>
5:13 pm - Monday April 19, 9790

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአርሲ እና ባሌ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶች (በላይ ማናዬ)

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአርሲ እና ባሌ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶች

 

በላይ ማናዬ (ለካርድ)

ሐምሌ 29/2012

መግቢያ

ድምፃዊ እና አክቲቪስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22 ቀን 2012 ምሽት 3፡00 ገደማ በአዲስ አበባ የግድያ ወንጀል ተፈፅሞበታል። በሀጫሉ ላይ የተፈፀመው የግድያ ዜና መሰማቱን ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ የፀጥታ ችግሮች ተፈጥረዋል፤ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። በጥቃቱም የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ንብረትም ወድሟል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የካሕናትና የምዕመናን ኅብረት የፀጥታ ችግሮች በነበሩባቸው አካባቢዎች የሚዲያ እና ሲቪክ ተቋማት ተወካዮችን ያካተተ ጉዞ ከሐምሌ 23-25/2012 ለሦስት ቀናት አድርጓል። እኔም የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚያደርገው መረጃ ማሰባሰብ ሥራ ለማበርከት በተወሰኑ ሥፍራዎች በጉዞው ተሳትፌ ያገኘሁትን መረጃ እንደሚከተለው አቀናብሬዋለሁ።

ይህ ዘገባ በተለይ በአርሲ እና ባሌ አካባቢዎች የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች በተለይም፣ በአርሲ ዴራ፣ አሰላ፣ ገደብ አሳሳ፣ ሮቤ፣ ጎባ እና አጋርፋ የደረሰውን ጉዳት መመልከት ችያለሁ። በነበረው ችግርም ሃይማኖትን እና ብሔርን የለዬ ግድያ፣ ዘረፋ እና ቃጠሎ መፈፀሙን ተረድቻለሁ። ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት ፖሊስ “ትዕዛዝ አልተሰጠኝም” በሚል ለሰዓታት ሁኔታውን በዝምታ መመልከቱንም ከዓይን እማኞች ሰምቻለሁ። በአንዳንድ ሥፍራዎች አሁንም የፀጥታ ስጋቱ አለ። በዚህ የተነሳም በተለይ፣ በአርሲ ዴራ፣ በገደብ አሳሳ እና አጋርፋ በርካቶች በቤተክርስቲያናት እና በትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ። መንግሥት ስጋታቸውን ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

  1. አርሲ፣ ዴራ

በዴራ ከተማ አስተዳደር ግድያ፣ ዘረፋ እና ቃጠሎ ተፈፅሟል። በጥቃቱ ማግስት በከተማዋ በሚገኘው መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን እስከ 400 በላይ ሰዎች ተጠልለው የነበር ሲሆን፣ አሁን ላይ (ከአንድ ወር በኋላ መሆኑ ነው) ቁጥራቸው ቀንሷል። አንዳንዶች ከአካባቢው ለቅቀው ወጥተዋል። ሆኖም፣ አሁንም በቤተክርስቲያኑ ተጠልለው የሚገኙት ሰዎች ከ150 በላይ እንደሚሆኑ የደብሩ አስተዳዳሪ ገልጸዋል።

በዴራ ሰኔ 22 ቀን 2012 ለ23 ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ በተፈፀመው ጥቃት 4 ሰዎች ተገድለዋል። ሆቴሎችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ዝርፊያም ተፈጽሟል። ችግሩ በጥይት ተኩስ እና በጩኸት የተጀመረ ነበር።

“ሀጫሉ ሞቷል እንደተባለ በከተማው ጩኸት ነበር። በሰዓቱ ጩኸቱን ሰምቶ ከቤቱ የወጣ ሰው ብዙ ነበር። ትንሽ ቆይተው እኛም እንገድላለን እያሉ የሚዝቱ ወጣቶች ተሰባሰቡ። ቀጥሎ ከተማዋ በተኩስ ተናጠች። ፖሊስና መከላከያ የደረሰልን መስሎን ነበር። ለካ ወጣቶች ከገጠርም በመኪና እየገቡ ኖሯል። በዚህ መልኩ የበለጠ እየተሰባሰቡ መጡ። የክርስቲያን ቤትና ሆቴልም እየተመረጠ መቃጠል ተጀመረ። ‘ነፍጠኛ አንድም እንዳይቀር’ እያሉ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ጀመሩ። ስቃይ ነበር። መከላከያ ብዙ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነበር የመጣው። እኔ እዚሁ ተወልጄ ያደግሁ ነኝ። ምን እንዳደረግን አልገባኝ”አበበች ፈለቀ፣ ከጥቃቱ ሸሽታ በመጠለያ የምትገኝ የዴራ ነዋሪ።

“ልጄን አርደው ነው የገደሉት። አስክሬን እንኳ ማንሳት አልቻልንም ነበር። በዕለቱ የሆነውን መናገር ይከብዳል። አሁንም ይዝቱብናል። ‘ከመጠለያ ውጡ’ ይሉናል። መንግሥት አጥፊዎችን ይቅጣልን። ገዳዮች ተቀጡ ሲባል ነው መስማት የምፈልገው” ደረጄ ፈለቀ፣ የተጎጂ ወላጅ አባት።

“ሰኔ 22 ለ23 አጥቢያ ስምንት ሰዓት ገደማ ነበር ጩኸት የሰማሁት። ‘ከቤትሽ ቶሎ ውጭ፤ ቤት እያቃጠሉ ነው’ ብለው ደወሉልኝ። መሣሪያ ይተኩሱ ነበር። ቆንጨራ፣ ገጀራም ይዘው እየጮሁ ይሯሯጣሉ። ኦሮምኛ ቋንቋ አውቃለሁ፤ ‘ምን ሆናችሁ ነው?’ አልኋቸው። ‘ሀጫሉ ሞቷል’ አሉኝ። ወደቤቴ ተመልሼ ከባለቤቴ ጋር ቤታችንን ዘግተን ተቀመጥን። ወዲያው ቤት መጥተው መደብደብ ጀመሩ። እንደምንም መስኮት ሰብረን ልጆቼን ይዤ ወጣሁ። ቤቴ እና ወፍጮ ቤቴ ተቃጠሉ። ልጆቼን ግን በእግዜር ቸርነት ከቃጠሎ አድኛለሁ” – እንዬ ቸሩ።

“እኔ ከዚህ በኋላ እዚህ ከተማ በሰላም የሚያኖሩን አይመስለኝም። አሁንም ስጋት አለብን። አስተዳደሮቹ ሁሉም ሙስሊሞች ናቸው። ሙስሊም ባለሀብቶች የጥቃቱ ደጋፊ የሆኑ አሉ። ወጣቶችን ከገጠር ጭኖ ያመጣቸው ማን ነው? ደግሶ የሚያበላቸውስ ማን ነበር? አሁንም ድረስ ያልተያዙ አጥፊዎች አሉ። መንግሥት ስጋታችን አልገባውም? አራት ሰዎች ናቸውኮ የታረዱብን። አርደው ቱቦ ውስጥ ነው የጣሏቸው። በአስክሬን ነው የተጫወቱት። የተቆራረጠ የሰው ልጅ አካል ይዘው ነው ሲጨፍሩ የነበሩት። መከላከያ ከመጣ በኋላ ነው አስክሬን ተነስቶ የተቀበረው። ደካማ እናቴን ይዤ ለመውጣት ያየሁትን መከራ አሁን ማስታወስ አልፈልግም” – ወገኔ ግርማ፣ የዴራ ከተማ ነዋሪ።

በዴራ ከተማ 76 ቤቶች ተቃጥለዋል። ከ50 በላይ የንግድ ቤቶችም ተቃጥለዋል። ከወደሙ ሆቴሎች መካከል የዶ/ር ናደው ተ/ጻድቅ ንብረት የሆነው “ምዕራፍ ሆቴል” ይገኝበታል። ዶ/ር ናደው ሆቴላቸው የተቃጠለው 12፡30 ጠዋት መሆኑን ገልጸዋል። ሆቴላቸው በአንድ ጊዜ አራት የሰርግ ድግሶችን ማስተናገድ የሚችል፣ በ2000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነበር።

