>

ሕዝብ ምን ያድርግ? (ከይኄይስ እውነቱ)

ሕዝብ ምን ያድርግ?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 


 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ ኹሉ ግፍና በደል እየደረሰበት ዝም ብሎ የሚመለከትበት ምክንያቱ ምንድን ነው ብሎ ከውስጥም ከውጭም ጣት መቀሰር ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎቻችን እያደረግነው ነው፡፡ ለዘመናት ልንፈታው ያልቻልነው እንቆቅልሽ ሆኖብን ዘልቋል፡፡ ጣት ቀሳሪዎቹም የዚህ ምሥጢራዊ እንቆቅልሽ አካል ነን፡፡ እውነቱን ለመናገር በእንደዚህ ዓይነቱ አስተያየት ከግምት ባለፈ መናገር ይከብዳል፡፡ ርእሰ ጉዳዩ በይነ-ዲስፕሊናዊ የሆነ ጥናት ይጠይቃል፡፡ እንደ ሕዝብ ያለንን የጋራ ሥነልቡና መመርመርን ስለሚጠይቅ ጥናቱን ከበድ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ በዚህ ላይ ወያኔ ትግሬና ኦነግ ባለፉት 30 ዓመታት የፈጠሩትን የጐሣ ሥርዓት ስንጨምርበት ጥናቱን የበለጠ ውስብስብ እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡ ደመናውን በመጠኑም ቢሆን የገለጡልን የፕሮፌሰር መሥፍን የቅርብ ጊዜ ሥራዎች ናቸው፡፡ 

ስለሆነም  ከእኔ በተሻለ በጥልቀትና በስፋት ላሰቡበት ምሁራን ወገኖቼ ሜዳውንም ፈረሱንም እነሆ በማለት ለጊዜው ትኩረቴን የመላምት ምልከታዬ ላይ አደርጋለሁ፡፡

ደጋግሞ በታሪክ እንደታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨቋኞች የሚደርስበት የግፍ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ ገንፍሎ ይነሳል፡፡ እንደ ማዕበል፡፡ ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ይወስዳል፡፡ ይህ ግን በዓመፃ እንጂ በተደራጀና ሥርዓት ባለው ትግል ስለማይመራ ጋሼ መሥፍን አንድ የጋራ ጠባያችንን ሊገልጽ በሚችል መልኩ እንዳስቀመጡት ጨቋኙን አስወግደን ጭቆናን ተሸክመን ለሌላ ዙር የጭቆና አዙሪት ወደየቤታችን እንመለሳለን፡፡ የአገዛዝ/የጭቆና ሥርዓቱ አዳዲስ ጨቋኞችን ሰይሞ ባለበት ይቀጥላል፡፡ ከሁለት ዓመታትም በፊት የሆነው ይኸው ነው፡፡ ልዩነቱ በሥልጣን ላይ የሚገኘው ባሰባሰባቸው የጥፋት ኃይሎች ምክንያት ከቀደመው የጥፋት/የግፍ ሬከርዱን በማሻሻል ረገድ የሚያሳየው ጭካኔ ነው፡፡ የምንናገረው ስም ለውጦ ስለቀጠለው ኦሕዴድ-ኢሕአዴግ ስለሚባለው የከፋ የአገዛዝ ሥርዓት ነው፡፡

1ኛ/ በቅድሚያ ሕዝቡ ምን ነካው? ምን አደነዘዘው? የምንል ወገኖች እኔና አንተን ምን ነካን? ምን አደነዘዘን? እኔ እና አንተ ተደምረን አይደለም እንዴ ሕዝብ የምንሆነው? ለምንድን ነው ሁሌ ጥግ ይዘን ሌሎች (ምስኪኖች) ሞተውልንና ከፍለውልን ከጨቋኝ ሥርዓት ለመገላገል የምንፈልገው? ጥቂት የማይባል ወጣት ከትምህርት ቤት እንደወጣ ትዳር ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ሚሽቴን፣ ልጄን፣ ቤት፣ መኪና፣ ሽሮ፣ ዘይት ወዘተ. እያለ ሲንደፋደፍ እንኳን ትልቁን አገራዊ ሥዕል ለማየት ቁሳዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል ገና ከማለዳው ለአገዛዞች ባሪያ ሆኖ ዝርፊያውንና አድርባይነቱን ይለማመዳል፡፡ በዚያው ቀልጦ ይቀራል፡፡ ከዚያ ጣት ቀሳሪ ይሆናል፡፡ ትዳር መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አገር ህልው ሆኖ ሥርዓት ካልያዘ ትዳር የሰቀቀን ሕይወት ነው፡፡ አብዛኛው ወገኔ በተለይ ወጣቱ ትዳር ከገባ የአገር የወገን ጉዳይ እስከነ አንካቴው ይረሳል፤ ወይም ሁለተኛና ሦስተኛ ጉዳይ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ነኝ የሚለውም ባመዛኙ የትርፍ ጊዜ ሥራው ነው፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ዓላማ፣ ፕሮግራም ቀርፀው ሕዝብን አደራጅተው ጭቆናን ሲፋለሙ አላየነም፡፡ አብዛኛው የወገኑን ብሶት ለማሰማት እንኳን ዳተኛ ነው፡፡ ወገኑ በጐሣ ማንነትና በሚከተለው ሃይማኖት ምክንያት በጅምላ ሲጨፈጨፍ አብዛኛው ዝምታን የመረጠ ነው፡፡ ተራ መግለጫ ለማውጣት እንኳን በጉትጎታና የአገዛዙን የልብ ትርታ እያዳመጠ ነው፡፡ 

2ኛ/ የማኅበረሰብ ድርጅቶች (ሲቪል ማኅበራት)፤ ከፖለቲካ ማኅበራትም በተሻለ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ በመዝለቅ ሕዝብን ሊያነቃንቁ፣ በጋራ ዓላማ ዙሪያ አሰልፈው ጨቋኝ አገዛዝን ለመገዳደርም ሆነ ልዩ ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ተግባራት ለማስተባበር የሚችሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ወያኔ/ሕወሓት በተለይ፣ ኢሕአዴግ የሚባለው የጐሣ አገዛዝ ባጠቃላይ በዘመቻ መልክ ካሽመደመዳቸው ኅብረተሰብ አቀፍ ተቋማት በዋናነት የሚጠቀሱት የማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከነባሮቹና ከመንግሥት ተጽእኖ ነፃ ሆነውና ባንፃራዊነት ጠንካራ የነበሩትን የመምህራን ማኅበር፣ የሠራተኞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተቋም፣ የጠበቆች ማኅበር፣ ልዩ ልዩ የሙያ ማኅበራት፣ የነጋዴዎች ማኅበር፣ ወዘተ. ከጎናቸው ሙሉ የአገዛዙ ድጋፍ ባላቸው፣ ዓላማቸውን በሳቱ፣ አገዛዙን በሚያገለግሉና በጥፋቱም ሙሉ ተባባሪዎች በሆኑ ተለጣፊዎች በመተካት የሲቪል ማኅበራትን በተግባር የመንግሥት/የገዢው ‹ፓርቲ› ድርጅቶች አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ ማኅበራት ራሳቸው ነፃ ሳይወጡ ሕዝቡን አርነት ሊያወጡ በሚችሉበት አቋም አይገኙም፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ ነፃነታችሁን መልሳችሁ ባዲስ መልክ እንደገና መደራጀትና ሕዝባችሁንም ማደራጀት ይጠበቅባችኋል፡፡ ምናልባት ወንድማችን ኦባንግ ሜቶ የሚመራው ዓይነት እንቅስቃሴ በጎ ጅምር ይመስላል፡፡ በውጭም የምትገኙ የማኅበረሰብ ተቋማት (ወገንን ከመከራ እየታደገ ያለውና ታማኝ ወንድማችን እንደሚመራው ዓይነት ተቋም አስተዋጽኦ ሳንዘነጋ) ኢትዮጵያና ሕዝቧን አስቀድማችሁ፣ አገዛዙ ለራሱ ዓላማ ከሚጠቀምባቸው ኤምባሲዎች ጋር ሳትለጠፉና ሳትከፋፈሉ ግልጽ ዓላማ ይዛችሁ ከተንቀሳቀሳችሁ ትልቅ አስተዋጽኦ ልታበረክቱ ትችላላችሁ፡፡

