>

"...ህገ መንግሥትም የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው፣ ፖለቲካም የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው”  (ደጀን የማነ በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር)

“…ህገ መንግሥትም የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው፣ ፖለቲካም የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው” 

ደጀን የማነ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ህግ መምህር

• በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት የመጀመሪያ፣ ተቀዳሚ እና በጣም ዝቅተኛ የሚባለው ኃላፊነቱ የዜጎችን ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ነው።
•ፖለቲከኛ ወንጀል ሲሠራ በወንጀል ሊጠየቅ ይገባል፤ መንግሥት ፖለቲከኛን በፖለቲካ አስተሳሰቡ ምክንያት አሠረ እንዳይባል ፈርቶ የሚተው ከሆነ አሁንም መንግሥት የህግ የበላይነትን እየጣሰ ነው
• የህግ የበላይነትን ከማስከበር ረገድ የመንግሥት አንደኛው ኃላፊነት ለአገሪቱ ህጎች ራሱ ተገዢ መሆኑ ነው። መንግሥት ህገ መንግሥቱን፣ የወንጀል ህጉን፣ የግብር ህጉን እና ሌሎች ህጎችን ማክበር ይጠበቅበታል፤ ግዴታም አለበት።
• መንግሥት የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት የዜጎችን መብት ያለመጣስ፤ ዜጎችን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ያለማሰር፤ ዜጎች ሲታሰሩ ህጉ በሚፈቅደው አግባብ የመያዝ፤ ወደ ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ የመሰማት፣ የመደመጥ መብታቸውን ማክበር አለበት።
• ፖለቲከኛ መታሰር ያለበት ፖለቲካ አስተሳሰቡን ስለሚያራምድ አይደለም። መታሰር ያለበት ወንጀል በመሥራቱ ነው። ሲፈታም በህግ አግባብ ይፈታል። በፖለቲካ አግባብ አይፈታም ማለት ነው። በፖለቲካ አግባብ ጫና ቢፈጠር እንኳ ጉዳዩ የተያዘው በፍርድ ቤት ወይም በፖሊስ በመሆኑ የፍርድ ሂደቱን መጠበቅ ይኖርበታል። ከወንጀል ድርጊቱ ነፃ ከሆነ ነፃ ይወጣል፤ ጥፋተኛ ከሆነ ይፈረድበታል፤ ማንም ሰው ከህግ በታች መሆኑን በዚህ ማሳየት ይቻላል።
• ከውጭ ፖለቲከኞች ከገቡ በኋላ ሀገር ውስጥ ያሉ ህጎችን አክብሮ የመንቀሳቀስ ግዴታና ኃላፊነት ነበረባቸው። አንዳንድ በተለያዩ ቡድኖች የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዳሉ ይታወቃል። በቡድኖች የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መንግሥት በዝምታ ሲያልፍ ነበረ።
• ያ ስህተት ነው። ስለዚህ እዚያ ላይ ስህተቶች ነበሩ። ማህበረሰቡ ወጥቶ ለመግባት እየተሳቀቀ፤ የደቦ ፍርድ ሰፍኖ፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለ ሆኖ ገደቦች ሁሉ ተላልፈው እንደዚያ ሲፈጸሙ ህግ የማስከበር ሂደቱ እምብዛም ነበረ። በጣም ብዙ ጥፋቶች እዚህ ሀገር ላይ ተፈጽመዋል።
• የደቦ የህግ ጥሰት ወይም የደቦ ፍትህ የሚባለው ህገ ወጥ ነው። ችግሮች በህግ አግባብ ነው መፈታት ያለባቸው። አንድ ቦታ ላይ የህግ ጥሰት ፈጽሟል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ካለ በቡድንም ሆነ በግል ለፖሊስ ተቋማት ነው ጥቆማ መሰጠት ያለበት። የወንጀል ስነ ስርዓት ህጋችን ከአንቀጽ 11 እስከ 22 አስቀምጧል።
• በደቦ የሚደረጉ የህግ ጥሰቶች በሚስጥር የሚደረጉ አይደሉም። በአደባባይ ህዝብ እያያቸው የሚፈጸሙ ናቸው። በደቦ የህግ ጥሰት የፈጸሙት ከወንጀል ተጠያቂነት ማምለጥ አይችሉም።
• እዚያ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች በተሳትፏቸው መጠን በፍርድ ቤት ሊጠየቁ ይችላሉ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን መጠየቅ ያለብን አንደኛ ጥያቄ መንግሥት የት ነበረ የሚለውን ጥያቄ ነው። በአደባባይ በግልጽ የሚደረግ ወንጀል የመንግሥት አካላት ከፌዴራል እስከ ክልል፤ ከክልል እስከ ዞን ወረዳ ቀበሌ እየተባለ የተለያዩ የፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ አደረጃጀቶች አሉ። እነዚያ የት ሄዱ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
