>
5:46 pm - Thursday February 2, 2023

በጥበብ ኃይል - የድድብናን ጥሬ ጉልበት ኳራንታይን የመክተቻ ጊዜው - አሁንም አልረፈደም!! (አሰፋ ሀይሉ)

በጥበብ ኃይል – የድድብናን ጥሬ ጉልበት ኳራንታይን የመክተቻ ጊዜው – አሁንም አልረፈደም!!!

አሰፋ ሀይሉ
(ራስ መኮንን ) ማን ናቸው? የፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራትስ…!?!

ይሄን የራስ መኮንንን ሐውልት ወያኔ ዘውድ የጫነላቸው የአደሬ ባለጊዜዎች ሊያፈርሱት ያልሞከሩት ሙከራ አልነበረም፡፡ በሐረር የራስ መኮንን አዳራሽ ይባል የነበረውን በመንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን የተገነባውን የከተማዋን ብቸኛ ዘመናዊ የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽና ትያትር ቤት – አደሬዎቹ – ሊያፈርሱት ፈልገው ነበር መሰለኝ፡፡ ትያትር የሌለው የትያትር ቤት ምን ይሠራለታል? እና ግን በመጨረሻ ቆንጆ ሀሳብ አገኙ! የአዳራሹን ስም ቀየሩት፡፡ ከ‹‹ራስ መኮንን አዳራሽ›› ወደ ‹‹ኢሚር አብዱላሂ አዳራሽ››፡፡ ከዚያ በኋላ ይሄን የራስ መኮንን ኤኩዌስትሪያን (የፈረስ ላይ ኃውልት) አደሬዎቹ በነካ እጃቸው ስሙን ቀይረው ‹‹ኢሚር አብዱላሂ ከነፈረሳቸው›› ብለው ይሰይሙታል ተብሎ ሲጠበቅ ምን እንዳሳያቸው እንጃ ሳይነኩት ቀሩ፡፡
አሁን ስንት ዓመታት ጠብቆ የቄሮውን ፍንዳታ የሀጫሉን ሞት ተከትሎ ይኸው ፈረሶ አየነው፡፡ የሚያሳዝነኝ የሀጫሉ ሞት ሳይሆን – ሃጫሉ ይህቺን ሳያይ መሞቱ ነው! ወይ ሃጫሉ! እንደዚያ ሀውልት ማፍረስ እንደናፈቀው ፍንግል ብሎ ቀረ? እግዜሩም አንዳንዴኮ ልግመኛ ነው መሠለኝ! ምናለበት አሁን ለእነዚህ ላልለመኑት ደደቦች ሀውልት አፍርሶ ከሚያሳይ – ለለመነው ለሀጫሉ አሳይቶት ቢወስደው?
አንዴ ታላቁ ፈላስፋ አርተር ሾፐንአወር ስለ ድድብና አጭር ፍች ስጥ ተብሎ ሲጠየቅ፡- ‹‹ድድብና ግብታዊ የማፍረስ ኃይል ነው›› አለ፡፡ ዓለም ለድድብና ፍች አጥቶ ቆይቶ አንዴ በአይኪው አንዴ በአፕቲትዩድ ቴስት፣ ምናምን እያለ መከራውን ሲበላ ነበረ፡፡ እና በዚህ የሾፐንአወር ፍች ተገላገለ፡፡ እውነት ነው፡፡ ለማፍረስ የድድብና ኃይል ብቻ በቂ ነው፡፡ ለማፍረስ ጥበብ አይጠይቅም፡፡ ወንድሙን ከገደለው ከቃየል – እስያን የፍርስራሽና የአፅሞች ተራራ እስካደረጋት እስከ ጋንጊስ ካህን፣ አውሮፓን ወደ ፍርስራሽነት ከቀየረው ሂትለር – ሰላማዊ ሰው የሚላወስባቸውን ህንጻዎች ፍርስራሽ እስካደረገው ቢንላደን ድረስ – ደደቦች ሁሉ ትልቅነታቸውን የሚለኩት ባደረሱትና በሚያደርሱት የማፍረስ ልክ ነው፡፡ ማፍረስ ኃይል ለደደቦች ብርቅ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በዚህ የግብታዊነት ኃይል ደደቦች በስነፍጥረት አንድነትን ከእንስሳት ጋር ይጋሩታል፡፡
