መክሸፍ እንደ ኦሮሚያ! የማይጠግ ቁስል…!!!
ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ/ ካናዳ
ሻሸመኔ ነገ ሌላ ልጇን ትቀብራለች፡፡ እናት፡፡ በዲዛይን ሰው፡፡ በእምነት ፕሮቴታንት፡፡ በፍርጃ ደግሞ፤ አማራ፡፡ ሙሉወርቅ ተጫኔ ስሜ፡፡ ለሚያምኑ፤ ሰው መሆን የፈጣሪ ዲዛይን ነው፡፡ ሀይማኖትም፤ ቢያንስ ነፍስ ካወቅን በኋላ የፍላጎት ጉዳይ ነው፡፡ ብሄር ግን፤ አንድም ውርስ አንድም ፍርጃ ነው፡፡ በችሎታችን፤ በስራችን፤ በምርጫችን የምናገኘው ሳይሆን፤ በትውልድ፤ በውርስ፤ በድንገት፤ በፍርጃ የሚጫንብን፡፡ ሙሉወርቅ፤ በትውልድና በፍርጃ አማራ ትመስላለች፡፡ በምርጫም በውርስም ግን፤ ኢትዮጵያዊ ነች፡፡ ብሄሩን መንገስት ካስቀመጠው 85 ዝርዝር ውስጥ ያልመረጠ ኢትዮጵያዊ፤ በፍርጃ አማራ ነው፡፡ እኛ የፍርጃ አማሮች ነን፡፡
ሙሉወርቅ፤ ከአመታት በፊት ያልፍልኛል ብላ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደደች፡፡ አስር አመታት ፈጋች፡፡ ከቀማኞች እየተጋፋች፤ ትንሽ ገንዘብ ቋጠረች፡፡ በደቡብ አፍሪካ በስደተኞች፤ በመጤዎች ላይ ያለው ጥላቻ በረከት፡፡ ዜኖፎቢያ ይሉታል፡፡ በዚያ በደቡብ አፍሪካ ያለው የመጤ ጥላቻ፤ የስደተኛ ኢትዮጵያዊያንም አልቀረላቸውም ነበር፡፡ ከስልሳ አመታት በፊት ኔልሰን ማንዴላን አስተናግዳ፤ ገንዘብና ፓስፖርት ሰጥታ፤ ውትድርና አሰልጥና፤ ሽጉጥ አስታጥቃ የላከች አገር፤ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም፤ እንደማንኛውም አፍሪካዊያን የጥላቻ ሰለባ ከመሆን አልተረፉም፡፡ ስለዚህ፤ ሙሉወርቅ፤ ደቡብ አፍሪካ ሲመራት፤ “እናንተ አገረ ብርቁዎች፤ እኔም አገር አለኝ” ብላ፤ የቋጠረችውን ጥሪት ይዛ ወደአገሯ ተመለሰች፤ ወደሻሸመኔ፡፡
ሙሉወርቅ፤ ገንዘቧን፤ የተወለደችበት፤ ያደገችበት፤ ለወግ ለማእረግ የበቃችበት፤ አያት ቅድመአያቶቿ የገነቡት ሻሸመኔ ላይ አፈሰሰች፡፡ ሚኒባስ ገዛች፤ ቤት ገነባች፤ ሱቅ ከፈተች፡፡ ልጇን፤ ይስሀቅን እያሳደገች፤ ጌታን እያሰመገነች መኖር ጀመረች፡፡ እነሆ የጊዮርጊስ አለት፤ የሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተነሳ ስሜት የማይሰጥ ጥፋት፤ የሙሉወርቅ ንብረቷ ሁሉ ወደመ፡፡ እሷ ባጥር ሾልካ አመለጠችና ወደ ባል ቤተሰቦች ተጠጋች፡፡ ለአመታት የለፋችበት ጥሪት ግን፤ በሰአታት ውስጥ ወደመ፡፡
ሙሉወርቅ፤ የተቃጠለ ቤቷን ሳታይ ለ43 ቀናት ቆየችና፤ የተረፈ አንድ ክፍል አለ ሲሏት፤ እሱን አጸዳድቼ ልግባ ብላ ወደወደመው ቤቷ ሄደች፡፡ ከቃጠሎና ዝርፊያ የተረፉ፤ የተበታተኑ ቁሳ ቁሶችን ስታይ፤ እንባዋንና ሀዘኗን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ ቤቷን አጸዳች፤ ጠረገች፡፡ እንባዋን ግን የሚጠርግላት አጣች፡፡ ልክ እንደመጽሀፍ ቅድሷ ራሄል፤ የሚያጽናናት አጥታ፤ ቀኑን ሙሉ ስታለቅስ ዋለች፡፡ ካስጠጓት የባሏ ወገኖችም ዘንድ ተመልሳ ገብታ እንባዋና ለቅሶዋ አላቆመም፡፡ መታጠቢያ ቤት ገባች፡፡ ቆየች፡፡ ጠበቋት፡፡ ጠበቋት፡፡ አሁንም ጠበቋት፡፡ አንኳኩ፡፡ ተጣሩ፡፡ መልስ የለም፡፡ በመጨረሻም ወደውስጥ ሲገቡ፤ ወድቃለች፡፡ ላትመለስ አንቀላፍታለች፡፡ ተደፋች፡፡ ሻሸመኔ፤ ነገ የምትቀብረው ይችሂን ምስኪን ነው፡፡ ይህቺን እናት፡፡ የአስር አመት ልጇ፤ ባቢ ይሉታል፤ እናቱን ለወዲያኛው ያጣል፡፡ ባለቤቷም እንዲሁ፡፡ ቤተሰቦቿም፡፡ የቤተክርስቲያኗ ልጆች እንዲህ እየዘመሩ እህታቸውን ይቀብራሉ፤
እንግዳ ነኝ እኔ ስኖር በዚህች አለም፤
ሀብቴም በሰማ ነው፤ ከዚህ ምንም የለም፤
መልአክ ይጠሩኛል፤ ከሰማ በር ከፍተው፤
ከእንግዲህ ይህ አለም፤ ፍጡም ቤቴ አይደለም …….
ሙሉወርቅ ኦርቶዶክስ ብትሆን፤
ሀሌ ሉያ; ሀሌ ሉያ; ሀሌ ሉያ፤ ንጽህተ ወንጽህት፤ ረስያ፤
እግዚኦ አእርፍ ነፍሰ አመትከ ወለተማርያም፤ አስካለማርያም፤ እህተ ማርያም፤ ወለተክርስቶስ፤ ወለተጊዮርጊስ …. (የክርስትና ስሟን በግምት ነው የሰጠሁት)፡፡
በርግጥም ሙሉወርቅ፤ ሀብቷ በሰማይ እንደሆን እንጂ፤ እዚህ ምድር ላይ ያለውን፤ የለፋችበትን፤ የተንከራተተችበትን፤ ወጣትነቷን የሰዋችበትን ሀብት፤ ትዳሯን በሽብርተኞች ተነጥቃለች፡፡ በሚተካው ሀብት ብቻ በተዋት፡፡ ሰቆቃው ነፍሷንም አልማረውም፡፡ በዚህ በሻሸመኔና በነገሌ አርሲ በሌሎችም የኦሮሚያ አርባ ወረዳዎች የደረሰው ትልቁ ጥፋትም፤ ገንዘቡ፤ ወይም ንብረቱ አይደለም፡፡ እነዚህ ይተካሉና፡፡ ዋናው ሰለባ፤ መተማመን፤ መከባበር፤ መኗኗር ነው፡፡ ሰው ከአመታት፤ ከዘመናት በፊት ከነበረ፤ በንጽጽር የሰከን፤ የመከባበር፤ የመተሳሰብ፤ በፈሪሀ-እግዚአብሄር የተቃኘ መስተጋብር ወርዶ እንዴት ባንዴ እንዲህ ያለው የጭካኔ መቀመቅ ወስጥ ይሰጥማል የሚለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለአሸናፊ መንግስት ገብሮ ሲኖር ይሄ የመጀመሪያው አይደለም፤ የመጨረሻውም አይሆንም፡፡ ነገር ግን፤ መንግስት እስከገበሩለት፤ ፖለቲካዊ ስልጣኑን እስካልተጋፉ፤ ከህዝብ ጋር ላይና ታች ሆኖ ይኖራል፡፡ ህዝብም ተከባብሮ ጎን ለጎን ይኖር ነበር፡፡ አሁን ግን የመጡት፤ ክልሉ ያሳደጋቸው፤ ለክልሉም የማይበጁ፤ ሽብርተኞች ናቸው፡፡ እነሆ በጣት የሚቆጠሩ፤ በመንገስት ካድሬዎችና ባለሀብቶች የሚታገዙ ሽብርተኞች፤ በሚሊዮን የሚቆጠርን ሕዝብ ሕይወት አመሳቀሉ፡፡ የሰኔ 23ቱ ትልቁ ሰለባ ያ፤ ነው፡፡ ሰውነት፡፡ ሰብአዊነት፡፡
