>

ደዌው እንደ መድኃኒት (ከይኄይስ እውነቱ)

ደዌው እንደ መድኃኒት

ከይኄይስ እውነቱ


የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዐላዊ የግዛት አንድነት የሚጠበቀው በኢትዮጵያዊ ዜግነት በመሰባሰብና ለዚሁ ዓላማ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተነጋሪ እንደ አንድ ሕይወት ነዋሪ ሆኖ በተግባር በመንቀሳቀስ  እንጂ በየመንደሩ በጐሣ በመሰባሰብ ሊሆን አይችልም፡፡  የኋለኛው ውጤትማ አገር ማፍረስ መሆኑን ከበቂ በላይ አይተንዋል፡፡ … እስከማውቀው ድረስ በዘር ተደራጅቶ የአገሩን አንድነት ያስጠበቀ ሕዝብ በታሪክ አልተመዘገበም፡፡ መበተኛው/ማፍረሻው ማሰባሰቢያ፣ ደዌው መድኃኒት ከሆነማ የኢትዮጵያ ህልውና በቋፍ ነው የሚለው ሥጋታችን መሠረት የሌለው ነው ማለት ነው፡፡

 

ለዚህ አስተያየት መነሻ የሆነኝ ‹‹ኢትዮጵያን ለማዳን በብሄር መደራጀት›› በሚል ርእስ የተላለፈ ዝግጅት ነው፡፡ ዝግጅቱ ከተላለፈ ካንድ ዓመት በላይ ቢሆነውም ለማዳመጥ ዕድሉን ያገኘሁት በቅርቡ  ነው፡፡ ርእሰ ጉዳዩ ግን የአገራችን ሕማም ማዕከል ነው፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ከማይደራደሩት መካከል አንዱ እንደሆነ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን እና በራሱም አንደበት ጭምር ምስክር የተሰጠለት ነው፡፡ ዝርዝሩን ለማወቅ የሚፈልግ ከፕሮግራሙ አገናኝ አድራሻ (https://youtu.be/-8-wd63HaRI) ማየት ይችላል፡፡ 

የመልእክቱ ጭብጥ ቃል በቃል ባይሆንም ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ይመስላል፤ 

የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› በሥራ ላይ እስከዘለቀ ድረስ በየዘራችንም ቢሆን ተደራጅተን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ እንታገላለን፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት በየትኛውም መንገድ ይምጣ፤ እሰየው ነው፡፡ ከተደባለቀ ጐሣ የሆንክ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ከሆነ አንዱን መርጠህ የፈለግክበት ጐሣ ውስጥ ገብተህ ሥራ፡፡ በተለይም ‹የአንድነት ጎራ› በሚል የተሰባሰቡ የፖለቲካ ማኅበራት አመራሮች አብዛኞቹ ከአማርኛ ተናጋሪው ማኅበረሰብ የተገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች አሁን መሬት ላይ ባለው እውነታ በጐሣ የተደራጁት ‹ክልሎች› ውስጥ ገብተው ማናቸውንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከጐሣ ክልሎቹ ፈቃድ ውጭ ማድረግ ስለማይችሉ፤ እነዚህም ጐሠኞች በገዛ ፈቃዳቸው የጐሣ ፖለቲካውንም ሆነ የጐሣ ክልሉን እንዲሁም ለዚህ ሕጋዊ መሠረት የሆነውን የወያኔ ‹ሕገመንግሥት› ስለማይተዉ ያለው አማራጭ ዓላማቸውን ሳይለቁ በጐሣ ተደራጅቶ ለኢትዮጵያ አንድነት መታገል ነው፡፡ የአንድነት አቀንቃኞች ነን የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በኦሮሞ ጐሠኞች የተደራጀው የዐቢይ ኦሕዴድ/ብልጽግና ወደ አንድነት ይወስደናል ብለው የሚያስቡ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለዐቢይ የሰጡት ድጋፍም ከዚህ እምነት የመነጨ ይመስላል፡፡ ታዲያ የአንድነት አራማጆች ነን የሚሉ ኃይሎችስ በጐሣ ተደራጅተው ይህንኑ ዓላማቸውን የማያሳኩበት ምን ምክንያት አለ? ስለሆነም በጐሣ ተደራጅቶ ወደ አንድነት እንሄዳለን የሚል ነው፡፡

 

