ጽዮን ታሪክ ነገሥት ላይ “ሀገረ ጋሣ” ተብሎ የተገለጸውን የአማራ ዐጽመ ርስት “ሀገረ ጋላ” ማለት ነው፤ ጽላልሽ የተባለውን ሰላሌ ብሎ በማቅረብ ኦሮሞዎች ነባር ኢትዮጵያውያን ነበሩ፣ ኢትዮጵያን የለቀቁበት ምክንያት በንጉሡ [በአምደ ጽዮን] ጭፍጨፋ ነው ብሎ አሳፋሪ ፈጥራ ጽፏል። “የበራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባ” ጸሐፊ ይህንን  ሁሉ  ፈጠራ አጋልጧል። ጸሐፊው ከማን ዐጽመ ርስት ላይ ማን እንደሠፈረ፣ ማን በመዋቅራዊ መንገድ ማንነት፣ ቋንቋ እና ባሕል ይደመስስ እንደነበረ እና ማን ወራሪ እንደነበረ በአስዳማሚ ብቃት፣ በሁልቁ መሳፍርት የታሪክ ምንጭ ተመስርቶ ታሪኩን አቅርቧል። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደገለጹት  “የበራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባ” የተሰኘው የፕሮፈሰር ሀብታሙ መጽሑፍ ለኢትዮጵያ ለሚታገል ድል መንሻ መሳሪያ ነው።
ኦነጋውያን ስለፊንፊኔ የፈጠሩት ተረት ባይኖር ኑሮ “በራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባን” የመሰለ አስደማሚ የታሪክ ሰነድ አይጻፍም ነበር። በእውነቱ  ኦነጋውያን ሳይታወቃቸው የረሣነውን ታሪካችንን እንድናውቅ ምክንያት ሰለሆኑ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። የደም ሙቀታቸውን ስለሚጨምረው ኦነጋውያን “በራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባ”ን ሊያነቡት አይችሉም። እንደለመዱት የታሪክ ምንጮችን ከተጻፉበት አውድ እያወጡ ሰሚ ካገኙ ማጮሀቸውን ግን ይቀጥሉበታል።
አሁን በኢያስፔድ ስም ያወጡትን የኢትዮጵያ ነገሥታት ቋሚ መናገሻ እንዳልነበራቸው ያሰረዳል ያሉትን ትርክት እንይ። በኢያስፔድ ስም የወጣው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፣
“ለማንኛውም ይቺን መርእድ ወልደ አረጋይ እና ዶናልድ ዶንሀም የጠቀሷትን በ16ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘውን የፖርቱጋላዊውን joao de Barros ማስታወሻ ልጥቀስና ላጠናቅቅ። An Armenian who was in those parts happened to make a watermill for the king for grinding wheat and other kinds of grains, which they ground and reground by hand only with great effort. After the king saw how the mill worked, he had it dismantled immediately, for he said that the thing was no use in his country because he always is moving his kingdom in encampments and he could not carry machines about that had to be fixed in one place.”
መጀመሪያ ዮሐንስ ደ ባሮስ ኢትዮጵያን አልጎበኘምና በኢያስፔድ ስም በወጣው ጽሑፍ ኢትዮጵያን እንደጎበኘ ተደርጎ የቀረበው ፍጹም ፈጠራ፣ ፍጹም ነጭ ውሸት ነው። ባሮስ በሕንድ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት በነበረችው በገዋ የሚኖር ሰው ነበር። ስለኢትዮጵያ መረጃ የነገረው አርመናዊ ትውልድ የነበረው የኢትዮጵያ አምባሳደር ማቴዎስ በ1509 ዓ.ም. በንግሥት እሌኒ ተልኮ ወደ ፖርቱጋል ለመሄድ ሕንድ በነበረበት ጊዜ ነው። መረጃውን  የጠቀሰው ዶናልድ ዶንሀም ደግሞ  የፕሮፈሰር መርዕድን ጥናት ሲጠቅስ ገጹን አሳስቶታል። ኢያስፔድም ስለ ምንጩ ተጨማሪ ማጣራት ሳያደርግና መረጃው በተጠቀሰው ቦታ መኖር አለመኖሩን ሳያረጋግጥ የተባለውን በመድገም የዶንሀምን ስህተት አባዛው።  ከዚህ በተጨማሪ ጽሑፉም  ከየት እንደተገኘ አይገልጽም። በርግጥ ይህንን አይነት ስርዓት የተላበሰ አሰራር  ከኦነጋውያን አንጠብቅም፤  ምክንያቱም እነሱ የሚያደክም ስራ አይወዱምና።
ከላይ የቀረበው የኢያስፔድ ጥቅስ በሶስት ምክንያት ፍጹም ውሸትና ኢያስፔድ ሊነግረን የፈለገውን ትርክት አይደግፍም። ሲጀምር ኢያስፔድ ሊነግረን እንደፈለገው ነገሥታቱ ቋሚ መቀመጫ እንዳልነበራቸው አያሳይም። ፕሮፈሰር መርዕድ ያቀረበው  የዮሐንስ ደ ባሮስ  ትክክለኛ ጥቅስ የሚከተለው ነው፤
“All the Ornaments and vestments they have, which are many, and more than could be expected among such barbarous people… go for them from India and Cairo and from other parts… And they could not be more brutish in skill because an Armenian who was in those parts happening to make for the king a watermill for grinding wheat  and all other kinds of grains, the flour of which they make between some stones by hand, more by regrinding than grinding, and this with great effort; after the king saw the work it did he had it dismantled right away saying that that thing was no use in his country because he was always moving  in a camp  throughout his kingdom and he would not carry with him those machines which are always fixed in one place! As if that device would serve only wherever he himself happened to be and not the people of his entire kingdom.”      [ ምንጭ፡ Aregay, M. W. (1984). Society and Technology in Ethiopia 1500-1800. Journal of Ethiopian Studies, 17, ገጽ 129]
ነገሥታቱ የጸጥታ ችግር ባለበት ስፍራ ሁሉ ይዘምታሉ። ዘመቻ በሚያደርጉበት ጊዜ የውኃ ወፍጮ ይዘው ሊዘምቱ አይችሉም። ለምሳሌ ዘመቻ የሚዘመተው ውኃ በማይገኝበት በበርሀ ቢሆን የውኃ ወፍጮው ወደ በረሀ ተይዞ ሊሄድ አይችልም። በተጨማሪም ዘመቻ የሚደረገው ለአጭር ጊዜ ነው። ለአጭር ጊዜ ለሚደረግ ዘመቻ የውኃ ወፍጮ ምንም ጥቅም የለውም።  ጥቅም አለው ከተባለ ንጉሡ በዘመተበት አውራጃ፣  ባረፈበት ካምፕ፣ ባለፈበት በአገደመበት ቦታ ሁሉ ወፍጮ መትከል አለበት ማለት ነው።  በመካከለኛው ዘመን የነበሩት የአውሮፓ ነገሥታትም እንዲሁ የመንግሥት ስራቸውን የሚያስፈጽሙት ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው ግዛታቸው ያለማቋረጥ በመንቀሳቀስ ነበር። የመካከለኛውን የአውሮፓ ዘመን ታሪክ የሚያጠኑ የአውሮፓ የታሪክ ምሑራን በዚህ መልኩ አገር የሚያስተዳድሩትን መሪዎች “ተንቀሳቃሽ ንግሥና” (“Itinerant Kingship/Court”) ይሏቸዋል። “ተንቀሳቃሽ ንግሥና” የአስተዳደር ዘይቤ ነው እንጅ የቋሚ መዲና መኖር እና አለመኖር ማሳያ አይደለም። “ከዐይን የራቅ ከልብ ይራቅ” እንደሚባለው ነገሥታቱ ከአንዱ አውራጃ ወደሌላ አውራጃ የሚንቀሳቀሱት አለሁ ለማለት፣ ግብር ለማስገበር፣ የመንግሥት ስራ ለማስፈጸም፣ አመጽ ሲነሳ ጸጥታ ለማስፈን፣ ወረራ ሲኖር ለመመከትና ስልጣናቸውን ለማስረገጥ ነው።
ስለ”ተንቀሳቃሽ ንግሥና” እጅግ ብዙ መጽሐፍት ስለታተሙ በአውሮፓ በሰፊው የነበረ ታሪክ ለመሆኑ ማንም በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላል። ለኦነጋውያን አብነት ይሆን ዘንድ ስለጀርመን የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት የተጻፈውን የሚከተለውን መጽሐፍ እንዲያነቡት እጋብዛለሁ (ምንም እንኳ እንደማያነቡት ባውቅም)፣ John W. Bernhardt, Itinerant Kingship and Royal Monasteries in Early Medieval Germany, c.936-1075 (Cambridge University Press, 1993). እነዚህ ተንቀሳቃሽ ነገሥታት ቋሚ መንበረ መንግሥት  ወይም ዋና ከተማ ያላቸው ናቸው። አንድ ንጉሥ ከአንዱ ግዛት ወደሌላው ግዛት ተንቀሳቀሰ ማለት ቋሚ መዲና የለውም ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክም እንዲዚያ ነበር። ዋና መዲናቸው የኛዋ በራራ የአሁኗ አዲስ አበባ ከፈካችበት ስፍራ የነበረችዋ ከተማ ነበረች!
