>

ደርግ ደግ አረገ...!!! (የትነበርክ ታደለ)

ደርግ ደግ አረገ…!!!

የትነበርክ ታደለ

 

 ደርግ – ደርግ – ደርግ – ደርግ !!!
እሰይ ደግ አረገ! እሰይ! — ፪፯ አመት ሙሉ አማኸው፣ አማኸው አንዲትም ከደርግ የተሻለ ስራ አልሰራህም! ደርግን ደመሰስኩ አልክ ዘፈን ጨፈርክ ግን በደስታህ መጠን ትውልድ ደመሰስክ እንጂ ምን ፈየድክ? እንኳን ጎሽ ደርግ እሰይ ደርግ! ሀሜት ሀሜት፣ ድቡሽት ጀግንነት፣ የወሬ አዋቂነት፣ የሴራ ማንነት፣ ተራ ዴሞክራሲያዊነት እንጂ ምን አመጣህ ሀገር ገደልክ እንጂ? እሰየው በደርግ ተወለድኩ፣ እንኳንም አወኩት፣ እንኳንም ቀመስኩት፣ እሰይ ደግ አደረገ – ደርግማ ጀግና ነው!
ወሬ ማን አቃተው? ሀሜት መተንተን ማን ከበደው? ስም መስጠት ማን ተሳነው? በወሬ በሀሜት በታርጋ ልጠፋ ሀገር ያጠፋህ አንተም አለህ – ደርግ ደግ አደረገ! ስለአንዲት ሀገር የፎከረ የማለ! ደርግማ ደርግ ነው ኢትዮጵያ ወይም ሞት ያለ!
የሰዎች ስርዓተ-መንግስት ደርግ ታሪክህ በደማቅ ቀለም ይጻፍ! አምላክ ሰው አድርጎ ፈጥሮኝ ሰውነቴን ሳልቀይር እንድኖር ያደረከኝ ደርግ ሆይ ውለታህን ቸሩ ፈጣሪ ይክፈልህ! (ይህ ጽሁፍ ደርግ መግደሉን ለማወደስ አይደለም!) ደርግ የሰዎች ስብስብ ነበርክ! ሀገር መስራት ትችላለህ፣ ዜጋ መቀረጽ፣ የሀገር አንድነት የህዝብ እኩልነት ማስፈን ታውቅበታለህ፣ የሌባን እጅ መቁረጥ፣ ከሀዲን አንገት ማስደፋት ታውቅበታለህ – ደርግ ሆይ ትችላለህ!
አጥፊዎች፣ ቦዘኔዎች፣ ገንጣዮች፣ የሀገር ራዕይ የሌላቸው፣ በህዝብ ቀሚስ ውስጥ ተሸሽገው የግል ሀብት የሚያካብቱ፣ በሀሰት ዴሞክራሲ የህዝብ ጀርባ የሚገጥቡ ወረኞችና ሴረኞች የደርግን የእግር እጣቢ አያህሉም።…… የማይግባባ ህዝብ ለመፍጠር፣ የማያስብ ትውልድ ለመቅረጽ፣ በጋራ መቆም የማይችል ህዝብ ለመንዳት ምን እውቀት ይጠይቃል? ሴረኝነት እንጂ፣ ሌብነት እንጂ፣ ተራ ሆድ አደርነት እንጂ! እንዲህ ያለ የመንጋ ስርዓት፣ እንዲህ ያለ ጋጠወጥ ባህል ለማዳበር ምን ተስጦ ይጠይቃል? ለምን እንዴት የማይል አመክኒዮ አልባ ሀሳብ የማይመራው፣ እውቀት የማይገባው፣ ማስመረቅ ምን ጥበብ ይጠይቃል?  …..
ደግ አደረኩ – በደርግ ዘመን ተወለድኩ! እሰይ ደግ አደረኩ ደርግን አወኩት! እሰይ አበጀሁ ከሰውነት እና ከዜግነቴ በታች የምርመጠመጥበት የጎጥ ቡድን አጣሁ! እንኳን ደግ አደረኩ ከሀገር በላይ የምሟገትለት የብሄር ቡድን ናቅሁ! እሰይ ደግ አደረኩ – እሰይ በደርግ ተወለድኩ! የወንበዴ መድሀኒት ደርግማ ወንድ ነበረ! – ደርግ ደግ አረገ!!!
Filed in: Amharic