አጋሰስ ከብቶችን በአንድ በዓለም የታወቀ የጥበብ ሥራ ላይ ብትነዳቸው በኮቴያቸው ይጨፈላልቁታል፡፡ ሰባብረው እንዳልነበር ያደርጉታል፡፡ ማፍረስ የደደቦች የተፈጥሮ ኃይል ነው፡፡ መፍጠር ነው ጥበብን የሚጠይቀው፡፡ የእጅ ሰዓትን ለመፍጠር ሳይንቲስት መሆንን ይጠይቃል ይል ነበር ፍራንክሊን፡፡ እውነትም የእጅ ሰዓትን የፈጠረው ሳይንቲስት ነው፡፡ የእጅ ሰዓትን ለመሰባበር ግን ድንጋይ የያዘ ጮርቃ ህጻን በቂ ነው፡፡ ድድብና ከተጸናወተህ – በግብታዊነት ታፈርሳለህ፡፡ ድድብናን ማጥፋት ከባድ ነው፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ድድብና ሊጠፋ የማይችል የሰው ልጅ ቋሚ ነው፡፡ የሰው ልጅ ማድረግ የሚችለው ነገር ድድብና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መገደብ ብቻ ነው፡፡ ድድብናን በኳራንታይን መክተት፡፡ ድድብና እንዳይሰራጭ፣ እንዳይባዛ፣ እንዳይዛመት ማምከን፡፡ የደድብናን እንስሳዊ የጥፋት ኃይል በተደራጀ የጥበብ ኃይል እንዲኮሰምን ማድረግ፡፡ መፍትሄው ይኄው ነው፡፡
ሄራርኪስ ኦፍ ፓወር የሚባል አለ፡፡ የኃይል ዓይነቶችን በኃይለኝነታቸው ደረጃ የሚከፋፍል ሳይንስ ነው፡፡ የዕውቀት ኃይል ትልቁ ኃይል ነው፡፡ የኒውክሊየር ኃይልን የሚፈጥረው – የብዙዎቹ ታላቅ ኃይሎች ምንጭ የሰው ልጅ የዕውቀት ኃይል ነው፡፡ ሌሎችም ብርቱ ኃይሎች አሉ፡፡ የኢኮኖሚ ኃይል፡፡ የገንዘብ ኃይል፡፡ ወታደራዊ ኃይል፡፡ የፖለቲካ ኃይል፡፡ የዕምነት ወይም ሪሊጀስ ኃይል፡፡ እና የጥሬ ጉልበት ወይም የጡንቻ ኃይል፡፡ ከዓለማችን የኃይል ምንጮች ሁሉ ‹‹ጥሬ ጉልበት›› የሚባለው ሰባተኛው የኃይል ዓይነት – እጅጉን ርካሹና እጅጉን የተናቀው የኃይል ምንጭ ነው፡፡ ጥሬ ጉልበት የሰው ልጆች በእንስሳዊ ተፈጥሯቸው የተነሳ ከእንስሳት ጋር የሚጋሩት አውሬያዊ ኃይል ነው፡፡
እና ታዲያ ድድብና – ጥሬ ጉልበት የመጨረሻው ርካሹ የኃይል አማራጭ እንደሆነ ከአለማወቅ ራሱ ይጀምራል፡፡ ካራ ያነሳ በካራ ይጠፋል፡፡ ጥሬ ጉልበት በጥሬ ጉልበት ይመታል፡፡ ነገር ግን ጥሬ ጉልበትን በቀላሉ የሚያጠፉ ብዙ ኃይሎች አሉ፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ከጥሬ ጉልበት ለመከላከል ከፈጠራቸው ኃይሎች አንዱ ህግ፣ ፍትህ እና መንግሥት የተሰኙ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ተቋማት በመፍጠሩ የተነሳ ራሱን ከጥሬ ጉልበት ለመከላከል ጥሬ ጉልበትን እንዳይጠቀም ተስማምቷል፡፡
