>
7:51 pm - Monday May 29, 2023

"ኑ እንዋቀስ!" (አሰፋ ሀይሉ)

 

“ኑ እንዋቀስ!”

አሰፋ ሀይሉ

  – ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ መለያየት ሞት ነው፣ 2010 ዓ.ም.*
እኛ ኢትዮጵያውያውን ከወራሪዎቻችን አንፃር ብዙ ጀግንነትና ብዙ ኩራት አለን፡፡ ከገዢዎቻችን አንፃር ደግሞ ብዙ ቅሬታና ብዙ ውርደት አከማችተናል፡፡ ለዛሬ የጀግንነቱ መወድስ ይቆይና፣ የቅሬታና የውርደት መዝገባችን ይገለጥ፡፡ ከገዢዎቻችን አንፃር ቅሬታ ሲያድርብን አንድም እንተርታለን፣ አለበለዚያም እንዘፍናለን፡፡ የምንተርተውና የምዘፍነው እምድጃ ዳር ሰው ሁሉ መተኛቱን አረጋግጠን ነው፡፡ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ዘመኗ ምንትዋብ አደባባይ ላይ የቅሬታ ተረትና ዘፈን አንሞክርም፡፡ እንዲያማ ቢሆን ቅሬታን ውርደት አይከተለውም ነበር፡፡ አንድ የቅሬታ ተረት እንጥቀስ፡-
‹‹ሹም ለሹም ይጎራረሳል፣ ድሃ ለድሃ ይለቃቀሳል››
ይሄ ቀቅሬታ ዛሬም አለ፡፡ በአደባባይ መተረት ግን ሞታችን ነው፡፡ ተረቱ የክት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ይሄን ተረት ይዞ ገበያ የወጣ ‹‹ልበ-ድፍን›› ለእርሱ ወዮለት፡፡ የቅሬታና የውርደት ታሪካችን የሚያመለክተው ይሄንኑ ነው፡፡
በጠላት ጊዜ ህዝባዊ የቅሬታ ተረት ይዘው አደባባይ የወጡ ሶስት ወንድማማቾች ነበሩ አሉ፡፡ ጣሊያን ይሄን ሰምቶ ባንዳዎቹን በመላክ ያለምንም ችግርና እንቅፋት ከህዝብ መካከል ወንድማማቾቹን መዝዞ ይዟቸው ሄደ፡፡ በዝግ ችሎት የፋሺስትን አንቀፅ ጠቅሶ ሶስቱም ላይ ሞት ፈረደ፡፡ ሰቀላቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ ሶስቱ ወንድማማቾች ለህዝብ ቅሬታ ሳይሆን ለምድጃ ዳር ዘፈን ተመለመሉ፡-
‹‹ወይ አውቀው አያውቁ፣
ወይም አይጠይቁ፣
የነሲቡ ልጆች ሶስቱም ባንዴ አለቁ!››
ይቺ ህዝባዊ ዘፈን ህዝባዊ ርድነትን ወደ ሰማዕቶቹ የማዞር ጥበብ አለባት፡፡ ቅሌቱ የማነው? የህዝቡ? ወይስ የሶስቱ ወንድማማቾች? የህዝብን ቅሬታ ይዞ አደባባይ መውጣት አለማወቅ ነው? አደባባይ መውጣቱ የሚያስከትለው ዕዳ የአደባባይ ወጪው ብቻ ነው? …
ይሄ ህዝባዊ ውርደት በኛ ታሪክ ውስጥ ተደጋግሟል፡፡ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት የሞቱት እንዲያ ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ከማይጨው ጦርነት በኋላ ወደ አውሮፓ መሸሻቸው ደጃዝማቹን አስከፋቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ አጋጣሚ ህዝቡ የሚጠቀምበትን ‹‹ህዝባዊ መንግሥት›› (ሪፐብሊክ መንግሥት) የማቋቋም ፍላጎት አሳዩ፡፡ ፍላጎታቸው ከጠላት መሸነፍ በኋላም (አፄው ከተመለሱ በኋላ) አልከሰመም፡፡ በዚህ ሳቢያ ግጭት ተፈጥሮ እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ህዝብ መሐል ሆነው፣ ለህዝብ ጥቅም እየታገሉ፣ የመጨረሻ አማራጭ ራስን ማጥፋት መሆኑ አይደንቅም? ለየትኛው ህዝብ ነው ‹‹ህዝባዊ መንግሥት›› እንዲቋቋም የጠየቁት? ህዝቡ የለም? ወና አገር ነው? እንደ አጥማቂው ዮሐንስ የበረሃ አንበጣ እየበሉ፣ በረሃ ላይ ነው የጮሁት? ካልሆነ ታዲያ…???
