>
8:34 am - Friday June 2, 2023

ዝክረ ልደት - በእንተ ንጉስ ወ ንግስት...!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

ዝክረ ልደት – በእንተ ንጉስ ወ ንግስት…!!!

ሳሚ ዮሴፍ

“…የምዘምተውም እኔው ራሴ ነኝና ተከተለኝ፤ መቃብርህን በገንዘብህ እንድትገዛ የምትገደድበት ጊዜ ሳይደርስ ለሀገርህ፣ ለኃይማኖትህ፣ ለሚስትህና ለልጅህ ስትል ተዋጋ! የሚደረገውም አዋጅ ይደርስሃል…!!!” 
—-
….አጤ ምኒልክ ሙሴ ኤልግንና ሙሴ ሸፍኔን ወደ ፈረንሳይ መንግሥት በመላክ ስለ ውጫሌ ውል እንዲያስረዱና መንግሥታቸውም አንቀጾቹ እንዲሰረዙ ለማድረግ በነገሩ ገብቶ እንዲገላግላቸው የሚቻላቸውን ቢያደርጉም፤ በጣልያን መንግሥት እምቢተኝነት ጥረቱ ባለመሳካቱ
ሚንስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንት የሚገኙበት ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ። እያንዳንዱ ሰው ስለተነሳው ችግር ያለውን አስተያየት ሀገር ፍቅር በተሞላበትና የጋለ መንፈስ ሲገልጽ ቆየ። እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው…
“እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣልያ ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ ወንድማቸውን ራስ ወሌን አተኩረው በማየት በተለመደው ጀግና አንደበታቸው የተሰበሰበውን ሕዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ…
“መልኩ ከመልካችን የማይመስል፣ ቋንቋው ከቋንቋችን የማይመስል፣ በባህር ከልሎ የሰጠንን ሀገራችንን የሚቀማ ጠላት መጥቶ እንዴት ዝም እንላለን፤ እንዋጋለን እንጂ” በማለት የሀገሪቱን ቁንጅና፣ ልምላሜ፣ የምታፈራውን የእህልና የከብት ዓይነት እያጣቀሱ በማንሳት “ኧረ ለመሆኑ ተራራው፣
ሸለቆው፣ ወንዛ ወንዙ፣ ጨፌው፣ ሜዳው ማነው ቢሉት የማነው ብሎ ሊመልስ ነው እንገጥመዋለን እንጂ!” በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ ልብ የሚነካና ወኔውን የሚቀሰቅስ ንግግር በማድረጋቸው ሕዝቡ የጋለ ጭብጨባ አሰማ።
አጤ ምኒልክ በመጨረሻ በሰጡት መደምደሚያ ቃል
“…የምዘምተውም እኔው ራሴ ነኝና ተከተለኝ፤ መቃብርህን በገንዘብህ እንዳትገዛ የምትገደድበት ጊዜ ሳይደርስ ለሀገርህ፣ ለኃይማኖትህ፣ ለሚስትህና ለልጅህ ስትል ተዋጋ። የሚደረገውም አዋጅ ይደርስሃል” በማለት የጉባዔው ፍጻሜ ሆነ።
ዝክረ ልደት
Filed in: Amharic