የአስተያየቴ ዓላማም አገራችን በዚሁ በጐሣ ፖለቲካ በተፈጠረ ውጥንቅጥ ምክንያት በጭንቅ ባለችበት ሰዓት በጎንዮሽ ከንቱ ንትርክ ተጨማሪ ችግር መፍጠር ሳይሆን የችግራችን አስኳል በመሆኑ ደጋግሜ በተለያዬ ጽሑፎቼ እንደገለጽኩት እምነቴን ለማጋራት በማሰብ እንጂ ለተወሳሰበው የአገራችን ችግር ያለቀለት መልስ ለመስጠት አይደለም፡፡ ይህን ዓይነቱን መፍትሄ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ ዘላቂውን በማሰብ፣ የሕዝብን ፍላጎት አስቀድሞና ሕዝብን በዓላማ ዙሪያ አደራጅቶ አገዛዙን ባለማቋረጥ መገዳደር ይጠይቃል፡፡ ያን ጊዜ በእምቢተኝነት በሚደረግ ሰላማዊ ማስገደድ አገዛዙ የቆመበትንና ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ የሆኑ ምሰሶዎችን አንድ ባንድ መናድ ይቻል ይሆናል፡፡

በቅድሚያ የዚህ አስተያየት አቅራቢ የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ በጥቂት ኢትዮጵያውያን በብቸኝነት (በሞኖፖሊ) የሚያዝ፣ ለዚህ ወይም ለዛኛው ማኅበረሰብ ብቻ የተሰጠ እና አንዱ ለሌላው የሚያረጋግጥለት ወይም የሚያፀድቅለት አቋም እንዳልሆነ በሚገባ ይገነዘባል፡፡ ባንፃሩም ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዐ ምድር በሕግም ሆነ በተግባር ሰፍኖ ያለው ዘርን/ጐሣን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ሲሆን፣ ‹ክልል› የተባለውም አስተዳደራዊ መዋቅር በዘር የተደራጀ፣ ‹የፖለቲካ ማኅበር› የሚል ስያሜ የያዙትና እንደ አሸን የፈሉትም የጐሣ ቡድኖች መሆናቸው ምድር ላይ የሚታይ እውነታ መሆኑንም ማንም ይረዳል፡፡ 

በሌላ በኩል ይህ በወያኔ መሠረቱ ተጥሎ እሱ በፈለፈላቸው የጐሣ ድርጅቶችና በካድሬዎቻቸው ስብከት የቀጠለው የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት ዕድሜው 30 ዘመን ቢሆንም፣ ባገር ህልውናና በሕዝብ አንድነት ላይ ያደረሰውና አሁንም የደቀነው አደጋ፣ የአእላፍ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት በአሰቃቂ ሁናቴ መቅጠፉና አሁንም መቀጠሉ፣ ዘላቂ የአካልና የአእምሮ ጉዳት ማድረሱ፣ ሀገራዊ ሀብት ማውደሙ፣ በገንዘብ የማይተመን ሀገራዊ እሤቶችንና ቅርሶችን ማጥፋቱ፣ በጐሣ በተደራጁ ሀገር-በቀል እና የውጭ ዜግነት ባላቸው አሸባሪዎች ጭምር የአገር ሰላምና ጸጥታ መድፍረሱ፣ የሕዝቡ ሰለማዊ ሕይወት መናጋቱ፣ ዜጎች በጐሣና ሃይማኖት ማንነታቸው ከኖሩበት አካባቢ መፈናቀላቸውና መሳደዳቸው መቀጠሉ፣ ወገኖቻችን በሥጋትና በመባነን እንደሚገኙ ወዘተ. የማይካድ ሐቅ ነው፡፡

