አጤ ምኒልክና የግዛት ማስፋፋት – የአገር ምስረታ እንቅስቃሴ ዎቻቸው…!!!
ሳሚ ዮሴፍ
አጼ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ አሳዳጊያቸው አጤ ቴዎድሮስ ያልሙት እና ጀምረው ያልጨረሱትን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም ለማሳካት ቆርጠው ተነሱ የጦር አበጋዛቸውን ራስ ጎበና ዳጨውን በማድረግ በፍቅር እና በሰላም የገበረውን እሰየው ብለው በመቀበል አሻፈረኝ ብሎ ጦር የሰበቀውን በመጣበት መንገድ በመመለስ ኢትዮጵያን አንድ አድርገዋታል።
አርሲ
——-
ደጃች ወልደ ገብርኤል አርሲን ለማቅናት ዘምተው ሀገሩን ቢይዙም የአርሲ ኦሮሞ አንገዛም ብሎ በማስቸገሩ ምኒልክ በ1874 ዓ.ም ዘምተው ነበር። አብዛኛው የአርሲ ሕዝብ አሜን ብሎ ሲገብር አንዳንድ ባላባቶች አስቸግረው ነበር።
ምኒልክ በ1874 ዓ.ም አርሲን መተው አስገበርኩ ብለው ተመለሱ። የምኒልክን መመለስ ያወቀው የአርሲ ሕዝብ ግን እንደገና በገዥው በደጃዝማች ወልደ ገብርኤል ላይ አመፀ።
ምኒልክ በ1878 ዓ.ም ወደ አርሲ ለመዝመት ግንቦት 5 ቀን ከእንጦጦ ተነሱ። በሶዶ፣ በከንባታ፣ በዝዋይ አልፈው፣ ጭላሎን፣ ሳቶን፣ ዲጋሎን አስገብረው አልባሶ ሜዳ ሰፈሩ።
በዚህም ጊዜ ኮጂ የሚባለው የአርሲ ባላባት በሌሊት ከደጃች ወልደ ገብርኤል ሰፈር ገብቶ አደጋ አደረሰ።
700 ያህል ሰዎችም ገደለ። ምኒልክ የሰፈሩት ከደጃች ወልደ ገብርኤል ሰፈር ራቅ ብለው ነበርና የአደጋውን መድረስ አልሰሙም። በዚያው ዕለት አንዲት የሸሸች ሴት ከንጉሡ ሰፈር ገብታ የአደጋውን መድረስ ነገረች። በማግስቱም ምኒልክ ለደጃች ወልደ ገብርኤል እርዳታ ላኩ። የእርዳታውን መድረስ ያላወቀው የአርሲ ሕዝብ እንደ ልማዱ አደጋ ለማድረስ በሌሊት ሲመጣ የምኒልክ ሠራዊት ፈጀው።
ከዚህ በኋላ አንዳንድ ጥቃቅን ግጭት ከመደረጋቸው በስተቀር የአርሲ ሕዝብ ገበረ። ንጉሥ ምኒልክም ለአርሲ አጎታቸውን ራስ ዳርጌን ሾሙ። የአርሲ ባላባቶች በገበሩበት ጊዜ የምኒልክ ሠራዊት ከአርሲ ሕዝብ ብዙ ሰው ማርኮ ነበር። በዚያን ዘመን በየትም ሀገር ላይ እንደሚደረገው ሁሉ
በጦርነት የተማረከ ለማራኪው ባሪያ ይሆን ነበር።
የሸዋውም ወታደር የማረከውን ሰው ባሪያ አድርጎ ያዘ።
ይህን ያወቁት ምኒልክ በዚያው በአርሲ ውስጥ እንዳሉ ሠራዊታቸውን ሰብስበው አዋጅ አስነገሩ፤ አዋጁም…
“…አርሲን ከግራኝ ወዲህ የገዛውና ያስገበረው የለም፤ እኛ ጥንትም የኛ ነው በማለት መጣንበት እንጂ አልመጣብንም፤
ባለማወቁ እከላከላለሁ ብሎ አለቀ ተጎዳም፤ ግን ባሪያ አድርገን ልንገዛው አይገባም፤ ወንድማችን ነውና የማረከውን ምርኮኛ በሙሉ ልቀቅልኝ፤ በአዋጅ ከለመንኩህ በኋላ ወስልተህ የአርሲን ሕዝብ ባሪያ አድርገህ የያዝህ ከተገኘህ እጣላሃለሁ፤ ልቀቅ ብዬሃለሁና ላምና ከብቱ ለስንቅህ ይበቃሃል ከብቱን ልቀቅልኝ…” የሚል ነበር። ከዚህ በኋላ የምኒልክ ወታደር የያዘውን ባሪያ አድርጎ አለማሠራቱ ቢያናድደውም በሙሉ ለቀቀ።
