>

ሀጫሉ…… (የትነበርክ ታደለ)

ሀጫሉ……

(የትነበርክ ታደለ)

በስራና በትምህርት ምክኒያት ለረዢም ጊዜያት ወደ ተለየኋቸው ቤተሰቦቼ መመለሴ ነው። ረዥሙን የአውቶቡስ ጉዞ ጨርሼ መንደራችን ስደርስ የልጅነት ህይወቴ ቶሎ ቶሎ ወደ አዕምሮዬ እየተመላለሰብኝ ሻንጣዬን አዝዬ ወደ ቤት ገባሁ።…….
ከዚህ ቀደም እንዲሁ ቆይቼ ስመጣ ታናናሽ ወንድሞቼም ሆኑ የሰፈሩ ልጆች ተሯሩጠው መጥተው ሻንጣዬን የሚቀበሉኝ ዛሬ ግን አንድም ሰው ብቅ ሳይል በመቅረቱ ቅር እያለኝ ወደ ቤት ስዘልቅ ቤቱም ጭር ብሏል።
“ሰው የት ሄደ?” ቤት ውስጥ ብቻዋን የጠበቀችኝ ሰራተኛ ጠየኩ።
“አጋሮ ሄደዋል?” ቤታችን ከአጋሮ ከተማ ወጣ ያለች መንደር ነች
“ሁሉም?” “አዎ! ዛሬ ሀጫሉ አጋሮ ይመጣል ተብሎ ቀን የወጡ ናቸው” አለችኝ
በእርግጥ ጅማ ስደርስ ሀጫሉ ሁንዴሳ የሚባል የኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝ ከአጋሮ መልስ ስራውን እንደሚያቀርብ ማስታወቂያ ሲለፈፍ ሰምቼ ነበር። ይሁን እንጂ የኛ ቤት ሰዎችን ጠራርጎ ይወስዳቸዋል የሚል ሀሳብ አልነበረኝም። በተለይ ዛሬ እንደምገባ አስቀድሜ ስልክ ደውዬ ተናግሬ ሳበቃ አንድም ሰው ሊቀበለኝ እንኳ እንዳይችል የሚያደርግ ነገር ይፈጠራል ብዬ አላሰብኩም።
ባለሶስት እግር በርጩማ አወጣሁና ከደጅ ቁጭ ብዬ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያስተማረችኝን ትልቋ ከተማዬን ትንሿን መንደሬን አስተውላት ጀመር። መንደሩ ውስጥ ያለው ነዋሪ በሙሉ ሀጫሉን ለማየት ወደ አጋሮ መሄዱ በደንብ ያስታውቅ ነበር። ጭር ብላለች።
ሀሳብ ወደ ኋላ ወሰደኝ። የኦሮሞ ሙዚቃዎችን የምታቀነቅነው የልጅነት መንደሬ። የሙዚቃ ክፍለጊዜዎቻችን ትዝ አሉኝ።……..እነ ዘሪሁን ወዳጆን ሙሉ አልበም (ካሴት) 10 ሙዚቃዎች በቃል አጥንተን ዴስክ እየደበደብን ፌስቲቫል አዘጋጅተን ለትምህርት ቤታችን የገቢ ማሰባሰቢያ ያቀረብናቸው ዘፈኖች…..
ኑ ወሊን ያደና – ወል መሌ ማልቀብና….
ሀዋ ሀዋ – ጃለሊኬ ደዋ…..
እያልን ያዜምናቸው
እንዲሁም
ቢሻን አዲስ አባባ – ኦል ጡሩረሞ ገድ ጡሩረኒ
ጡጡጢ ነዱንገዱ – ዱረቱ መቃ ኑረቱለኒ፤
አስ ኮቱ አሲን ጅራ – ቀለዮ ሙዲንኮ ዋሚጊራ
እያለ በልጅነት አዕምሯችን አንዴ አዲስ አበባ አንዴ አዋሽ አንዴ ወለጋ የሚያዞረን አብተው ከበደ በፍቅር የሚደመጡ የመንደራችን ነዋሪዎች ተመራጭ አቀንቃኞች ነበሩ።
ከዚያ በኋላ በኦሮሚኛ ሙዚቃ ብዙም እንዲህ አሸንፎ የገዛኝ አልነበረም።……… ታዲያ ከስንት አመት በኋላ እንደምመጣ አስቀድሜ የነገርኳቸው ቤተሰቦቼን በሙሉ ጠራርጎ የወሰዳቸው የትኛው አቀንቃኝ ነው የሚለው ጥያቄ እየተመላለሰብኝ ሳለ ነበር ተግተልትለው የመጡት።