 

3ኛ/ የሃይማኖት ተቋማት፤ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ሆን ተብሎ በዕቅድና በዝግጅት ከሥር መሠረታቸው እንዲናጉ፣ ዓላማቸውንና ተልኳቸውን እንዲስቱ ከተደረጉ ማኅበራዊ ተቋማት በመጀመሪያው ረድፍ የሚገኙት የሃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤክ (ኢርተቤክ) ላይ ለ27 ዓመታት በወያኔ ትግሬ፣ አሁንም ባለው አገዛዝ፣ በ‹ፓርቲው› በኦሕዴድ፣ በሽብርተኛው ኦነግና ከነዚህ ጋር ግንኙነት ባላቸውና ሁናቴዎች በተመቻቸላቸው አክራሪ እስልምናን ሽፋን ባደረጉ ሽብርተኞች ቀጥተኛና ሁሉን አቀፍ የጥፋት ዘመቻ ሲካሄድባት የቈየና እየተካሄደባትም ይገኛል፡፡ ኢሕአዴግ የሚባለው አገዛዝ የባዕዳን ቅጠረኛ ባንዳ በመሆን የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና፣ ኢትዮጵያዊነትንና መልካም እሤቶቿን ለማጥፋት የቅድሚያ ኢላማው ያደረገው ይህችን ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ዓለምአቀፋዊት ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት በመሆኗና በዘመናት የማይናወጸው አስተምሕሮዋና ሥርዓቷ (ስለ ሀገር አንድነትና ሰላም፣ ስለ ሕዝብ አንድነትና እኩልነት አጥብቃ መጸለይዋ ማስተማሯ – ጠላቶቿን ከእግሯ በታች ፈጥነህ አስገዛላት፤ ሕዝቧንና ሠራዊቷንም ጠብቅ እያለች ሰርክ ትጸልያለች) ለጐሣ/የዘር መድልዎ ሥርዓት በፍጹም ስለማይመች በመንግሥታዊ መዋቅር የታገዛ ጥቃት እየደረሰባት ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ የዘቀጠ ግብረ ገባዊና ሥነ ምግባራዊ ድቀትና ልሽቀት የገጠመው ኅብረተሰብ (በተለይም በአብዛኛው ወጣት ትውልድ) የታየው በተጠቀሱት ሦስት ዐሥርታት የመሆኑ ምሥጢር አንድም በኢርተቤክ. እና ምእመኖቿ ላይ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በቅንጅት እየተካሄደ ያለው ጥፋት ነው፡፡ በቅርቡ ኦሕዴድ በቄሮው ሽመልስ በኩል ያስተላለፈው ሰይጣናዊ መልእክት የጥፋት ዘመቻው አገዛዛዊ አቋም የመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ወያኔ በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር (በቤተ ክህነቱ፣ በአድባራትና ገዳማት) ውስጥ ገብቶ የራሱን ካድሬዎች ከመሙላት ጀምሮ ሀብትና ቅርሷን መዝረፍና ማውደሙ፤ ተረኞቹ ኦሕዴዳውያን እና እነሱን ተገን ያደረጉ ጽንፈኛ ኃይሎች ደግሞ ጥፋቱን እጥፍ ድርብ አድርገውት ምእመናንና ካህናት ላይ ጄኖሳይድ በመፈጸም፣ አድባራትና ገዳማትን በማቃጠል፣ ቤተክርስቲያኒቷን ለሁለት ለመክፈል ሙከራ በማድረግ እየፈጸሙ ያሉት ደባ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ጥቂት የማይባሉ ሆዳቸውን አምላካቸው ያደረጉ፣ በሥነምግባር የዘቀጡና ለአጥፊዎቹ ተባባሪ የሆኑ ‹አገልጋዮች› መኖራቸው የዐደባባይ ምሥጢር መሆኑ ችግሩን የተወሳሰበ አድርጎታል፡፡

በአንፃሩም በማውቀው በኢርተቤክ ምሳሌነት ተናገርኹ እንጂ በኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ተቋምም ዘንድ ብንሄድ ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውና በቀውስ ውስጥ የሚገኝ ተቋም መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡

4ኛ/ ሽምግልና፤ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ባህላዊ እሤቶች አንዱ የሽምግልና ተቋም ነው፡፡ ሕግ በማስከበር፣ ዕርቀ ሰላምን በማውረድ፣ በግለሰብ፣ ማኅበረሰብና ኅብረተሰብ ያለ የሰዎች ግንኙነቶች ሰላማዊና የሠመሩ እንዲሆኑ ከፍተኛ ተሰሚነትና ሚና ያለው ይህ ተቋም ዛሬ ላይ (አንዳንድ ቦታዎች ላይ ርዝራዡ ባይጠፋም) የተናቀና የቀለለ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች መጫወቻ በመሆኑም የነበረውን ክብር አጥቷል፡፡ በመንፈሳዊ ልልነት፣ ይህንንም ተከትሎ በደረሰብን ከፍተኛ የግብረገብና ሥነ ምግባር ዝቅጠት ከተመቱት ተቋማት አንዱ ሽምግልና በመሆኑ፣ እንኳን መደበኛ ተግባሩን ሊያከናውን ከአጥፊዎች ጋር ‹ተባባሪ› የሆነበትን ጥቂት የማይባሉ አጋጣሚዎችን ለመታዘብ በቅተናል፡፡

ባጠቃላይ ከቤተሰብ ጀምሮ ያሉን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማት የመከኑ (dysfunctional) ሆነዋል፡፡

5ኛ/ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገው ትዕግሥት እና ከዚህ የባሰ አታምጣ የስንፍና አነጋገር

