>
5:13 pm - Saturday April 19, 6600

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ግልብጥብጡን የሚያወጣው የአዲስ አበቤነት ንቅናቄ...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ግልብጥብጡን የሚያወጣው የአዲስ አበቤነት ንቅናቄ…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

ተደጋፊ ተደማሪዎች እንኳን ደህና መጣችሁ!
ከዛሬ ሁለት አመት በፊት “የአዲስ አበባ ግዛት የማስመለስ ንቅናቄ” ይፋ ስናደርግ ጥቂት የማይባሉ “ተደጋፊ ተደማሪዎች” ተሳልቀውብን ነበር። የዋሽንግተን ዲሲን “ግዛት የማስመለስ ንቅናቄ” ልምድ መውሰድ አለብን ስንል ” ይህ ሌላ፣ ያ ሌላ” በማለት ወርፈውን ነበር። የበርሊንን ልምድ በአካል ተገኝተን በመመልከት እኛም ይህን መንገድ መከተል አለብን ስንል እንደ ቅዠት ተቆጥሮብን ሲሾፍብን ነበር።
ዛሬ ቀኑ ደርሶ “ተደጋፊ ተደማሪው” ሂሱን በአግባቡ ሳይውጥ “የአዲስ አበባ ክልል ሎዲንግ…” ማለት ጀምሯል። እርግጥ ይሄ ሀይል የጀርባ አጥንት ስለሌለው እንደ ሐረግ ከአራቱ “የኦሮሙማ” ፍንካቾች አንዱ ላይ ተደግፎ ውሃ እየጠጣ የሚፋፋ በመሆኑ አሁንም በአቋሙ እምነት የሚጣልበት አይደለም። ነገ ተጠምጥሞ የተደመረበት ግንድ ሲቆጣው ከመሞት መሰንበት በሚል ወደ ቅርፊቱ ሊመለስ ይችላል። ይህም ሆኖ ለጊዜው ለያዘው አቋም ” ጐሽ!ጐሽ! በርታ!” ማለት ያስፈልጋል። እንኳን ደህና መጣችሁ! እግዜር ራሳችሁን ችላችሁ እንድትቆሙ ይርዳችሁ! ማለት ያስፈልጋል።
 “የምርጫ መወዳደሪያ ማኒፌስቶ” 
በዚህ አጋጣሚ ባልደራስ ከንቅናቄው ምስረታ ጀምሮ፣ በተፈጠረው አስገዳጅ ሁኔታ የፓለቲካ ፓርቲም ከሆነ በኃላ በፓለቲካ ፕሮግራሙም ሆነ ለጊዜው ምርጫው በመራዘሙ ይፋ ከማድረግ በተቆጠበው “የምርጫ መወዳደሪያ ማኒፌስቶ” አንዱ የትግል ማዕከል የአዲስ አበባ ክልልነት መሆኑን አውቃለሁ። በዚህ አጋጣሚ በባልደራስ ልክ በፕሮግራሙ ላይ ያስቀመጠ የፓለቲካ ፓርቲ ካለ ለመስማትና ለማመስገን ዝግጁ መሆኔን ከወዲሁ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።
 
የኦሮሙማን ተስፋፊነት መግታት 
 በሌላ በኩል በቀድሞ አዴፓ( አሁን የአማራ ብልጽግና) ውስጥ ባሉ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ የሀሳቡ ደጋፊዎች መኖራቸውን፣ በአጀንዳ ደረጃ ጉዳዩን አንስተው እንደተወያዩበት፣ የአዲስአበቤን ንቅናቄ በማቀጣጠል የኦሮሙማን ተስፋፊነት መግታት እንደሚቻል እምነት እንዳላቸው አለመግለጽ የህሊና እዳ ነው። ይሄ ብልጽግና ውስጥ ያለ ህዳጣን አመራር ስልጣን ወዳድና ህዝብን ስለሆነ አዲስአበቤ መነቃነቅ ከጀመረ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለውን ትግል ሊመራና አጀንዳውን አደባባይ ሊያወጣው ይችላል።
በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ወደ ቀድሞው ግዛትነት መመለስ የኢትዮጵያን ፓለቲካ ግልብጥብጡን እንደሚያወጣው፣ የኢትዮጵያ የመዳኛ አንዱ መንገድ መሆኑ ግንዛቤ እየተያዘበት መመጣቱ እጅግ የሚያስደስት ነው። ከዚህ በኃላ አጀንዳውን ከነብር ጭራ መያዝ ጋር ማዛመድ ነው።
አዲስአበቤነት-ይለምልም!
የአዲስ-አበባ-ግዛትነት-በትግላችን-ይመለሳል!
Filed in: Amharic