እነ አቶ እስክንድር ነጋ በምስክሮች አቀራረብ ላይ አስተያየት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ
ታምሩ ጽጌ
* አቶ እስክንድር በራሳቸው እንደተናገሩት ‹‹ጉዳዩ የፖለቲካ ይዘት ስላለው ጊዜ ያስፈልጋልና ጊዜ ይሰጠን፤›› ብለዋል!
* … ሌላኛዋ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ቀለብ ደግሞ “የፖለቲካ እስረኛ እንደመሆናችን ፍርድ ቤቱ ለከሳሽም ሆነ ለተከሳሽ እኩል ዕድል ሊሰጥ ይገባል፤ በመሆኑም ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
* በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በደረሰ የሰዎች ሞትና ንብረት ውድመት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛና ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ፣ ዓቃቤ ሕግ በቅድመ ምርመራ ችሎት በሚያሰማቸው ምስክሮች ላይ ያላቸውን አስተያየት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡
ትዕዛዙን ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የሰጠው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የመጀመርያ ደረጃ ተረኛ ችሎት ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ዓቃቤ ሕግ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩና በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩለት ለፍርድ ቤት ዝርዝራቸውን ባቀረባቸው ምስክሮች ላይ ያላቸውን መቃወሚያ ወይም አስተያየት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጠው ለዛሬ ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ጠቅሶ በአቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወ/ሮ ቀለብ ሥዩም ላይ የሚመሰክሩ ሰባት ምስክሮች እንዳሉት ለፍርድ ቤቱ አሳውቆ፣ ሦስት ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩና አራት ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎ እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ እነ አቶ እስክንድርም በዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ መስጠት እንዳለባቸው ያቀረቡትን ሙግት ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ፈቅዶላቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ የምርመራ መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 በመጥቀስ የከፈተውን ቀዳሚ ምርመራ አስመልክቶ ያቀረበውን ቀዳሚ ምርመራ የማድረግ ውሳኔ ግልባጭና የምስክሮችን ዝርዝር እንዲያቀርብ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሁለት ገጽ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ወጣቶችን በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ጽሕፈት ቤታቸው በመሰብሰብ፣ አዲስ አበባ መመራት ያለባት በአዲስ አበቤዎች እንጂ አሁን ባለው አመራር መሆን እንደሌለበት በመንገርና ለአመፅ በማነሳሳት ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የድምፃዊ ሃጫሉን ግድያ አስከትሎ በአዲስ አበባ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ማብራራቱን ገልጿል፡፡ በተፈጠረው ሁከትና ግጭት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ንብረቶች መውደማቸውንም ዓቃቤ ሕግ መግለጹን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱና ንብረቶች ከመውደማቸው አንፃር ጉዳዩን የሚመለከተው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢሆንም፣ በምርመራ ወቅት የተገኙ የሰዎች ማስረጃዎችን ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑን ስላመነበትና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ባሉት ድንጋጌዎች የተፈቀደ መሆኑን በመጠቆም፣ በተጠርጣሪዎች ላይ ምስክሮቹን በቀዳሚ ምርመራ ሥርዓት ማሰማት እንዲችል እንዲፈቀድለት መጠየቁንና ምስክሮቹም ሰባት መሆናቸውን በዝርዝር ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ለተጠርጣሪዎቹና ታዳሚዎቹ አሳውቋል፡፡ ሦስቱ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩና አራቱ ደግሞ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ መጠየቁንም አክሏል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች (ሁለት ናቸው) ካዳመጡ በኋላ ጥያቄው ሰፊ ምላሽ የሚፈልግና ከደንበኞቻቸውም ጋር መወያየትና መመካከር ስለሚያስፈልጋቸው ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የውሳኔ ግልባጭና የምስክሮቹ ዝርዝር ተሰጥቷቸው ምላሹን በአጭር ቀጠሮ ውስጥ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱን ጠየቁ፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ጥያቄ የተጠርጣሪዎቹን መሠረታዊ መብት የሚመለከቱ ጥያቄዎች በመሆናቸውና የመከላከል መብታቸውንም የሚያጣብቡ ስለሆኑ፣ በደንብ ዓይተውና ተዘጋጅተው ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም ጠበቆቹ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለቀረበው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ቀዳሚ ምርመራ የሚሠራው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ከአንቀጽ 80 እስከ 93 በተደነገገው መሠረት ነው፡፡ ዓላማውም ማስረጃን ማቆየት እንጂ ሙግት ወይም ክርክር የሚካሄድበት አይደለም፡፡ በሕጉ አንቀጽ 81 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን በመጠቆም ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ እንዳስረዳው ሕጉ ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ያለው ድንጋጌ ዓላማ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል በቀዳሚ ምርመራ አስጠብቆ ክስ የሚመሠርት ሲሆን፣ ለቀጣይ ፍርድ ቤት ለማቆየት እንጂ ውሳኔ የሚሰጥበት እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ለተጠርጣሪዎቹ ዕድል የተሰጠው በሕጉ አንቀጾች ላይ የሚያነሱት ክርክር ካለ በሚል እንጂ ፍርድ ቤቱ እያየ ያለው ክስ አለመሆኑንና ክርክር የሚያቀርብበት እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ሥነ ሥርዓቱ በግልጽ ደንግጎ እንዳስቀመጠውና ከቀዳሚው ምርመራ አንፃር የጊዜ ጥያቄ የሚቀርብበት ባለመሆኑ፣ ያላቸውን ሐሳብ ወይም አስተያየት በችሎት ተነጋግረው እንዲገልጹ ዕድል ሰጥቷል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ግን በድጋሚ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዓቃቤ ሕግ ጊዜ ተሰጥቶት በጽሑፍ ስላቀረበ እነሱም ጊዜ ተሰጥቷቸው በውሳኔ ግልባጩም ላይ ሆነ በቀዳሚ ምርመራው ላይ ያላቸውን መቃወሚያ እንዲያቀርቡ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በድጋሚ ለተጠርጣሪዎቹ እንደገለጸው በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 83 ላይ እንደተደነገገው፣ ዓቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ የከፈተው ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ሲወስን ወደ ፍርድ ቤት መላክ እንደሚችል በመደንገጉ ነው፡፡ ክርክር የሚቀርብበት እንዳልሆነም ተናግሯል፡፡
አቶ እስክንድር በራሳቸው እንደተናገሩት ‹‹ጉዳዩ የፖለቲካ ይዘት ስላለው ጊዜ ያስፈልጋልና ጊዜ ይሰጠን፤›› ሲሉ፣ ሌላኛዋ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ቀለብ ደግሞ የፖለቲካ እስረኛ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ ለከሳሺም ሆነ ለተከሳሽ እኩል ዕድል ይሰጣል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረው፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ‹‹በፍርድ ቤቱ ጥርጥር አይግባችሁ፡፡ እኩል ነው የሚዳኛችሁ፡፡ መነጋገር ያለብን ሕጉ ምን ይላል? በሚለው ላይ ይሁን፡፡ የመናጋገር መብታችሁ ሲከበር መነጋገር ያለብን በሕጉ መንፈስና ሥርዓት መሆን አለበት፡፡ ሕጉ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ በሚሰጠው ብይን (ውሳኔ) ሕጉ አላግባብ ተተርጉሟል ካላችሁ ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ፡፡ ሁሉም ነገር በሕግ ሥርዓት ውስጥ ነው የሚያልፈው፤›› ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎችና በዓቃቤ ሕግ የቀረበውን ክርክር ከሰማ በኋላ ብይን ሰጠቷል፡፡ የቅድመ ምርምራ የሚመራው በሕጉ ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ባለው ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡ ዓላማውም ማስረጃን ጠብቆ ክስ የሚመሠረት ከሆነ ለቀጣዩ ፍርድ ቤት ጠብቆ ለማቆየት ነው፡፡ በመሆኑም የተጠርጣሪ ጠበቆች ዓቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ያቀረበው ውሳኔና የምስክሮች ዝርዝር እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በቀዳሚ ምርመራ ሊያሰማቸው ያዘጋጃቸውን ምስክሮች አቅርቦ ማሰማት እንደሚችል ሕግ ስለተፈቀደለት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ተጠርጣሪዎች በምስክሮች አሰማም ላይ ያላቸውን ተቃውሞና አስተያየት ለዛሬ ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ወጣቶችን በማደራጀትና በገንዘብ በመርዳት በከተማው ውስጥ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ብጥብጥ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ በተወሰዱት አቶ ልደቱ አያሌው ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ተጨማሪ ሰባት የምርመራ ቀናት ተፈቅዷል፡፡ ከ14 የምርመራ ቀናት በኋላ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረቡት አቶ ልደቱ ላይ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሁለት የሰነድ ማስረጃ ማለትም ‹‹የኢትዮጵያ የህዳሴ ዕርቅና አንድነት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም›› እና ‹‹ለውጡ ከድጡ ወደ ማጡ›› የሚሉ ማግኘቱን፣ ሁለት ሽጉጦችንና በብርበራ ሰነዶችን ማግኘቱን፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለምርመራ መስጠቱን፣ የምስክሮች ቃል መቀበሉንና ሌሎች ምርመራዎች እንደሚቀሩት በማስረዳት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
አቶ ልደቱ በሰጡት መልስ ተገኘ የተባለው የሰነድ ማስረጃ አንደኛው በአደባባይ የገለጹት መሆኑንና ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ዕርቅና አንድነት የሽግግር መንግሥት›› የሚለው ገና ረቂቅ መሆኑን፣ ሽጉጦቹም አንደኛው በ1991 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ፖሊስ ፈቃድ የወጣበትና የአባታቸው ውርስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሌላኛው ሽጉጥ በ1998 ዓ.ም. የፓርላማ አባል ስለነበሩና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ስለነበር ‹‹ትመልሳለህ›› ተብለው ከመንግሥት የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ አምስት ጊዜ ታስረው የተገኘባቸው ነገር ስለሌለ በፍርድ ቤት አለመከሰሳቸውን ተናግረው፣ አሁንም የታሰሩበት ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማስረጃ ከተገኘባቸው ለመጠየቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የልብ ሕመምተኛ መሆናቸውንና እሑድ ሐምሌ 19 ቀን ወደ አሜሪካ ለመብረር እየተዘጋጁ እያሉ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. መያዛቸውን በማስታወስ የልብ ሕመምተኛ በመሆናቸው መቼና በምን ጊዜ ምን እንደሚሆኑ ስለማያውቁት የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲታከሙ ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ተጠርጣሪዎች ማስክ ሳያደርጉ በታሰሩበት ክፍል ስለሚገቡ ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሥጋት እንዳላቸውም በመግለጽ፣ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ እሳቸውን ፍትሕ የሚሰጣቸው ፍርድ ቤት እንጂ ፖለቲካ ባለመሆኑ ዋስትናቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ጤናቸውን በሚመለከት ከዕለቱ ጀምሮ አገር ውስጥ ባለና ጥሩ ሕክምና በሚሰጥ ሐኪም ቤት እንዲታከሙ እንዲደረግ ትዕዛዝ በመስጠት፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራው አጠናቆ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀርብ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ ለነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