>

በሀገራችን በአውሬያዊ ድርጊቱ የሚኮራ ‘‘ሂትለራዊ’’ ትውልድ እንዴት ሊበቅል ቻለ?! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

በሀገራችን በአውሬያዊ ድርጊቱ የሚኮራ ‘‘ሂትለራዊ’’ ትውልድ እንዴት ሊበቅል ቻለ?!

 

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፤


ከአንድ ዓመት በፊት ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ የተባሉ ምሁር በተገኙበት ሕዝባዊ መድረክ ላይ በሀገራችን እየሆነ ባለው አረመኔያዊ/አውሬያዊ ድርጊት የተነሣ ልባቸው ክፉኛ አዝኖ፤ ‘‘አሁን ክፉ የተባለውን ድርጊት ሁሉ አድርገን ጨርሰናል፤ ምንም የቀረን የክፋት ዓይነት የለም፡፡ አሁን የቀረን ነገር ቢኖር ደግ ነገር ማድረግ ነው፡፡’’ ብለው ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ከዓመት በኋላ ሌላ የክፋት፣ የጭካኔን ጥግን በኢትዮጵያችን ምድር ለማየት በቅተናል፡፡

‘‘የካህናቱን ፊት አላፈሩም፣ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም፣ ለእናቶችና ለሕጻናቱም አልራሩም፤’’ እንዲል አይሁዳዊው ነቢይ፣ ኤርምያስ፡፡ (ሰቆቃው ኤርምያስ ፬፤፲፮)፡፡ በእናቱ ሆድ ላለ ፅንስ እንኳን የማያራሩ፤ ‘‘የነፍጠኛ ልጅማ በእኛ መሬት ላይ መወለድ የለበትም፤’’ በማለት ነፍሰ ጡር እናትን በባለቤቷና በልጆቿ ፊት ያለ አንዳንች ርኅራኄ በአረመኔያዊ መንገድ የገደሉ፣ ለሕጻናትና ለሽማግሌዎች የማይራሩ፣ ካህናትን የማያፍሩ ‘‘ሂትለራዊ ጭካኔን’’ የተለማመደ ዘረኛ ትውልድን በዘመናችን፣ በሀገራችን ላይ ለማየት በቅተናል፡፡

ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን በክፋት የሠለጠነ፣ ከሰብአዊነት የተፋታና ይህን አውሬያዊ ድርጊቱን እንደ ጀብዱ፣ እንደ ጀግንነት የሚያወድስ ‘‘ሂትለራዊ ትውልድ’’ በዚህች ኢትዮጵያ ምድር እንዴት ሊበቅል ቻለ?! በሚለው ጥያቄ ላይ እስቲ ጥቂት አብረን እንቆዝም፡፡ በአብሮነት ቁዘማችን ጋር በተያያዘ፣ አንድ በዓለማችን የተፈጸመ የናዚ/ሂትለራዊ የጭካኔ ድርጊትን ለዛሬው ጽሑፌ እንደ መንደርደሪያ እንዲሆነኝ መርጫለሁ፡፡

የናዚው ሂትለር በአፍሪካውያን ምርኮኛ ወታደሮች ላይ ካደረጋቸው ዘግናኝ ግፎች መካከል ይህ በአሰቃቂነቱ ይጠቀሳል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ጀርመናዊው ሂትለር በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከፈረንሳይ ጎን ሆነው ሲዋጉ የተማረኩ አፍሪካውያን የፈረንሳይ ወታደሮችን ለበርካታ ቀናት በወኅኒ አጉሮ ምንም ምግብ እንዳይሰጣቸው አደረገ፡፡ በአንድ እለትም በሂትለር ወታደራዊ ቀጭን ትእዛዝ እነዚህን በረሃብ አለንጋ የሚገረፉ አፍሪካውያን ምርኮኛ ወታደሮች ከታጎሩበት ቤት ወጥተው በወኅኒ ቤቱ ሜዳ ላይ ተሰብስበው እንዲቆሙ ተደረጉ፡፡