በዴራ ከተማ የተገደሉ ሰዎች ዝርዝር፡-

  1. መርን ሲነጋ
  2. መርሻ ደረጄ
  3. ፈይሳ (ያባታቸው ሥም ያልታወቀ
  4. ሰለሞን አበራ (በምዕራፍ ሆቴል አርፈው የነበሩ ከሮቤ የመጡ እንግዳ)

በዴራ ከተማ የተፈፀመው ጥቃት ሃይማኖትን እና ብሔርን የለየ (“ነፍጠኛ” እየተባለ) ሥም ዝርዝር ተይዞ የተፈፀመ ስለመሆኑ ተጎጂዎቹ ገልጸዋል። የዶዶታ ወረዳ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሃይደር እና አንዳንድ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ተጎጂዎቹ ቢናገሩም፣ ከሌላ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም። ሆኖም፣ የጥቃቱ ተሳታፊዎች በሙሉ ባለመያዛቸው ተጎጂዎቹ አሁንም ሌላ ጥቃት ይፈፀምብናል በሚል ስጋት ላይ ናቸው።

(በዴራ ከተማ በነበረው ቃጠሎ ሲሊንደር ፈንድቶ ሁለት ጥቃት አድራሾች መሞታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አመፁን ለመቆጣጠር በተኮሰው ጥይት የተገደሉ መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል። ሆኖም፣ ይህን መረጃ ከአካባቢው አስተዳደር ማረጋገጥ አልቻልኩም።)

  • አሰ

በአሰላ ከተማ ንብረትነቱ መስፍን ጥበቡ የተባሉ ግለሰብ የሆነ የእንጨት ሥራ ፋብሪካ በቃጠሎ እንዲወድም ተደርጓል። በቃጠሎው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረቱ እንደወደመ መስፍን ገልጸዋል። ቢሯቸውም ተቃጥሏል።

“ተወልጄ ያደግሁት አሰላ ከተማ ነው። ኦርቶዶክስ በመሆኔና ቤተክርስቲያን ታግዛለህ ተብዬ ነው ተደጋጋሚ በተጠና ሁኔታ ጥቃት የሚፈፀብኝ። ጥቃት አድራሾቹ ከገጠር በመኪና ተጭነው የመጡ ናቸው። የአካባቢው ኅብረተሰብ ቃጠሎውን ሊያጠፋ ሲል ፖሊስ ነው ‘ወደ እሳቱ መጠጋት አይቻልም’ እያለ የከለከለው። ፖሊስ እና የአካባቢው አስተዳደር ተባባሪ ነበር። የቀበሌው ሊቀመንበር ዋና ተሳታፊ ነበር። በመኪና ተጭነው የመጡትን አቅጣጫ አሳይቶ፣ መለስ ብሎ ልብስ ቀይሮ ነበር ወደ ሕዝቡ የተቀላቀለው። ግልጽ ትብብር ነው ያደረገው። አሁን ታስሯል መሰለኝ። ይሄ ፋብሪካ ውድመት ሲፈፀምበት አሁን ለ2ኛ ጊዜ ነው። ጥቅምት 12/2012ም አቃጥለውብኝ እንደገና በብድር ነው ሥራ አስጀምሬው የነበረው” – መስፍን ጥበቡ፣ ንብረት የወደመባቸው

የእንጨት ፋብሪካው ለ40 ሰዎች ቋሚ እና ለ60 ሰዎች ጊዜያዊ ሥራ የፈጠረ ነበር። መስፍን አሁንም ስጋት እንዳለባቸውና ቤታቸው እንደማያድሩ ገልጸዋል። መኖሪያ ቤታቸውም በዕለቱ ተዘርፏል።

“ነፍጠኛ፣ የምኒልክ ወገን” እያሉ ነው ጥቃቱን ያደረሱት ብለዋል።

  • ገደብ አሳሳ

በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ በሰዎች እና ንብረት ላይ ጥቃት ከደረሰባቸው ሥፍራዎች አንዱ ሲሆን፣ በ11 ወረዳዎች ጥቃት ተፈፅሟል። በአሳሳ ከተማ ብቻ 3 ወንዶች እና አንዲት ሴት፣ በድምሩ በ4 ሰዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈፅሟል። ግድያው አንገት በማረድ፣ ሰውነት በመቆራረጥ፣ በስለት ደጋግሞ በመውጋት እና በጥይት የተፈፀመ ነው። በአሳሳ ከተማ የተገደሉ ሰዎች ዝረዝር፦