በጎንደር ዘመነ መንግሥትም የነበረው አስተዳደር “የተንቀሳቃሽ ንግሥና” ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ጥልቅ ምርምር ያደረገው ዶናልድ ክራሚ በጎንደር ዘመንም ነገሥታቱ አንዴ ጎጃም ባሕር ዳር አቅራቢያ ከሚገኘው ይባባ፤ ሌላ ጊዜ በጌምድር ደብረ ታቦር አቅራቢያ ከሚገኘው አሪንጎና ከዋና ከተማቸው ጎንደር  ከተማ ያለማቋረጥ ይንቀሳቀሱ እንደነበረ የሚከተለውን ይነግረናል፤
However, contrary to what has been commonly been believed, even by scholars, Ethiopia’s rulers did not stop their habit of annual procession until well into the eighteenth century, if then. Gondar was above all a winter residence… For much of the rest of the year the emperor led the court on a regular pattern of travels which took it to the provinces which marked the kingdom’s heartland. Sub capitals as it were, sprang up to mark regular stopping places, at Arengo near Dabra Tabor, and Yebaba in the hills above Bahr Dar (Land and Society in the Christian Kingdom pf Ethiopia from the Thirteenth through Thirteenth Century [(Urbana: University of Illinois Press, 2000),  ገጽ  74.]
የበራራም ታሪክ እንዲሁ ነው።  በኢያስፔድ ስም የወጣው ጽሑፍ ግን  joao de Barros ኢትዮጵያን ጎበኘ ባለበት ወቅት ስለ አንድ ንጉሥ ከካምፕ ወደ ካምፕ መዘዋወር የተጻፈውን  ሌላ ትርጉም በመስጠት joao de Barros የኢትዮጵያ ነገሥታት ዋና ከተማ እንዳልነበራቸው አድርጎ  እንደጻፈ ያቀርባል። የጃወ ደ ባሮስ ጽሑፍ ዋናው የተጠቀሰበት አውድ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለእደጥበብ ስለነበራቸው ዝቅተኛ ፍላጎት (ያውም ውሸት የሆነ) በተያያዘ እንጅ ሰለቋሚ ከተማ በተያያዘ ጉዳይ አይደለም። በተጨማሪም ጃኦ ደ ባሮስ የጻፈውን ስለአንድ የኢትዮጵያ ንጉሥ ከካምፕ ወደ ካምፕ በተለያዩ አውራጃዎች ቀደም ሲል በተጠቀሱት ምክንያት መዘዋወሩን እንጂ ዋና ከተማውን መቀየሩን አይደለም። ኦነጋውያን ታሪክ ነው ብለው የሚደርቱት  ካምፕ የተባለውን ዋና ከተማ፤ ስለአንድ ንጉሥ የጻፈውን ለኢትዮጵያ ነገሥታት በሙሉ የተጻፈ አስመስለው እየቀየሩ በማቅረብ ነው።
ሌላው ኢትዮጵያን የማያውቃትና ያልጎበኛት ጃዎ ደ ባሮስ በጻፈው የኢትዮጵያ ነገሥታት ለእደጥበብ (technology)፣ ለስነሕንፃና ለስነጥበብ ቅድሚያ አይሰጡም በሚል ያቀረበው ነገር ያረጀ ያፈጅ ነጭ ውሸት ነው። ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ ስለተቀበለው ትክክል ነው ማለት አይደለም። ስለአንድ ጉዳይ የታሪክ ፍርድ የሚበየነው በአንድ ነጠላ መረጃ ተመስርቶ ሳይሆን ብዙ ማገናዘቢያ ከተመረመረና በብዙ የተለያዩ መረጃዎች መደገፉን ወይም አለመደገፉን ካረጋገጡ በኋላ ነው። ከዓፄ ዳዊት ጀምሮ  እስከ ዓፄ ልብነ ድንግል የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ የእደ ጥበብ ሽግግር እንዲደረግ ወደ አውሮፓ ያልላኩት የመንግሥት ልኡክና  ያልደከሙት ድካም አልነበረም። “በራራ—ቀዳሚት አዲስ አበባም” ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ አስደናቂ ማስረጃዎችን ይዛለች። ዮሐንስ ደ ባሮስ አርመናዊው ትውልድ ያለው የኢትዮጵያ አምባሳደር ማቴዎስ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጥበብን በሚመለክት ዝቅተኛ ፍላጎት አላቸው የሚለው ሀሰት መሆኑን በዘመኑ የነበረው ዓጼ ልብነ ድንግል ለፖርቱጋል ነገሥታት የጻፈው ደብዳቤ ይመሰክራል። ዐፄ ልብነ ድንግል ከፖርቱጋል ነገሥታት የጠየቀው እርዳታ ጠቅላይ የእደ ጥበብ ሽግግር (complete technological transfer) እንዲደረግ እንደነበረ በጻፈው ዳብዳቤ ይነግረናል፤ “ሐውልት የሚቀርጹ፣ የእጅ ባለሙያዎች፣ መጽሐፍ አታሚዎች፣ ግንበኞች፣ መድኃኒት ቀማሚዎች፣ ሐኪሞች፣ ወርቅና ብር አንጥረኞች፣ ነፍጥ ሠሪዎችና እንዲሁም ለአገሬ የሚያስፈልጉትን ማናቸውንም ነገሮች መስራት የሚችሉ የጅ ጥበብ ባለሞያዎች እንድትልክልኝ እለምንህአለሁ። ወንድም ወንድሙን እንደሚለምን ሁሉ በዚህ ጉዳይ እንድትረዳኝ እለምንህአለሁ” (Alvares, The Prester John, vol. 2, 502-506)።
“የአማርኛ ግእዝ ነው ዳኛ”፣ “ሊቃውንት ይናገሩ፣ መጻሕፍት ይመስክሩ” እንዲሉ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችም ያሳዩት ይኽንኑ ሀቅ ነው። ለአብነት የሁለት ምሁራን ጥናቶችን እንጥቀስ። አንደኛው በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ግንኙነት በጥልቀት ያጠናቸው የቬረና ክረብስ ጥናት ነው (Verena Krebs, “Windows onto the World: Culture Contact and Western Christian Art in Ethiopia, 1402-1543”)። ሁለተኛ እና እጅግ በጣም አስደናቂ ጥናት እ.ኤ.አ. በ2017  ዓ.ም. የታተመው በመካከለኛ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያን እና የአውሮፓን ታሪክ በጥልቀት ያጠናው የጣሊያናዊው የማቴዎስ ሳልቫዶር ጥናት ነው (Matteo Salvador, The African Prester John and the Birth of Ethiopian European Relations, 1402-1555 (New York: Routledge, 2017)።
በራራ ከተማ አለማቀፋዊ ከተማ እንደነበረች፣ በአውሮፓና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ግንኙነት ማዕከል እንደነበረች፣ ከዓፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ መዲና እንደነበረች፣ በከተማዋም ከዓፄ ዳዊት ዘመን ጀምሮ የአውሮፓ ማኅበረሰብ ይኖርባት እንደነበረ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥናቱ በዝርዝር አስረግጦ የጻፈው ማቴዎስ ሳልቫዶር ነው። ይህን ለማወቅ የሚፈልግ ቢኖር “ሸዋ  ከ1400 እስከ 1526” (ማለትም ከዓፄ ዳዊት እስከ ዓፄ ልብነ ድንግል ዘመን) ብሎ የሰየመውን የመጽሐፉን 5ኛውን ምዕራፍ ይመልከት (The African Prester John፣ ገጽ 128-153). የበራራ ሌላው አስደናቂ ታሪክ በ1450 ዓ.ም. በተሳለው የዓለም ካርታ ውስጥ በደማቁ ተስላ መገኘቷ ነው። የበራራ ሌላው አስደናቂ ታሪክ ከተማዋ በግራኝ አሕመድ የሽብር ወረራ ከፈረሰችም ከብዙ ምዕት ዓመት በኋላ እንኳ በኢትዮጵያውያን ልቦና ታትማ መኖሯ ነው። ለምሳሌ በራራ ከተቃጠለች ከ150 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1681 ዓ. ም.  ኢትዮጵያዊው የቤተ አማራ የመካነ ስላሴው አባ ጎርጎሬዎስ እና ጀርመናዊ ኢዮብ ሉዶልፍ ስለኢትዮጵያ ታሪክ በጋራ በጻፉት መጽሐፍ የነገሥታቱ፣ የመሳፍንቱ ዋና መቀመጫ እንደነበረች መገለጿ ነው። ከሁሉም የሚያስደንቀው በዓፄ ምኒልክ ዘመንም የዳዊት ከተማ በራራ ታሪኳና ዝናዋ ሳይረሳ በኢትዮጵያውያን ልብ ታትሞ መኖሩና ዳህራዊት በራራ ለሆነችው ለአዲስ አበባ መቆርቆር ምክንያት መሁኗ ነው።