• ሁሌም ፖሊስ የማያያቸውና የማይደርስባቸው ወንጀሎች ሊኖሩ ይችላሉ። ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ፖሊስ ወይም ሌላ የህግ አካል ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን የፖሊስ ኃይል እያየው የሚፈጸምን ወንጀል፤ ወንጀል ለመፈጸም በሚያስችል መንገድ፤ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሊያስነሳ በሚያስችል መንገድ ሰዎች የጦር መሳሪያ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እየታየ ለማስቆም ተገቢው ጥረት ካልተደረገ ቁጥር አንድ ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግሥት ነው። መንግሥት ሲባል ወረዳ ላይ ከተፈጸመ የወረዳው ፖሊስ፤ የመንግሥት አስተዳደር ለምንድን ነው በአግባቡ የማይሠራው ብለህ ትጠይቃለህ ማለት ነው።
• አንድ የወንጀል ምርመራ በሂደት ላይ እያለ፤ ፖሊስም አቃቤ ህግም በዚያ ሂደት ላይ እያሉ የፖለቲካ ውሳኔ ተወስኖ ወንጀል ምርመራ ሂደቱ እንዲቋረጥ ማድረግ፤ ከህግ ውጪ በሆነ የምህረት አዋጅም ሆነ የይቅርታ አዋጅ ከሚፈቅደው ውጪ ሰዎችን መልቀቅም የህግ የበላይነትን መቃወም ነው። ምክንያቱም ፖለቲካውም ሆነ ሁሉም ከህግ በታች ስለሆኑ።
• ሰዎች ሲታሰሩ፣ ሲያዙና ሲፈረድባቸው በህግ አግባብ ቢሆን፤ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆነው ውሳኔ ቢሰጡ ከዚያ መጨረሻ ላይ በምህርትም ሆነ በይቅርታ የሚፈቱ ሰዎች ያንኑ ህግን መሰረት አድርገው ቢሆን በህግ የበላይነት ማመን በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት የመጣል ነገር ይኖራል።
• ሰዎች የሚታሰሩትም ሆነ የሚፈቱት ከህግ አግባብ ውጪ ከሆነ፤ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ከሆነ ማህበረሰቡ መንግሥትን ይታዘባል። ስለዚህ መንግሥት ሥራውን የሚሠራው በህግ አግባብ አይደለም። በፖለቲካ አመለካከት ነው ሥራ እየተሠረ ያለው ብሎ ወደ ማመን ይሄዳል።
• የዜጎች ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ማለት አንደኛው ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ካለ ወይም ጥቃት የሚፈጽም አካል ካለ እሱን መከላከል ነው። ከውስጥ ካለው ሁኔታ አንጻር ከደቡብ እስከ ሰሜን፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ዜጋው ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የማይፈራበትና፤ ቢንቀሳቀስም ጥቃት የማይደርስበት መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት።
• አንድ መንግሥት የጸጥታ አካሉ ጠንካራ ነው የሚባለው አንደኛው የታቀዱ የወንጀል ድርጊቶች ካሉ ቀድሞ በመከላከል ነው። በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ወንጀልን ቀድሞ መካለከል የሚባል ነገር አለ። መንግሥት ወንጀልን ቀድሞ የመከላከል ሥራ መሥራት አለበት።
• ዜጎች ግብር የሚከፍሉት ሰላምና ደህንነቴን መንግሥት የሚባል አካል ይጠብቅልኛል ብሎ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ጠባቂ የሌለው መንግሥትን ተማምኖ ነው። ምክንያቱም ግብር ይከፍላል። ለጸጥታ መዋቅሩ የሚሰጠው ደሞዝ ከህዝብ በግብር የሚሰበሰበብ ነው። ስለዚህ ህዝቡ መንግሥት ላይ መተማመን አለው ማለት ነው። ጥቃት ቢደርስብኝ መንግሥት ይከላከልልኛል ብሎ ነው። ስለዚህ መንግሥት ጥቃትን የማስቆም ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
• ከሀገር ውጪ ግለሰቦችም ሆኑ ሚዲያዎችን ተጠቅሞ ሀገር ውስጥ የተለያዩ ችግሮችን የሚፈጥሩ አካላትን መንግሥት ሊያደርግ የሚችለው እነዚያ ሚዲያዎች የተከፈቱበትና የሚኖሩበት ግለሰቦቹ ያሉበት ሀገር ላይ በወንጀል ድርጊት የሚጠይቅ ከሆነ ወንጀለኛን አሳልፎ መስጠት የሚል ስምምነት ስላለ እሱጋ መሠራት አለበት። ምክንያቱም አንዳንዶቹ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ ዜግነታቸው የሌላ የሆነ ሰዎች አሉ።
• እነሱጋ ዞሮ ዞሮ በብሄራዊ ጥቅሜ ላይ ወንጀል ተፈፅሟል ብሎ የሚያስብ እና እንዲህ ዓይነት ነገር እያደረሱብኝ ነው ብሎ ካሰበ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት መኖር አለመኖሩን ፈትሾ ስምምነቱ ካለ ሀገራቱ አሳልፈው እንዲሰጡ መጠየቅ ያስፈልጋል።
Filed in: Amharic