ከረሃብ የተነሳ መቆም ያቃታቸው ምርኮኞቹ ካሁን አሁን ለረሃባችን ማስታገሻ ዳቦ ሊሰጡን ነው ብለው ጠባቂ ወታደሮቹን በሕይወትና መካከል ሆነው በዓይናቸው ሲማጸኑ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሂትለር በረሃብ በደከሙት አፍሪካውያን ወታደሮች መካከል አንድ በግ እንዲለቀቅ አዘዘ፡፡ በረሃብ እየተሠቃዩ ያሉ አፍሪካውያን ወታደሮች ወደ መካከላቸው የገባው በግ ላይ በፍጥነት ተከመሩበት፡፡ ረሃብ ክፉኛ ያንገላታቸው ምርኮኞች ያለ የሌለ ጉልበታቸውን ተጠቅመው በጥርሳቸውና በእጃቸው እየዘነጣጠሉ ያን በግ ለመብላት መራኮት ጀመሩ፡፡

ይህን አሳዛኝ፣ አሰቃቂ የሆነ ትዕይንት የናዚ ወታደሮች ዘና ብለው በቪዲዮ እየቀረጹ ነበር፡፡ ወገን ረሃብ ክፉ ነው፡፡ በእኛ ሀገርም በዐጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፤ ‘‘ክፉ ቀን’’ እየተባለ በሚጠራው አስከፊው የረሃብ ዘመን የገዛ ልጇን የበላች አንዲት እናት ተከሳ በምኒልክ ችሎት ፊት ቆማ እንደነበረ ታሪካችን ያወሳል፡፡ ረሃብ ከሰብአዊነት መንደር ያወጣል፤ ሰው ከመሆን ክብርም ያፈልሳል፡፡ እናም ረሃብ ከሰብአዊነት ድንበር የገፋቸውን የአፍሪካውያኑን ምርኮኞች በመካከላቸው የተገኘውን በግ በቁሙ ዘነጣጥለው ለመብላት ሲያደርጉ የነበረውን መራኮት የሚያሳየውን ቪዲዮ ናዚዎች ለጀርመን ሕዝብ ለእይታ አበቁት፡፡

ክርስቲያኖችን ከተራቡ አውሬዎች፣ ከአንበሳና ከነብር ጋር እያታገለ በሮም ስታዲየም ሲዝናና ከነበረው ሮማዊው ቄሳር ኔሮ ጀምሮ የዘረኝነት ልክፍት የተጣባው ናዚ ሂትለር- ‘‘ጥቁር ሕዝብ/አፍሪካዊ የምድሪቱ ጥፋትና ጉስቁልና ናቸው፤’’ በሚል ስሑት፣ ዘረኛ እሳቤ ጥቁሮችን በረሃብ እያሠቃየ በእንዲህ ዓይነቱ አርመኔያዊ የጭካኔ ድርጊቱ ሲዝናና እንደነበር ታሪክ በአሳዛኝነቱ፣ በአሰቃቂነቱ መዝግቦታል፡፡   

ዛሬም በእናት ምድራችን ኢትዮጵያ ሂትለራዊ ዘረኝነት የተጋባባቸው ጎጠኞችና ጨካኞች በሰው ሥቃይ የሚዝናኑ፣ እኩይ ድርጊታቸውን እንደ ጀብዱና ጀግንነት የሚቆጥር ትውልድን እያየን ነው፡፡ በክፋትና በዓመፃ ሥራቸው ናዚዎችን ለማስናቅ ውድድር ላይ ያሉ የሚመስሉ ሰዎች በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለሙትን፣ የተመኙትን- የግፍ፣ የጭካኔ፣ አረመኔያዊ ድርጊት ያለ ምንም ከልካይ እየፈጸሙ ነው፡፡ ሰውን ዘቅዝቆ ከመግደል/ከመስቀል አንስቶ እንደ ሙሴ ዘመን የገዛ ወገናቸውን በድንጋይ ወግረው ገድለው- በግዳያቸው ፊት ፎቶ የሚነሱና ቪዲዮ የሚቀርጹ፤ በዚህ የክፋታቸው ጥግ፣ የሰብአዊነታቸው መንጠፍ ደስታቸውን የሚያጣጥሙ፣ ጀግንነታቸውን የሚያወድሱ አረመኔዎችን፣ ጨካኞችን በዘመናችን እየተመለከትን ነው፡፡

