>
5:18 pm - Wednesday June 15, 4022

አሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ርግማን ነው ወይስ የአገዛዞች ማጭበርበሪያ? (ከይኄይስ እውነቱ)

 

አሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ርግማን ነው ወይስ የአገዛዞች ማጭበርበሪያ?

ከይኄይስ እውነቱ


በአገር አመራር እና በሕዝብ አስተዳደር ረገድ አገራችን ኢትዮጵያ ሰው አልበቅልባት ካለ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊቈጠር ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ዐሥርታት በእኩያን የተተከለው የጐሣ ፖለቲካ ላገራችን ርግማን ሲሆን፣ ይህንን የሚያራምዱት መንደርተኞች ደግሞ ርጕማኖች ሆነው ይህችን በፈጣሪ የታደለች ሀብታም አገር የድኆች መኖሪያ ፣ የድንቊርናና የተዋርዶ መናኸሪያ አድርገዋታል፡፡ 

ዘረኛነት/ጐሠኛነት መቼም የማይስተካከል ጎዶሎነት፣ መቼም የማይቀና ስንኩልነት፣ መቼም የማይድን የሃሳብ ምክነት ነው፡፡ ይህን ጎዶሎ፣ ስንኩል እና የመከነ አስተሳሰብ ይዞ እንኳን አገርን ቤተሰብን ለመምራት አይቻልም፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ድኩም አእምሮ ላገር ለሕዝብ የሚጠቅም ሃሳብ መፍትሄ ሊፈልቅ አይችልም፡፡ ስለሆነም ርግማኑ፣ አገር በእንደነዚህ ዓይነት ድውያነ አእምሮ እጅ መውደቋ እንጂ የኢትዮጵያ ችግር አሐዳዊ ወይስ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚለው አልነበረም፡፡ ዛሬ ይህ የሥርዓት መንግሥት ጉዳይ በተወላገደ ጭንቅላት ተወላግዶ ቀርቦ፣ ወንበዶች ሕዝብን ማስፈራሪያ መሣሪያ አድርገውታል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ዐዋቆች ተገፍተውና ተገልለው አየሯ ሙሉ በደናቊርት ተሞልቷል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች አእምሮ በነዚህ ርጕማን ርኵስ አስተሳሰብ ተበክሏል፡፡ ለአየር፣ ለድምፅ ብክለት ተጠሪ አካላት እንዳሉ ሁሉ፣ ትውልድን ለሚያጠፋው ለአእምሮ ብክለት ተጠሪው ማን ይሆን?

አሁን ባለንበት ዓለም በየትኛውም አገር የመንግሥት አስተዳደር ዕርከኖች አሉ፡፡ እነዚህም ዕርከኖች ጠቅለል ባለ መልኩ ማዕከላዊ እና አካባቢያዊ (ንዑሳን በሓውርት/sub-nationals) ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ በየአገሩ የሚኖሩ ሕግጋተ መንግሥት በነዚህ ሁለት ዕርከኖች ሥልጣንን የሚያደራጁበትን መንገድ መሠረት አድርጎ አንድ አገር አሐዳዊ ወይም ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት ይዘት አለው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሆኖም አሐዳዊነት ወይም ፌዴራላዊነት የመንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲ) ሥርዓት መገለጫ አይደለም፡፡ አንዱ የጭቆና ሌላው የነፃነት ምልክት አይደለም፡፡ በዓለማችን አሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ተከታዮች ሆነው መንግሥተ ሕዝብ ያቆሙ፣ በተቃራኒው ደግሞ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተከታዮች ሆነው የአምባገነኖች/የፈላጭ ቆራጮች መፈንጫ የሆኑ በርካታ አገሮች አሉ፡፡ ስለሆነም አሐዳዊነት ወይም ፌዴራላዊነት ለመንግሥት ሕዝብ ዋስትና አይደሉም፡፡ በቊጥርም ደረጃ ሲታይ አብዛኛው የዓለም ሀገራት አሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ያሏቸው ናቸው፡፡ ከ193ቱ የተመ.ድ. አባል ሀገራት 165ቱ አሐዳዊ መንግሥታት ናቸው፡፡ ጎላ ካሉት ውስጥ የተባበረው የእንግሊዝ ዘውዳዊ መንግሥት፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ቻይና ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም አሐዳዊ ሥርዓት በዓለም ላይ የተለመደው ዓይነት ሥርዓተ መንግሥት ነው፡፡ (https://www.thoughtco.com/unitary-state-government-pros-cons-examples-4184826