ወለጋ
——-
የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ሠራዊታቸውን ወደ ወለጋ እየላኩ በግብር መልክ ሳይሆን በዝርፊያ ወለጋን አዳክመውታል። የወለጋው ባላባት ሞረዳ ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ጋር በውድም ይሁን በግድ ተወዳጅተዋል።
የሸዋው ምኒልክ እና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት በወለጋ ምክንያት እንባቦ ላይ ተዋግተዋል። ንጉሥ ተክለሃይማኖት ባላባቱን ሞረዳን ሲይዙ ንጉሥ ምኒልክ ደግሞ ልጃቸውን ኩምሳን በወዳጅነት ያዙ።
ንጉሥ ምኒልክ በ1878 ዓ.ም ራስ ጎበና ዳጨውን ወደ ወለጋ ልከው ጎበና ከኩምሳ ጋር እንዲነጋገሩ አደረጉ።
ጎበናም የምኒልክን ሀሳብ ለኩምሳ ሲናገሩ “…በሰላምና በፍቅር ብትገባ መሬቱ የእናንተ ነው፤ በወለጋም ከኩምሳ በላይ የሚሾም ሰው የለም፤ ሀገሩንም የምታስተዳድረው እና የምታስገብረው አንተ ኩምሳ ነህ፤ ለምኒልክ መገዛትህን የምታስታውቅበት በየዓመቱ ትገብራለህ፤ ከዚህ በተረፈ በበላይነት እንጂ በውስጥ ግዛታችሁ አንገባም….” ብለው በዚህ ከተስማሙ በኋላ ባላባቱ ኩምሳ ገቡ።
ንጉሥ ምኒልክም ኩምሳን ክርስትና አንስተው ስማቸውን ገብረ እግዚአብሔር አሏቸው፤ የደጃዝማችነትም ማዕረግ ሰጥተው የወለጋ ገዥ ብለው ሾሟቸው።
በ1880 ዓ.ም ደርቡሾች ወለጋን ወረሩ፤ ምኒልክም በጎንደር በአምባ ጫራ በኩል የመጣውን የደርቡሽ ጦር ለመውጋት ሄደው በአጤ ዮሐንስ ትእዛዝ ተመልሰው እንጦጦ መግባታቸው ነበርና በወለጋ በኩል የገባውን የደርቡሽ ጦር እንዲወጉ ራስ ጎበናን አዘዟቸው። ራስ ጎበናም ሄደው ተዋግተው ድል አድርገው ተመለሱ። ለአጤ ምኒልክም ግዳይ ጣሉ፤ ምኒልክም ፈረስ ከነወርቅ መጣብሩ፣ ባለ ወርቅ ጋሻ፣ ባለ ወርቅ ጫሜ ጎራዴ፣ ማለፊያ ጠበንጃ፣ የወርቅ ዝናር፣ ባለ ወርቅ ለምድ ወርቅ ኮፊያ፣ ግምጃ ሱሪ፣ ግምጃ መታጠቂያ፣ ቀጭን ድርብ ሸለሟቸው።
———-
የወላይታው ንጉሥ ጦና አልገብርም ብለው አስቸገሩ። እንዲያውም የገበረውን ሀገር ሁሉ እየወጉ እንደገና እንዲከዳ ያደርጉ ጀምር። በዚህ ምክንያት ራሳቸው አጤ ምኒልክ በ1887 ዓ.ም ኅዳር 7 ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ወላይታ ጉዞ ጀመሩ። ወላይታ ሾኒ ከተባለው ቦታ ሲደርሱም
መልክተኛ ለጦና ላኩባቸው “…ሰዉን አታስፈጅ ሀገርህንም አታስጠፋ ግብርህን ይዘህ ግባ…” አሉ።
ንጉሥ ጦናም ምኒልክ ለላኩባቸው መልእክት “…በሀገሬ ክርስቲያን አይገባበትም ገፍተው ከመጡ እዋጋለሁ እንጂ ለክርስቲያን መንግሥት አልገብርም…” ብለው መለሱ።
