>
5:13 pm - Monday April 19, 3943

አማርኛ እና አማራኛ (የፖለቲካ ቋንቋ እና የቋንቋ ፖለቲካ ልዩነት (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

አማርኛ እና አማራኛ

(የፖለቲካ ቋንቋ እና የቋንቋ ፖለቲካ ልዩነት)

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ

አንድ የፌስቡክ ቀልደኛ “አማርኛ” እና “አማራኛ” ይለያያሉ ብሎ በምሳሌ ሲያስረዳ አስታውሳለሁ። ጉዳዩ ግን ከቀልድም በላይ ነው። አሜሪካ እና እንግሊዝ ከአነጋገር ዘዬ በስተቀር መሠረታዊ የቋንቋ ልዩነት የላቸውም፤ ወይም ያላቸው ልዩነት ጎጃምና ላስታ ካላቸው እምብዛም የጎላ አይደለም። ነገር ግን ሁለቱም እንግሊዛዊ አልተባሉም። እንግሊዛዊነት እና እንግሊዝኛ ተናጋሪነት ለየቅል ናቸው። የእንግሊዝ ጥንተ ኀያልነት እንዲሁም ቅኝ ገዢነት ቋንቋውን በዓለም አሰራጭቶታል። በዚህም እንግሊዝኛ ተናጋሪነት በዓለም ላይ ከፖለቲካዊ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅሞች አሉት። ነገር ግን ቋንቋውን የእንግሊዝ ወይም የእንግሊዛዊነት መለያ አድርጎ ማየት ለስህተት ይዳርጋል። እውነቱን ለመናገር የቀድሞ ቅኝ ተገዢዎች የቅኝ ግዛትን ክፉ መንፈስ በአፈ እንግሊዝ ነው ተሟግተው ፈጣሪዎቹን የገሰፁት። ቋንቋ ብሔር የለውም፤ ብሔር ግን ቋንቋ ሊኖረው ይችላል።
አማርኛ ተናጋሪዎችን በሙሉ እንደ አማራ የመመልከት አባዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ መግባባት ላይ እንዳይደረስ ተፅዕኖ አድርጓል። ጊዲዮን ኮኸን “The Development of Regional and Local Languages in Ethiopia’s Federal System” በሚል በሠሩት ጥናት ላይ ቋንቋ “የማይተማመኑበት የማንነት መለያ” (unreliable identity maker) ቢሆንም ቅሉ፣ በኢትዮጵያ ግን ለዘውግ (‘ethnicity’) “ዋነኛ” የማንነት መለያ ተደርጎ ይቆጠራል ብለዋል። ኮኸን ‘የአካባቢ ቋንቋዎች መበልፀግ በብሔሮች/ዘውጎች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ይቀርፋል የሚል ግምት አለ፤ ይህም ግምት የሰዎቹ የዘውግ ማንነት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይመነጫል የሚል ሌላ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው’ ይላሉ። ይህ ድምዳሜ ነው በኢትዮጵያ ላለው ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት መንስዔ የሆነው አማርኛ ቋንቋ ነው በሚል ቋንቋውን ከፖለቲካው ነጥሎ ማሰብ እንዳይቻል ያደረገው።
ፖለቲካው የአማርኛ ቋንቋ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ መሆኑ የአፍ መፍቻቸው አማርኛ የሆኑ ሰዎችን የበለጠ ዕድል የሚሰጥ ስለሆነ ሌሎቹንም መጥቀም የሚቻልበትን መንገድ መንደፍ አለበት። አማርኛ ተናጋሪውን እንደ ጠላት መቁጠር፣ ቋንቋውንም የአንድ ባሕል የበላይነት መጫኛ ማድረግ ግን የታሪክን ስህተት መድገም ነው። የብሔር ፖለቲከኞች ከአማራ ሕዝብ፣ ከአዲስ አበባ ሕዝብ እንዲሁም ሌሎች ከተሜዎች ጋር እልህ የተጋቡበት ምክንያትም ቋንቋን ብሔር እንዳለው በማሰባቸው ነው። በዚህ ቀጭን ልዩነት መካከል ያለውን ተጠቃሚነት እና/ወይም ተጎጂነት ችግር ለመፍታት የቋንቋ ፖሊሲ ጉዳይ በቅጡ አጀንዳ መሆን አለበት። ምክንያቱም የጠራ የቋንቋ ፖሊሲ ቋንቋን ኢ-ፖለቲካዊ እና ኢ-ዘውጋዊ (depoliticize and de-ethnicize) ያደርገዋል።
ልሣነ ፖለቲካ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚዘወረው በአማርኛ ቋንቋ ነው። መረራ ጉዲና (ዶ/ር) የሽግግር ጊዜውን ሲያስታውሱ ኦነጎች በአስተርጓሚ ሲያወሩ መለስ ዜናዊ ግን ፖለቲካውን በአማርኛ ያሾሩት ነበር ብለው ጽፈዋል። እርግጥ ነው የኦነግ መሪዎች ትርጁማናቸውን እንኳን ወደ እንግሊዝኛ እንጂ ወደ አማርኛ እንዲመልስ አልቀጠሩትም። ይህንን ያደረጉበት ምክንያት አማርኛን እንደ አማራኛ ስለፈረጁት ነበር። የዛሬዎቹ የኦሮሞ ፖለቲካ መሪዎች ግን በዚህ አይሸወዱም፤ ይልቁንም ብዝኀ ቋንቋ ተናጋሪነታቸውን እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ ይጠቀሙበታል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሪዎችም ይሁን እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት ተቃዋሚዎች ከአንድ በላይ የአገር ውስጥ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። የወደፊቱ የቋንቋ ፖሊሲም ኢትዮጵያውያንን ብዝኀ ቋንቋ ተናጋሪ ለማድረግ ቢቀረፅ የምናተርፈው ይበዛል።