በኢያስፔድ ስም ኦነጋውያን በለቀቁት ጽሑፍ “በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የአቢሲኒያ ነገሥታት” “ቋሚ መናገሻ/ማዕከል እንዳልነበራቸው ከታደሰ ታምራት አንስቶ እስከ ላጲሶ፣ ከመርዕድ ወልደአረጋይ አንስቶ እስከ ሪቻርድ ፓንክረስት ድረስ አሉ የተባሉ የታሪክ ጸሐፊዎች የተስማሙበት ሀቅ ስለሆነ” ይላሉ። (የኢትዮጵያም የሀበሻም ነገሥታት ላለማለት ነው የውጭ ሰዎች  አቢሲኒያ በሚሉት ኢትዮጵያን የሚጠሩት እንጂ ራሱን አቢሲኒያዊ ብሎ የሚጠራ ንጉሥም ሆነ ሕዝብ አልነበረም። [አሁንም  በድጋሜ እጠይቃለሁ!  “የሰው ወርቅ አያደምቅ” ነውና ስማችንን እንኳ ለመጥራት እስከሚከብዳችሁ ድረስ እኛን እየጠላችሁ  ለምን ርስታችንን ለቃችሁ  ወደምትሄዱበት አትሄዱም?]  ይህ ኦነጋውያን ስለታሪክ ሙያ፣ ስለታሪክ የሙያ ስነምግባር መሰረታዊ የሆነውን ነገር እንኳ የማያውቁ መሆናቸውን ብቻ ነው የሚያሳየው።  የታሪክ እውቀት ያድጋል፣ ይሰፋል፣ ይቀየራል። ይህ የሚሆነው ደግሞ አዳዲስ መረጃዎች በአይነት እና በስፋት ሲገኙ ነው። ይህ  ባይሆን ኑሮ የታሪክ ትምሕርት ክፍል በቋሚነት እና በተደራጀ መልኩ አይሰጥም ነበር። የፕሮፌሰር ታደሠ ታምራት እና የፕሮፈሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ ጥናቶች ከታተሙ ብዙ ዘመን አልፏል። ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ታሪክ በቀዳሚዎቹ የታሪክ ምሁራን የማይታወቁ (እድሜ ለinternet እና ለdigital humanities ላመጡት አብዮት) በቀላሉ የሚገኙ፣ በቀዳሚ የታሪክ ምሁራን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት የነበረቸውን አስተሳሰቦች የሚሽሩ እጅግ ብዙ፣ የብዙ ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ተገኝተዋል።
ለምሳሌ ታደሠ ታምራት Church and State የተባለውን መጽሐፍ ሲጽፍ ፀፄ ዘረዓ  ያዕቆብ የጻፈውን በቅርብ ጊዜ  ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ ያሳተሙት  “ጦማረ ትስብዕት” ስለተባለው አስደናቂ መጽሐፍ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ይሕ መጽሐፍ በበራራ መጽሐፍ ላይ ታሪካቸው ስለቀረበውና ከበራራው ሊቅ ከግብጻዊው ዮሐንሥ ዘበራራ ጋር ስለሃይማኖት ጉዳይ ስለተከራከሩት  ስለገማልያል እና ዘሚካኤል ታሪክ የያዘ አስደናቂ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ በወቅቱ ስለማይታወቅ  ፕሮፈሰር ታደሰ አልተጠቀሙበትም። የፍራ ማውሮ የዓለም ካርታም እንዲሁ በፊት በቀላሉ አይገኝም ነበር። ዛሬ የካርታው ዲጅታል ቅጅ በየትምሕርት ተቋማቱ ይገኛል (እኔም አለኝ)። ታደሰ ታምራት በChurch and State መጽሐፍ ሌላው የሳቱት የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት በይኩኖ አምላክና በአምደ ጽዮን ዘመን  በወረራ እንደሰፋ መተረካቸው ነው። ይህ ግን ተረት ተረት ነው። ሌላውን ሁሉ ትተን ሶማሊያዊው  አጥኚ ዶክተር ዐሊ አብዲራህማን ኸርሲ እ.ኤ.አ. በ1977 ዓ.ም. በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ “The Arab Factor in Somali History: The Origins and Development of Arab Enterprise and Cultural Influences in the Somali Peninsula” በሚል ባቀረበው የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱ፣ የ10ኛ እና የ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዐረብ ተጓዦች የመዘገቧቸውን የታሪክ ማስረጃዎች በመጥቀስ ገጽ 117 ላይ፡- “Tenth and eleventh century Arab sources all describe Zaila as an Abyssinian Christian city which traded peacefully with the Yamani  ports across the Red Sea” በሚል ካቀረበው የታሪክ ጥናት እንኳን ሸዋ ከይኩኖ አምላክና ከአምደ ጽዮን ዘመን ሶስት መቶና አራት መቶ ዓመታት በፊት ዘይላ የኢትዮጵያ ከተማና  የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ይኖሩበት የነበረ የኢትዮጵያ ክፍል እንደነበር መገንዘብ ይቻላል።
ፕሮፈሰር ታደሰ ታምራት በተለምዶ የሰለሞናውያን ዘመን በሚባለው ወቅት ኢትዮጵያ በወረራ እንደሰፋች የጻፉት በወቅቱ የአረብ ምንጮችን ስላላገኙ እንጂ ማዕከሉን ሸዋ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሜን የመጣ ሳይሆን የደቡብ ኢትዮጵያ ሰዎች አምጽው ነበር  መንግሥቱን ወደነሱ በማምጣት የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ገዢ የነበረውን ይኩኖ አምላክን ያነገሡት። በመጨረሻው የዛጔ ንጉሥ ያመጹት እና በ1270 አሸንፈው ይኩኖ አምላክን ያነገሡት የጋፋት፣ የአማራ፣ የወጅ፣ የአርጎባ እና የጉራጌ ነገዶች (የወጅ ሰዎች ሰለተዋጉና ወጅ ጉራጌ ይኖር ስለነበረ) ናቸው። ሁሉም በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ነበሩ። እነዚህ ነገዶች የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት በኃይል አሸንፈው ከደቡብ ተነስተው ወደአገራቸው አመጡት እንጅ መንግሥት በኃይል ከሰሜን መጥቶ ማዕከሉን ሸዋ ላይ አላደረገም። ኦነጋውያን ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሜን ወደደቡ ሰፋ ይላሉ። ታሪኩ የሚያሳየው የያኔው የደቡብ ኢትዮጵያ ነገዶች የኢትዮጵያን መንግሥት ከሰሜን ወይም ከላስታ ላሊበላ ወደሸዋ ጎትተው እንዳመጡትና  የደቡብ ሰዎች ወደማዕከላዊ መንግሥት ሄዱ እንጅ የማዕከላዊ መንግሥት ከሰሜን ወደደቡብ በኃይል አልመጣም።