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ዴሞክራሲ እውን ሆኖባቸዋል በሚባሉ አገሮች እንኳን እንከን የለሽ አሐዳዊ ወይም ፌዴራላዊ ሥርዓት የለም፡፡ አነሰም በዛም ቢያንስ በሥልጣን ክፍፍል ረገድ ፍርድ ቤት የሚደርሱ ውዝግቦች አሉ፡፡ በሁለቱም ሥርዓተ መንግሥታት በሕገ መንግሥትም ሆነ በተግባር ለማዕከላዊው እና ለአካባቢ አስተዳደሮች ያለው የሥልጣን ክፍፍል፣ የፖለቲካ ነፃነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን (autonomy) ከአገር አገር ወጥነት ያለው አይደለም፡፡

ባንፃሩም ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ነገር ግን በሕገ መንግሥታቸው ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች በማዕከላዊው እና አካባቢያዊ ግዛቶች መካከል የሥልጣን ክፍፍል የሚያደርጉ እና ባንፃራዊነት የፖለቲካ ነፃነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ተግባራዊ የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ፤ ከመሠረታዊ የፌዴራላዊነት መርሆዎች ጋር የማይተዋወቁ፣ እጅግ ማዕከላዊ በሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ማዕከላዊውን እና አካባቢያዊውን አስተዳደር በጥብቅ የሚቈጣጠሩ፣ በሕገመንግሥታቸው ባስቀመጧቸው የአካባቢ አስተዳደር ሥልጣን ውስጥ እንደፈለጉ ጣልቃ የሚገቡ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማሻሻል ረገድ የአካባቢ አስተዳደሮች ሚና እንዳይኖሯቸው ያደረጉ፣ ብሔራዊ ፖሊሲዎች ቀረፃ ውስጥ ድርሻ የሌላቸው፣ በተግባር አሐዳዊ (de facto unitary) የሆኑ አገሮች ቊጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ከፊል አሐዳዊ ከፊል ፌዴራላዊ መዋቅር ያላቸውም አገሮች አሉ፡፡ ይህንን መካከለኛ አወቃቀር በሕገመንግሥት ተጽፎም ሆነ ሳይጻፍ ተግባራዊ አድርገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸው እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው የለየላቸው አገዛዞችም አሉ፡፡

አገሮች ከሁለት አንዱን ሥርዓተ መንግሥት ለመምረጥ ግምት ውስጥ ከሚያስገቧቸው ታሳቢዎች መካከል የአገሩ ታሪካዊ ሥሪት (ራሳቸውን የቻሉ ነፃ ግዛቶችና ሕዝቦች ኅብረት ተሰባስበው የመሠረቱት ወይስ ባንድ በታወቀ መልክዐ ምድር በዘመናት መስተጋብር ተሳስሮ የኖረ ሕዝብ /ልዩ ልዩ ነገዶችና ጎሣዎች/የመሠረቱት)፣ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛት፣ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የተፈጥሮ ሀብት ሥርጭት፣ የጐሣ÷ የሃይማኖትና የባህል ስብጥር ይጠቀሳሉ፡፡

የአሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ብያኔ

አሐዳዊ መንግሥት የምንለው ማዕከላዊ መንግሥቱ ሉዐላዊ ሆኖ፣ በሕግ የተቀመጠ ሙሉና የበላይ ሥልጣን የያዘበት፣ በመንግሥቱ ሥር ያሉ ግዛቶች በማዕከላዊው መንግሥት ቊጥጥር ሥር ሆነው የማዕከላዊውን መንግሥት ሕጎች የሚያስፈጽሙበት ወይም እንዳስፈላጊነቱ ማዕከላዊው መንግሥት በሕጋዊ ሂደት አማካይነት (through devolution) የተወሰነ ነፃነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን (autonomy) በውክልና ሊያስተላልፍ የሚችልበት፣ ሕገመንግሥታዊ የመንግሥት አደረጃጀት ዘይቤ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንዳነሳነው ይህንን አደረጃጀት ተከትለው ሕዝባቸውን በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች የሚያስተዳድሩ እንዳሉ ሁሉ፣ በልዩ ልዩ መልኩ (ጨካኞች፣ ፈላጭ ቆራጮች፣ አምባገነኖች፣ ተቃውሞን በጭራሽ የማይፈቅዱ ባለአንድ ፓርቲ ጉልበተኞች ወዘተ.) የሚገለጹ አገዛዞችም አሉ፡፡ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተጠቀሱትን ዓይነት የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠባቸውን ወይም ጥቂት ‹ልሂቃን›/ቡድኖች የተቈጣጠሩአቸውን አገዛዞች ብዙዎች ከአሐዳዊ መንግሥት ጋር ባንድነት አይደምሯቸውም፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሠረት የደርግ ‹ኢሕዴሪ›ም ሆነ የወያኔ ‹ኢፌዴሪ› እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስም እና ከይስሙላ ‹ሕገመንግሥት› በዘለለ ‹አሐዳዊ› እና ‹ፌዴራላዊ› እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አይደሉም፡፡

ባንፃሩም የአሐዳዊው መንግሥት ተቃራኒ ተደርጎ የሚወሰደው ፌዴሬሽን እራሳቸውን በከፊል የሚያስተዳድሩ ግዛቶች ወይም አካባቢዎች ኅብረት በማዕከላዊ የፌዴራል መንግሥት ሥር የሚተዳደሩበት ሕገመንግሥታዊ አደረጃጀት ነው፡፡ የተጻፉ ሕግጋተ መንግሥትን መሠረት በማድረግ ከአሐዳዊ መንግሥት አካባቢያዊ አስተዳደሮች በተለየ የፌዴሬሽን አባል መንግሥታት/ግዛቶች በውስጥ ጉዳያቸው የተሻለ ነፃነት አላቸው፡፡ በአባል ግዛቶቹና በማዕከላዊው ፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው የሥልጣን ክፍፍልም የፌዴራል ሥርዓቱን በሚያደራጀው ሕገመንግሥት በግልጽ ይመለከታል፡፡

ይሁን እንጂ የኛዎቹ የጐሣ ደናቁርት እንደሚቀባጥሩት አሐዳዊነት ማለት አንድ ባህል፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ/አመለካከት ማለት አይደለም፡፡ ወይም የመንግሥትን ሥልጣን የጨበጠው አካል የሌሎች ማኅበረሰቦችን ማንነት ጨፍልቆ አንድ ወጥ የሆነ ማንነት በግድ የሚጭንበት ሥርዓት ማለት አይደለም፡፡ በርግጥ ቋንቋን በሚመለከት ከአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ብቸኛ የራሷ ፊደል/ጽሑፍ ያለው ቋንቋ ያላት ኢትዮጵያ (ጊዜው የመንደርተኞች ሆኖ እንጂ ቢያውቁበት ብሔራዊ መመኪያነትና ኩራቱ ለሁላችን ነበር) ለኢትዮጵያውያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪቃ መግባቢያ መሆን የሚችል ብቁ ቋንቋ አበርክታለች፡፡ ይህ በዘመናት የታሪክ ሂደት የዚህኛው ማኅበረሰብ ብቻ የማይባል፣ ነገድ/ጐሣ አልባ ቋንቋ ብሔራዊ መግባቢያ ሆኖ በአራቱም ማዕዝናት ያሉ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦችን (የየአካባቢያቸውን መግባቢያ ቋንቋ ሳያጠፋ) አስተሳስሯል፡፡ ዛሬ ይህንን ‹ጅማት› ለመበጠስ ግዝገዛው ከተጀመረ ሦስት ዐሥርታት ተቈጥረዋል፡፡ 

አሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓት በመንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲ) ከታጀበ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባጠቃላይ አካባቢያዊ ማንነቶችን ማክበር ብቻ ሳይሆን አድገው በልጽገው ለጋራ ብሔራዊ ማንነት ታላቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሥርዓት ነው፡፡ ፌዴራላዊው ሥርዓተ መንግሥትም በዴሞክራሲ ላይ ከተመሠረተ ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ አገር አሐዳዊም ይሁን ፌዴራላዊ ለአገሩ ዕድገት ለሕዝቡም ሥልጣኔና ብልጽግና ሲባል በዓለም ሀገራት ኅብረት ውስጥ የራሱ ልዩ መለያ አለው፡፡ ይኸውም የታወቀ የጋራ መልክዐ ምድር፣ የጋራ ብሔራዊ ታሪክ፣ የጋራ መግባቢያ ብሔራዊ ቋንቋ፣ የጋራ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ፣ የጋራ ብሔራዊ መዝሙር፣ የጋራ ብሔራዊ ባህል፣ የጋራ የእሤቶች ሥርዓት፣ የጋራ ብሔራዊ ሥነ ልቦና ናቸው፡፡ እነዚህ የአንድ አገር ሕዝብ የጋራ መለያዎች የሚገነቡት እጅግ እልህ አስጨራሽ በሆነ ሂደት ነው፡፡ ደጋ መውጣት÷ ቆላ መውረድ፣ ፍቅርና ጠብ፣ ጦርነትና ሰላም፣ ወረራና ሰፈራ፣ ንግድና ፍልሰት፣ ቀጠናና በሽታ፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ ሥራ ፍለጋና ጋብቻ፣ መንፈሳዊና የጉብኝት ጉዞዎች ወዘተ. በመሳሰሉት መስተጋብሮች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡  ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ በዚህ ዓይነቱ የሺህ ዘመናት ሂደት ድርና ማግ የተሸመነች አገር በመሆኗ፣ የተሠራንበት የባህል÷ የሃይማኖት÷ የቋንቋ÷ የነገድ/ጐሣ ብዝኃነት ሰበዝ፣ አለላና ቀለማት ኢትዮጵያዊነት የሚለውን የአንድ ሕዝብ የጋራ ማንነት ለመሰበዝ እንቅፋት አልሆነንም፡፡ ይሁን እንጂ ከመሠረታቸው የተነጠሉና ከሥራቸው የተነቀሉ እንዲሁም በቅልውጥ የሚኖሩ የጐሣ/ዘር ፖለቲከኞች በበታችነት ስሜት እያቃሰቱ፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን በብዙ ድካምና ጥንቃቄ ከሠሩት የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ‹ስፌት›፣ አለላ÷ ሰበዙንና ኅብረ ቀለማቱን አንድ ባንድ እየመዘዙ በመጣልና በማውጣት ሀገር አልባ ሊያደርጉን ቈርጠው ተነስተዋል፡፡

ሆኖም ለሁለቱም የመንግሥት አስተዳደራዊ አደረጃጀቶች የማዕዝን ደንጊያ የሆነውን ዴሞክራሲ መገንባት ከተቻለ (ከሁለት አንዱን ወይም ቅይጡን መምረጥ በጥናትና በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጸም ሆኖ) ጥቂት ዘረኛ ፖለቲከኞችና ጀሌዎቻቸው በተወላገደ አእምሮአቸው እንደሚያስቡት ሳይሆን ሕዝብ በዜግነቱ ለዘመናት ሲመኛቸውና ሕይወቱን ጭምር ሲገብርላቸው የቈያቸው የዴሞክራሲ ትሩፋቶች – ነፃነት፣ እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ፣ መልካም አስተዳደር፣ ዕድገትና ልማት – እውን የማይሆኑበት ምክንያት አይኖርም፡፡

በሌላ በኩል አሐዳዊነት የዘረኞች መጠቀሚያ ሲሆን፣ አሐዳዊ ጐሠኛነትን (ethnic unitarism) እና አሐዳዊ ባህልን (cultural unitarism) በሌሎች ማኅበረሰቦች ክስረትና ውድመት ይፈጥራል፡፡ የሌሎች ማኅበረሰቦችን የአገር ባለቤትነት፣ መብትና ነፃነት ይነጥቃል፡፡ የሌሎች የሚሉትን ታሪክና ቅርስ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ ሃይማኖትና ባህል ከማጥፋት ወደኋላ አይልም፡፡ ዘላቂውን ለብልጭልጩ ይሰዋል፡፡ ወያኔና የአሁኑ ተረኞች እንዳደረጉትና እያደረጉ እንዳሉት ማለት ነው፡፡ ከማዕከል እስከ ክፍለ ሀገሩ የኛ፣ ከከተማ እስከ ገጠር መሬት የኛ፣ የገፀ ምድርና የከርሠ ምድር ሀብት የኛ፣ ከመንግሥት እስከ ግል መገናኛ ብዙኃን የኛ፣ ከባንኩ እስከ ታንኩ የኛ፣ ዐዋቆች÷ መካሮች ÷ ሽማግሎች ÷ ከሳሾችና አስታራቆች እኛ፣ ሁሉም እኛ/የኛ፡፡ በነገራችን ላይ መለ የመሸጉት ወንበዶችም ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ይህን ኢትዮጵያን ለኛ ብቻ የሚሉት አባዜ ስለቀረባቸውና ባሳደጉት ‹ባሪያ› ተረኝነቱን በመነጠቃቸው ነው፡፡ 