ህግ ከዚህ ጥሬ ጉልበት ማኅበረሰብን የሚጠብቅ ካልሆነ ህግ አይባልም፡፡ መንግሥት ከጥሬ ጉልበት ሀገርን የማይጠብቅ ከሆነ መንግሥት አይባልም፡፡ ከጥሬ እንስሳዊ ጉልበት ስጋት ነጻ ያልሆነ ማህበረሰብ መንግሥት አለኝ ማለት አይችልም፡፡ መንግሥት የሚባለው ተቋም ከተራ ጥሬ ጉልበት ህዝብን ሊከላከል ካልቻለ ሁሉም እና እያንዳንዱ ባለው ጥሬ ኃይል ሁሉ ራሱን አስታጥቆ ህልውናውን ከአፍራሾች መጠበቅ ግዴታ ሊለው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሁሉንም ወደ ጥንታዊው መንግሥት አልባ ስቴት ኦፍ ኔቸር (የጭካኔና የጥርጣሬ ጋርዮሻዊ አኗኗር) ይመልሳል፡፡ አይፈለግም፡፡ አይመከርምም፡፡ በዚህ የሰለጠነ ዘመን ላይ ተሆኖም አይናፈቅም፡፡
መፍትሄው ድድብናን እና የድድብናን ጥሬ ኃይል በእንጭጩ መግታት ነው፡፡ ድድብና የሚገባውን ትክክለኛ ቦታ እስኪያገኝ – የጥበብ ኃይል መደርጀት የግድ ይለዋል፡፡ ሾፐንአወር እንዳለው ድድብና ግብታዊ የማፍረስ ኃይል ነው፡፡ መፍጠር አያውቅም፡፡ ማፍረስ ብቻ፡፡ ማጥፋት ብቻ፡፡ ድድብና ከደቀነበት የመፍረስና የመፈራረስ አደጋ ራሱን ለመጠበቅ የሚፈልግ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ የድንቁርናን ኃይሎች በጥበብና በሥርዓት ደርጅቶ መፋለም አለበት፡፡ የዘመናዊው ዓለም ሰብዓዊ ፍጥረት ራሱን በኃይልና በብርታት አጠንክሮ በዕውቀት አንጾ፣ ስልትና ሥርዓት ነድፎ ድንቁርናን በብልሃትና በጥበብ የመጋፈጥ ሰብዓዊ የህልውና ግዴታ አለበት፡፡
ስልትና ብልሃት፣ ጥበብና አስተዋይነት – የድድብናን ጥሬ ጉልበት ቀድመው መገኘት አለባቸው፡፡ ድድብና የጥበብ ባሪያ እንጂ ጥበብ የድድብና ባሪያ ልትሆን አልተጣፈችም፡፡ የሰው ልጅ የጥበብ ባሪያ እንጂ የድድብና ባሪያ ሊሆን ከቶ አልተፈጠረም፡፡ ይዋልም ይደርም ጥበብ ድንቁርናን ድል መንሳቷ አይቀሬ የታሪክ ሃቅ ነው፡፡ የፈረሰም መገንባቱ፣ የወደቀም መነሳቱ የማይቀር የታሪክ ሃቅ ነው፡፡ ራሳችንን ከፈራረስንበት የድድብና ባርነት ነጻ እናውጣ! ፍትህ በሚገባ ይበየናል! ኢንተርናሲዮናል የሰው ዘር ይሆናል! ይኸው ነው!
መኮንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ
 (ራስ መኮንን ) ማን ናቸው? የፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራትስ…!?!
 
 … ራስ መኮንን በዓለም አንድ ጥቁር ሰው እንኳንስ በኃያላን ያለም ነገሥታት በክብር እየተጠራ ሊሸለም ይቅርና ሙሉ መብት እንዳለው ሰው በማይቆጠርበት በዚያ ዘመን… በሥራቸው፣ በምግባራቸው፣ በሕዝባቸው የተባበረ ክንድ፣ በሥልጣኔያቸው የተነሣ… እነዚያን ለጥቂት ውድ ሰዎች ብቻ ተመርጠው የሚሰጡትን እጅግ የከበሩ ታላላቅ ዕውቅናዎችና የክብር ሽልማቶችን ያገኙ ታላቅ ሰ ናቸው…!!!