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሃይማኖተኛ (የአንድ ዓይነት እምነት ተከታይ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሃይማኖተኛ ሁሉ መንፈሳዊ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት እረኛው ከመንጋው ተካክሎ በመበደል መንፈሳዊነት በጽሑፍ እንጂ በተግባር የማይታወቅ ቃል እየሆነ መጥቷል፡፡ መልካም ጠባይ ለመያዝ፣ በጎ ለመሥራት ግን የእምነት እርሾው ያለው ይመስለኛል፡፡ ይህ የእምነት ጠባዩ ጨቋኞችን ትዕግሥት በሚያስጨርስ ሁናቴ እንዲታገሥ አድርጎታል፡፡ አንድም ላገሩ ህልውናና አንድነት ባለው ስሱነት እና ወደ በቀልና ኃይል ቢኬድ የሚደርሰውን ጥፋት በማሰብ በደልን እንዲታገሥ አድርጎታል፡፡ አንድም አገዛዞች የሚያደርሱበትን ጭቆና እንደ ፈቃደ እግዚአብሔር በመቊጠር ለነፃነቱ፣ ለመብቱ፣ ባጠቃላይ ለኑሮው መውሰድ የሚገባውን ኃላፊነት በፈጣሪው ላይ ጥሎ በሞግዚት ለመተዳደር መምረጡ ግፍና ጭቆናን አዝሎ ለመዝለቁ አንድ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ በዚህም አግባብ ይመስለኛል ጋሼ መሥፍን ሕዝባችን እንደ ሕፃን ኃላፊነቱን በሞግዚት ላይ አኑሮ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠው በማለት የጻፉት፡፡ በተጨማሪም የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ከዚህ የባሰ አታምጣ እያለ አገዛዝ የጫነበትን ቀንበር የመቀበል አዝማሚያ ለመረዳት የሚያስቸግር የጋራ ጠባይ ይመስላል፡፡ ምናልባት ምሁሩ እንዳሉት የተቃውሞው ‹ሰላማዊ ሰልፉን› በዓፀደ ቤክ ተሰባስቦ ለፈጣሪው እያሰማ መቀጠሉን መርጦ ይሆን?

ሌላው በጎ እንዳልሆነ የጋራ ጠባያችን ሊታይ የሚችለው የነገሮችን አካሄድና አዝማሚያ በቅጡ ሳናጤን፣ በቂ መረጃና ማስረጃ ሳይኖረን ድምዳሜ ላይ መድረስ፣ ሃሜትና ሹክሹክታን ተቀብሎ ማናፈስ፣ ጊዜ ወስደን ግራና ቀኙን ሳናይና ሳናጣራ፣ ካለፈ የታሪክ ሂደትም በቂ ተሞክሮ ባለመውሰድ እንዲያው በስሜትና በችኮላ በትንሹም በትልቁም ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ ስናደርግ እንገኛለን፤ በተመሳሳይ መልኩ ነገሮች መስመር ሲስቱ ለማውገዝ፣ ለመኰነንና ‹በደንጊያ ለመውገር› የምንሄድበትም ርቀት ቅጥ ያጣ ይመስላል፡፡ ይህ ዓይነቱ በቀላሉ የመታለል፣ የመሞኘትና የመደናገር ሚዛናዊነት የጎደለው ስሜት ከድንቁርና የመነጨ ነው እንዳንል የተማረውና ማይሙን፣ ወጣቱን÷ ጎልማሳና አዛውንቱን የሚያስተባብር መሆኑ ያስደነግጣል፡፡ ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ እጃቸው ላይ የወደቀች ያልበሰሉ የጐሣ አለቆች አደናገርናቸው÷አሳመንናቸው፣ ለነሱ ተጨንቀን የምንሠራ መስለን አፈዘዝናቸው አደነገዝናቸው እያሉ የሚሣለቁብን፡፡

6ኛ/ አብዛኛው የኅብረተሰባችን ክፍል ከፊደል የማይተዋወቅ ማይም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን የተፈጥሮ አስተዋይነት ቢኖረውም ያልተማረ ኅብረተሰብ ለአገዛዞች መንሰራፋት ለም መሬት መሆኑ እሙን ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ባለፉት 30 ዓመታት የወያኔና ወራሾቹ ትውልድ ገዳይ የትምህርት ሥርዓት በቅጡ ሳይታሰብባቸው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በየመንደሩ በተከፈቱ ‹‹ዩኒቨርስቲዎች›› እና አንዳንድም ኃላፊነት የማይሰማቸው የግል ‹‹ኮሌጆች›› ውስጥ ገብተው የወጡ በርካታ ፊደል የቈጠሩ ‹‹ማይማንን›› አፍርቷል፡፡ ውጤቱም ለአገዛዝ የሚመችና ርስ በርሱ በጐሣ ተቧድኖ የሚናረት ወጣት አስገኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከደረጃ በወረደ ትምህርትና መመዘኛ የትምህርት ማስረጃ ምስክር ወረቀት በመስጠት ገንዘብ ከሚያመርቱ ተቋማት (diploma mills) እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ይዘናል የሚሉ ቀፎ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በማዕርጋችን ካልጠራችሁን እያሉ አቧራ የሚያስነሱበትም ይኸው ዘመን ነው፡፡ ማፈሪያነታችንን ወደ ጥግ ልውሰደውና ባሕር ማዶ ጭምር ሄደው የተለያዩ የትምህርት ማዕርጋት ይዘው (አንዳንዶችም በውጭ ዩኒቨርስቲዎች ጭምር እናስተምራለን የሚሉ) አገር የሚያምሱ ሕዝብ የሚያተራምሱ ከዕውቀትና ከእውነት የተጣሉ ሐሳውያን ምሁራን እንደ ዕንጉዳይ የፈሉትም በዚሁ ዘመን መሆኑ ከአገዛዝ የመላቀቂያ ጊዜአችንን አራዝሞታል፡፡ 

7ኛ/ ምሁራን፤ የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያችን አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋ ባገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም ልካ በልዩ ልዩ የዕውቀት መስክ ያስተማረቻቸው ወገኖቻችን ቊጥር ጥቂት አይደለም፡፡ አለመታደል ሆኖ እነዚህ ወገኖቻችን አገራቸው ፊደል በቈጠሩ ደናቁርት እየታመሰች ባለችበት ጊዜ በአራቱ የዓለም ማዕዝናት ተበትነው ለባዕዳን እንደ ሻማ እየቀለጡ ይገኛሉ፡፡ ብርሃን ዕውቀታቸውና ጥበባቸው በጨለማ ድንቁርናና በሞት ሲዖል በተመሰለ የኑሮ ዐዘቅት ውስጥ የሚገኝ ሕዝባቸውን ሊታደግ አልቻለም፡፡ ዐደባባይ ወጥተውም ሆነ ሳይወጡ አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ በአገዛዞች የሰፈነውን የግፍና ጭቆና ሥርዓት ሲታገሉ፣ ሕዝባቸውም ከድህነትና ድንቁርና እንዲወጣ የበኩላቸውን ሲያበረክቱ የነበሩና እያበረከቱም ያሉ ጥቂት ምሁራን መኖራቸው ርግጥ ነው፡፡ ባንፃሩም የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ሆነው ከመጣው አገዛዝ ጋር ባድርባይነት በመቆም የሕዝባቸውን ሰቈቃ የሚያራዝሙ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ እነዚህም በያዙት የአካዳሚ ምስክርነት ብቻ ምሁራን ይባሉ እንደሆነ አላውቅም፡፡ 