ርእሰ ጉዳዬ በዋናነት አሐዳዊ ሥርዓተ መንግሥትን በሚመለከት ያለውን የተዛባ አመለካከት በጥቂቱ ለመዳሰስ በመሆኑ፣ ለዚሁ ዓላማ ሲባል ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ከፅንሰ ሃሳብ አኳያ በአለፍ ገደም ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡ በአገራችን ዐውድ እንዳላነሳው በወረቀትም በተግባርም ያለው ውሸት ነው፡፡ በወያኔ ሰነድ የተቀመጠው የጐሣ/ቋንቋ ፌዴራላዊነት ሲሆን ይህም ‹ክልል› ብሎ በፈጠራቸው ‹አገሮች› ወጥነት ባለው መልኩ አልተቀመጠም፡፡ ‹ደቡብ› የሚባለው (አሁን በተረኞቹ እየፈራረሰ ያለው ክፍላተ ሀገር) ‹ክልል› ይህን ያፈርሰዋልና፡፡ ባንፃሩም በተግባር ያለው የ‹ክልሎችን› አስተዳደር ስንመለከት አሁንም ሆነ በዘመነ ወያኔ ማዕከላዊ መንግሥቱን የሚመራው አንድ ማዕከላዊ ፓርቲ በሚልካቸው የፓርቲ ሹመኞች በሞግዚት የሚደረግ አስተዳደር ሲሆን (የአባይ ፀሐዬና የስዩምመስፍን አቻ አባዱላን ዐቢይ ‹ደቡብን› እንዲያስተዳድር/እንዲያፈርስ? በሞግዚትነት እንዳስቀመጠው፣ አ.አ. ላይ ሕገ ወጡን ታከለን እንደመደበው)፣ ‹የክልሎች ሕገመንግሥት› የተባለውን ጽፎ በመስጠት፣ በበጀት ዝግጅትና ድልድል፣ በፖሊሲዎች ቀረፃ፣ የኢኮኖሚ አውታሮችን በመቆጣጠር ወዘተ. ያለው ሥርዓት ወያኔና ጀሌዎቹ በተወላገደ አእምሮአቸው ‹አሐዳዊ› የሚሉት መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ያውም በንቅዘት፣ በወንጀል፣ የአገርን አንድነትና ሉዐላዊነት በማናጋት ላይ የተመሠረተ ‹አሐዳዊነት›፡፡ ስለሆነም የወያኔዎችና ተረኞቹ ክስ የሕዝብን ጩኸት መቀማት ይመስላል፡፡ የ‹አሐዳዊነት› ታንቲራ ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት ተቋማዊ ያደረገው ቅጥፈት አካል ነው፡፡

ለማጠቃለል አሐዳዊም ሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓቶች ሕገ መንግሥታዊ የአገር አስተዳደር አደረጃጀት ዘይቤዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ጠቀሜታም ጉዳቶችም አሏቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ባለመሆኑ አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎቻቸውን ከዚህ አላነሳንም፡፡ መታወቅ ያለበት ሁለቱም እንከን የለሽ የአስተዳደር መዋቅር ሥርዓቶች አይደሉም፡፡ እያንዳንዱ አገር/ሕዝብ የራሱን ልዩ ገጽታ ከግምት በማስገባት ካሉት ዐዋቆች ጋር ተማክሮ፣ ከሁለት አንዱን ወይም ቀይጦ የሚበጀውን መምረጥ ይችላል፡፡ ከዕብደትና ድንቊርና ወጥተን ወደ ዐቅላችን ስንመለስ እውን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ አሐዳዊ የመንግሥት አደረጃጀትን የተወገዘ አድርጎ መቊጠር ዐላዋቂነት ነው፡፡ 