ጌታቸው አንተነህ እና ደርቤ አዶ “Language Policy in Ethiopia: History and Current Trends” በሚል ርዕስ በሠሩት ጥናት ላይ እንደገለጹት የእስካሁኑ የመንግሥት ቋንቋ ፖሊሲ የሚገለጸው በተለይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ መወሰኑ ላይ ነው። መንግሥት ይህንን የመረጠበት ምክንያት የአፍ መፍቻ ቋንቋ የማንነት መሠረት ስለሆነ፣ በትምህርት አሰጣጥ (‘pedagogy’) ረገድ ጥቅም ስላለው እና ተማሪዎቹን ለራሳቸው ያላቸውን ግምት የማሳደግ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ ስላለው በሚል ነበር።
ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማራቸው በጣም ጥሩ ነገር ነው። የጎደለው ነገር ተማሪዎች በአገሪቱ እና በአካባቢያቸው መገበያያ ለመሆን የበቁ ቋንቋዎችን በተጨማሪነት እንዲያዳውቁ ትኩረት አለመሰጠቱ ነው። በቋንቋ ፖሊሲዎቻችን ውስጥ ያለው ክፍተት አካባቢያዊነትን ከአገር ዐቀፋዊነት፣ አገር ዐቀፋዊነትን ደግሞ ከዓለም ዐቀፋዊነት ጋር ማዋደድ አለመቻሉ ነው።
የበድሉ ዋቅጅራ መንገድ
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) “ጠርዝ ላይ” የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። አንዱ ምዕራፍ የኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ ያተኩራል። መነሻቸው የ1999ኙ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ሲሆን፣ በዚያ መሠረት በርካታ ተናጋሪ ያላቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና ሲዳምኛ መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህ አምስቱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ መሆን አለባቸው ብለው ተሟግተዋል። በተጨማሪም፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አፋቸውን የሚፈቱባቸው ቋንቋዎች በየጊዜው ተመሣሣይ ማዕረግ ማግኘት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የኦሮሞ ፖለቲካን ከሚንጡት ጥያቄዎች መካከል የቋንቋ ጉዳይ ግንባር ቀደም ነው፤ ኦሮምኛን ተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ማድረግ ብዙ ጊዜ የተነሳ ጥያቄ ቢሆንም መንግሥት መልስ ከመስጠት የሚያሰጋው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ጉዳዩ ሰላምና መረጋጋት የማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሰላም እጦቱ ሰለባ ለሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነገር ነው። ነገር ግን ኦሮምኛን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ከማድረግ ጎን ለጎን ሊታሰብበት የሚገባው ክልሎችም ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑ ነው። አለበለዚያ ጎዶሎ መፍትሔ ይሆናል። ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አማርኛ ተናጋሪዎች፣ ሶማሊ ውስጥ ያሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች፣ ወዘተ. በመረጡት ቋንቋ የመማር፣ የመሥራት እና የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት ዕድል ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ ቋንቋን ኢ-ፖለቲካዊ እና ኢ-ዘውጋዊ የሆነ መግባቢያ እና መገልገያ ያደርገዋል።
Filed in: Amharic