ታዲያ አገርና ወገን ከመቼውም ጊዜ በተለየ በምትፈልጋቸው በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ምሁራን ባገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙት የት ደረሱ? የተለያዩ ግምቶችን ማስቀመጥ ቢቻልም ስለተወሰኑቱ (በተለይም አረጋውያኑ) ግን አንድ ነገር መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይኸውም እነሱ የኖሩበት ዘመንና ኅብረተሰብ እንዲሁም ቀደምቶቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዕውቀትና ለእውነት ዋጋ የሚሰጡ፣ አነጋገራቸው በፈሊጥና በጨውነት የለዘበ፣ ለማዳመጥ የሚፈጥኑ ለመናገር የሚዘገዩ፣ በተቃራኒ ሆኖ ለሚሞግታቸው ተገቢውን ክብር የሚሰጡ ወዘተ.  በመሆናቸው፤ ባንድ ወገን ከአገዛዙ ባለሟሎችም ሆነ በሚቈጣጠሯቸው የመንግሥትና የግል ብዙኃን መገናዎች፣ ባለንበት ጊዜ ደግሞ በክፍያ በሚያሰማሯቸው የፀጥታ ክፍላቸው ቅጥያዎች አማካይነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍ ብዬ በጠቀስኩትና እንደ አገር በደረሰብን ግብረገባዊና ሥነ ምግባራዊ መራቆት ምክንያት በትውልዱ የሚታየው የዕውቀትና ጥበብ ባዶነት እንዲሁም ለእውነት ግዴለሽነት በጐሣ ፖለቲካው የተዘራው ጥላቻ ተጨምሮበት በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚደረጉ አብዛኛዎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚካሄዱ ንግግሮች፣ ውይይቶች፣ ክርክሮች በብልግናና ዘለፋ የተሞሉ መሆናቸው ያራቃቸው ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት አገርና ወገንን ሊታደግ የሚችለው ምክራቸውም ሆነ ሊያደርጉት የሚችሉት አስተዋጽኦ በአገዛዙም ሆነ ዙሪያውን ባጀቡት ዘረኞች ዘንድ በበጎ የሚታይ አይመስልም፡፡ ቀዳሚ ትኩረቱ ምን ቁም ነገር ተናገሩ ሳይሆን፣ እነማን ናቸው የተናገሩት? ነገዳቸው ከየት ነው? የሚለው ሆኗል ፡፡ ይሁን እንጂ አገርን ለማዳን  ሲባል የሚከፈል መሥዋዕትነት በመሆኑ ሳይዘገይና የማይጠቅም ጸጸት ውስጥ ከመግባት አስቀድሞ ለሚወዷት አገራቸውና ላስተማራቸው ደሀ ወገናቸው አሁን ሊደርሱለት ይገባል የሚል ወንድማዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

8ኛ/ ከፊሉ በንቅዘትም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ባንፃራዊነት የተሻለ ገቢ ያለው ነጋዴው ወይም ፊደል የቈጠረው የኅብረተሰብ ክፍል፣ ከምሁር ተብዬው የተወሰነው አሁን ያለበትን/የሚገኝበትን ሁናቴ እንደ ‹‹ተደላደለ ጥጋት›› (“comfort zone”) በመቊጠር ይኸው ‹‹ምቾት›› እንዳይነካበት በማሰብ ከሕዝብ ጋር ለትግል ከመነሳት ይልቅ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት እያለ ነባሩ ሁናቴ (status quo) ተጠብቆ እንዲቀጥል ይፈልጋል፡፡ እውነቱን ለመናገር ‹‹ነባሩ ሁናቴ›› የምንለው ባንፃራዊነት ከትናንት ያልተሻለው ዛሬ ሳይሆን ይቀራል?

9ኛ/ የፖለቲካ ባህላችን እንጭጭነት፤ ፖለቲካን አገርና ሕዝብን ወደ ተሻለ የሥልጣኔና ዕድገት ደረጃ ማሸጋገሪያና ማገልገያ አንድ ቊልፍ መሣሪያ አድርጎ ከማየት ይልቅ ለሥልጣን መወጣጫና የግል ወይም የቡድን ጥቅም ማግኛ አቋራጭ መንገድ ወይም መተዳደሪያ አድርጎ የመመልከቱ አባዜ ሥር የሰደደ መሆኑ ባንድ ወገን፤ በሌላ በኩል ከ60ዎቹ ጀምሮ ሲራመድ የቈየው የጥላቻ፣ የሸፍጥ፣ የመጠላለፍና ያለመተማመን እንዲሁም የተዛባ የታሪክ አረዳድ የሠለጠነበት ፖለቲካ በመሆኑ ሕዝብን በአንድ ዓላማ ዙሪያ አስተባብሮ ከአገዛዝ ሥርዓት መንጥቆ የሚያወጣ ሊሆን አልቻለም፡፡ 

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካን በቅንንነት ለማራመድ የማይቻል ተግባር እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ይመስላል፡፡ ሰሞኑን በእብሪት፣ በማንአለብኝነትና በእንጭጭነት ፖለቲካ ‹ቁማር› ነው ሲል የኦሮሞው ግዛት የጐሣ ም/አለቃ ባልታረመ አንደበት የተናገረው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል እንደ እስክንድር ዓይነቱ የሞራል ከፍታ ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ ባገዛዙና የጐሣ ፖለቲከኞች ቁም ስቅሉን ከማየቱ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት እንሠራለን በሚሉ የፖለቲካ ማኅበራት ጭምር በበጎ ዓይን የማይታየው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ስም የተሰባሰቡትና ቊጥራቸው ከመቶ በላይ እንደሆነ የሚነገርላቸው (በጣት ከሚቈጠሩቱ በስተቀር) ፣ ባይወክሉትም እንወክለዋለን ብለው በሚናገሩለት ማኅበረሰብ ስር ተወሽቀው የሥልጣን ፍርፋሪ የሚጠባበቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይሆኑ የጐሣ ማኅበራት ናቸው፡፡ አገሪቱን በጉልበት ለሚመራው ኦሕዴድ አጃቢና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ገጽታ ለመስጠት የተሰባሰቡ ኃይሎች ናቸው፡፡ መሠረታቸው ጐሣ በመሆኑ ግጭት ለመቀስቀስ ባያንሱም ሕዝብን በአንድ ዓላማ ሥር አስተባብረው ቁም ነገር ሊሠሩ አይችሉም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ባንፃሩም መሠረታችን ዜግነት ነው የሚሉት ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶችም አንድ ሁለት ብለን ከምንጠራቸው በቀር የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ቁመና የላቸውም፡፡ ውስጣዊ አንድነትና ዲስፕሊናቸው የላላ በመሆኑ፣ አንዳንዶቹም በቂ የመራጮች ሕዝባዊ መሠረት መፍጠር ባለመቻላቸው ዓላማቸውን አቀናጅተው በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አቋም ላይ የሚገኙ አይመስሉም፡፡ በተጨማሪም አገዛዙን የሚመራው የጐሣ ‹ፓርቲ› ከወያኔ ኢሕአዴግ በጸጋ በተቀበለው የተንኮልና መሠሪነት ውርስ እውነተኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲችል ለመበታተን ይህም ካልተሳካ ለማዳከም ወደኋላ እንደማይል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም የኦነጋዊው ኦሕዴድ ‹ጥንካሬ› የሃሳብ፣ የዓላማ፣ የፕሮግራምና የርዕይ ሳይሆን ቀድሞ ወያኔ ከማዕከል እስከ ገበሬ ማኅበር የዘረጋለት መዋቅር፣ በሌብነት፣ ልዩ ልዩ ወንጀሎችና በጥቅማ ጥቅም የሰበሰባቸው ካድሬና አባላት፣ ከመንግሥት መዋቅር ሳይለይ ለ‹ፓርቲ› ተልእኮ ማስፈጸሚያ የሚጠቀምባቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት፣ መንግሥታዊ ብዙኃን መገናኛዎች፣ የጸጥታ÷ ፖሊስ፣ ወታደራዊና ልዩ ኃይል እንዲሁም በአባላቱ አማካይነት የኢኮኖሚ አውታሮችንና ቢሮክራሲውን በዚህም ሥር ያሉ ኤምባሲዎችን ጭምር መቈጣጠሩ ነው፡፡ (የሕዝብንና የመንግሥትን ሀብት ለድርጅታዊ ዓላማ መጠቀምን ነው ንቅዘታዊ ጥንካሬ ያልሁት፡፡) 