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ከዓመት በፊት ጠርዝ ላይ በሚለው መጽሐፉ እንዳለው፤ ‘‘ዛሬ ግለሰባዊ የሥነ-ምግባር ጉድለትን ተሻግረን፣ በማኅበረሰባዊ የሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ ጉዞ ከጀማመርን ውለን አድረናል፤ በሂደትም ወደ መቀመቁ እየወረድን ነው፡፡ በአደባባይ ሰዎች ሲቃጠሉና ሲሰቀሉ፣ እንደ አስደሳች ትርኢት ከብበን እንመለከታለን፡፡ በቡድን እናፈናቅላለን፣ እንዘርፋለን፡፡ አደባባይ የሚያቃጥሉትና የሚሰቅሉት የማኅበረሰባዊ ዝቅጠት ትያትራችን ተዋናዮች ብቻ ናቸው፡፡ ከየመድረኩ ጀርባ ሁላችንም ተሳታፊዎች ሆነናል፡፡ ይህን ግፍ በአደባባይ ከተመለከትነው ጀምሮ፣ ዜናውን ሰምተን በሰላም ተኝተን እስካደርነው ድረስ- ሁላችንም በሥነ-ምግባር ዘቅጠናል፡፡’’

በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥና አረመኔያዊ ድርጊት መካከል ደግሞ ሕዝብ ራሱን እንዳያይ የሚደልሉት ብዙ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡ ለሽልማት የሚያሞግሱ አዝማሪዎች፣ ለቁራሽ የሚያወድሱ ባለቅኔዎች፣ የአንተ ጎሣማ እያሉ ሥራን ሳይሆን ንቀትን የሚያስጠኑ ቤተ ዘመዶች፣ የተበደልህ ነህ፣ ደም መመለስ አለብህ የሚሉ ወገኖች ትውልድ ራሱን በማየት ካለበት ችግር እንዳይወጣ እንቅፋት እየኾኑ ነው፡፡

የሌለንን እንዳለን አድርገው የሚናገሩ ‘‘ነቢያት’’ ነን ባዮች፣ ጥፋት እየመጣ ሰላም ነው የሚሉ የአዎንታዊ ስብከት አደራጆች፣ ዛሬ ላይ ትላንትን እንድንኖር የሚያደርጉ ጠብ አውራሾች፣ ያልጨረሱትን ክፋት በልጆች ለመፈጸም የሚጥሩ ዕድሜ ያላስተማራቸው ምንዱባኖች ኢትዮጵያን ክፉኛ እየጎዷት ነው፡፡ እንደው ለመሆኑ አገር ተጎዳ ለማለት ያስቀምጥነው የሬሳ ኮታ ስንት ይሆን?! የምንቆጨው በስንት አንገት ይሆን?! ፍትሕን ለማስፈን የምንነሣው በስንት ሕፃናት መሰየፍ፣ በስንት ሴት እህቶቻችን መታገት ይሆን?! ኮታው ስላልታወቀ ጥፋት ቀጣይ እየሆነ፣ ጭካኔን እየለመድነውና እየተለማመድነው ነው፡፡

በመጨረሻም የሆነስ ሆነና ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔና አረመኔያዊነት እንደ ክብር ዘውድ የተቀዳጀ ትውልድ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተፈጠረ መጠየቅ የለብንም ትላላችሁ?! እነዚህን ታዳጊ ልጆችና ወጣቶች ለእንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ ያበቃቸውና በእናታቸው ማኅፀን ላሉ ለሕጻናት፣ ለእናቶች፣ ለአረጋውያንና ለሃይማኖት አባቶች እንጥፍጣፊ ርኅራኄ በውስጣቸው እንዳይኖር ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?

የሞቱትና የተገደሉት የእናንተ ብሔር/ጎሳ ብቻ አይደሉም፣ የተጠቁት እናንተ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ አይደሉም በሚሉ በሰው ሕይወት ላይ ቁማርን የሚቆምሩና- ክብር የሰው ሕይወትን በጎሳና በነገድ ለመመዘን፣ ለመመደብ የሚመዝኑ የመንግሥት ሹማምንቶቻችን የሥነ-ምግባር ዝቅጠትና የሞራል ወድቀት/ልