>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7116

‹‹ የቴዎድሮስ መንፈስ አልሞተም እያደረ ሕይወት ይጨምራል እንጂ...!!!››  (በታርቆ ክንዴ)

‹‹ የቴዎድሮስ መንፈስ አልሞተም እያደረ ሕይወት ይጨምራል እንጂ…!!!›› 

በታርቆ ክንዴ

ለውጥን ለምን ፈራን ? ከትናንት መንገድ የዛሬው የተሻለ ነው፤ ከዛሬው ደግሞ የነገው ይሻላል፤ ይህ የመልካም አሳቢዎች ራዕይና ተስፋ ነው፡፡ ዛሬንና ትናንትን በተመሳሳይ መንገድ መሄድ አይቻልም፡፡ የሰው ልጅ ዘመንን ከራሱ ጋር እያስማማ የሚሄድ እንጂ ቆሞ ዝም የሚል አይደለም፡፡ ክፉ አስተሳሰብ እንጂ ክፉ ዘመን የለም ፡፡ ሰው ዘመንን ይዋጃል እንጂ ዘመን ሰውን አይዋጅም፡፡
ኢትዮጵያውያን  በዘመን ዑደት  በተለያዩ መሪዎች እየተመሩ፣ የተለያዬ ታሪክ እየሰሩ የመጡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያን ዘንድ መሽቶ በነጋ ቁጥር ጥቂትም ብትሆን ለውጥ ሳይታይበት ያለፈችበት ዘመን የለም፡፡ ነገር ግን ገሚሱ ለውጥ ሲፈልግ ገሚሱ ደግሞ በትናንቱ መንገድ መሄድ ስለሚፈልግ ለውጡ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ የተሳካ እንዳይሆን የሆነበት ዘመን በርካታ ነው፡፡   ልብ ይበሉ በቅርብ መጣ የተባለውን ለውጥ ብቻ አላልኩም የሕይወትና የታሪክ  ለውጥን እንጂ፤
ታላቁ የጥበብ ሰው  ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ባንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡‹‹ የዓለምን ታሪክ ብንመለከት አዲስ ታሪክ አዲስ ሥርዓት የሚያመጣ ንጉሥ ሁሉ በሕይወት ሳለ መከራ አይለዬውም፡፡ ሕዝቡ እንደአውራ  ደመኛው ያዬዋል፡፡ ደግነቱም የሚታወቅ ሲሞትና ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው፡፡ የዓዳምን ዘር ባሕሪይ በጠቅላላው ብንመለከት አዲስን ነገር የሚወድ ወገን አናገኝም፡፡ ካባቶች የቆዬውን ካልሆነ በስተቀር፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያባቶቹን ልማድ ሲለውጡበት ዝም ብሎ ባልተቀበለም፤ጢስ እንደገባባት ንብ በተሸበረ በተናወጠም ነበር እንጂ፤ ወዬለት ለዚያ ንጉሥ የዛሬውን ከደማችን ጋር የተዋሃደውን የድንቁርና ስርዓታችን ሊለውጥ ለሚነሳው፡፡ በኋላ ስም ያገኛል እንጂ በሥጋው አይጠቀመም፡፡››  ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ለሀሳባቸው ማጠናከሪያነትም የባለ ራዓዩን መሪ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ያነሳሉ፡፡