ስለሆነም ይህ ንቅዘትን መሠረት ያደረገ ‹ጥንካሬ› ቀደም ብለን ከጠቀስናቸው ድክመቶች ጋር እውነተኛ ተቃዋሚዎች ሕዝብን ለአንድ ዓላማ አሰልፈው የጭቆና ሥርዓትን/አገዛዝን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለው በምትኩ ለመንግሥተ ሕዝብ መሠረተ የሚሆን መደላድል ለመትከል የሚያደርጉትን ጉዞ እጅግ ፈታኝ ያደረገው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አስቀድመው ስትራቴጂያዊ ትብብር በማድረግ ሕዝብን ማደራጀት ከቻሉ በንቅዘት ላይ የተመሠረተውን የአገዛዙን ተግዳሮት አንድ ባንድ መናድ ይቻላል፡፡ 

የመፍትሄ ሃሳብ፤

ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበ ለመጣው አገራዊ ችግር አንድ ወጥና ያለቀለት መፍትሄ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ የአገራዊ ችግሮቻችን ማጠንጠኛ የሚባለውን ዋናውን ምክንያት ወይም ባህርይ በመለየት (diagnose በማድረግ) ረገድ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳው ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በሕግና በመዋቅር የተተከለው የጐሣ ፖለቲካ/የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ገዳይ ደዌ ነው፡፡ ለዚህ የሚሰጠው መፍትሄ ለበሽታዎቻችን ሁሉ ፍቱን ፈውስ ነው የሚል አመለካከት ባይኖረኝም የቀሩትን ደረጃ በደረጃ አክሞ ለማዳን ፋታ እንደሚደሚሰጠን እና መልካም ጅምር እንደሚሆን ግን ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ 

የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና ደኅንነት፣ የጋራ ዕጣ ፈንታ ያለን የአንድ አገር ሕዝብነት፣ በውስጧ የሚኖሩ የተለያዩ ነገዶችና ጐሣዎች እኩልነት፣ የሕግ የበላይነትን፣ የጋራ ኑሮ መሻሻልና ዕድገትን አስቀድሞ ለሚነሳ (ከዚህ ውጭ ሌላ ድብቅ አጀንዳ/ፍላጎት የሌለው ካልሆነ በቀር) ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ቡድንም ሆነ ማኅበረሰብ ገዳይ ደዌውን ለማዳን የሚያቅተን አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የደረደርኳቸው ታሳቢዎች በሙሉ በጐሣው ሥርዓት ጥያቄ ውስጥ ገብተው በሕውሓትም ሆነ በኦሕዴድ በሚመራው ኢሕአዴግ ገዢዎችና ካድሬዎቻቸው አማካይነት የተወሰነው የኅብረተሰባችን ክፍል ጠርዛዊ (እንደ ዘመኑ አባባል ዋልታ የረገጡ) አመለካከቶች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ ስለሆነም መፍትሄው ፖለቲካን ከሕግ አጣምሮ የሚይዝ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ 

በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ በሆነው፣ ገዢው ‹‹ፓርቲ›› ኦሕዴድ (ብልጽግና) ከ7 ወራት በፊት በድብቅ በጠባብ መድረክ በሽመልስና በጓዶቹ በኩል ያስተላለፈውና ተግባራዊ ሲያደርግ የቈየው የድርጅቱን ዓላማ፣ ፍላጎትና አቋም እንደተረዳነው አገዛዙ በፖለቲካዊውም ሆነ በሕጋዊው መፍትሄ ለመነጋገር በጎ ፈቃድ ያሳያል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጠ/ሚሩም በባሌው ጉብኝት ወቅት ‹ብልጽግና ፓርቲ› (በእውነተኛ ስሙ ኦሕዴድ) የኦሮሞ ነው ብሎ በግልጽ ነግሮናል፡፡ የሽመልስ ንግግር የዚያ ቅጥያ ነው፡፡ ስለሆንም የድርጅቱ አቋም ነው፡፡ የድርጅቱ አቋም ከሆነ ደግሞ ይህ ያቀርብሁት የፖለቲካ መፍትሄ በትግል እንጂ በዐቢይና ጓዶቹ መልካም ፈቃድ እውን የሚሆን አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በ16ኛው ክ/ዘመን የኦሮሞ ወረራ መንፈስ ኢትዮጵያን በራሳቸው መልክና አምሳል ጠፍጥፈው በመሥራት ለይ መሆናቸውን እንዲህ ሲሉ አርድተውናልና፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን እኛ እንደምንፈልጋት አድርገን እንፈጥራታለን፤ እየፈጠርናትም ነው››፡፡

ይሁን እንጂ በውድም ሆነ በግድ (በሕዝብ ጫና) አገዛዙን ወደ ጠረጴዛ እንዲመጣ ጥረት (engage) ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

ፖለቲካዊው መፍትሄ የአገዛዙን የፖለቲካ መልካም ፈቃድ የሚጠይቅ ሆኖ ብዙዎቻችን (ተራ ዜጎችም ሆንን አንዳንድ የማኅበረሰብ/ሲቪክ/ ተቋማት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት) ደጋግመን እንዳቀረብነው ሁሉንም የኅብረተሰባችንን ክፍሎች የሚያሳትፍ ብሔራዊ መግባባት የምንለው አገራዊ ጉባኤ ነው፡፡ ይህም ባለያዩን አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ በውይይት መግባባትን፤ የሽግግር ጊዜ ፍትሕንና ዕርቀ ሰላምን የሚያካትት ይሆናል፡፡ ለዚህ አገርን የማዳን ጥሪ የአገዛዙ መልካም ፈቃድ ካልተገኘ በመፍትሄአችን ታሳቢ ባደረግናቸው ቁም ነገሮች የሚስማማው የኅብረተሰባችን ክፍል በሙሉ ባሉን የሲቪክ ተቋማት እና ዜግነትን መሠረት ባደረጉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት አደራጅነት ሕዝብን ሁለንተናዊ ለሆነ ሰላማዊ ትግል አደራጅቶ ማንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡ 