እንደዚህ አስተያየት አቅራቢ እምነት ቀድሞ በወያኔ አሁን ደግሞ በኦሕዴድ የሚመራው የጐሣ አገዛዝ የ‹ሕግ›፣ የ‹ፓርቲ› እና መንግሥታዊ መዋቅሮችን ተጠቅሞ በግዴታም ሆነ በውዴታ በርካታ ተከታዮችን ማፍራቱ ባይካድም፣ እስከ የሌለውን ግፍና በደል ለፈጸሙ ወንጀለኞች (ከከፍተኛ አመራሮች እስከ ተራው ካድሬ) መሸሸጊያ ዋሻ መሆኑና ቀጣይነቱንም አጥብቀው የሚፈልጉት እነሱ መሆናቸው ቢታወቅም፣ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ (እንደ ሰለጠነው ዓለም ነፃና ተአማኒ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ድምጽ /public opinion poll/ የሚካሄድበት አገር ባይሆንም) ፍላጎት መብቱና ነፃነቱ ተከብሮለት በእኩልነት፣ በአንድነት፣ ባንድ አገር ሕዝብነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን መሆኑን በየጊዜው አስመስክሯል፡፡ ግፍና በደሉን ተሸክሞ ትዕግሥት በተላበሰ ጨዋነት የመታዘቡም ጥልቅ መልእክት አገሩ በጐሠኞች ሳትከፋፈል ባንድ ሕዝብነት ለመኖር ያለውን ጽኑ ፍላጎት አመልካች ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ‹ለውጥ› የተባለው ሁናቴ ሲመጣም በመላው ኢትዮጵያ በዐደባባይ ወጥቶ ያሳየው ይኽንኑ ስሜት መሆኑ አይካድም፡፡ ታዲያ ጐሠኛነቱ ሠልጥኖብን የማይታረቅ ቅራኔ አድርገው እያጦዙት ያሉት እነማን ናቸው? የነማን ፍላጎት ነው? በጐሣ ተደራጅተው ሽብር እየፈጸሙ ያሉትና የጐሣ ፓርቲዎችን በበላይነት የሚመሩት ግለሰቦች፣ ካድሬዎቻቸውና ጭፍን ደጋፊዎቻቸው መሆናቸውን ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል፡፡

ከፍ ብዬ በተጠቀስኩት መርሐ ግብር ላይ የተንፀባረቀው ሃሳብ አዘጋጅና አቅራቢ አምኖበት ያደረገው ቢሆንም ጋዜጠኛው በግልጽ እንደተናገረው ያለንበት አገራዊ ሁናቴ ከገባንበት አጣብቂኝ መውጫ የሌለው (dead end) መሆኑን በመናገሩ ተስፋ የመቁረጥና የንዴትም (frustration) ስሜት ይንፀባረቅበታል፡፡ ቢጨንቅ፣ ቢቸግር፣ መላ ቢጠፋ የተሰነዘረ ሃሳብ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም ወንድማችን በጐሣ መደራጀት ሳያስፈልገን ከገባንበት አገራዊ ምስቅልቅል የሚያወጣ መንገድ ካለ አሳዩኝ ሲል ተማፅኖውን አቅርቧልና፡፡ ምንም እንኳን የሃሳቡ አደገኛነት ቢታየኝም ጋዜጠኛው ወንድማችን አውጥቶ አውርዶ የያዘውን የግል አቋሙን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ ወንድማችን እንዳልኸው ባሻህ መንገድ ሁሉ የኢትዮጵያ አንድነት አይጠበቅም፡፡ ባሻህ መንገድ ሁሉ ወደ አንድነት አይደረስም፡፡ ይህ እኮ የ30 ዓመታቱ የወያኔ የወራሹ የኦሕዴድ (ኢሕአዴግ) የዘር አገዛዝ ይቀጥል ብሎ መስማማት ነው፡፡ አንተ በዝግጅትህ እንደገለጽኸው ከላጋር ወደፒያሳ በሚወስደው ዋና ጎዳና ፊትህን ወደ ብሔራዊ ቴአትር አቅጣጫ አዙረህ እየተጓዝኽ ፒያሳ ወደሚገኘው ማዘጋጃቤት ለመድረስ ማለም ነው፡፡ ወያኔም ሆነ አሁን ያለው የኢሕአዴግ አገዛዝ ‹በጐሣዎች መፈቃቀድ የተመሠረተች ኢትዮጵያ› ብለው በአጥፊ ‹ሰነዳቸው› አስቀምጠዋል፡፡ አስቀምጠዋል ብቻ ሳይሆን ዘጠኝ ‹አገሮችን› ፈጥረዋል፡፡ ይሄ ቊጥር እንደሚጨምርም በደቡቡ የአገራችን ክፍሎች ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ጐሣዎች ሲፈቅዱ አብረው የሚኖሩባት፣ አላማረንም ሲሉ ተገንጥለው ሰማንያ የመንደር አገዛዞችን የሚመሠርቱበት በታኝ ሥርዓት ነው የተዘረጋው፡፡ 