ውርደት አይመስለንም እንጂ፣ የውርደት ታሪካችን ብዙ ነው፡፡ ሊጋባ በየነ ወንድማገኝ የተሰኙ መኳንንት ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ፀብ ገጠሙ አሉ፡፡ መቼም ለራሳቸው አይደለም፡፡ ለራሳቸው ቢሆንማ ሊጋባነቱ በበቃቸው፣ ካልበቃቸውም ተለማምጠው በተጨመረላቸው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሊጋባ በየነ ‹‹ሃይ ባይ›› ህዝብ በሌለበት አሰቃቂ ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ውሃ ተከልክለው በውሃ ጥም አርረው ሞቱ፡፡ ይህ ሲሆን እኛ ምን አደረግን? ማድረጉ ይቅር ምን አልን? ምንም!! እንደውም የጭካኔውን ፍርድ የሚያበረታታ ዘፈን አወረድን፡-
‹‹ጠጅ አልጠጣም ብሎ እንደተጀነነ፣
ውሃ-ውሃ እያለ ሞተ አሉ በየነ!››
ዘፈንን ከክብር በላይ አስበልጠን እናይ ይሆን? ካልሆነ በላይ ዘለቀን ያህል አውራ አሰቅሎ ለዘፈን ማድላት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ‹‹በላይዬ ሸጋው በላይዬ፣ በላይዬ ጀግናው በላይዬ›› ብሎ መዝፈን ከበላይ በላይ ይጠቅመን ይሆን?
‹‹ተሰቀለ ቢሉ ካፖርታው ነው ብዬ፣
ተሰቀለ ቢሉ ጠበንጃው ነው ብዬ፣
ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሰውዬ!››
ቢያንስ በሞቱ አልተሾፈበትምና የበላይ ሁኔታ ከሌሎቹ ይሻላል፡፡ ከእነ አቶ በዛብህ ለማለት ነው፡፡ አቶ በዛብህ በጥይት ተደብድቦ ሲገደል ልብሱ በባሩዱ እሳት ስለተያያዘ አካሉ ተቃጠለ አሉ፡፡ ያኔ እንዲህ ተብሎ ተዘፈነበት፡-
‹‹አንተም ክፉ ነበርክ፣ ክፉ አዘዘብህ፣
እንደ ገና ዳቦ፣ እሳት ነደደብህ!››
ግለሰብ ምን ክፉ ቢሆን የገዢዎችን ያህል ኃይል የለውምና ጉዳቱ ያን ያህል ነው፡፡ እንደውም መንግሥትን በማስጋት የማለዘብ ጠቀሜታ ሳይኖረው ቀረ ብላችሁ ነው? እንኳን ህዝባዊ ቅሬታ ያለው ቀርቶ፣ ከግለሰብ ጋር ተጋጭቶ የሸፈተን ግለሰብ ገዢዎች ‹‹ምሬሃለሁና ግባ!›› ማለታቸው ህዝብ ማኩረፊያ እንዳያደርጋቸው ሳይሆን ይቀራል?
በዚህ ዘመን ግለሰባዊ ተጋፋጭነትን በህዝባዊ መንፈስ አቅፎ-ደግፎ መከላከል የታየው ትንሽም ቢሆን በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የክስ ሂደት ላይ ነበር፡፡ ሁኔታው የክስ መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ሲላክ አብሮ የተዳፈነ ይመስላል፡፡ እንደ በላይ ዘለቀ በአደባባይ ባይሰቀሉም፣ እንደ ፊታውራሪ ታከለ ራሳቸውን ባያጠፉም፣ እንደ ሊጋባ በየነ በውሃ ጥም ባይከነተሩም.. እዚህ ዘመን ላይ ህዝብን ያሉ ግለሰቦች ፍዳ እየተቀበሉ ነው፡፡ እኛ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከስላቅ፣ ከተረትና ከዘፈን ባሻገር የያኔዎቹ ኢትዮጵያውያን የረበበባቸው ምንቸገረኝነት እንደሰፈነብን ነው፡፡
ግለሰብ ከህዝብ የበለጠበት ዘመን ቢኖር ይሄ ጊዜ ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግፉአኑ ግለሰቦች ህዝብ ከእነሱ የሚጠብቀውን ሩቡን እንኳ እነሱ ከህዝብ የማይጠብቁ ሆደ ሰፊዎች ናቸው፡፡ ዝምታቸው ለተረዳው ይጫጫናል፡፡ የተወሰነባቸውን ያለቅሬታ መቀበላቸው ይወቅሳል፡፡ በእስርም ውስጥ እያሉ በአቋማቸው መፅናታቸው ‹‹እኛ ማነን?›› እንድንል ግድ ይላል፡፡ ለመሆኑ እኛ ማነን? …