ስለዚህ አዳዲስ ማስረጃ  ሲገኝ የቀደመው ያረጀ ያፈጀ የታሪክ አሰተሳሰብ ይለወጣል። ፈረንሳይቷ የታሪክ ተመራማሪ ማሪ ሎ ዴራት የታደሠ ታምራትን መጽሐፍ በብዙ መልኩ አርቃ፣ አስተካክላ፣ በአፍጢሙ ደፍታዋለች። አዳዲስ መረጃም ባይገኝ የአንድ የታሪክ ምሁር እይታና ትንታኔ በየምክንያቱ ይቀየራል። ኢትዮጵያ በመካከለኛው ዘመን ቋሚ መዲና አልነበራትም የሚለው የቀደሙ ምሁራን በተገለጠላቸው፣ በተረዱትና በዘመናቸው በነበራቸው መረጃ መሰረት የደረሱበት ድምዳሜ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ፣ አዲስ መረጃ ተገኘ አልተገኘ የማይቀየር የቅዱስ መጽሐፍ ወይም  የእግዚአብሔር ቃል አይደለም። ኦነጋውያን ወዳልኖሩበት ዘመን 150 ዓመት ተጉዘው ከምኒልክ ዘመን ላይ ተቸክለው እንደቀሩት ሁሉ በዓለፉት 50 ዓመት ስለኢትዮጵያ ታሪክ የታሪክ ምሁራን ያሳተሟቸውን ተቆጥረው ያማያልቁ አዳዲስ የታሪክ መጽሐፍ ስላነበቡና ለማንበብም ፍላጎት ስለሌላቸው በበራራ የተገለጠውን ታሪክ አይቀበሉትም፤  በርግጥ የሚገርመን ቢቀበሉት ነበር።
በኢያስፔድ ተስፋየ ስም የወጣው ጽሑፍ ለብዙ ሺህ ዓመታት የኖረበትን በኦሮሞ ወረራ ዘመን የፈለሰውን የአማራውን ዐፅመ ርስት ዳሞት ውስጥ ኦሮሞ ነበር የሚል ሌላ ፈገግ የሚያሰኝ ፈጠራም ይዟል። “ሀሰት ተናግሮ የሰው እርስት ነቅሎ” እንዲሉ ይህ  የኦነጋውያን መለያ ጸባይ ነው። በተለይ የአማራ ዐጽመ ርስት ከሆነ አይለቁትም። ከላይ እንዳልኩት ኦነጋውያን አማራውን እጅግ ይጠላሉ፣ በወረራ የያዙትን የአማራውን ዓፅመ ርስት ግን ነፍሳቸው እስኪወጣድረስ  ይወዱታል። “ሀሰት እውነትን እንጨት ብረትን አይመክቱም” እንዲሉ ዳሞትን  [የዛሬውን ወለጋን] የኦሮሞ የጥንት ርስት ለማድረግ መሞከር ከንቱ ምኞት ነው። የኦነጋውያን የውሸት ክምር የሚጀምረው ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ኦሮሞ ዳሞትና ሸዋ ውስጥ ይኖር ነበር፣ የኢትዮጵያ ነባር ሕዝብ ነው በማለት ነው። መረጃ አድርገው ያቀረቡትን ቅራቅንቦ ለአብነት ጥቂቱን የመረመርን እንደሆነ የአእምሮ ዝግመት ያለበትን ሕጻን እንኳ የማያሳምን ትርክት ነው።
በሜጫ ኦሮሞ የጥንት አጽመ ርስቱን በ16ኛው ምዕት ዓመት ቢነቀልም የዳሞት የጋፍት እና የዳሞት የአማራ ሕዝብ ጀግና ጥንታዊ ነው። ዳሞቶች ዘማቾች፣ ወታደሮች ነበሩ። “ዳሞት እዳው ሞት፣ መብሉ ዱቄት” የሚባለው የጥንት ብሂል ይህንኑ የሚያጠናክር  ነው።  ኦነጋውያን ዳሞት ውስጥ ኦሮሞ ይኖር ነበር ለሚሉት ተረት መረጃ አድርገው ያቀረቡት የዳሞት መሪ የነበረው ሞተለሚ ቃሉ ኦሮምኛ ነው ከሚለው ተነስተው ነው። ሞተለሚ በአምደ ጽዮን ዘመን የነበረው የዳሞት መሪ ስም ነው። እነሱ ግን ቃሉን ኦሮምኛ ለማስመሰል ሞተለሚን ሞቲ ለሚ (mooti lammi) ማለት ነው፣ ትርጉሙም “የአገሩ ንጉሥ” ማለት ነው ይላሉ። አንኮበርንም የኦሮሞ ለማድረግ ጥንት ይኖር የነበረ ኦሮሞ ነው ይሉና መረጃ አድርገው የሚያቀርቡት ግን  በምኒልክ አያት በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን ሽዋን ጎብኝቶ የነበረው Charles Johnston የሸዋ ሰዎች ነገሩኝ ብሎ የጻፈውን ተረት ነው። ኦነጋውያን የታሪክ ምሁራን ሁሉ መረጃ አድርገው የሚያቀርቡት እንደዚህ ያለውን ቅራቅንቦ ነው። አንድ ቃል የሆነውን ሞተለሚን በመነጣጠል ሞቲ ለሚ የሚያደርጉት የኦሮሞኛ ቃል እንዲመስልላቸው ነው። በዚሕ መንገድ ከሄድን “መተማን” ሞቱማ፣ ምንጃርን መነ ጃራ፣ እናውጋን እነ አጋ እያሉ ይቀጥላሉ። ዝቋላንም የኦሮሞኛ ቅርጽ ለማስያዝ “ጩቃላ” እያሉ በመጥራት ሲጃጃሉ ይውላሉ። “ሞኝና ብርድ ያስቃል”፤ “መላጣ ሰው የፀሐይ ወዳጅ ነው ያለውን ኹሉ ያሳያታልና” የሚባሉ ስነቃሎች አሉ። ዝቋላን የኦሮሞኛ ቅርጽ ለማስያዝ የሄዱበት ርቅትና መጋጋጥ ሞኝነታቸውን ግልጥልጥ አድርገው ያሳዩበት ነው።
አንድ ቃል የሆነውን  ሞተለሚን ኦሮምኛ ለማስመሰል ሞቲ ለሚ (mooti lammi) አድርገው ሲበልቱና የታሪክ ማስረጃ  ለማድረግ ሲሞክሩ ሞተለሚ የሚለው ስም  መቶ ሎሚ፤ መቶ ለማ፤ መጥቶ ለማ፤ ሞቶ ለማ ወዘተ ወደሚል  የአማርኛ ፍቺ ተሸንሽኖ ቃሉ የአማርኛ ቃል ነው የሚል  ክርክር ሊቀርብ እንደሚችል አያስቡም።
ሌላው ቢቀር ሞተለሚ ኦሮሞኛ ነው ቢባል እንኳ በታሪክ ከተመዘገበው፣ በሰፊው ከሚታወቀው የኦሮሞ ታሪክ ጋር በሁለት ምክንያት ፍጹም ይቃረናል። አንደኛው ምክንያት ኦሮሞዎች በወራሪነት እና በሰፋሪነት ወደኢትዮጵያ ከገቡ ጀምሮ እስከ 19ኛው ምዕት ዓመት ድረስ የሚታወቁበት የፖለቲካ ድርጅት ዲሞክራሲያዊ ነው እየተባለ የሚወራለት፣ እጅግ የሚኮሩበት፣ በዓለም ቅርስነት ባስመዘገቡት፣ 28 የኢትዮጵያ ነገዶችን ባጠፋው በገዳ ነው። የገዳ ድርጀት ደግሞ የንጉሣዊ መንግሥት አደረጃጀት ከመፈጠሩ በፊት የነበረ ሥርዓት ነው። የጥንቱ የዳሞት ንጉሥ ሞተለሚ ኦሮሞ ነው ከተባለ ኦሮሞዎች የንጉሣዊ መንግሥትነት ስልጣኔ ታሪካቸውን ትተው ወድ ቅድመ መንግሥት ድርጀት ወደሆነው ወደገዳ ድርጀት የኋልዮሽ አድገዋል ማለት ነው። ከመንግሥትነት ስልጣኔ ታሪክ ወደቅድመ መንግሥት ድርጅት ያደገ ሕዝብ ከኦሮሞ በቀር እስከ አሁን በዓለም ታሪክ ታጽፎ ያገኘነው የለም።  ለነገሩ የአማራን ዐጽመ ርስት የኦሮሞ የሚያደርግ መረጃ የሚመስል ተልካሻ ነገር ከተገኘ ገዳ ምን አባቱ ነው።
ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት በዳሞት አውራጃ በስፋት የሚኖረው የጋፋት-የአማራ ሕዝብ እና የአማራ ሕዝብ ነው።  (C. CONTI ROSSINI, Gadla Yared, 1904, texte, p. 22/23, traduction, p. 24)። ከጥንት ጀምሮ ኦሮሞዎች በአውራጃዎች በሰፊው መኖረ እስከጀመሩበት እስከ 17ኛው ምዕት የነበረውን የዳሞት ታሪክ  በሰፊው ያጠናቸው ፈረንሳይቷ የታሪክ ተመራማሪ አይዳ ቦውንጋ ስትሆን የጥናቷ ርዕስ  “Le Damot dans l’histoire de l’Éthiopie (XIIIeXXe siècles): Recompositions religieuses, politiques & historiographiques” በሚል  በUniversity of Paris  እ.ኤ.አ. በ2013 ያጠናቀቀቸው PHD dissertation ነው። የአይዳ የምርምር ሥራ ዓላማ የአማራውን ርስት የመንቀል ልክፍት እንዳደረባቸው እንደ ኦነጋውያን አገሩን ለመውረስ ሳይሆን በታሪኩ በመደነቅ ያጠናችው ጥናት ነው። ዳሞት እና ቢዛሞ የአማራ/የጋፋት አጽመ ርስት ለመሆኑ አይዳ በጥናቷ የጠቀሰቻቸውን የጽሑፍ የታሪክ ምንጮች ማየት ይቻላል። አይዳ ከአምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተጻፉትን  ታሪከ ነገሥቶች፣ ገድላትን፣ የአውሮፓ ተጓዢዎች የጻፏቸውን የታሪክ ምስክሮች እና የግራኝ አሕመድን የጦርነት ታሪክ የጻፈውን የአረብ ፈቂሕን መጽሐፍ በዋቢነት ዘርዝራለች። ሁሉም መረጃዎች የሚያሳዩት ዳሞት የጋፋት/የአማራ ዓጽመ ርስት እንደነበር ነው። ገድለ ያሬድ የዳሞት የጥንት ሕዝብ የጋፋት ሕዝብ እንደሆነና የዛግዌ ነገሥታት ወደአውራጃ ዘምተውበት እንደነብረ ይነግረናል።