‹‹ያ ቋረኛ ንጉሥ ተበጣጥሰው የነበሩትን የአበሻን መንግሥት ክፍሎች  አዋደደ፡፡ ሕዝቡንም ከሹሞች ቀምበር አርነት ሲያወጣ አገር በጄ ብሎ ትምህርትንም ሊከፍት አሰበ፡፡ መላው ሕዝብ በሹሞች ተነሳበት አሳበደውም፡፡ በመጨረሻም ለበዓድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ በገዛ እጁም ሞተ፡፡ አዕምሮ የሌለው ሕዝብና ልጅ ጠቃሚውን አይወድም፤ የቴዎድሮስ ሃሳብ ግን አልተፈጸመም እንጂ አልሞተም፡፡ አባ ታጠቅ ለራሱ ቢከፋው የማይረሳውን ስም ተክሎ ሞተ፡፡ …..ሹሞች እስካሁን ድረስ በገንዘባቸው እንደ ገዙት ርዕስት ያዩታል፡፡ ከእርሱ በሚወጣው ግብር የታያቸውን ያደርጋሉ( ከገበሬው ማለታቸው ነው) በተቻላቸውም ያለ ሹምና አሽከር ከአነርሱ በቀር ሌላ ጌታ አያውቅም፤ አጣም አገኜም ከቸርነታቸው ነውና፡፡ የሆነ ሆኖ የዛሬ ሹማምንት እንደ ድሮዎች አይደሉም፤ መንግሥት በላያቸው እንዳለ ጥቂት ይታወቃቸው ጀምረዋልና፡፡ እያደረም አጥብቆ ሳይታወቃቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ የቴዎድሮስ መንፈስ አልሞተም እያደረ ሕይወት ይጨምራል እንጂ፡፡…››
ዘመንህን እና የምትመራውን ሕዝብ የሚቀድም ሀሳብ ስታመጣ እንደክፉ ትቆጠራለህ፡፡ ይህ ሲሆን አንደኛ ሀሳብህን የሚሰማሕ ስታጣና በወገኖችህ ፊት ሲዞርብህ ትከፋለህ፤ ተስፋም ትቆርጣለህ፡፡ በሌላ በኩል ያቀድከውን መልካም ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥቂት ጊዜ አስበህ ብዙ ጊዜ ይወስድብሃል፡፡ በዚህ መካከል ራዕይ እንደያዝክ የተስፋ እንጀራ እየበላህ፣ የተስፋ ጠጅ እየጠጣህ ሳይሳካ ታሸልባለህ፡፡ ለውጥ ትጋት ይፈልጋል፡፡ ለውጥ መስዋትነት ይጠይቃል፡፡ ችግራችን ለውጥን አለመውደድ ሳይሆን ለለውጥ የሚደረገውን መስዋዕትነትና ድካም ለመክፈል ሰነፍ በመሆናችን ነው፡፡ ወተት ለመጠጣት ማለቢያ ማዘጋጀት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከማለቢያው አስቀድሞ ላም መግዛት፣ ላሟን ከኮርማ ጋር ማገናኜት፣ እስክትወልድ መታገስ፤ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ላሟን ማብላት፣ መንከባከብ ከሌባና ከበሽታ በጥንቃቄ  መጠበቅ  ያስፈልጋል፡፡ ጭድ ካልሰጠኻት ወተትም አትሰጥኽምና አትጠብቅ፡፡ ሳትሰጥ መቀበል ሁልጊዜ አይገኝም፡፡  ትንሽ ሰጥተኽ ብዙ ለማትረፍ ጥረት አድርግ፡፡ ግን ራስህን ለመጠቀም ስትል ሌሎችን እንዳትጎዳ ጥንቃቄ አይለይህ፡፡
ለቴዎድሮስ ራዕይ አለመሳካት በዘመኑ የነበሩትን ሹሞችና ዘመናዊነት ያልገባውን ማሕበረሰብ ተወቃሽ እናደርጋለን፡፡ እኛስ ዛሬ ለመጪው ትውልድ ተወቃሽ ላለመሆናችን ምን ያክል እርግጠኞች ነን? ኢትዮጵያዊነትን ምን ያክል ከራስ ጥቅም በላይ አብልጠን እንመለከተዋለን? የግል ጥቅም በማሕረሰብ ውስጥና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ያለ መሆኑን ሁልጊዜም ልንረሳው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ትውልድ  የራሱን ታሪክ መስራትና የቀደመውን ታሪክ ማስቀጠል ግዴታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህን ግዴታ ከተወጣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ክብር ከተሰቀለበት የክብር ማማ ላይ ከፍ እንዳለ ለዘላለም