ይህ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ቆሞ የሚታየው የአፄ ምኒልክ ኃውልት አይደለም፡፡ ይህ ታላቅ ኃውልት በሐረር ከተማ መሐል አደባባይ የቆመው የተፈሪ መኮንን (የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ወላጅ አባት የመኮንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ ኃውልት ነው፡፡ ሐረር ወደ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ተጠቃልሎ የገባው ቀደም ባለው የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ-መንግሥት ነበር፡፡* /*እዚህ ላይ በምኒልክ ዘመን በሐረር ስለሆነው ግን በተጨማሪ የአፈወርቅ ገብረየሱስን ‹አጤ ምኒልክ› ልብ ይሏል፡፡/ መኮንን በ14 ዓመታቸው ጀምረው አንኮበር በሚገኘው የንጉስ ምኒልክ ቤተመንግስት በአባታቸው ተወስደው ከምኒልክ ጋር ልዩ ወዳጅነትን አዳበሩ፡፡ በ1879 ዓ.ም. መኮንን የሐረር ሹም (አስተዳዳሪ) ሆኑ፡፡ በመጀመሪያው በታላቁ የአድዋ ጦርነት መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ የጣልያንን ጦር በመጠራረግ ቁልፍ ሚና የተወጡ ጀግና ነበሩ፡፡ በግላጭ ስያሜውን አይጠሩበት እንጂ በምኒልክ ዘመን የታወቀላቸው የዲፕሎማትነት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሚና ነበራቸው፡፡ በ1894 ዓ.ም. መኮንን እንግሊዝ ሃገር በመሄድ በንጉስ ኤድዋርድ ሰባተኛ የንግሥና ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡ መኮንን ኢጣልያን፣ ፈረንሣይን እና ጀርመንን ጎብኝተዋል፡፡ ከዓለም ኃያላን ሃገራት መሪዎች እጅ ከተሰጧቸው እጅግ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው የክብር ሜዳይ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የየእንግሊዝን የቅዱስ ሚካኤልንና የቅዱስ ጊዮርጊስን የከፍተኛ ተዋጊ አዛዥነት የክብር ኮከብና ኒሻን ሜዳይ (Badge & Star of the Order of St. Michael and St. George (Knight Commander)) ተሸልመዋል ፡፡ የራሺያን የቅዱስ አንን ከፍተኛ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the Russian Order of St. Anne) ተሸልመዋል፡፡ የፈረንሣይን የሶስተኛው ሪፐብሊክ ወታደራዊ ሠልፈኞች ከፍተኛ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the French Legion d’Honneur (Third Republic)) ተሸልመዋል፡፡ የኢጣልያን ከፍተኛ የንጉሠነገሥት የክብር ዘውድ የኮከብ ሜዳይ (Star of the Order of the Crown of Italy) ተሸልመዋል፡፡ የኦቶማንን ከፍተኛውን የኦስማኒያ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the Ottoman Order of Osmania) ተሸልመዋል፡፡ በ1898 ዓ.ም መኮንን ሲያልፉ ልጃቸው ደጃች ይልማ መኮንን የሐረር ሹም ሆነው ተተኩ፡፡ በዓመት በኋላ ደግሞ ይልማ መኮንን የሐረር ሹምነቱን  ወደፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለሚሆኑት ለታናሽ ወንድማቸው (ለአባታቸው ልጅ) ለተፈሪ መኮንን አስተላለፉ፡፡
እኚህን በዓለም አንድ ጥቁር ሰው እንኳንስ በኃያላን ያለም ነገሥታት በክብር እየተጠራ ሊሸለም ይቅርና ሙሉ መብት እንዳለው ሰው በማይቆጠርበት በዚያ ዘመን… በሥራቸው፣ በምግባራቸው፣ በሕዝባቸው የተባበረ ክንድ፣ በሥልጣኔያቸው የተነሣ… እነዚያን ለጥቂት ውድ ሰዎች ብቻ ተመርጠው የሚሰጡትን እጅግ የከበሩ ታላላቅ ዕውቅናዎችና የክብር ሽልማቶችን ያገኙት እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሰው… መኮንንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ… በእውነት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ክብርና ፍቅር ሊለገሣቸው የሚገባ እጅግ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን ለመላው አፍሪካና.. ለመላ የዓም ጥቁር ሕዝቦች የምንጊዜም ኩራት የሚሆኑ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ቅድም እንዳልነው እዚህ አዲስ አበባ በቅ/ጊዮርጊስ የሚገኘው ኃውልት የመኮንን አይደለም፡፡ የእሳቸው ያለው ሐረር ከተማ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው.. በፒያሣ ኃብተጊዮርጊስ ድልድይ አቅራቢያ የሚገኘውን… እስካሁን ድረስ የሚፈስሰውንና ብዙዎችም የሚቀዱለትና የሚጎነጩለትን.. የብረት ቅጥር የተሰራለትን የምንጭ ውሃ ያየ ሰው ካለ ግን ያ ማለት፡- የልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሣ ምንጭ ነው፡፡ ‹‹ታሪኩን የማያውቅ ሰው.. ልክ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን መለየት እንደሚሳነው ህፃን ነው፡፡›› ይል ነበር አንድ ታላቅ ወዳጄ፡፡ ራሳችንን እንፈልግ፡፡ ራሳችንን እናግኝ፡፡ ራሳችንን እናክብር፡፡ እና ራሳችንን እንሁን፡፡ መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
Filed in: Amharic