ከዚህ በኋላ ምኒልክ ሠራዊታቸውን እየመሩ ኅዳር 23 ቀን ቆንጦላ ሰፈሩ። ምኒልክ ቆንጦላ እንደሰፈሩ እጅግ የበዛ የጦና ሠራዊት ሊዋጋ መጣ። ምኒልክ ጦሩ እንዲዋጋ ከማዘዛቸው በፊት ጥቂት ሰዎች ወጥተው ጦርነት ገጠሙ።
በዚያም ከምኒልክ ሠራዊት 75 ሰዎች ተገደሉ። ምኒልክ እሄን እንደሰሙ ሊቀ መኳስ አባተንና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው ተዋጊውን አባራው የእነሱን ሠራዊት እንዲመልሱ አዘዙአቸው። በጅሮንድና ባልቻም የጦናን ሠራዊት አባረው የእነሱን ሠራዊት ወደ ሰፈር መለሱ።
ይህ ከሆነ በኋላ ንጉሥ ምኒልክ በሰላም ተጉዘው ከጦና ዋና ከተማ ደልቦ ላይ ኅዳር 27 ቀን ሰፈሩ። ጦና ግን ከዚያ አልነበሩምና ካሉበት ድረስ መልእክተኛ ልከው “…ሀገር ከጠፋ በኋላ ሊያቀኑት ያስቸግራል፤ ገንዘብም በግድ ካልሆነ በቀር በፍቃድ የሰጡት አያልቅም፤ ሀገርህን አታስጠፋ ግብርህን ይዘህ ግባ” ብለው ላኩባቸው። እሳቸው ግን አልገባም ብለው ቀሩ። አጤ ምኒልክ ዳሞት ተራራ ላይ ከወጡ በኋላ ጦራቸውን አሰልፈው በለው ብለው አዘዙ።
የታዘዘውም ሠራዊት በአንድ ጊዜ ወላይታን በሙሉ ያዘ። ጦናም ከወላይታ ወጥተው ወደ ቦረዳ ሸሹ። የምኒልክ ሠራዊትም ተከታትሎ በጥይት አቁስሎ ጦናን ያዛቸው።
ጦናም ተይዘው ምኒልክ ፊት ከቀረቡ በኋላ ምኒልክም
“አወይ ወንድሜን እንዲያው በከንቱ ሕዝብ አስጨረስክ” ብለው ወቅሰው ቁስሉ እንዲታጠብና እንዲታከም አደረጉ።
ሠራዊቱ ብዙ ከብት ማርኮ ነበርና የተማረከው ከብት በሙሉ ለባላገሩ እንዲመለስ አዋጅ አስነገሩ። የባላገሩ ከብት እስኪመለስና ጦናም እስኪያጋገሙ ጥቂት ቀናት ከርመው ጦና ካገገሙ በኋላ የወላይታን ሕዝብ ሰብስበው “…እንግዲህ የሚያስተዳድርህ ልጄ ወዳጄ ጦና ነው እና ተገዛለት፤ አውቆ ሳይሆን ሳያውቅ እኔን የበደለ መስሎት ሰው አስጨረሰ እንጂ ከድሮ አያቶቻችንም ቂም የለንምና መልሼ እሱኑ ሾሜልሃለሁ…ከእንግዲህ ወዲያ ብታምጽ በራስ እወቅ ግብሬንም አግባ…” የሚል አዋጅ አስነግረው የወጓቸውን ጦናን ሾመው ጥር 11 ቀን አዲስ አበባ ገቡ።
እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ የተጓዘው ዊልቤ በ1893 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ “…በጠረፍ ያሉት ሰዎች ምኒልክ ጥሩ ሰው እንደሆነ ያውቃሉ። ምኒልክ ሁሉም ሰው በኃይማኖቱ ይደር ስላለና በሕዝቡ መሀል አድሎና የኃይል ሥራ ስለማይሠራ ይወዱታል፤ ሲያወሩም ‘እንደ ሌሎቹ ንጉሦች መስሎን ሸሽተን ነበር፤ በኋላ ይቅርታ እየጠየቅን ተመለስን፤ ያኔ ተታለን ነበር’ ይላሉ፤ አሁን ግን ግብራቸውን እየገበሩ በሰላም ይኖራሉ…” በማለት ስለ ወላይታ ሕዝብ ጽፏል።
ምንጭ…
ጳውሎስ ኞኞ
አጤ ምኒልክ
የቀረቱን የግዛት መስፋፋት በሚቀጥለው ጽሑፍ እንመለከታለን