የኢትዮጵያን አንድነት እፈልጋለሁ የሚል ኢትዮጵያው ተረድቶታል ወይም ሊረዳ ይገባዋል ከሚባሉት መሠረታውያን ዋናውና የመጀመሪያው ፖለቲካን በጐሣ ማደራጀት (የዘር ፖለቲካ) የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና ፀር መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዐላዊ የግዛት አንድነት የሚጠበቀው በኢትዮጵያዊ ዜግነት በመሰባሰብና ለዚሁ ዓላማ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተነጋሪ እንደ አንድ ሕይወት ነዋሪ ሆኖ በተግባር በመንቀሳቀስ  እንጂ በየመንደሩ በጐሣ በመሰባሰብ ሊሆን አይችልም፡፡  የኋለኛውማ ውጤቱ አገር ማፍረስ መሆኑን ከበቂ በላይ አይተንዋል፡፡ ጋዜጠኛው ወንድማችን ይህንን በሚገባ እያወቀ ነው ለውይይታችን ርእስ የሆነውን ሃሳብ የሰነዘረው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በዘር ተደራጅቶ የአገሩን አንድነት ያስጠበቀ ሕዝብ በታሪክ አልተመዘገበም፡፡ መበተኛው/ማፍረሻው ማሰባሰቢያ፣ ደዌው መድኃኒት ከሆነማ የኢትዮጵያ ህልውና በቋፍ ነው የሚለው ሥጋታችን መሠረት የሌለው ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ዘርና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው እልቂት የጐሣ ፖለቲካው ውጤት አይደለም ወይ? 

ጋዜጠኛው ደጋግሞ እንደገለጸው በአንድነት ስም የተሰባሰቡ የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ዓላማ አንድነት አለን እያሉ ርስ በርሳቸው መተማመንና አንድ መሆን አቅቷቸው ሲሰባሰቡና ሲበተኑ ኖረው አንዳች ቁም ነገር ሊሠሩ አልቻሉም፡፡ እነሱ አክብረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ እንዲያከብራቸው የሚፈልጓቸውን አገራዊ እሤቶች ጥናትና ምርምር አድርገው ሳያሳውቁ በስሜትና በሆያ ሆዬ ብቻ ስለ አንድነት መጮኽ ስብስቡን አንድ ሊያደርገው ባለመቻሉ ተማምነውና ተቀራርበው ሊሠሩ በሚችሉበት ጐሣ ተሰባስቦ ለኢትዮጵያ አንድነት መሥራቱን እንደመፍትሄ አቅርቦታል፡፡ 