  1. ተፈሪ በላይነህ
  2. መጦሪያ ላቀው
  3. ስንቅነሽ ገብረየሱስ
  4. ታምራት አዱኛ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል በከተማዋ ተወልደው ያደጉት የ87 ዓመት አዛውንቱ ተፈሪ በላይነህ እና ባለቤታቸው ስንቅነሽ ገብረየሱስ በቤታቸው ተቀጥቅጠው የተገደሉ ሲሆን፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎች አስክሬናቸውን በመቆራረጥ መንገድ ላይ ጎትተዋል። አስክሬናቸው የተነሳውም ከሰዓታት በኋላ የመከላከያ ኃይል መድረሱን ተከትሎ ነበር።

ወጣት ታምራት የተገደለው ሰኔ 24 ቀን 2012 በጩቤና በገጀራ ነው። ይህም አመፁ በከተማዋ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ስለነበር ነው።

በገደብ አሳሳ ሰኔ 23 ቀን 2012 ወጣቶች ፖሊስ ጣቢያ በር ጎማ ሲያቃጥሉ ፖሊስ በዝምታ ይመለከት እንደነበር ተጎጂዎች ተናግረዋል። በዚህም ጥቃቱ የአካባቢው አስተዳደር እና ፖሊስ ይሁንታ ያለበት ነበር ሲሉ ገልጸዋል። ጥቃት የደረሰባቸው ሥም ዝርዝር ተይዞ “ነፍጠኞች” (በተለይ ክርስቲያኖች) ላይ ነበር።

በከተማዋ ዝርፊያ እና ቤት ቃጠሎም ተፈፅሟል። ቤተክርስቲያንን በመርዳት የሚታወቁ ሰዎች ዋና ዒላማ ነበሩ – ተጎጂዎች እንደሚሉት። ጥቃት አድራሾቹ ከገጠር እንዲመጡ የተደረጉም ይገኙበታል። በአሳሳ የተፈፀመው ጥቃት የጀመረው ጠዋት 12፡00 ሰኔ 23 ቀን 2012 ነበር።

በጥቃቱ ማግስት ከ300 በላይ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች በአሳሳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው ነበር። አሁን ላይ ከአካባቢው በመልቀቅና ከወዳጅ በመጠጋት ብዙዎች ከመጠለያ ወጥተው ቁጥራቸው ቀንሷል – የደብሩ አስተዳዳሪ እንደተናገሩት። በቤተክርስቲያን የተጠለሉትም እስካሁን ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት አላቸው።

(በአሳሳ ከተማ አመፁን ለመቆጣጠር በነበረው ተኩስ የተገደሉ ሰዎች መኖራቸው ነዋሪዎች ቢገልጹም ከአስተዳደሩ ማረጋገጥ አልቻልኩም።)

  • ባሌ ሮቤ

ሮቤ ከተማ በሰዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም። ሆኖም፣ አንድ መኖሪያ ቤት እና 3 ንግድ ቤቶች ተቃጥለዋል። ንግድ ቤቶቹ ጥቅምት 12 ቀን 2012 በተነሳው አመፅም ተቃጥለው ነበር። በጥቅምቱ ጥቃት ወቅት ንብረታቸው የወደመውና ተጎጂዎች ሆነው ሳለ እስካሁንም ያለፍርድ የታሰሩ እንዳሉ ሚሚያ ባልቻ የተባሉ የጉዳቱ ሰለባ ገልጸዋል።

“ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ስለሆንሁ ብቻ ሁለት ጊዜ ቤቴ ተቃጥሏል። ቤተክርስቲያን ታሰራለህ ተብሎ የታሰረም አለ። ጥቅምት የታሰሩ እስካሁን አልተፈቱም። በዚያ ወገን ደግሞ ‘ቤታችሁን ያቃጠልነው እኛ ነን’ እያሉን እስካሁን ያልተጠየቁ አሉ። ምን እየተሠራ እንደሆን አይገባኝም። ይሄው 7 ልጆችን ይዤ በችግር ላይ አለሁ። አሁንም መቼ እንደሚጎዱን አላውቅም። ስጋት ላይ ነን” –  ሚሚያ ባልቻ፣ ንብረት የወደመባቸውና ተካ አስፋው የተባሉ ባለቤታቸው የታሰሩባቸው።

ሮቤ ከተማ ጥቅምት ላይ ከተፈፀመው ጥቃት አንፃር ሲታይ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የተፈፀመው ጥቃት ቀላል የሚባል እንልሆነ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ጥቅምት 13 እና 14/2012 በሮቤ እና ዲንሾ ከተሞች አምስት ሰዎች ተገድለው እንደነበርም ያስታውሳሉ። እነዚህም፦

  1. በላይ አደሬ
  2. እሸቱ ጌታሁን
  3. ዳምጠው ዘርፉ
  4. ተስፋዬ ድሪባ
  5. ታምራት በቀለ ነበሩ።

በወቅቱ የነበረው የንብረት ውድመትም ከባድ ነበር – ብለዋል ነዋሪዎች።

  • ባሌ ጎባ

በባሌ ዞን ጎባ ከተማ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ሆኖም፣ በከተማዋ ታዋቂ የሆነው “ይልማ ሆቴል” በቃጠሎ ወድሟል። የሆቴሉ ባለቤት የሆኑት አቶ ተስፋዬ ይልማ እንዳሉት “ይልማ ሆቴል” 33 ቋሚ ሠራተኞች ነበሩት። ሠራተኞቹ ለጊዜው መሰናበታቸውን ተናግረዋል። ሆቴሉ ከ1950ዎቹ ጀምሮ አግልግሎት የሰጠ ነበር። መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ብለዋል – ተስፋዬ።

“ጥቃቱ ሲፈጸም ፖሊስ መቆጣጠር ይችል ነበር፤ መከላከልም ይችል ነበር። የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያኮ እዚሁ ከተማችን ውስጥ ነው ያለው። ሆኖም፣ ፖሊስ ምንም አላደረገም። ይሄ በጣም ያሳዝነኛል” ተስፋዬ ይልማ

ከባድ ጉዳት የደረሰበት “ይልማ ሆቴል” ይሁን እንጂ፣ በጎባ ከተማ መስታወት መሰባበርን ጨምሮ በ46 ሱቆችና ቤቶች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

  • ባሌ አጋርፋ

በባሌ ዞን ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ዋነኛው አጋርፋ ወረዳ አምቤቱ ቀበሌ ይገኝበታል። ከጉዳቱ ተርፈው በአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ኮሌጅ ት/ቤት ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች በርካታ ናቸው። ተጎጂዎቹ እንደሚሉት የተፈናቃዮች ቁጥር 1253 ሲሆን፣ የአጋርፋ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ ሽመልስ ቶሎሳ በበኩላቸው ተፈናቃዮች 1144 ናቸው ብለዋል።

በአጋርፋ አምቤቱ ቀበሌ 5 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። መኖሪያ ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ ሞተር ብስክሌቶችና ሌሎች ንብረቶች ተቃጥለዋል። የንብረት ዝርፊያ ተፈጽሟል።

በአጋርፋ አምቤቱ የተገደሉ ሰዎች ዝርዝር፦

  1. አስቻለው አባቡ
  2. አስፈራ ትርፌ
  3. ሰለሞን በላይነህ
  4. ኃይሌ ጌታቸው
  5. ትዕግስት አስራት ናቸው።

እንደተነገረኝ ‘አስቻለው አባቡን አንገቱን አርደው፣ ዓይኑን አውጥተው አቃጥለውታል። ኃይሌ ጌታቸው አንገቱን አርደው ገድለው ጥለውት አስክሬኑን አላስነሳም፣ እዚህ አትቀብሩም በሚል ከልክለው አካሉን አውሬ በልቶት መከላከያ ከደረሰ በኋላ የተቆራረጠ አካል ተሰብስቦ በ3ኛ ቀኑ ነው የተቀበረው። አስፈራ ትርፌ እና ሰለሞንም በተመሳሳይ ታርደው የተገደሉ ናቸው።’