ሙሉወርቅን አላውቃትም፡፡ አባቷን አቶ ተጫኔን፤ ባለቤቷን፤ ልጇን ወይም ሌሎች የቅርብ ዘመዶቿንም አላውቃቸውም፡፡ አጎቷንና የአጎቷን ልጆች ግን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ አጎትዋ ፶ (ሀምሳ) አለቃ በቀለ ወርቅነህ በጎልማሳነታቸው ወራት፤ ኢትዮጵያን ለ30 አመታት በውትድርና ያገለገሉ ጀግና ናቸው፡፡ ልጆቸው፤ እነ ሰሎሞን በቀለ፤ አንዱአለም በቀለ፤ መሰረት በቀለ አብሮአደጎቻችን ናቸው፡፡ መሲ፤ አብራኝ አንድ ክፍል ተምረናል፡፡ ዛሬ፤ የበቀለ ቤተሰቦች ሀዘን ላይ ናቸው፡፡ ነገ፤ የወንድማቸው፤ የአጎታቸውን ልጅ፤ ሙሉን ይቀብራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ወይም ለማጥፋት; ሌላ ስንት ቀብር ያስፈልግ ይሆን? ሻሸመኔ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን አምታተው እንደዘገቡት፤ ታርዳ ሳይሆን፤ በተዘዋዋሪ በጊዮርጊሱ እለት በደረሰባት ሰቆቃ ድንጋጤ፤ ከቀናት በኋላ የሞተችውን ነፍሰጡር፤ ሜሮንን የዛሬ ሶስት ሳምንት አካባቢ ቀብራለች፡፡ እነሆ፤ ሻሸመኔ፤ ነገ፤ ሙሉወርቅን ትቀብራለች፡፡
የሰኔ ጊዮርጎስ እለት የተፈጸሙትን ብዙ አሰቃቂ ታሪኮች እየሰማሁ ልጽፋቸው እልና፤ እንደው ነገር ማካረር፤ ማባባስ ይሆን?፤ ልተወው?፤ ልናገረው?፤ ስል ከራሴም ከጓደኞቼም እመክራለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ታሪኮችን መተረክ፤ በቀልን፤ ቂምን፤ የመልስ ጥላቻን ሊያጎለብት ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ታሪክ እንደማይደገም ዋስትና የለም፡፡ ሻሸመኔ እንዲህ አይነት አዘቅት ውስጥ መስጠም የጀመረችው የዛሬ 2 አመት አንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ዘቅዝቃ የሰቀለች እለት ነው፡፡ ያን ያደረጉ፤ ከበው ሰልፊ ይነሱ የነበሩት ላይ እርምጃ ተወስዶ ቢሆን፤ እነዚህ መንግስት-ሰራሽ ሽብርተኞች ዛሬ የግድያ ፈቃድ እንደተሰጣቸው አይሰማቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም የደረሰውን ግፍና ሽብር፤ መናገሩ፤ ምናልባት እንዳይደገም፤ የፌደራሉም የክልሉም መንገስታትም የማያዳግም እርምጃ እንዲወስደድ ያደርግ ይሆን በሚል ስሌት እንጂ፤ ነገሩን ለማክረር አይደለም፡፡ ነገሩ ከዚህ በላይስ ምን ይከራል፡፡?