በዳሞት ይኖሩ የነበሩት ተዋቂ ጋፋቶችም ከ14ኛ ክፍለ ዘምን ጀምሮ እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በተጻፉ የተለያዩ የታሪክ ምንጮች ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። ከሁሉም የታሪክ ምንጮች ይልቅ ሰለጋፋቶች በጣም ዝርዝር መረጃ የያዙት ለዐፄ  ይስሐቅ በጥንት አማርኛ የተገጠመ የዘፈን ግጥም፣ የአፄ ሰርፀ ድንግል፣ የአፄ ሱስንዮስ እና የአፄ ኢያሱ ታሪከ ነገሥቶች ናቸው። ለይስሀቅ በተገጠመው የዘፈን ግጥም ከተዘረዘሩት ውስጥ ለምሳሌ ገምቦ፣ሻትና ዜት ይገኙበታል። ይህን ለማወቅ የሚሻ ቢኖር የአይዳን የዶክትሬት ጥናት ያንብብ።
ስለዳሞት በጣም ዝርዝር መረጃ የያዘው ገድለ ተክለ ሃይማኖት (1214-1313) ነው። ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ለዳሞት ሕዝብ ክርስትና አስተምረዋል። ነገር ግን የዳሞት ክርስትና ከተክለ ሃይማኖት ይቀድማል፣ ከጋፋት ሕዝብም በተጨማሪ የአማራ ሕዝብ ይኖርበት ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰው በመካከለኛ ዘመን የተጻፈው ገድለ ያሬድ የዛጔ ነገሥታት ወደዳሞት ዘመቻ ያደርጉ እንደነበረ ይነግረናል። ክርስትና ሃይማኖት ዳሞት የተሰበከ ምን አልባት በዚሕ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ተክለ ሃይማኖት ዳሞት ታቦት አግኝተው እንደነበረ ገድላቸው ይነግረናል። ክርስትና እንዲስፋፋ የረዳውም አማርኛ ቋንቋ በሰፊው መነገሩ ነው። ተክለ ሃይማኖት ካጠመቋቸው የዳሞት መኮንኖች ውስጥ አንዱ ድርዓ አሰገድ ሲሆን ጸሐፌ ትዕዛዝ የሚል ማዕረግ ያለው ነበር (ወመኮንኖሙ ጠሐፈዘዝ [ጸሐፌ ትእዛዝ] ዘይሰመይ ድርዓ አስገድ” ያላል ገድሉ)።
ድርዓ አስገድ ለክርስትና አዲስ እንዳልነበረ ማስረጃ ደግሞ የሚከተለው ነው፤
(“ይህን በሰማ ጊዜ የአገሩ መኮንን ደነገጠ፣ ከፊቱም ሰገደለት፤ ‘በሰማያት የምትኖረው እኛ ግዝሐር [እግዚአብሔር ለማለት ነው] የምንልህ አምላክ ነህን?’” (“‘ወሶበ ሰምዐ መኮንነ ሀገር ደንገፀ ወሰገደ ቅድሜሁ ወይቤሎ አንተኑ አምላክ ዘንብሎ ግዝሐር ዘይነብር ውስተ ሰማይ’”)። (Getatchew, EMML 1834, Gadla Qedusan, Hayq Estifanos, 86b and 87b) ይህ ዝርዝር በራራ-ቀዳሚት አበባ ምእራፍ 2 ላይ በሰፊው ተገልጿል።
ድርአ አሰገድ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ተክለ ሃይማኖት ታምራት ሲያደርግ አይቶ እንደሆነ ገድሉን ጠቅሶ የበራራ-ቀዳሚት አበባ ጸሐፊ በሰፊው ተንትኖታል። “እኛ ግዝሐር የምንለው” ማለቱ ድርአ አሰገድ ክርስትና አዲስ እንዳልሆነበት ያስረዳል። ተክለ ሃይማኖት ዳሞት ውስጥ ታቦት አግኝተው እንደነበረ በገድሉ ተጽፎ ይገኛል። ነገር ግን የዳሞትን የክርስትና ጥንታዊነት የሚያስረዳልን ዐፄ አምደ ጽዮን በ1308  ዓ.ም. ዳሞት ዘምተው በነበሩበት ጊዜ ያገኙት ታቦት ነው። ታቦቱን ኃይቅ እስጢፋኖስ አምጥተው እንደተከሉት ንጉሡ ያጻፈው ጥሬ ምንጭ  እንዲህ ይነግረናል፦
“ወዘኢየሱስሂ ታቦት ዘአምጻእክዎ እም ዳሞት ወአንበርክዎ ወስተ ዘጌት መካን ወሀብኩ ወአጕለትኩ ዓነ ዓምደ ጽዮን ንጉሥ ወስመ መንግሥትየ ገብረ መስቀል። ሠለስተ ጒልተ ዘገይት፣ ጺሎት፣ ገንደይት። ከመ ይምሐረኒ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ አመ እቀውም ቅድሜሁ ወከመ ይሰረይ ኅጢአትየ በብዝኅ ምሕረቱ ወከመ ያኑኅ መዋዕልየ ዘእንበለ ደዌ ወሕማም በዳኅን ወበሰላም። ወዘንተ ሠለስተ ጒልተ ዘወሀብኩ ለኢየሱስ ዘሄዶ ወዘተአገሎ ወዘገፍዖ እመሂ ሐፃኔ ሰገራት ወእመሂ አቃንጸን ኵሉነ ኮነ ከዊኖ በቅድመ አብ፣ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ውጉዝ ይኩን አሜን በአፈ ፫፻፲ወ፰ ርቱዓነ ሃይማኖት ውጉዘ ይኩን አሜን።” (Getachew, EMML 1832, Arba’ettu Wangel, Hayq Estifanos, f29a)”
ትርጉም፤ 
ከዳሞት ያመጣሁትን የኢየሱስን ታቦት በመካነ ዘጌት ውስጥ አስቀመጥኩት። የመንግሥት ስሜ ገብረ መስቀል የሆነው እኔ ዓምደ ጽዮን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመጣ በቀኙ እቆም ዘንድ፣ በብዙሕ ምሕረቱ ኅጢያቴን ያስተሰረይልኝ ዘንድ፣ በዘመኔ ያለሕማም እና ደዌ በሰላም እና በጤና ያኖረኝ ዘንድ ዘገይት፣ ጺሎት [እና] ገንደይትን ሶስት [መሬቶች] ጉልት አድርጌ ሰጥቼ ጎለትኩ። እነዚህን ሶስት ጉልቶች ለኢየሱስ ሰጠሁ። ይህንን የቀማ ወይም የተቃወመ ወይም የገፋ ሐፃኔ ሰገራትም ሆነ አቃንጸን ሁሉም በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ፊት የተወገዘ ይሁን፣ ሃይማኖታቸው በቀና በ318 [የቤተ ክርስቲያን አባቶች] አፍ የተወገዘ ይሁን። አሜን።
ከተክለ ሃይማኖት በኋላ ዳሞት ክርስትና እንዲያስተምር በዓፄ አምደ ጽዮን ዘመን በነበሩት በአቡነ ያዕቆብ የተመረጠው መድኃኒነ እግዚእ (አንዳንድ ምንጮች አድሃኒ የተባለ መነኩሴ ነው ይላሉ) ናቸው። ስለዚህ  ጉዳይ ፈረንሳይቷ የታሪክ ተመራማሪ ማሪ ሎ ዴራት እና አይዳ በሰፊው ጽፈዋል።  (Derat, Le domaine des rois éthiopiens, chapters 3 and 6; Lusini, Studi sul Monachesimo, chapters 2-4) እነመድኃኒነ እግዚእ ከአማርኛ ኛ ቋንቋ ውጭ እንዳስተማሩ የሚያስረዳው ነገር የለም።
አምደ ጽዮን በ1308  ዓ.ም.  በኋላ ዳሞትን በቀጥታ ያስተዳደሩት በንጉሡ በሚሾም  መኮነን አማካኝነት ነው። ከ1308 በኋላ የዳሞት ንጉሥ  ወይም ሞቲ የሚባል የለም። ኦነጋውያን የኢትዮጵያን ምንጮች ጠቅሰው ሞተለሚን ኦሮምኛ ለማስመሰል ሞቲ ለሚ (mooti lammi) ወይም ንጉሥ ለሚ የሚሉት የሚጠቅሷቸው የኢትዮጵያ ምንጮች በዘመኑ ዳሞት የሚተዳደረው በንጉሥ ሳይሆን በንግሡ በሚሾመው መኮነን አማካኝነት መሆኑንና የዳሞት ሠራዊትን የሚመራው እራሱ ንጉሡ እንደሆነ እየነገሯቸው ነው። ለዚህ አብነት የሚሆነው በ1324 ዓ.ም.  ከይፋቱ ሽፍታ ከሰብራዲን ጋር ሲዋጋ ንጉሡ የመራው የዳሞትን ጦር መሆኑን ማውሳቱ በቂ ነው። በራሳቸው መስፍኖች የሚተዳደሩ ሀድያ እና ይፋትም  ነበሩ። የዳሞት አስተዳዳሪ አንዳንዴ ዳሞት ጽሐፌ ላም ሌላ ጊዜ ቢትወደድ ይባላል። ከዚያም ቀጥሎም የጎጃም እና የዳሞት አስተዳዳሪ ማእረግ ራቅ ማሰሬ ሆነ። አይዳ በጥናቷ እንዳረጋገጠችው ከ1460 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አጼ ሱስንዮስ ዘመን  ደረስ ገዢው ጸሐፌ ላም ይባል ነበር።
ጀርመናዊ የሕግ ታሪክ ተመራማሪ ጀ. ቫሬንበርግ ባሳተመው በአምደ ጽዮን ዘመን በተጻፈው በስርዓተ መንግሥት ላይ የሚከተለውን እናገኛልን፣ 
 “ወአዲ ናየድዕ በበክፍላቲሆሙ አህጉራተ ወዘከተማ ዣን ቤት ጠባቂ ምዝክር ዘግራ ዘውስጥ መጓዝት። ዳሞት ጻፈ ላህም፤ እናርያ፣ ቀንድሂ፣ ኮንትንሂ፣ ዜት፣ ማንጥራ፣ ገደሉታ፣ ቢዛሞ፣ ኮንች፣ ከንምቦ (ገንቦ የሚባለውን የጋፋት ወረዳ ያሁኑ ወለጋ ውስጥ) ወኩሉ ጋፋት ዘማዕዳተ ጉደር። [ J. Varenberg, 12]።  ጸሐፈ ላሙ እነዚህን ሁሉ ያስተዳድር ነበር። ብዙዎቹን ወረዳዎች ኦሮሞዎች ሲወሯቸው ስማቸውን ቢቀይሯቸውም ኮንች ግን  እስካሁንም አለ። ሌላው የዳሞት ክፍል የነበሩት ቢዛሞና ሻት የሴት ወይዘሮች አገር ተብለው ከተዘረዘሩት ጋር እናገኛቸዋለን። “ የግራ ዌዛዝር” አገሮች ተብለው የተዘረዘሩት እኒህ ናቸው፣ “የግራ ዌዛዝር ሊቀ ማእምራን ጽራዠ ማሰሬ ባዕል ተከል፣ ገነተ ጊዮርጊስ፣ መራሕ ቤቴ፣ ቢዛሞ፣ ሻት፣ በድል ወጻት፣ በድል ጉሜ፣ አትሮንሰ ማርያም፣ ግሼ። [ J. Varenberg, 12]።
ስለዳሞት የተጻፉ አንዳንድ ምንጮች አካባቢውን ብሔረ/ደወለ አግአዚ ብለው ይጠሩታል። ስለዚህ ስያሜ አይዳ  ቀደም ብየ የጠቀስሁት ጥናቷ ገጽ 275 ላይ በሰፊው ታስረዳለች። አግአዚ በአክሱማውያን እና ከአክሱማውያን ዘመንምን በኋላ የነበረ ስያሜ ነው። ኢዮብ ሉዶልፍም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የአጋዚያን አገር ይላሉ ይለናል። (J. LUDOLF, Histoire de l’Éthiopie, vol. 1, 2009, p. 31, note 4)።
እንግሊዛዊ ወሊስ በጅ ያሳተመው በዘመኑ የተጻፈው የአቡነ መባ ጽዮን ገድል የሚከተለውን ይነግረናል፣ 
“ወእምዝ ተንሥአ ተንሥአ ወሖረ መንገለ አጋዕዝእ አመ ፳ወ፪ለወርኃ የካቲት በእለተ ሰኑይ ወተራከብዎ በፍኖት ብዙኃን ጋፋት በሥምረቱ ለእግዚአብሔር እንዘይወጽኡ ኀበ ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ ከመ ይትመዝገኑ በኀቤሁ በእንተ ዘተጠምቁ ወአምኑ በስመ ሥላሴ በውእቱ መዋዕል”)።
ትርጉም፤ 
ገድሉ መባ ጽዮን በየካቲት 22 ቀን ወደአጋዚያን አገር ተነስቶ ሄደ፣ በመንገዱም ንጉሡን ዘርአ ያዕቆብን ለማግኘት ይጓዙ የነበሩትን ብዙ ጋፋቶችን አገኝ ይለናል። መባ ጽዮን ጋፋቶችን እንዲያስተምር በንጉሡ የተሾመ ነው። The lives of Mabâ’ Sĕyôn and Gabra Krĕstôs. The Ethiopic texts ed. with an English translation and a chapter on the illustrations of Ethiopic mss., by E. A. Wallis Budge. With ninety-two colored plates and thirty-three illustrations፣ 25 folio 68a)።
ሌላው በራራ ከተማ በንግድ ስራ ላይ ይኖር ለነብረ ነጋዴ የተጻፈ ሰነድ የሚከተለውን ይነግረናል፣ 
“ወሀሎ አሐዱ ነጋዲ በደወለ አግዓዚ ዘይፈርሆ ለእግዚአብሔር ወያፈቅራ ፈድፋደ ለእግዝዕትነ ቅድስት ድንግል በክልኤ ታቦተ መንፈስ ቅዱስ ማርያም ማሪሃም። ወአሐተ ዕለተ ተሳየጠ ገብረ እምስያጠ ዳሞት በንስቲት ንዋይ። ወሆረ ለአርብሖ ውስተ ምስያጠ በራራ በዕለተ ሀሙስ።” [Getatchew, “From the Markets of Damot to that of Barara,” ገጽ 176]
ትርጉም፤ 
“የማርያም ተአምር። አማላጅነቷ ከወዳጇ ከሃብተ ኢየሱስ ጋር እስከ ዘለዓለም ይሁን። አሜን። የማርያምን ተአምር ስሙ። ድርብ ድንግል የሆነች የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነች የእመቤታችን የማርያም ማሪሃም እጅግ ወዳጅ የሆነ ነጋዴ በአግዓዝያን አገር (ኢትዮጵያ) ይኖር ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ከዳሞት ገበያ በርካሽ ዋጋ ባሪያ ገዝቶ ለማትረፍ ሀሙስ ዕለት [ወደሚውለው] ወደበራራ ገበያ ሄደ።”
በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው ገድለ መርሐ ክርስቶስም እንደቀረበው በአዳል ሽፍቶች ተፈንግሎ በታምር ያመለጠ ክርስቲያን አገሩን የአጋዚያን አገር ይላታል፣ “ ወእንዘ ይወስድዎ ውስተ ምስያጥ ይቤ ውእቱ ብእሲ ኦ አምላክ አቡየ መርሀ ክርስቶስ ተመጠዋ ለነፍስየ እንዘ ክርስቲያናዊ አነ እስከ ማ ዕዜኑ አመከኒ ናሁ ኮነ በሀቤየ ኵሉ ዓለም ጽልመተ። እምይእዜ ኢይሠርቅ ኀቤየ ፀሓይ ወኢይሬእያ ለሀገርየ ዓግዓዚት። [ገድለ መርሀ ክርስቶስ፣ ገጽ 131]። ይህ የሚያሳየው አግአዚያን የሚባሉት ጋፋቶችን  ጭምር እንደነበር ነው።
ክርስትና በሰፊው ከመሰበኩ በፊት እና ከተሰበከም በኋላ በሸዋ እና በዳሞት ጋፋቶች፣ ሞተለሚ እና አማሮችም የሚያመልኩት አምላክ ደስክ የተባለውን አምላክ ነው። (Ayda, 150-152). ዐፄ  ዘርዓ ያዕቆብ ይኽን አምላክ ለማጥፋት ብዙ ደክመዋል። የንጉሡ ታሪከ ነገሥት የሚከተለውን ይነግረናል፤ “ወኮነ በመዋዕሊሁ ለንጉሥነ ዘርአ ያዕቆብ ድንጋጼ አቢይ ወረአድ ላዕለ ኵሉ ሰብእ ዘኢትዮጵያ በእንተ ፍትሐ ኵነኔሁ ወኃይሉ። ወፈድፋደሠ በእንተ እለ ይብሉ ሰብእ። ሰገድነ ለደስክ ወለዲያብሎስ”። [ J. PERRUCHON, Les chroniques, 1893, p. 4. (አይዳ 259)]  እንግዲህ ደስክ አማራውም፣ ጋፋቱም፣ ሞተለሚም የሚያመልከው ከቅድመ ክርስትና ጀምሮ የነበረ አምላክ የኦሮሞዎች አምላክ ከሆነው ዋቃ ከሚሉት እንኳ የሥም መመሳሰል የለውም።
ገድለ ተክለ ሃይማኖቱም መተሎሜ ይለዋል እንጅ ሞቲ ለሚ አይለውም፤ እናቱንም እስላንዲን ይላታል፣ “ወእንዘ ሀለው ከመዝ ተንሥአ ፩ እልው ገብር ዘስሙ መተሎሜ ወስማ ለእሙ እስላንዳኒ።” [E.A.W. BUDGE, The life of Takla Haymanot, vol. 1, 1906, texte, p. 8, traduction, p. 21]። ገብር ባርያ ማለት እንደሆነ ያስተውሏል። ገድለ ያሬዱ ደግሞ ስሙን ማታሎሚ የተባለ የዳሞት መኮነን ይለዋል። [C. CONTI ROSSINI, Gadla Yared, 1904, texte p. 23, traduction, p. 22።] ለአምደ ጽዮን በተገጠመው የአማርኛ ግጥም አጻጻፉ ሞት ለሚ ነው እንጂ ሞቲ ለሚ አይደለም። [GUIDI, ‘‘La canzoni’’, (1889), p. 64, chant n°10, lignes 38-39]።
የአምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥትም መጥቀስ ይቻላል። የይፋቱ መስፍን ሰብረዲን በንጉሡ ላይ ሸፍቶ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ላይ የራሱን ሹሞች እስተዳዳሪ አድርጎ ለመሾም እቅድ እንደነበረው የአምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥት ይነግረናል። የሰብረዲን እቅድ በመስፍን የሚገዙትን፣ በመስፍን፣ በነጋሺ የሚገዙትን በነጋሺ፣ በጸሀፊ ላም የሚገዙትን የራሱን ጸሐፊ ላህም ለመሾም ነበር። በዚህ መሰረት በዳሞት መኳንንት እና መሳፍንት፣ በወረብ፣ በወጅ፣ በግራርያ፣ በእንደገብጣን፣ በሙገር፣ በጽላልሽ እና በሌሎችም ብዙ አውራጃዎች አንዳንድ መስፍን፣ በቤተ አማራ እና በአንጎት ጸሐፈ ላም፣ በጎጃም ነጋሺ ለመሾም እቅድ ነበረው። [Marrasini, Lo Scettro e La Croce, 52] ሞተለሚ የዳሞት አውራጃ ንጉሥ የማዕረግ ስም ቢሆን ኑሮ ስሙ ሞተለሚ ተብሎ የናትና ያባቱ ስም አይጠቀስም፤  ልክ እንደጎጃም፣ እንደ አንጎት እና ቤተ አማራ ሁሉ ሰብረዲን በዳሞት ሞተለሚ የመሾም እቅድ ይኖረው ነበር።  ስለዚህ ሞተለሚ የማይነጣጠል የገዢው ስም እንጂ የማዕረግ ስም አይደለም። የሞተለሚ አባቱም እናቱም በየገድላቱ ተጽፈው እናገኛለን። ሞተለሚ የማ እረግ ስም ከሆነ የሰውየው ስም ሊጠቀስ ይገባል። ለምሳሌ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሚለውን እንይ። ንጉሠ ነገሥት የሚለው ማዕረግ ነው። ኃይለ ስላሴ የሰውየው ስም ነው። ወደሞተለሚ ስንመጣ ከዚሕ ተቃራኒ ነው። መተለሚ ማዕረጉ ከሆነ ለምን የሰውየው ስም አልተመዘገበም የሚል ጥያቄ ይነሳል ብለው ኦነጋውያን አያስቡም።
የግራኝ አሕመድ የዘመቻ ፀሐፊ አረብ ፈቂህ ስለዳሞት እና በዳሞት ስለሚኖሩት ሰለጋፋቶች በሰፊው ጽፏል። ከምባታ በስተደቡብ የሚያዋስነው ገንዝ የተባለው የጥንት አውራጃ ጋፋቶች የሚኖሩበት የዳሞት ወረዳ እንደነበረ አረብ ፈቂህ ይነግረናል። አፄ ሰርፀ ድንግል በዳሞት ብዙ ጊዜ አሳልፏል። ሕይወቱም ያለፈው በ1589 ዓ.ም.  ሻት (ምናልባት ያሁኑ ሻምቡ) በተባሉት ጋፋቶች መኖሪያ ወረዳ በዘመቻ ላይ እንዳለነው። በሰርፀ ድንግል ዘመን ማለትም በ1560ዎቹ ዳሞትን አዝማች ተክሎና አዝማች ፋሲሎ፣ በ1570ዎቹ ደግሞ ጸሐፌ ላም ተክለ ጊዮርጊስ አስተዳድረውታል። የጥንቱ ዳሞት የመጨረሻው አስተዳዳሪ ደጃዝማች አስቦ (አስበ ድንግል) ሲሆን ዘመኑም በ1580ዎቹ ነው። [  C. CONTI ROSSINI, Historia regis, 1907, 17፣ 35፣ 51]  በአይዳ ጥናት ከገጽ 306-359 እንደቀረበው የሜጫ ቦረና ኦሮሞ ጎሳዎች የዳሞት አማራና ጋፋት ሕዝብ የጥንት ዐጽመ ርስት በወራራ ይዘው ለብዙ ሺሕ ዓመታት ከኖሩበት አፅመ ርስታቸው ያፈናቀሏቸው ከ1580 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1607 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነው። የአይን እማኙ አባ ባሕርይ የዳሞት እና የሸዋ የጋፋት እና የአማራ ነባር እና እጅግ ጥንታዊ ሕዝብ አሳዛኝ ፍጻሜ በዜናሁ ለጋላ ክፍል 18 ላይ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፤
“ወሙላታ ዘቦረን አጽሐቦሙ ለክርስቲያን ዘዳሞት ወዘረዎሙ ወአጥፍአ ሀገሮሙ። ወኮኑ በድወ በዘመኑ ምድረ ሸዋ ወዳሞት።”
ትርጉም
የቦረን ሙልአታ የዳሞትን ክርስቲያኖች አዳከማቸው፣ በታተናቸው፣ አገራቸውን አጠፋው፣ በሱ ዘመን ሸዋና ዳሞት ምድረ በዳ ሆኑ።
በዚህ መልኩ የቦረን የኦሮሞ ጎሳዎች የሚፈናቀለውን አፈናቅለው፣ የሚገደለውን ገለው ከሞት የተረፈውን የሞጋሳ ልጅ አድርገው ማንነቱን አጥፍተው በአማራና በጋፋት ነባር ሕዝብ አጽመ ርስት ላይ እንደሰፈሩ ቀሩ። የጥንቱን ዳሞትና ቢዛሞ በውስጣቸው የሚገኙትን ወረዳዎችም  በኦሮሞኛ ስሞች ቀየሯቸው።
የጋፋትና የአማራ ሕዝብ ከጥንቱ ዳሞት በኦሮሞዎች ተግፍቶ የተሰደደ ወደጎጃም ነው። አዲሱን አውራጃቸውን በጥንቱ አገራቸው ስም  ዳሞት አሉት። በ1762 ዓ.ም. አካባቢ የአባይን ምንጭ ለማየት የመጣው  ታዋቂው ስኮትላንዳዊ ተጓዥ ጀምስ ብሩስ ጎጃምን በጎበኘበት ወቅት  የጋፋት አማርኛ  በሰፊው ይነገር ነበር። ጉብኝቱን ሲጨርስ የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል የሆነውን መጽሐፈ ሰለሞንን በጋፋት አማርኛ አስተርጉሞ ወደ አገሩ ይዞ ተመልሷል። መጽሐፉን ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሞ ያሳተመው ተዋቂው የጋፋትኛ፣ የአማርኛ እና የግዕዝ ቋንቋዎች ምሁር ወልፍ ሌስላዎ ነው። የጋፋትኛውን አንዱን ቅጠል ለአብነት አትሜው አለሁ። ስለጋፋት እና ጀምስ ብሩስ ካጻፈው ከጋፋትኛ መጽሐፍ ያገኘነውን ጋፋትኛና የአማርኛ ትርጉም ቀጥዬ ላቅርብ።
እነ አማርኛን፣ አርጎባን፣ ጉራጌን፣ ዛይንና ሀረሪን የሚጠቀልለው የኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች አቢይ ቅርንጫፍ የሆነው የደቡባዊው የኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች ወገንነቱ የማያጠራጥረው ጋፋትኛ ቋንቋ፣ ተናጋሪዎቹ አብዛኞቹ ወደ አማርኛ ተናጋሪነት ከፊሎቹ ደግሞ ወደኦሮምኛ ተናጋሪነት በመለወጣቸው፣ በጥቂት የውጭ ሀገር ተጓዦችና የስነልሳን ተመራማሪዎች በተሰነዱ ጥቂት መዛግብት ከተያዙት ጥቂት ምንባቦቹ በስተቀር ህልውናውን አጥቷል። ስለጋፋት ቋንቋ ምንነት የጩልቅታ ያህል ከሚያሳዩን ከነዚህ መዛግብት የተገኙ ሀረጎችን ወደ አማርኛ ተርጉመን ስንመለከት ለአማርኛ የነበረውን ቅርበት እንገነዘባለን፦
ጋፋትኛ
ለቡሽ አልጄ እከፍቲ ተነሤት። እጅጄ መከርቡሽ ያትሁዋጉ ዳጅ። ዜቤጄ መከርቡሽ ያትፈሉ ነቸው። እጅጄ ፀበጡመ ወደይከፍትሽ መራቸተ እከፍቲ ተነሤት ለቡሽ አልጄ። አልጄ ቡሽ አሖረ። ለቡጄ ደነፀፀቺ እመጸወትሽ የተነሠጉ። ዋሸሁመ ቀበፅሁኒ ጸራሁኒ አላምበላበለም። አገረኒ የሚአቅቡ አበዘቡሽ ደረሱኒ። ማፁኝ ጌሜሱኝ። ከመድሞጀ ላጀ ሰርነቂዬ ወሰዱ። (Wolf Leslau, Gafat Documents and Grammar, ገጽ 105፣ አምድ 8፣ መስመር 8 – 20)
ትርጉም
ለጓደኛዬ ልከፍት ተነሳሁ። እጄ ከርቤውን ደፋው። ጣቶቼም ከርቤ ተነከሩ። ለጓደኛዬ ልከፍት ተነስቼ እጄ በሩን ለመክፈት ተዘርግቶ ነበር። ጓደኛዬ ሄደ። ከቃሉ የተነሳ ልቤ ደነገጠች። ፈለግሁ አላገኘሁትም፤ ተጣራሁ አልመለሰም። አገር የሚጠብቁ ዘበኞች አገኙኝ። ደበደቡኝ፤ ገመሱኝ (ፈነከቱኝ)። ከገላዬ ላይ ልብሴን ወሰዱ።
ለዐፄ አምደ ጽዮን በዘመናቸው በነበረው አማርኛ የተጻፉላችውን የውዳሴ ግጥሞች አንብቦ የዚያ ጊዜው አማርኛ ከዛሬው አማርኛ ጋር ያለው ልዩነት ለሚያስደንቀው ሰው። አንባቢን  ከታች የታተመውን ጋፋትኛ ከዚያ ጊዜው አማርኛ ጋር እንዲያስተያየው እጋብዛለሁ። ዐፄ አምደ ጽዮን ዛሬ ተነስተው በዘመናቸው አማርኛ ቢናገሩ ከአሁኖቹ አማርኛ ተናጋሪዎች ይልቅ ከጋፋትኛ ተናጋሪዎቹ ጋር የተሻለ ሊግባቡ እንደሚችሉ አይጠረጠርም። በአምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥትር ጊዜ በነበረው አማርኛና ጋፋትኛ የነበረው ልዩነት ልክ በአሁኑ ጊዜ በጎጃም አማርኛና በጎንደር አማርኛ ወይንም ደግሞ በሸዋ አማርኛና በወሎ አማርኛ መካከል ያለውን ልዩነት ያሕል ነበር ብሎ መገመት ይቻላል።
እስከደርግ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ድረስ ደቡብ ምእራብ ጎጃም በሚገኘው በወምበርማ ወረዳ ውስጥ የጋፋት አማርኛ የሚችሉ በጣም ጥቂት አዛውንቶች ይኖሩ ነበር። የታሪክ ተመራማሪው ታደሰ ታምራት እኒህኑ አዛውንቶች አግኝቶ የተወሰኑ ቃላትን ለመመዝገብ ችሎ ነበር። (Taddese Tamrat, “Ethnic Interaction and Integration In Ethiopian History: The Case of the Gafat”, Journal of Ethiopian Studies 21 (1988): 121–154)
በአሁኑ ጊዜ በጎጃም የጋፋት አማርኛ ቀበሊኛው ቢረሳም ታሪኩ አልተረሳም። ጋፋት በጎጃም የደግነት ተምሳሌት ነው። አንድ ወንድ ሚስቱን “እሷ እኮ ሰው አይደለችም ጋፋት ናት”  ካለ በጣም “የዋህ፣ ደግ ናት” ማለቱ ነው። ትልቅ ሰው ሲሞት “ጋፋት” ሞተ ይባላል። ክስታኔና ጋፋትኛ እጅግ በጣም ተመሳሳይ እንደሆነ ሌስላው ጽፏል። በጉራጌኛ ጋፋት የሚለው ቃል ይታወቃል። ስለጋፋት የሚከተለውን የጉራጌ ስነቃል አግኝቻለሁ፤ “የዄተና ጋፋትም ኤምበሬ” (የእኩል ከሆነ “ጋፋት”ም አይኑረኝ”)። ጋፋት በጉራጌኛ ሰፊ ሜዳ ማለት ነው።