“ሰለሞን ባለቤቱ ነው። ልጆችም ወልደናል። እሱም እኔም ኦሮሞዎች ነን። ነገር ግን ‘ክር ያሰረ ኦሮሞ አናውቅም’ እያሉ ነው ያሳደዱን። ‘ኦሮሚያ ሳውዲ አረቢያ ናት’ ይሉ ነበር። ባለቤቱ ሰለሞን ‘ክሬን አልበጥስም’ ብሎ ነው የታረደው። አራት ልጆቻችንን ይዤ እንዲህ ሆኜ ቀረሁ። ‘አብሮን የሰገደ ብቻ ነው ኦሮሞ’ ይላሉ” የኔነሽ ማሞ፣ የሟች ባለቤት።

“እምነት ተኮር ጥቃት ነው የነበረው። እዚህ ሕይወታችንን ለማትረፍ ነው የተጠለልነው። ቃጠሎ እና ዝርፊያ ነበር። ክርስቲያኖች ብቻ እየተለዩ ነው የተጎዱት። ሙስሊሞች በመከላከል ተብሎ ሁለት ተጎድተዋል መሰለኝ።… ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ከባድ ነው። ሰው ተገድሎ ዓይኑ እየወጣ ብዙ ግፍ ደርሷል። አስክሬን የሚያነሳ እንኳን አልነበረም። መከላከያ ከመጣ በኋላ ታጅበን ነው አስክሬን የሰበሰብነው። ጦር፣ ገጀራ፣ ሌላም ይዘው ነበር። ፖሊስ አልደረሰልንም ነበር። ዕቅድ ነበራቸው መሰለኝ። ከባድ ነበር። እኛን ለመከላከል የተባበሩ ሙስሊሞች ነበሩ። በእነሱ ነው እኛ የተረፍነው”  – ወጣት ኪያ ጣሰው፣ ተፈናቃይ።

“ከመስከረምና ጥቅምት ጀምሮ ክርስቲያኖችን በመስደብ፣ በማስፈራራት ያዋክቡ ነበር። ቤተክርስቲያን የሚሔዱትን፣ ክር ያሰሩትን ይሳደባሉ። አዝመራና የቀንድ ከብቶች ይዘረፋሉ። ችግሩ የቆየም ነው። ሰኔ 23 የሆነው ድርጊቱ ነው፤ ሐሳቡ ቆይቷል ባይ ነኝ። ሟች ኃይሌ ጌታቸው ዘመዴ ነው። እኔ ገና ወጣት ነኝ፤ በዚህ ዕድሜዬ የተቆራረጠ አካል ሰብስቤ እንድቀብር ተገድጃለሁ። በጣም አሰቃቂ ነበር። እኔም ‘ይታረድ’ ተብዬ ሥም ዝርዝር ወጥቶብኛል። ፌስቡክ ላይም ጽፈውብኛል። ክርስቲያን ስለሆንኩ ነው፤ ‘ነፍጠኛ’ ይላሉ። እኔ ተወልጄ ያደግሁት እዚህ ነው። የት ሂድ ይሉኛል?”ወጣት ጎሳ ታደረግ፣ ተፈናቃይ።

ከጥቃቱ በመሸሽ ከአንድ ወር በላይ በአጋርፋ ግብርና ቴክኒክ ኮሌጅ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች በመንግሥት በኩል በቂ ዕርዳታ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገልጸዋል። አሁንም የደኅንነት ስጋት አለባቸው። አንዳንድ ጥቃት አድራሾች የታሰሩ ቢሆንም፣ አመፀኞችን በገንዘብና በሥልጣን ላይ ሆነው የሚደግፏቸው ግን አልተያዙም ይላሉ ተፈናቃዮች። ሌላ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችልም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የአጋርፋ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ ሽመልስ ቶሎሳ በበኩላቸው በወረዳው 347 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል 14 የፖሊስ አባላት ሲሆኑ፣ 7ቱ ደግሞ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ናቸው። ሽመልስ ጥቃቱ ‘ሃይማኖትም፣ ብሔርም ተኮርም ነበር’ ለማለት እንደማይችሉ፣ ‘ነገር ግን ሁኔታው ፖለቲካዊ እንደነበር’ ተናግረዋል።