ይኖራል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ሠዓት ለለውጥ ለሚተጉና ለለውጥ ቦታ በሌላቸው ሁለት ሃሳቦች መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ አዲሱ ለውጥ ይፈልጋል የቆዬው ደግሞ የመጣሁበት መንገድ ልክ ነው ይላል፡፡ ለውጥ ፈላጊው ለውጥ ለምን እንደሚያስፈልግ ምክንያቶቹን ሲያቀርብ ለውጥ የማይፈልገውም የራሱን ምክንያቶች ያቀርባል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ለውጡ ባሰበው ልክ እየፈጠነ እንዳልሆነ ቅሬታ ሲያሰማ ቢስታዋልም የለውጡን ሃሳብ ግን በብዛት ይደግፋል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ለውጡ ምንም ሊሆን ይችላል፤ የቆዬውን መንገድ ግን ማዬትና በዚያ መንገድ መጓዝ አይፈልግም፡፡  ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነቱ፣ በአንድነቱ፣ በማንነቱና በሌሎችም ጉዳዮች ተፈትኖበታል እና፡፡ የአገር አደራ ተሰጥቶት ለዚያውም ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ በስልጣን ላይ የቆዬ መሪ ኢትዮጵያ መርከብ ናት፡፡ እኔ ደግሞ ውቅያኖስ  ነኝ ውቅያኖሱ ሲናወጽ ኢትዮጵያም ትጠፋለች እያለ መዛት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ብዙ ዓመታት በብቸኝነት አራምደውት ያልተሰማው ሃሳብ ዛሬ አማራጭ ሃሳብ ሲቀርብ እንዴት እንሰማለን ብለው አሰቡ? ኢትዮጵያ ውቅያኖስ እንጂ መርከብ አለመሆኗንስ ማን በነገራቸው፡፡
አሁን ሁለት  ሀሳቦች ለኢትዮጵያዊያን ቀርበዋል፡፡ አንደኛዋን የመምረጥ ደግሞ የዜግነትና የሰውነት መብታቸው ነው፡፡ ሌላ መልካም ሀሳብ ማምጣትም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን  የትናንቱ መንገድ ረጅም ዓመት ተጉዘውበት የጋራ መዳረሻ አጥተው በተለያዬ መንገድ ሄደው ሊጠፋፉ ሲል መንገድ መቀዬር እንዳለባቸው ተስማምተው የጋራ መስመር ለማስመር እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ የትናንቱ ማለቴ ከዘመነ ደርግ ወዲህ ያለውን ስርዓት  ነው፡፡ የትናንቱ መንገድ በጋራ አለማስሄዱ ብቻ ሳይሆን ከትናንት ወዲያ የነበረው መንገድ ልክ እንዳልነበረ እና ከትናንት ወዲያ ሲመራ የነበረው ሁሉ ተከታዮቹን ያሰቃይ ነበር እያለ ዛሬ በጋራ  እንዳይሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያዊያን ዕድል አምልጧቸዋል፡፡ ያ ዕድል ዛሬ መመለስ ባይችልም ታሪክ ሆኖ ግን ያስተምራል፡፡ ለውጥን አለመቀበል ችግር ላይኖረው ይችላል  ለውጥ የሚፈልጉትን ማሰናክል ግን ኢ ሞራላዊ ነው፡፡ እኔን ስማኝ ካልሰማህ ግን ጀሮህን እቆርጠዋለሁ፤ ማንንም መስማት አትችልም ማለት ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ሁልጊዜ ፋሲካ የለም፡፡‹‹ አስለምደዋለሁ እግሬን ያለ ጫማ እንደ አጌጡ መኖር አይገኝምና›› እንዲሉ በመልካም ጊዜ ለችግር ቀን ማሳብ ተገቢ ነው፡፡ በክፉ ጊዜ ደግሞ መልካም ማሰብ፤ ዕድልን ዳግም ለማምጣት የሌሎችን ነብስ መብላትም ነውር ነው፡፡ ሁልጊዜም በጫማ መጓዝ ላኖር ይችላል፡፡ በባዶ እግር መሄድ ይመጣል፤ ዕድላችን ካልተጠቀምን እግር ማጣትም ይከተላል፡፡
