>
5:18 pm - Friday June 15, 3562

የሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዕለተ ሰማዕትነት ሐምሌ 22 ቀን መታሰቢያ!!! (በድሉ ዋቅጅራ)

የሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዕለተ ሰማዕትነት ሐምሌ 22 ቀን መታሰቢያ!!!

በድሉ ዋቅጅራ

ሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ያችን ሰአት
     «እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ!!!»
ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ። አኩሪ በሆነ አባታዊ ኃላፊነታቸው ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸውን አረጋግጠው  ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም በሰማዕትነት አለፉ።
ስለ አቡነ ጴጥሮስ ክብር 
.
.
‹‹. . . .
የኔ ልጅ!
እውነትሽ ብርሀን ሲከላው፣ ጊዜና ትውልድ ሲከዱት፤
ለዘመኑ ኩነኔ ይሆናል፣ በንስሀ አያጸዱት፡፡
በላይ ዘለቀ ሀቅ አንቆት ነው፣ እንቢ ለእውነቴ እንዳለ፤
ቀንዲሉን በልቡ ይዞ፣ ውስጡ እንደተቃጠለ፤
ጀግናው ሽፍታ ተብሎ አደባባይ የተሰቀለ::
አቡነ ጴጥሮስ ባደባባይ፣ በጥይት የተደበደበ፣
ደብር እንዲፈታ ሽፍታ፤
እውነቱና ሕይወቱ፣ ህይወቱና እምነቱ፣ ብሎት ነው አልፋታ፡፡
ኧረ ስንቱ የኔ ልጅ! ኧረ ስንቱ!
የቆረበለት እውነት ወደሮ፤
አንገቱ ላይ ተቋጥሮ፤
ስንቱ በሀቁ ታንቆ፣ እህል ውሀው እንዳለቀ፤
ለቆረበለት እውነቱ፣ በክብር እንደወደቀ፡፡
ቤቱ ይቁጠረው ልጄ፡፡
አጥተውት መሰለሽ ልጄ፣
በላይ ዘለቀ አድር ቢል፣ እጅ ቢነሳ አስመስሎ፤
ጴጥሮስ ለፋሽስት ቢሰብክ፣ የሀገር ወገን እውነቱን፤
የአካል የመንፈስ፣ እምነቱን ጥሎ፤
ጊዜ አጨብጭቦ፣ ወርቅ ተሸልመው፤
እንበለ ሀጥያት፣ ቅዱሳን ተብለው፤
በህይወት እንደሚኖሩ፤
እውነት ሽረው እንደሚከብሩ፤
አጥተውት መሰለሽ ልጄ!
ልጄ፣ እውነት ከህይወት ይከብዳል፤
በመኖር ከህይወት ተገኝቶ፣ መልሶ ህይወትን ይበላል፡፡ .. ››
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
         የአባታችን በረከት ይደርብን!
Filed in: Amharic