መንግሥት ከሮጡለት ውሻ ነው፡፡ የገቡበት ይገባል፡፡ ግን በመሮጥና በመሸሽ ትጋት ደክመናል፡፡ ከኛ ተነጥላው ‹‹ለውሻው›› ክራንቻ ጥርስ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን መለስ ብሎ ለማየት እንኳ ፍርሃታችን አልፈቀደልንም፡፡ ከሚሸሽ ህዝብ ተነጥሎ፣ በውሻው ለመዘንጠል ወስኖ የሚቆም ግለሰብ ማፍራት ለህዝብ ኩራቱ ነበር፡፡ አቋሙ ምንም ይሁን ምንም፣ የሚያሯሩጥ ገዢን ዓይን-ለዓይን የሚገጥም ግለሰብ መፍጠር ለህዝብ መታፈሪያው ነበር፡፡ እኛ ግን አንዱን ለወንጭፍ ሌላውን ለወፍ ዳርገን ምንም ያልተፈጠረ ለማስመሰል እንጥራለን፡፡ እንዲህ ያለ ህዝብ መታፈሪያ ግርማው ምንድነው? ‹‹ሲጭኑት አህያ፣ ሲጋልቡት ፈረስ›› መሆኑም አይደል? ከእንዲህ ያለ ትቢያ ውስጥ እንዴት ያለ ‹‹ጨዋ ህዝብነት›› አንጥረን እናወጣ ይሆን??
አንሰማውም እንጂ ከወደታች የሚነፍስ ‹‹ኑ እንዋቀስ›› የሚል ፀጥተኛ ድምፅ አለ፡፡ ድምፁ የግለሰቦች ነው፡፡ የሚዋቀሰው ከአካላችን ሳይሆን ከህሊናችን ጋር ነው፡፡ የአገልግሎት ዋጋቸውን በልተን በዕዳችን ያስጠየቅናቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ ጡጫና እርግጫ የጠገቡት እነርሱ እያሉ እኛ ግልምጫ የሚሸሽ ውርደታም ህዝብ ሆነናል፡፡ ልጆቻችንን ሰብስበን የእነሱን ልጆች በትነናል፡፡ ቤተሰቦቻችንን ሸክፈን የእነሱን ቤተሰብ አንከራተናል፡፡ ቤታችንን አሙቀን የእነሱን ጎጆ አቀዝቅዘናል …
‹‹ኑ እንዋቀስ!›› ይላል ንፋሱ፡፡
እንደኛ ‹‹ጨርቄን ቅሌን›› ስላላሉ፣ ‹‹ጨርቅና ቅል›› እንደሌላቸው መቁጠር የጨዋ ህዝብ ወግ አይደለም፡፡
‹‹ኑ እንዋቀስ!›› ይላል ንፋሱ፡፡ 
/የፅሑፉ ምንጭ፡- ከዓለማየሁ ገላጋይ፣ ‹‹መለያየት ሞት ነው›› በሚል ርዕስ፣ በ2010 ዓ.ም. ካሳተማት አነስ ያለች ጥራዝ፣ ከገጽ 28-31 ‹‹ኑ እንዋቀስ!›› በሚል ርዕስ ሥር (ለታሪክ ፍርድና ለህሊናችን ኢትዮጵያውያን ራሳችንን እንድንመረምር ደራሲው በጥቂቱ ነገር ግን በስል ልሳን ካሠፈረልን የወቀሳ ጽሑፍ) በቀጥታ የተወሰደ ነው፡፡ ለደራሲው እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር፣ ለሁላችን መልካም ጊዜ፡፡/
————————–
| *ደራሲው ዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹መለያየት ሞት ነው›› የምትል መጽሐፉን መታሰቢያነቷን ያበረከተው በወቅቱ እስር ላይ ለነበረው ወዳጁ ‹‹ለተመስገን ደሳለኝ (ተሜ)›› ይሁንልኝ በማለት ነበር፡፡ ደራሲውን በድጋሚ አመሰገንኩ፡፡ ደግሞ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፏን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለብዶ በአንዱ የተቀደሰ የጠረጴዛ ምሽት ወጋችን መዘዝ አድርጎ በሥጦታ ያበረከተልኝን የመድኃኒዓለሙን ውድ ተናፋቂ ወዳጄን ‹‹መለያየት ሞት›› ቢሆንም – ይኸው በመጽሐፍ ሥጦታህ የተነሳ አልተለያየንም፣ ከድርሰቱም፣ ከወቀሳውም እፍታ አብረን እየኮመኮምን ነው – ስለ ሥጦታህ ከልብ አመሰግናለሁ – ብዬ መሰናበት ፈለግኩ፡፡| 
 
ለሁላችን ልቦናውን ይስጠን፡፡ 
 
እነሆ ተሰናበትኩ፡፡
Filed in: Amharic