አገርን በዕውቀትና በሕግ የበላይነት ያስተዳደሩ፣ ክህሎቱ ያላቸውና ልምድ ጠገብ የፖለቲካ መሪዎች (statesmen) ይመስል ወያኔና ተረኞቹ ራሳቸውን ‹ፌዴራሊስት› ምንትሴ ሲሉ መስማት እና ይህንንም እንቶ ፈንቶ ተቀብለው የሚያራግቡ ቅጥረኛ የገደል ማሚቶዎች መገኘታቸው የሚገርም ነው፡፡ የፖለቲካችንንም ጥሬነት አመልካች ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መልክዐ ምድር ላይ አሐዳዊ፣ ፌዴራላዊ እና ኮንፌዴራላዊ የሚባል ነገር ወሬው ካልሆነ ሁሉም በተግባር የለም፡፡ አንዳንድ ብዙኃን መገናኛዎችም በቂ ፅንሰ ሃሳባዊ ግንዛቤ ሳይኖራችሁ ሰዉን አታሳስቱ፡፡ ሙያን በሚመለከት ማናቸውም ጉዳይ ዐዋቆችን ጋብዙ እንጂ ራሳችሁ ሁሉን-ዐወቅ ኤክስፐርት የማድረግ አባዜ ቢቆም ሁላችንም እናተርፋለን፡፡

አሁን ጐሠኞቹ ጌታቸው ወያኔ በጻፈላቸው ‹ሰነድ› መሠረት (ወረርሽኙን ጥግ አድርገው) ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀን ከሌት እየተጣደፉ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡ በየክፍላተ ሀገሩ ያለውን ተልእኮ የዐቢይ ኢሕአዴጋዊው ‹ብልጽግና› ሲመራው፣ አዲስ አበባን በሚመለከት ደግሞ ሕገ ወጡ የዐቢይ ሹመኛ ከአለቃው ጋር በጥምረት ማፈናቀሉን፣ መሬት ወረራውን፣ ነዋሪዎች የገነቡትን የጋራ መኖሪያ ቤት ለተረኞች አሳልፎ መስጠቱን፣ ታሪክና ቅርስ ማጥፋቱን (ለአብነት ያህል ዖፈ ጣዎሱ እና በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን የማፍረሱ ዘመቻ)፣ ቢሮክራሲውን በጐሣ አንድ ወጥ ለማድረግ መሥራቱን፣ ከ‹ወንጀለኛ ነጋዴዎች› ጋር ተባብሮ ኅብረተሰቡን ማዘረፉን፣ ባጠቃላይ የኦሮሞ የጐሣ ፖለቲከኞች የሚያስቧትንና ‹የኛ› የሚሏትን አ.አ. ወያኔ ከ25 ዓመት በፊት የፈጠረላቸው ‹ኦሮሚያ› የሚሉት ‹አገር› አካል ለማድረግ ‹ፕሮጀክታቸውን› በማጠናቀቅ የአ.አ. ነዋሪዎችን የከተማቸው ባይተዋር ለማድረግ ተቃርበዋል፡፡ በዚህ በመናገሻ ከተማችንም ሆነ በየክፍላተ ሀገሩ የሚደረገውን አገራዊ ጥፋት፣ የወያኔን አጥፊ ‹ሰነድ› ለማስከበር በሚል ሽፋን በጐሣ ያደራጁትን ‹የአገር መከላከያ› ÷ ፖሊስ÷ ልዩ ኃይል÷የጸጥታ ኃይሎችን አሰልፈው ሕዝብንና አንድ ሁለት ተብለው የሚቈጠሩ ተቃዋሚ ኃይሎችን የማፈኛ መሣሪያ አድርገዋል፡፡ ለጊዜው የጨለማው ኃይሎች የበረቱ ይመስላል፡፡ ወረርሽኙም ባተ-ክረምቱም ጨለማውን ያፀናው ይመስላል፡፡ ሕዝቡም ትክክለኛ መረጃ የሚሰጠውና በሥርዓት የሚያደራጀው አጥቶ በውዥንብርና ድንግዝግዝታ ውስጥ ይገኛል፡፡ 

መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችንን ነፍሳት ይማርልን፡፡ 

Filed in: Amharic