“ሀጫሉ ማን ነው?” ሰላምታችንን ገና በቅጡ ሳንጨርስ ነበር በአግራሞት የጠየኩት። እናቴ እንኳ ሳትቀር ከልጆቿ ጋር ተያይዛ ለኮንሰርት በዚህ ዕድሜዋ የወሰዳት።
በጥያቄዬ ተገርመዋል። ያሳለፍኩትን ጊዜ እኔ አውቀዋለሁ። ሙዚቃ የማዳምጥበት ጊዜው ብቻ ሳይሆን የተረጋጋም አዕምሮም አልነበረኝ። ከኮንሰርቱ ይዘውት የመጡትን የአርቲስቱን አልበም ከፍተው እንዳዳምጠው ለቀውኝ እነሱ ለእንግዳቸው የሚሆን ነገር ለማዘገጃጀት ገቡ።
ማሾኮ!
…አን ሶሶዳዴ በረና – ቀልቢ ኮቲ ጊቤ ገመ ጃለዴ ሰኚ ሞቲ!
ጂማ ጂርታ አቲ ቁባን ሲቀባ ቢያ ሂንፈጋኔ
ያደኬቲን ቆባ ጉምጉማ መሌ ሂንመራኔ
[ጂማ ውስጥ ነሽ ከሀገር እንዳልወጣሽ አውቃለሁ
በናፍቆትሽ ተብሰልስዬ እንዳበደ ለብቻዬ አወራለሁ]
…….እኔ ራሴ የተጠራቀመው ናፍቆቴ ድንገት ገነፈለብኝ። ሀገሬ፣ መንደሬ፣ ከተማዬ፣ የልጅነት ህይወቴ በሙሉ ተከለበሰብኝ፣ እምባዬ እንደ ደራሽ ወንዝ ፊቴን አጥለቀለቀው።…….እናቴ ከማጀት ስትመለስ እኔ እያለቀስኩ ነበር።
…..ሀጫሉን እንዲህ አስለቅሶኝ ነበር የተዋወኩት።……..
“ከንኮ ለጴን ሱማፍ ኑጊ ቱማ
ነቲ ታቴካ አከ ሱሲ ቡና
[እንደ ቡና ሱስ ሆነሽብኝ
ልቤን እንደ ኑግ ጨመቅሺብኝ]
ልጅነት ክፉ ነው። ያየ የሰማውን በሙሉ በአለት ላይ እንደ ተጻፈ መዝግቦ የዘለዓለም ትዝታ ያደርጋል። ……
“ጅማ ነሽ ወይስ አጋሮ …” እያለ ካቀነቀነላት ከዝነኛው ድምጻዊ ከነዋይ ደበበ ኮንሰርት በኋላ ብዙም አይነ ግቡ ሳትሆን በአቧራ ታጥና የኖረች በድህነት ቆዝማ የበይ ተመልካች የሆነችው አጋሮ ከተማ በሀጫሉ ሁንዴሳ ኮንሰርት ገና መቀስቀሷ ነበር። በዚህ ኮንሰርት በተደረገ ማነቃⷅያና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም ከተማዋን ለማደስ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በወቅቱ ሰምቻለሁ። እኔም በሀጫሉ ሙዚቃ ዳግም ለኦሮምኛ ሙዚቃዎች ተቀስቅሼ ሳምንቱን ሙሉ ይህንኑ አልበም እየደጋገምኩ ሳጣጥም ቆይቼ ኑሮ ወደሚጎትተኝ የስራ ሀገሬ ተመለስኩ። – ..
ሀጫሉ ሁንዴሳ በወጣትነት እድሜው በርካታ ስራዎቹን በፍቅር፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ ጉዳዮች እያደረገ ህዝቡን እያዝናና እያነቃ ገና ወደ ፊት ለመፈንጠር እየተንደረደረ ሳለ በጨካኞች እጅ ተገደለ። እንግዲህ በኦሮሞ ሙዚቃ ውስጥ ይህን ኮከብ የሚተካ እስክናገኝ ስንት አመታት እንጠብቅ ይሆን?
Filed in: Amharic