ከወንድምህ ጋር ከተጋጨህ ከቻልክ ራስህ ካልሆነ በአገር ሽማግሌ ቀርበህ ችግርህን ፍታና ታረቀው፡፡ አሳልፈህ ግን ለበዓድ አትስጠው፡፡ ወንድምህ ያለሆነህን በዓድ ለአንተ አይሆንህም፡፡ በዓዱ ወንድምህን የሚያጠፋው የአንተ ትክሻ እንዲቀልና አንተን እንደፈለገ እንዲገዛህ እንጂ ጠላትህን ገድሎ እንደፈለክ እንዲያደርግህ አይመሰልህ፡፡ የእርሱ ዓላማ ብቻህን አስቀርቶ ሀብትህንና ንበረትህን እንደፈለገ መውሰድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊያን የሚሻላቸው ወዳጅ ምድር ላይ የለም፡፡ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን አሳልፈህ ለበዓድ ብትሰጥ ጊዜው ይረዝም ካልሆነ በስተቀር አንተም ለበዓድ መሰጠትህ አይቀርም፡፡ ወንድምህን፣ አገርህንና ማንነትህን የሸጥክለት በዓድ ለወንድምህና ለአገርህ ያልሆንክ ለእርሱ እንደማትሆነው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አንተንም በእጁ ያደርግሃል፡፡ ለውጥን ከአገርህ ህዝቦች ጋር አጣጥም፡፡ አንተ የተሻለ የለውጥ ሃሳብ ካለህ በመልካም መንገድ አምጣው፡፡ ግዴታ ካልሰማችሁኝ ግን አትበል፡፡
ዘመንፈሱስ ቅዱስ አብርሃ  ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ ወወልደ ሕይወት በሚለው መጽህፋቸው ላይ ስለአገር፡- ‹‹ ከነብስህ አብልጠህ ሀገርህን ውደድ፤ ሀገር ሰው ታደርጋለች፣የልብ ኩራት ትሆናለች፣ታበላለች፣ታጠጣለች፣ታለብሳለች፣ታኮራለች፣ታስጌጣለች፣ታስደስታለች፣ትጦራለች፤ ትሸከማለች፣ሀገር የሕይወት ምሽግና ተገን ናት፤ ሀገር ምዕልዓተ ልብና ተስፋ ናት፤ የእድሜ ብርሃን ጽኑ ጋሻ ናት፤ እረፍትና ሰላም ትሰጣለች፤ ሀገር ታሞቃለች ጌታ ታደርጋለች፤ ከክፉ ሁሉ ትጠብቃለች፤ የሚመስላትና የሚስተካከላት ነገር የለም፤ ሀገር ከሕይወት ትበልጣለችና በሕይወት ትለወጣለች፤ ……ፍቅር የሀጥያትን ብዛት ትሠውራለችና ከሁሉ በፊት እንደ እሳት የምታንበለብል ፍቅር ትኑራችሁ፡፡ ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተ ለሰዎች አድርጉላቸው ሰዎች በእናንተ ላይ ሊያደርጉላችሁ የማትፈልጉትን እናንተ ለሰዎች አታድርጉባቸው፡፡ ወንድሞቼ የሃገሬ ወጣቶች  ሆይ ይህ የተጣለባችሁን ከባድ የሀገር ፍቅር አደራ! አደራችሁን ከሕይወታችሁ የበለጠ አጠንክራችሁ ለማያዝ ያብቃችሁ፡፡››
ወዳጄ አገርህን ለድርድር ካቀረብክና ከባንዳዎች ገር ከተመሳጠርክ አገርህን አጥተህ ስታለቅስ ትኖራለህ፡፡     ለውጥ አትፍራ፣ ምንም ይሁን ክፉን በመልካም ነገር ለመለወጥ ሁልጊዜም ጣር፡፡  ካጠፋህ ይቅርታ ጠይቅ፤ ይቅርታ የሐጥያትን ስር ትነቅላለችና፡፡ እያወክ ግን አታጥፋ፤ የአገር መውደዱን ይስጠን፡፡
Filed in: Amharic