የዘገባው ውስንነቶች

ይህ ዘገባ የተዘጋጀው በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የካሕናትና ምዕመናን ኅብረት የጉዞ ፕሮግራምና ትኩረት የተገደበ በመሆኑ መረጃዎችን ከተለያዩ ወገኖች ለመሰብሰብ ውስንነት ነበረው። በዚህ ዘገባ የአጋርፋ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊን ለማነጋገር ከመቻሌ በስተቀር በመንግሥት ወይም በገዢ ፓርቲው በኩል፣ ወይም ከፖሊስ ያለውን መረጃ ከየአካባቢዎቹ ለመሰብሰብና ለማጣራት ጊዜና ሁኔታው አልፈቀደልኝም።

በተጨማሪም፣ ምንም እንኳ ጉዞው በአምስት የፌድራል ፖሊስ አባላት እጀባ የተደረገ ቢሆንም፣ የፀጥታ ስጋት ስለነበር በከተሞቹ በነፃነት ተንቀሳቅሶ ተጓዳኝ መረጃዎችን መሰብሰብ አዳጋች ነበር። የጉዳት ሰለባ ሥፍራዎችንም ተዘዋውሮ ለመመልከት ከጥቂቶች በስተቀር አልተቻለም። ለምሳሌ፣ አጋርፋ በመጠለያ ካሉ ተፈናቃዮችና የጉዳቱ ሰለባዎች መረጃ ከመሰብሰብ ያለፈ፣ ጉዳቱ የደረሰባትን አምቤቱ ቀበሌ ተገኝተን መመልከት አልቻልንም።

ለዘገባው የዋሉ የመረጃ ምንጮች

  1. የአርሲ ዴራ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ
  2. ደረጄ ፈለቀ (በጥቃቱ ልጃቸውን ያጡ)
  3. አበበች ፈለቀ (ተፈናቃይ)
  4. እንየ ቸሩ (ከጥቃቱ የተረፉ)
  5. ወገኔ ግርማ (ከጥቃቱ የተረፉ)
  6. ቀሲስ ከፍያለው (የቤተክርስቲያን አገልጋይ)
  7. ዶ/ር ናደው ተ/ጻድቅ  (ሆቴል የወደመባቸው)
  8. መስፍን ጥበቡ  (የእንጨት ፋብሪካ የወደመባቸው)
  9. የአሳሳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ
  10. ዶ/ር ንጉሡ ለገሰ (የካኽናትና የምዕመናን ኅብረት መሪ)
  11. የሟች ስንቅነሽ እና የባለቤታቸው መጦሪያው ቤተሰቦች
  12. ተስፋዬ ይልማ (ሆቴል የወደመባቸው)
  13. ማሚያ ባልቻ (ንብረት የወደመባቸውና ባለቤታቸው የታሰረባቸው)
  14. ሽመልስ ቶሎሳ (የአጋርፋ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ)
  15. ታደሰ ኢድአ (ተፈናቃይ)
  16. የባሌ አገረ ስብከት ኃላፊ
  17. ወጣት ኪያ ጣሰው (ተፈናቃይ)
  18. ወጣት ጎሳ ታደረግ (ተፈናቃይ፣ ዘመድ የተገደለበት)
  19. የኔነሽ ማሞ (ባለቤታቸው የተገደለባቸው)

በተጨማሪም፦ በቦታው በመገኘት የተደረገው ምልከታ ትልቅ የመረጃ ግብዓት ሆኗል። ፎቶዎችና ቪዲዮዎችንም ማስቀረት ተችሏል።

—-

* ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ይህንን ዘገባ አቀናብሮ ለመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ከላከ በኋላ ከሌሎች ሁለት የአስራት ቴሌቪዥን ባልደረቦቹ ጋር እስካሁን ባልተገለጸ ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።

Filed in: Amharic