ሌላው ሕጋዊ መፍትሄ ያልኩት የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሙሉ በሙሉ ተቀድዶ እንዲጣልና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ አዲስ ሕገ መንግሥት መጻፍን ይመለከታል፡፡ አገዛዙ አገርንም ሆነ ራሱን ማዳን ከፈለገ ለዚህም የፖለቲካ መልካም ፈቃድ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ እላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ህልውና ጥያቄ በመሆኑ የተደራጀ ሰላማዊ የሕዝብ ትግል ከማድረግ ውጭ ምርጫ የለም፡፡ የማስመሰያውን ‹ሕገ መንግሥት› በሚመለከት በቅርቡ አንድ ምሁር በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ አንድ ወጥ አቋም አለመኖሩን ወይም በማሻሻልና በመቀየር መካከል የተምታታ አመለካከት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ በቅድሚያ ሕገ መንግሥት ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሰነድ መሆኑን በጥቅሉ በማስታወስ፣ እንደኔ አረዳድ ሦስት ምክንያቶች ያሉት ይመስለኛል፡፡  1ኛ/ በሕግ ሙያ ያልሰለጠኑ ሰዎች (lay persons) ንግግር ሲሆን፤ 2ኛ/ ባለሙያም ሆኑ አልሆኑ ‹ሰነዱ› የሚያስፈልገው በተወሰኑ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ ማድረግ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ፤ እና 3ኛ/ ግለሰባዊ ወይም ድርጅታዊ አቋም የያዙ ሰዎች አመለካከት፤ እነዚህን ምክንያቶች በጥቂቱ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

የመጀመሪያውን አመለካከት የሚወክሉ ሰዎች ከሕግ ውጭ በሌላ መስክ ትምህርት የቀመሱ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ዋናው ፍላጎታቸው የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› አገራዊ ችግር መፍጠሩን ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ ተሻሽሎም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ማየትን ይፈልጋሉ፡፡ በሁለቱ ጽንሰ ሃሳቦች መካከል ያለውን ሙያዊ (technical) ልዩነት ግምት ውስጥ ሳያስገቡ እየቀያየሩ ይጠቀማሉ፡፡ ባጭሩ በጽንሰ ሃሳቦቹ አጠቃቀም ረገድ ወጥነት አይታይባቸውም፡፡

ሁለተኛውን አመለካከት የሚያራምዱት በጽንሰ ሃሳቦቹ አጠቃቀም ረገድ ግልጽና ወጥነት ያላቸው ሲሆን፣ ችግር ፈጥረዋል የሚባሉ ድንጋጌዎችን ብቻ በመለየት ማሻሻያ ማድረግ በቂ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች ናቸው፡፡

ባንፃሩም ሦስተኛውን አመለካከት የሚያንፀባርቁት ጽንሰ ሃሳቦቹን ቢረዱም ባይረዱም ፖለቲካዊ ውገና በመያዝ (በተለይም የአገዛዙን አለቃ በጭፍን በመደገፍ እና ‹እያስጠናን ነው› የሚለውን የአንድ ወቅት ንግግሩን ተከትለው ማሻሻልንና መቀየርን በተለዋዋጭነት ሲጠቀሙ ይታያል፡፡

የዚህ አስተያየት አቅራቢ ‹‹የማስመሰያ ሕገ መንግሥት›› (façade constitution) እንኳን ተብሎ ሊጠራ ብቁ ስላልሆነው ሰነድ በተለያዩ ጊዜያት ሃሳቡንና አቋሙን በጽሑፍ አካፍሏል፡፡ ፍላጎቱ ያለው የሚከተሉትን አገናኝ ድረ ገጾች መመልከት ይችላል፡፡

(https://www.ethioreference.com/archives/7242;http://www.zehabesha.com/amharic/archives/89902;https://www.ethioreference.com/archives/16899);https://www.ethioreference.com/archives/18158)

ይህ የወያኔ ‹ሰነድ› የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ሊጣል የሚገባው ስለመሆኑ በተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የቀረቡ ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው (https://youtu.be/McPHNsYsZE4; https://youtu.be/yPnhbWW-Uc0; https://youtu.be/QOKeBEtd-r4)፣ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

ሀ/ ሕገ መንግሥትን መጻፍ/ማርቀቅ፣ በሥራ ላይ እንዲውል ፈቃድን/ስምምነትን መግለጽ፣ ማፅደቅ የሕዝብ ሉዐላዊነት መገለጫ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥትን የመጻፍ ሂደት ከሌሎች ተራ ሕጎች አወጣጥ ሥርዓት በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ በተለይም በማፅደቁ ሥርዓት የሕዝብን ቀጥተኛ ውሳኔ የሚጠይቅ ሰነድ ነው፡፡ በዚህረ ረገድ ወያኔና ኦነግ ያዘጋጁት ‹ሰነድ› የግላቸውና እነሱ ጠፍጥፈው የሠሯቸው የጐሣ ቡድኖች ፕሮግራም እንጂ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዐላዊነት ስላልተገለጸበት ሙሉ ለሙሉ መቀየር ይኖርበታል፡፡ 

ለ/ ሥልጣን ባለው የሕግ አውጪ አካል የሚወጡ ሕጎች ሁለት ዓይነት ውስጣዊ ገጽታ አላቸው፡፡ እነዚህም በጽሑፍ (በቃላት) የተገለጸው ሕግ/ንባቡ (letter of the law) እና ሕጉ የወጣበትን ዓላማና ፍላጎት የሚያሳየው የሕጉ መንፈስ (spirit of the law) ናቸው፡፡ የሕጉ መንፈስ በንባቡ ላይ ያለውን ማኅበራዊና ሞራላዊ ትርጕም አጠቃላይ ስምምነት/ፈቃድ ያሳያል፡፡

እነዚህ ሁለት ገጽታዎች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ከሕገ መንግሥት ጀምሮ በመጨረሻው ዕርከን እስከሚገኘው ሕግ /መመሪያ/ ይፋ በሚሆኑበት በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው የሚወጡትን እና የሕግ ሥርዓታችን መገለጫ የሆኑ ዋና ዋና መስኮችን /የፍትሐብሔር፣ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የእነዚህ ሥነ-ሥርዓቶች፤የንግድ፣ የባሕር/ የሚገዙ ሕጎች ሥርዓትን በያዘና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተደራጅተውና በመጽሐፍ/መድበል ተዘጋጅተው /Codified ሆነው/ የሚገኙትን ይመለከታል፡፡  