ይህ ጸሐፊ በማንነቱ ግፍና በደል የደረሰበትና እየደረሰበት ያለ ማኅበረሰብ በማኅበረሰብ ድርጅት (ሲቪክ ማኅበር) መልክ ተደራጅቶ ራሱን የመከላከል፣ መብትና ጥቅሙን ማስከበር እንዳለበት ያምናል/ይደግፋል፡፡ ደጋግሞም በጻፋቸው አስተያየቶች ገልጾአል፡፡ ፖለቲካን በጐሣ ማደራጅት ግን በእሳት መጫወት ነው፡፡ ‹አብን› የሚባለው የጐሣ ድርጅት ለምን አብነት አይሆነንም? ዝቅ ብዬ እንደምገልጸው ጐሣ ያልሆነን ሕዝብ በጐሣ አደራጃለሁ ብሎ ሲባክንና ከጥፋት ወደ ጥፋት ሲሸጋገር እያየነው ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ጋዜጠኛው ወደ ጠርዝ የተገፋ ንግግር ያደረገው፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቀው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የአንድ ወይም ካንድ በላይ የሆኑ ጐሣዎች አባል ነው በሚል ታሳቢ ይመስላል፡፡ በርግጥ እውነታው ይሄ ነው ወይ? በቅድሚያ የአማርኛ ተናጋሪው ማኅበረሰብ የአንድ ጐሣ አባል ነው ወይ? ይህንን ሕዝብ ወደ ጐሣነት ያወረደው የቅርቡ የወያኔ የጐሣ ፖለቲካ አይደለም ወይ? ይህ ሕዝብ መነሻው ከሆነውና በታሪክ ከሚታወቀው የአማራ ሳይንት ነገድነት ወጥቶ፣ ቋንቋው የመንግሥት ሆኖ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ የመንግሥት ሕዝብ በመሆኑ ጐሣ/ነገድ አልባ መሆኑን አንጋፋ የታሪክና የቋንቋ ምሁራን (ጐሠኞች ባይቀበሏቸውም) ደጋግመው ተናግረዋል/ጽፈዋል፡፡ ስለሆነም በጐሣ ሳጥን ውስጥ ገብተህ ተደራጅና ለአንድነት ታገል የሚባል ሕዝብ አይመስለኝም፡፡ ለምን የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪውን ሕዝብ ዛሬ ታይተው ነገ ሊኖሩ በማይችሉ ራሳቸውን ኅብረ ብሔራዊ ብለው በጠሩ ጥቂት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እንመዝናለን? በመጀመሪያ ደረጃ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ጠንካራ ከሆነ የተወሰነ የመራጮች ሕዝባዊ መሠረት (constituency) ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን በጐሠኛነት የማያምነው ሕዝብ ሁሉ ወኪል ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ክርክር በጐሣ ለተደራጁትም ስብስቦች ይሠራል፡፡ ሌላው ምንም እንኳን ወያኔና አሁን ያለው አገዛዝ ለራሳቸው የጥፋት ተልእኮ አስገድደውት የጐሣ መታወቂያ ቢለጥፉበትም ቊጥሩ በቀላሉ የማይገመት፣ ድብልቅ ጐሣ ካላቸው ወላጆች የተገኘውን ጨምሮ ራሱን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ውጪ የጐሣ/ነገድ ማንነት እንዳለው የማይቀበል የትየለሌ ዜጋ አለ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች እንደሚያምኑት ጐሣ በውልደት የሚገኝ ተፈጥሯዊ ሳይሆን ሰዎች ተስማምተው የተቀበሉት በአእምሮአቸው የሚገኝ ኅብረተሰብ ፈጠር አሳብ (social construct) ነው፡፡ በርግጥ ሥር በሰደደ ጥላቻ ለተመረዙት፣ በማይጠረቃ ፍለጎትና የሥልጣን ፍትወት ለታወሩት ‹የተማሩ› የጐሣ ደናቁርትም ሆኑ በነዚህ መርዛማ ስብከት ለጠፋው ትውልድ ይህንን መናገር ትርጕም ላይሰጥ ይችላል፡፡

አይሆንም እንጂ የየትም ፍጪው ዶቄቱን አምጪው አስተሳሰብ የመጨረሻ መጨረሻ የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ በጐሣ ተሰባስቦና የጐሠኞችን ልብ በውይይት አሸንፎ የአገር አንድነትን ማምጣት አይቻልም፡፡ የጨነቀው ርጕዝ ያገባል ዓይነት አስተሳሰብ ካልሆነ በቀር፡፡ ሰሞኑን በርዕዮት ሜዲያ በሁለት ወንድሞቻችን መካከል የተካሄደውን ‹‹ውይይት›› የታዘበ አስቀድመው ጽንፈኛ አቋም ከያዙ ጐሠኞች ጋር ጨዋና የሠለጠና ውይይት ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት ይችላል፡፡ (https://youtu.be/d9069Tt6uUk ርዕዮት ሃሰሳ||ነፍጠኝነት እና የሀገር ባለቤትነት እና የብሄር ፖለቲካ 7/24/2020) ዛሬ ፖለቲካን በጐሣ ካዳራጁት አብዛኛዎቹ ቡድኖች ከአገዛዙ በሚሠፈርላቸው ድርጎ ነዋሪዎች/ተጠዋሪዎች እንጂ ዓላማ፣ ፕሮግራም፣ ርዕይ፣ ከሁሉም በላይ የራሳቸው የመራጮች ማኅበረሰባዊ መሠረት ያላቸው አይደሉም፡፡ በጐሣ ተደራጅቶ ውይይት እንዲደረግ የሚፈለገው ከነዚህ ጋር ነው ወይስ ከሽብርተኞቹ ወይስ በአገዛዙ ዙሪያ ከተሰባሰቡት ጐሠኞች ጋር?

በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚናገሩ መደበኛም ሆኑ የማኅበራዊው ብዙኃን መገናኛዎች፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ ራሳቸውን ቀስቃሾች (አክቲቪስቶች) ብለው የሚጠሩ ግለሰቦች፣ አንዳንድ ምሁራን ጭምር እንደሚሉት ‹‹የአንድነት ጎራ›› እና ‹‹የጐሠኞች ጎራ›› የሚባል ኢመደበኛ ክፍፍል እሰማለሁ፡፡ በርግጥ ጊዜው ፖለቲካ በጐሣ እንዲደራጅ ተፈቅዶ በርካታ የጐሣ ቡድኖች የሚፈነጩበት በመሆኑ ጐሠኛነታቸው አንድ ጎራ ውስጥ ሊከታቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ኢትዮጵያ በታሪክ ህልው ሆና ለዘመናት የኖረች አንድ ሉዐላዊት አገር፣ ሕዝቧም (የብዙ ነገዶች /ጐሣዎች ውጤት ሆኖ) አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን አብዛኛው ሕዝቧ ያምናል/ይቀበላል፡፡ በእኔ እምነት ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መደበኛው አቋም (default position) ነው፡፡ ለጊዜው በጐሠኛነት እባጭ ስለተሸፈነ መደበኛነቱን አያስቀረውም፡፡ ይህንን መደበኛ አስተሳሰብና አቋም ለመገዳደር በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተፀንሶ በወያኔ ፍሬ ያፈራው የጐሠኛነት ሥርዓት በኢትዮጵያ ላይ የበቀለ የታሪክ ‹‹እባጭ›› ወይም ደዌ ነው፡፡  ይህ እባጭ/ደዌ በበሽታው ከተጠቁት ጋር በመነጋገር የሚወገድ አይደለም፡፡ ከዚህ ደዌ የምንገላገለው መሠረቱ የሆነውን የወያኔ አጥፊ ‹ሰነድ›፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ የተዘረጋውን መዋቅር (‹ክልል›) እና ሥርዓት በማስወገድ ብቻ ነው፡፡ ከእንደነዚህ ዓይነት ኃይሎች ጋር ሃሳብ/ፅንሰሃሳብን መሠረት ያደረገ በዕውቀት፣ እውነት፣ ምክንያታዊነትና ጨውነት ላይ የተመሠረተ ሥልጡን ንግግር ማድረግ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የሐሰት ትርክት ሰለባ ሆነው ለጥላቻ የተዳረጉትን ወጣቶች በመደበኛ ትምህርትና በሃይማኖት መምህራን ጭምር ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚገባ ግን አያጠያይቅም፡፡ አገራዊ መልካም እሤቶችን የሚያውቁ፣ በግብረገብነት የታነፁና ስለአገራቸው በእጅጉ የሚያሳስባቸው ምሁራን ከእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ የሚርቁበት አንዱና ዋናው ምክንያት ብልግናና ዘለፋ ዋና ገጽታው በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ 

ከመነሻውም ጐሠኛነት የሰው ልጅ አእምሮ ሳይዳብር በኋላቀርነት፣ በእንስሳነት/መንጋነት የሚመራ የአነዋወር ዘይቤ በመሆኑ ለአመክንዮ፣ ለምክንያትና የሠለጠነ አስተሳሰብ ሕግ የሚገዛ አይደለም፡፡ የምናገረው ስለ ባለ ሜንጫዎቹ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ጐሠኛነት ሲሠለጥን ውጤቱ ያው ነው፡፡ ከክ/ሀገር፣ አውራጃ፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ መንደር እያለ እስከ ቤተሰብ ይዘልቃል፡፡ የኅብረተሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ አፍርሶ ታዝበናል፡፡ ጠላት ሳይፈጥር የሚፀና አመለካከት አይደለም፡፡ የሚጋጨው አካል ሲያጣ በዚህ ደዌ የተጠቃው ግለሰብ ከራሱ ማንነት ጋር (ድብልቅ ቢሆን አንዱን ወዶ ሌላውን እስከመጥላት የሚያደርስ) ሁሉ መጣላት ይጀምራል፡፡ ባጭሩ የፖለቲካ ጐሠኛነት ክፉ ደዌ በመሆኑ ጤናማ እና መጥፎ ተብሎ ልዩነት የሚበጅለት አይደለም፡፡  

በመጨረሻም አገራችን የምትገኝበት አሳሳቢ ሁናቴ ለጊዜው የሚያዝ የሚጨበጥ የሌለው ቢመስልም ዋና አገራዊ ሕማም ብለን የለየነውን ጐሠኛነት/መንደርተኛነት ላገራዊ አንድነት እንደ መፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ አደገኛ ነው፡፡ ስለሆነም አንባቢ በሙሉ ‹‹ማንም የቆመ ያለ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ›› የሚለውን የርእሰ መጻሕፍቱን ቃል ያስተውል፡፡  

Filed in: Amharic