እንግዲህ! የዳሞት ታሪክ በአጭሩ ከፍ ሲል የቀረበውን ይመስላል። በእውነቱ  በታሪክ ምንጣፍ ተጉዘን ልንጠይቀው የሚገባ ተገቢው ጥያቄ   ኦነጋውያን በፈጠሩት ተረት ላይ  ተመስርተው የሚያስተጋቡት ልዩ ጥቅም የሚሉት የንቀት ጥግ ሳይሆን  አማራው (ጋፋቱ) ካሳ ይከፈለው፣ ርስቱ ይመለስለት የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው። ነገር ግን በነሱ ተብሶ የፈጠራ ታሪክ እየጻፉ  ባለርስቱን ዳግም ሲገሉት፣ ሲያጠልሹት ይውላሉ።
እንግዲህ! ኦሮሞ ኢትዮጵያን እንደወረረ ብቸኛውን የኦሮሞ ታሪክ ምንጭ አባ ባሕርይንና የአባ ባሕርይን ጽሑፍ ደግፈው የጻፉ የኦሮሞ ብሐርተኞችን ጭምር ጠቅሼ በጻፍሑት ታሪክ ላይ የተሰነዘረው ትችት ሲመረመር ከፍ ሲል በሰፊው እንዳቀረብሁት የፈጠራ ትርክት እንጂ አንዳች ታሪክ የለበትም። ጽሑፌን ከማጠናቀቄ  በፊት በጣም  የሚያስቀኝን  የኦነጋውያንና የተከታዮቻቸውን አንድ ሌላ ተቃርኖ ላንሳ።
ኦነጋውያን ለዲግሪ ማሟያና ለሌሎች ጥናቶቻቸው በብቸኛነትና በዋናንት የሚጠቅሷቸውን የኢትዮጵያ ምንጮችን ነው። እነሱ የሚጠቅሷቸውን የኢትዮጵያ ምንጮች ጠቅሰን እኛ ስንጽፍ ግን ተረት ተረት ነው ይሉናል። ኦነጋውያን አዙረው ማሰብ ስለማይችሉ የኢትዮጵያ ምንጮችን ተጠቅመው  የሚጽፉ ሰዎች የሚያቀርቡትን ታሪክ ተረት ተረት ነው ሲሉ እነሱ ራሳቸው የኢትዮጵያን ምንጮች እስከቻሉት ድረስ ዝቀው የጻፉት ወረቀትም ተረት ተረት እንደሆነና እኛ ስንጠቀማቸው ተረት ተረት እያሉ የሚያጣጥሏቸውን  የኢትዮጵያን ምንጮች ተጠቅመው ባቀረቡት ወረቀት ያገኙት ዲግሪና እድገትም የማይገባቸውና ሊነጠቁ እንደሚገባ አይገነዘቡም።
ከሁሉ በላይ የሚያስደንቀኝ <<የኛ>> የሚሉትን አንድም የተጻፈ የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ የማይችሉ ሰዎች ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የተጻፉ የኢትዮጵያ ምንጮችንና በዘመኑ በተመዘገቡ የውጭ አገር ምንጮች የሚደገፉ ታሪኮችን ዛሬ ላይ በሚፈጥሩት ትርክት ላይ ተመስርተው  የተፈተጉ የኢትዮጵያ ምንጮች ተረት ተረት ለማድረግ የሚያሳዩት ድፍረት ነው። እንደ ኢያስፔድ አይነት ለማሰብ ፍቃደኛ ያልሆኑ የኦነጋውያን ካድሬዎችና ደጋሚዎቻቸውም ይህ የኦነጋውያን ግብዝነት ተጋብቶባቸው ከኦነጋውያን ሰዎች ውጭ የኢትዮጵያ ምንጮችን ተጠቅመው ለነሱ የማይጥም ጥናት ካዩ  ከምላሻቸው ሁሉ የሚቀድመው  ምንጮችን ተረት ተረት ናቸው የሚል ነው። ደጋሚዎቹ  የኢትዮጵያ ምንጮችን ተረት ተረት የሚሏቸው ተረት ተረት እንደሆኑ ስላረጋገጡ ሳይሆን የኦነግን ትርክት ስለማይደግፉ ብቻ  ነው። እነዚህ ደጋሚዎች ሌላም ከኦነጋውያን የወረሱት ትምህርት አላቸው። ይህም የኦነጋውያንን ትርክት የማይደግፈውን ታሪኩ ሁሉ የኦሮሞን ሕዝብ የሚያንቋቋሽሽና የኦሮሞን ሕዝብ የሚሰድብ አድርገው በማቅረብ ጸሐፊዎችን ለማሸማቀቅ ይሞክራሉ። ሆኖም ግን ይህ አካሄድ ሀሳብ፤ እውነትና ማስረጃ የሌላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት የተባነነበት ስልት ነው።
እኔ ከቀናት በፊት ባቀረብሁት ጽሑድ ብቸኛውን ቀዳሚ የኦሮሞ የጽሑፍ የታሪክ ምንጭ የጋሞውን መነኩሴ አባ ባሕርይን በመጥቀስ  ኦሮሞ ፈረስ ግልቢያ የለመደው ኢትዮጵያን መውረር በጀመረ በአርባ አመቱ መሆኑን የጻፍሑትን ታሪክ መሞገት ያልቸሉትና  «የማይመቱት ልጅ፣ ሲቆጡት ያለቅሳል፣» ዓይነት የሆኑት ኦነጋውያንና ደቀ መዝሙሮቻቸው የኦሮሞን ሕዝብ እንዳንቋሸሽሁና እንደሰደብሁ አድርገው ጥላሸት ሊቀቡኝ  ሞክረዋል። እነዚህ ሰዎች አማራው በኦነጋውያን ከርስቱ ሰፋሪ ተብሎ ሲፈናቀል አይተዋል ወይም አፈናቅለዋል። አማራውን በርስቱ ሰፋሪ ሲሉ ያላፈሩት ሰዎች በማስረጃ ወራሪው ወራሩ  ሲባል  ግን የተሰደቡና የተንቋሸሹ ይመስላቸዋል። ሌላው ቢቀር የኦሮሞ ብሔተኛው ፕሮፈሰር  መሐመድ ሐሰን ኢትዮጵያን እንደወረረ “THE OROMO OF ETHIOPIA, 1500-1850 : WITH SPECIAL. EMPHASIS ON THE GIBE REGION” በሚል ርዕስ በጻፈው የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ወረቀቱ ገጽ 137፣ 138፣ 140፣ 147፣ 149፣ ወዘተ ላይ ጽፏል።  ይህን ታሪክ ግን ሌላ ሰው ሲያቀርበው  ኦሮሞ እንደተሰደበና እንደተንቋሸሸ አድርገው ያቀርቡታል።
እኔም በጽሑፌ ኦሮሞ ኢትዮጵያን መውረሩን ያቀረብሁትን የዛሬውን የኦሮሞ ትውልድ ሳይሆን ከገዳ ሜልባህ ዘመን ጀምሮ እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ድረስ ያለውን  በሉባዎች የተመራውን የኦሮሞ የገዢ መደብ ኢትዮጵያን የወረረበትን የታሪክ ዘመን ነው። በዚህ ዘመን ኦሮሞ ኢትዮጵያን እንደወረረ ከሁሉ በላይ የጻፉት እንደ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን አይነት የኦሮሞ ብሔርተኞችና እንደ ወለጋው ገዢ ቁምሳ ሞሮዳ አይነት የኦሮሞ ገዢዎች ናቸው። ይህንን በታሪክ የተደገፈ እውነት እኛ ስንናገረው ግን በኦነጋውያንና በደቀመዝሙሮቻቸው ኦሮሞን የሰደብንና ያንቋሸሸን፤ የደብተራ ታሪክ ያቀረብን ተደርገን ጥላሸት እንቀባለን።  ይህ ግን በተፈተጉ የታሪክ ማስረጃዎች የተመዘገበውንና ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እንድንረሳው ያደረጉንን ከ1514 ዓ.ም. — 1881 ዓ.ም. ድረስ ከባሌ በታች የተነሱ የኦሮሞ ሉባዎች ያደረሱትን የአራት መቶ ዓመታት ጥፋት፣ ግፍና በደል፤  ነባሮቹን የኢትዮጵያ ነገዶች ወረው በመደምሰስ በያዙት የነባሮቹ ርስት ላይ የሰፈሩትን ኦሮሞዎች ሕገወጥ ወራሪዎች መሆናቸውን የሚያሳዩ ታሪኮችን  የበለጠ እንድናቀርብ እንጂ ተሳቀን ትውልዱ እዚህ የደረሰበትን እንዳናሳውቅ ሊያደርገን ከቶ አይችልም።
በመጨረሻም ሳይመረምሩ ኦነጋውያን ያራገፉባቸውን የአህይነት ጭነት ተሸክመው እየዞሩ ወሬ ሲደግሙ ለሚውሉ የዋሆች “ላታድርበት አታምሽ፣ ለአዘልቅበት አትዋሽ” ፤ “መላዕክት የፈሩትን ሞኞች ይደፍሩታል፤ ማይምነት ለድፍረት፣ ፍቅረ ንዋይ ለክሕደት ይመቻል” የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ ልሰናበት!
ከላይ  የታተሙት ሁለት ዶሴዎች ናቸው። የመጀመሪያው ዶሴ የጋፋትኛ ጽሑፍና የአማርኛ ጽሑፍ መካከል ያለው ዝምድና  ምን እንደሚመስል አንባቢ እንዲያመሳክር ያያዝሁት ሲሆን  የተቀሩት ገጾች ደግሞ በጽሑፉ የተጠቀሰው ፖል ሔንዝ ለመለስ ዜናዊ የጻፈው ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው  በገጽ ሶስት መጫረሻና በአራተኛው ገጽ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው የተሰመረበት የደብዳቤው ክፍል በዚህ ጽሑፍ ቀደም ብዬ የጠቀስሁትን የፖል ሔንዝ የደብዳቤ የሚያሳይ ነው።
Filed in: Amharic