ለሕግ ተራ የሆነው ሰው ንባቡን/ቃሉን ብቻ በማየት የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ስላካተተ በጎ/ጥሩ ገጽታዎች እንዳሉት በመግለጽ ትኩረቱን የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ማሻሻል ላይ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሕግ የሚተረጐመውና ሥራ ላይ የሚውለው ሕጉን ያወጣው አካል ሰነዱ ባጠቃላይና እያንዳንዱ ድንጋጌ በተናጥል የተቀረፀበትን ዓላማና ፍላጎት (legislative intent) መሠረት አድርጎ ነው፡፡ የሕግን መንፈስ በሕገ መንግሥት ዓውድ ስናየው በበላይ ሕጉ የሚተዳደረውን አገርና ሕዝብ (ነገዶችና ጐሣዎች) የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ፖለቲካ፣ ሥነ ልቦና ወዘተ ይመለከታል፡፡ በነዚህ የጋራ በሚባሉት ታሳቢዎች ላይ ስምምነት ከሌለ በሠለጠነ ሕዝብ ዘንድ የሚደረገው በጥናትና ምርምር ላይ ተመሥርቶ በሚካሄድ አገራዊ ጉባኤ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ነው፡፡ ለዚህም ነው በፖለቲካው መፍትሄ ረገድ ብሔራዊ መግባባትን አጽንዖት ሰጥቼ ያቀረብሁት፡፡

ከወያኔ ‹ሰነድ› በስተጀርባ ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች (ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ግምባሮች በተለይም ሕወሓትና ኦነግ) በኦፊሴላዊ መግለጫቸው (manifesto) የተመለከቱት ትርክቶች፣ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ታሪክ ያላቸው አረዳድ በዚህ 30 ዓመታት በጽሑፍና በተግባር ያየንው ነው፡፡ በተግባርም ‹ሰነዱ› አገር መበተኛ ተደርጎ መሠራቱን የወያኔውን ትተን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ላስተዋለ ኢትዮጵያዊ በጐሣ ፖለቲካውና ‹ሰነዱ› በፈጠረው ‹ክልል› የሚባል ኢትዮጵያውያንን ባገራቸው ባይተዋር ባደረገ መዋቅር 9 ሀገር-አከል ግዛቶች መፈጠራቸውና ይህንኑ ‹ሰነድ› መሠረት አድርገው በርካታ በደቡቡ የአገራችን ክፍል የሚገኙ ጐሣዎች ጥያቄአቸውን አቅርበው አገዛዙ (የራሱን ቅድመ-ሁኔታዎች እያስቀመጠ) ቊጥራቸውን ከፍ ለማድረግና ብተናውን ለማቀላጠፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ‹ሕገ መንግሥት› ብለው በኢትዮጵያውያን ላይ የጫኑትን ሰነድ መንፈስ ከነፃ አውጪ ድርጅቶቹ መግለጫዎች፣ አመራሮቻቸው በተለያየ ጊዜ ካደረጉት ንግግሮችና ምድር ላይ እየተደረገ ካለው እውነታ መገንዘብ የሚችል ይመስለኛል፡፡ የብዙ ዜጎች ሕይወት በጐሣ ማንነታቸውና በሚከተሉት እምነት ምክንያት እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁናቴ ጠፍቷል፤ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል፤ ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት ወድሟል፤ ከቤት ንብረታቸው በገፍ ተፈናቅለው ባገር አልባ ስሜት ባዝነውና ባክነው ቀርተዋል፡፡ ጥፋቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህንን አገራዊ ምስቅልቅል ያስከተለ ‹ሰነድ› በከፊል እናሻሽለው የሚለው አነጋገር በነዚህ ዜጎች የተፈጸመውን ግፍ አለማሰብ ነው፡፡

ሐ/ ‹ሰነዱ› በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት (legitimacy) ፤ አንድ ሕገ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ስለሚኖረው ተቀባይነት የሕገ መንግሥት ሕግ ሊቃውንት በርካታ ጥራዞች የጻፉበት እና  የተለያዩ የአስተሳሰብ አድባራት (schools of thought) የሚያራምዷቸው አመለካከቶች የሚንፀባረቁበት ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካ ፍልስምናም ረገድ (የመንግሥት፣ የአንድ ፖለቲካ ሥርዓት ሕዝባዊ ተቀባይነት) የታወቀና መሠረት ያለው ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ ከፍ ብዬ በጠቆምኋቸው አድራሻዎች ስለ ሕገ መንግሥት ተቀባይነት ያነሳኋቸው ቁም ነገሮችን መመልከቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ለዚህ አስተያየት ዓላማ ግን ጥቂት ነጥቦችን ባጭሩ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ 

የሕግ መንግሥት ተቀባይነት ከሕግ፣ ከማኅበራዊ እና ከሞራል ዕይታ አንፃር ሊታይ ይችላል፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት ተቀባይነት ስናነሳ ሰነዱን ለመጻፍ ከሚደረገው ዝግጅት ሂደት/ሥነ ሥርዓት ጀምሮ ንድፉን፣ ቅርፁን እና ይዘቱን የሚመለከቱ ዐበይት ውሳኔዎችን ያካትታል፡፡ ሌላው ሕገ መንግሥት በእሤቶችና ፍልስምና መግለጫነት ሳይወሰን እነዚህን እሤቶች በተቋማት አሠራሮች ውስጥ ማካተትንና ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ለሰነዱ ተቀባይነትም እንደ አንድ መለኪያ ይታያል፡፡ 

ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቅ አንስቶ የአገር የበላይ ሕግ ሆኖ እስከሚታወጅበት ሂደት በሕግ የተቀመጡ ሥነ ሥርዓቶችን ማለፉ ሕጋዊ ተቀባይነቱ (legal legitimacy) የሚታይበት ገጽታ ሲሆን፣ በሌላ በኩል እንደ ኢትዮጵያ ያለች የብዙ ነገዶች/ጐሣዎች ጥንታዊት አገር ባላት የዘመናት የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ፣ አብሮነቱ በፈጠረለት የአንድ አገር ሕዝብነት የጋራ መገለጫ የሆኑ መልካም የእሤት ሥርአቶችን ፈጥሯል፤ በፀረ ቅኝ ግዛትና ፀረ ፋሺስታዊ ተጋድሎው የሚታወቅ የጋራ አኩሪና ገናና ታሪክ ባለቤት ነው፤ በእምነት÷በባህል÷ በልማድና በአእምሮ ጠባይዕ ባገኘው ዕውቀት ለሕግ ልዕልናና ለፍትሕ ያለውን ጥልቅ ግንዛቤና አክብሮት ‹በሕግ አምላክ› በሚል ረቂቅና ምጡቅ አስተሳሰብ የጋራ ሥነ ልቦና ያዳበረ ሕዝብ ነው፤ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ብቸኛውን የጽሑፍ ቋንቋ ቀርፆ ኢትዮጵያውያንን በጋራ የሚያግባባ ብሔራዊ ቋንቋ ባለቤት የሆነ ሕዝብ ነው፡፡ እነዚህ ለአብነት ያህል ያነሳናቸው የጋራ እሤቶችና ቅርሶች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኩራት ምንጭነት አልፈው ሊጠብቃቸውና ሊከባከባቸው የሚፈልጋቸው በገንዘብ የማይተመኑ ውድ ሀብቶቹ በመሆናቸው የአገራችን የበላይ ሕግ በሚሆነው ሰነድ ውስጥ እንዲካተቱ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ እንዲሆኑም ይፈልጋል፡፡ ማኅበራዊ ዕውቅናና ተቀባይነት (social legitimacy) የምንለው ይህንን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተወሰኑ የኅብረተሰባችን ክፍሎች ዘንድ መግባባት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ የፖለቲካው መፍትሄ አስፈላጊነት እዚህም ጋር ጎልቶ ይታያል፡፡

በሦስተኛነት የምናየው የሞራል ተቀባይነት (moral legitimacy) የምንለው ሲሆን፣ይህም ሕገ መንግሥት ባቋቋማቸው ተቋማት የሚሰጡ ፍርዶችም ሆኑ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ፍትሕን የሚያሰፍኑና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸው፤ የተቋሞቹ አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ እንዲሁም ከመንግሥትና ባለሥልጣናቱ ለሕዝብ የሚሰጡ መረጃዎች እውነትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው በአብዛኛው ሕዝብ ሕሊና ተዳኝቶ የሚገኘውን ውጤት ይመለከታል፡፡

ከነዚህ ሦስት መመዘኛዎች አኳያ የወያኔ ‹ሰነድ› በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በሚመለከት የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ድምጽ በየጊዜው ተካሂዶ የተያዘ መረጃ ባይኖርም (ይህንን በሙያ ብቃትና በገለልተኝነት የሚያካሂዱ ተቋማት ስለመኖራቸው መረጃ የለኝም) ባለፉት 30 ዓመታት ምድር ላይ ካለው እውነታ ተነሥተን እና ከዛሬ 2 ዓመት በፊት ወያኔን ከሥልጣን ያስወገደውን ሕዝባዊ ዓመፃ ስናስታውስ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያልተቀበለው ‹ሰነድ› ሰለመሆኑ መናገር ይቻላል፡፡ የሩቁን ትተን አሁን አገዛዙ በተቈጣጠረው ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ላይ እየተፈጸመ ያለው ‹የዳኝነት ሂደት› የወያኔን አገዛዝ የደገመ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የከፋ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም ሁሉ እየታዘበ ነው፡፡ በፌዝ ፍርድ ቤት ፍትሕ ማፌዣ ስትሆን፣ በሕዝብ አስተያየት ዐደባባይ የሚሰጥ ፍርድ በመደበኛ ፍርድ ቤት ከሚሰጥ ዳኝነት የበለጠ ተሰሚነት ይኖረዋል፡፡ እውን ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያችን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነበር?

ለማጠቃለል አሁን ኦሕዴድ በሚመራው አገዛዝ የሚታየው አዝማሚያ የፖለቲካ ምሕዳሩ እየጠበበ ለሰላማዊ ትግልም መላወሻ የማይሰጥ እየሆነ መጥቷል፡፡ ንጹሐንና ሰላማዊ ዜጎች በውኃ ቀጠነ ምክንያት እየታሰሩ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሕዝብን ጸጥታን ያስከብራል ተብሎ በሚታሰብ የፖሊስ ሠራዊት እና የአገር ዳር ድንበር እንዲያስከብር ተልእኮ በተሰጠው የአገር መከላከያ ኃይል ድብደባና እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ለአብነት በወላይታ የተፈጸመውን ያነሷል፡፡ ይህ መገፋት ባስቸኳይ ካልቆመ ወዴት ይወስደን ይሆን? የትኛውም መንግሥት ሆነ አገዛዝ በዝቅተኛ መጠን የሚጠበቀውን ሕዝባዊ ተቀባይነት ካላገኘ መጨረሻው ውድቀት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ጽሑፌን በሁለት ማሳሰቢያዎች ልቋጭ፤

1ኛ/ ባለፈው ሰኔ 23/2012 ዓ.ም. ባገራችን በተለይም ወያኔ ኦሮምያ ብሎ በሰየመው ግዛት እና በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በዘረኝነት የሰከሩ ሀገር-በቀል አሸባሪዎች በመንግሥት መዋቅር (በባለሥልጣናትና በመንግሥት ታጣቂ ኃይላት) ታግዘው፣ አስቀድመው ዐቅደውና በቂ ዝግጅት አድርገው ከሁለት መቶ አርባ በላይ በሚሆኑ ወገኖቻችን ላይ ዘር/ጐሣን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ እና አክራሪ ፖለቲካዊ እስልምናን ሽፋን አድርገው የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ምእመናን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ) ፈጽመዋል፡፡ የአገዛዙ መሪና ባለሥልጣናት እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው ጄኖሳይድ መፈጸሙን በማስተባበል ተጠምደዋል፡፡ ይህ ክህደታቸው የጄኖሳይዱ አካል መሆናቸውን ከሚያሳይ በቀር ሌላ ትርጕም የለውም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ያለምንም በደላቸው ንጹሐን በሆኑ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያና የቤት ንብረት መውደምና መፈናቀል ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን እየገዛሁ ነው ከሚል አገዛዝ የሚጠበቀው ዝቅተኛ ተግባርና ኃላፊነት (ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ቢኖር የዘር ፍጅቱን በቂ ዝግጅት በማድረግ ማስቀረት ወይም ጥፋቱን መቀነስ ይቻል ነበር) በግፍ ለተገደሉት ዜጎች ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጅ፤ እልቂቱ በተፈጸሙባቸው ቦታዎች በአካል ተገኝቶ በሕይወት የተረፉትን ማጽናናት፤ ለወደመ ቤትና ንብረታቸው ካሣ እንዲያገኙ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ያላደረገ ወይም ማድረግ የማይችል የአገዛዝ ሥርዓት፣ ‹የአገር መሪ› እና በሥሩ ያሉ ባለሥልጣናት ተጠያቂና ኃላፊ የሚሆኑለት ሌላ አገርና ሕዝብ አላቸው ማለት ነው? አሁንም አልረፈደምና የማይረሳውን ጉዳይ አዳዲስ አጀንዳዎች በመፍጠር ለማዘናጋት ከመሞከር ይልቅ ሰውን ባትፈሩና ባታፍሩም እግዚአብሔርን ፈርታችሁ ለወገኖቻችን ተገቢውን ድጋፍና ማጽናናት አድርጉ፡፡

2ኛ/ ምን ዓይነት የፖለቲካ ትርፍ እንደምታገኙበት ባይገባኝም ለጀዋርና መሰሎቹ በመናጆነት የታሠሩትንና የፌዝ ፍርድ ቤት መጫወቻ የሆኑትን ንጹሐን የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችን (እነ እስከንድርን፣ ይልቃልን፣ ልደቱን፣ አስቴርን፣ ቀለብን፣ ስንታየሁን እና ሌሎችን ንጹሐን) ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንድትፈቱ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህ በታች መውረድ ያስተዛዝባል፡፡

Filed in: Amharic