ነገ ሻሸመኔ፤ ከ200 መቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን፤ በብሄራቸው፤ በሀይማኖታቸው፤ በንብረታቸው ምክንያት ከተገደሉ ከ45 ቀናት በኋላ፤ እነሆ አንድ ተጨማሪ ልጇን ትቀብራለች፡፡ ነገ፤ ከነገሌ አርሲ ቀበሌ 01 አዳራሽ አጠገብ የሚኖሩት የ፶ (ሀምሳ) አለቃ በቀለ ቤተሰብ፤ ሻሸመኔ 04 ቀበሌ፤ ከአቡነ ተክለሀይማኖት ቤ/ክ አጠገብ የምትኖረውን የወንድማቸውን ልጅ፤ ሙሉወርቅን ይቀብራሉ፡፡ ሌላ የኦሮሚያ ክልል ክሽፈት ማህተም፡፡ ሙሉወርቅ ላይ አያበቃም፡፡ ይቀጥላል፡፡ የክልሉ እንጂ የሕዝቡ ክሽፈት አላልኩም፡፡ ምክንያቱም፤ ሕገመንግስቱ በስህተት፤ በማሰኑ ካድሬዎች ባይተረጎምና ባይተገበር ኖሮ፤ ኦሮሚያ በክልሉ የሚኖሩ፤ ለመኖር የመረጡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንጂ፤ የአንድ ብሄር ብቻ አይደለችምና፡፡
ኦሮሚያ ንብረትነቷ የአንድ ብሄር ብቻ ነው ብንል እንኳን፤ ባለፈው ጽሁፌ ላይ እንደሞገትኩት፤ የሀጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመው ግፍ፤ አቃፊነት መገለጫው ነው የተባለው የኦሮሙማ ተቃራኒ ነው፡፡ ሴትና ሕጻናት፤ ሽማግሌዎችና ካህናት፤ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን መግደል ጀግንነትም የኦሮሞም አይደለም፡፡ ትግልም አይደለም፡፡ ለክልል አቅመ አዳም አለመድረስና አገር ወይም ክልል ማስተዳደር አለመቻል እንጂ፡፡ በውስጣቸው የሚኖሩትን ዜጎች ሕይወትና ንብረት መጠበቅ ካልቻሉ፤ ክልሎች ለአቅመ ክልልነት አልደረሱም፡፡ የሙሉወርቅ ታሪክ መነገርም፤ የክልሉም፤ የፌደራሉም መንግስት፤ ሀላፊነታቸውን ተረድተው፤ የዚህን ጥፋት ምንጭ ከስር ከመሰረቱ እንዲመረምሩና እርምጃ እንዲወስዱ እንጂ ሌላ አላማ የለውም፡፡
ሙሉወርቅ ከአመታት በፊት ወደኢትዮጵያ ስትመለስ፤ የአስቴርን ዘፈን እየዘፈነች ይመስለኛል፡፡ እነዚያ አገረ ብርቁዎች፤ ተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካ ሽብርተኞች ሲያራውጧት፤ እኔ አገር አለኝ ብላ፤ በሩቁ የሚታይ አገሯን ፍለጋ ወደኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡ ወደሻሸመኔ፡፡ ትታት የሄደችው ኢትዮጵያ ግን ተለውጣለች፡፡ እነሆ ከደቡብ አፍሪካ ዘረፋ ሕይወቷንና ንብረቷን ያተረፈቸው ሙሉወርቅ፤ በገዛ ወገኖቿ ድርጊት ንብረቷንም ሕወቷንም ተነጠቀች፡፡ ከስላሳ አመታት በፊት ማንዴላን ያሰለጠኑ፤ ሽጉጥ ያስታጠቁ፤ የሜጫና ቱለማው፤ ጄነራል ታደሰ ብሩ ቀና ብለው ይሄንን ድርጊት ቢያዩ፤ በደረሰው ነገር የሚሸማቀቁ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ይሄ ድርጊት በምንም አይነት መልኩ የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም፡፡ የክልሉ መስተዳደር ግን ተጠያቂ ነው፡፡ ክልልነት እዳ አለው፡፡ የፌደራል መንግስቱም ጭምር፡፡ ትናንት በወላይታ፤ ከቀበሌ ጥይት በፈጠነ መልኩ የ17 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ መካለከያ፤ በሻሸመኔ የነሙሉወርቅ ንብርት ለሰአታት ሲነድ፤ ትእዛዝ አልደረሰንም ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ የክልሉን ልዩ ሀይልና የከተማዎቹን ፖሊስ ተዉት፡፡ ያ ሁሉ ከሆነም በኋላ፤ ባህርዳር ሄዶ ችግኝ የሚተክለው አብይ አህመድ፤ እስካሁንም ድረሰ፤ ሻሸመኔ ጎራ ብሎ፤ የደረሰውን ውድመት አልጎበኘም፡፡ ለሻሸመኔ ሕዝብ ሀዘኑን አልገለጸም፡፡ በእውኑ አብይና ሙሉወርቅ አንድ ጌታ ይጋሩ ይሆን? እነግዲያውስ ጌታ ይፍረድ፡፡
እስከዚያው ግን፤ በያለንበት መንግስታዊም ግለሰባዊም ቡድናዊም ሽብርን እንዋጋ፡፡ የሙሉወርቅን ነፍስ ይማር፡፡ መጽናናትን ይስጣቸው፡፡