>
5:18 pm - Saturday June 15, 4346

ኢትዮጵያ ውስጥ  እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ባግባቡ መመረጅ አለበት!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ኢትዮጵያ ውስጥ  እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ባግባቡ መመረጅ አለበት!  

አቻምየለህ ታምሩ

* የዘር ማጥፋቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ቄሮዎች መታወቂያ እየጠየቁና አስቀድመው ባዘጋጁት የስም ዝርዝር መሰረት ያካሄዱትን  የዘር ማጥፋት መካድ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ አካል መሆኑን ስለማያውቁ አይደለም!
 
በሰው ዘር ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ሁሉ ይርጋ የሌለው  የዘር ማጥፋት ከሌላው  አይነት ወንጀል ሁሉ ይለያል።  የዘር ማጥፋት  ከሌሎች የወንጀል አይነቶች  ከሚለይባቸው  ባሕርያቱ አንዱ ግልጽ የሆኑ መስፈርቶች ያሉት የወንጀል አይነት መሆኑ ነው። ለምሳሌ ሰው መግደል በድንገት ሊሆን የሚችል ነገር ሲሆን ዘር መጥፋት ግን ዝግጅት፣ ቅንጅትና ድርጅት የሚጠይቅ ነው። ይህ ዝግጅት፣ ቅንጅትና ድርጅት ከትርክት መፍጠር ጀምሮ እስክመፈጸም፤ ለተፈጸመው ወንጀል ከለላ እስከመስጠት ይደርሳል።
የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝና ግብረ በላዎቹ በሻሽመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በዝዋይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተድበስብሶ እንዲታለፍና ዓለም እንዳያውቀው ታትረው በመስራት ላይ የሚገኙት የዝጅግቱ፣ የቅንጅቱና የድርጅቱ አካል መሆናቸውን ስለሚያውቁ እንጂ  የዘር ማጥፋቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ቄሮዎች መታወቂያ እየጠየቁና አስቀድመው ባዘጋጁት የስም ዝርዝር መሰረት ያካሄዱትን  የዘር ማጥፋት መካድ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ አካል መሆኑን ስለማያውቁ አይደለም።
ሆኖም ግን  የዘር ማጥፋት አካሄዶ ማምለጥ አይቻልም።  የዘር ማጥፋት ወንጀልን እንኳን በሕይወት  እያሉ በሞትም ማምለጥ አይቻልም። ለዚህም ነው የዛሬ ሰባ፣  መቶና ሁለት መቶ ዓመት የተደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዝግጅት፣ ቅንጅትና ድርጅት ውስጥ የነበሩ ወንጀለኞችን  ማደኑ እስካሁን ያላበቃው። ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን  የዘር ማጥፋትን የሚቃወም ሁሉ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያሳዩ ማስረጃዎችን [ምስሎችና ቪዲዮዎች]፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎችና ተባባሪዎች ሙሉ ማንነት የሚያሳዩ ሰነዶችን ማሰባሰብና ማደራጀት ከተቻለ ነው።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ባለው የዘር ማጥፋት ውስጡ የሚደማ፣ ለግፉአን ፍትሕ ይገባቸዋል ብሎ የሚያስብና የሚጣላ ኅሊና ያለው ሁሉ እየተካሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት ዝግጅት፣ ቅንጅትና ድርጅት የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለፍትሕና  ለታሪክ እንዲቀመጡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ማስረጃዎችን  አመሳክሮ ማደራጀት  ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ከባድ ነገር አይደለም። የተማከለ ድርጅትም አያስፈልግም። በተለይ አገር ቤት ያለ ሰው በእጁ ላይ ባለው ስልክ ተጠቅሞ  ቀደም ሲል የዘረዘርኳቸውን ወሳኝ ማስረዎች መሰብሰብ ይችላል።
ማስረጃዎቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ቀጣዩ ተግባር የተሰበሰበውን ማስረጃ አደራጅቶ ፤ ትርጉም ሰጥቶ፤ ሁኔታ አበጅቶና መልክ አስቀምጦ ለፍትሕና ለታሪክ ማብቃት ይችላል ተብሎ ለሚታመን ሰው መላክ ነው።  በየመንደሩ፣ በየፖለቲካ ፓርቲው፣ በየሃይማኖት ተቋሙ፣ በየማኅበሩ፣ ወዘተ ያለው ሁሉ ይህንን በማድረግ ቢተባበር በአገዛዙ ለመሸፈን እየተሞከረ ያለውን የዘር ማጥፋት ዛሬ ለፍትሕ፤ ነገ  ደግሞ ለታሪክ ማብቃት፤ የዘር ማጥፋት ዘመቻውንና ገዳዮቹን ለመደበቅ፤ ተጠቂዎችን ደግሞ በመወንጀል ላይ የሚገኘው  የአፓርታይድ አገዛዝ  ፍጡር የማታለያ ልብሱን አውልቆ በዓለም ፊት እንደ አዳም ራቁቱን እንዲታይ ማድረግ ይቻላል።
Filed in: Amharic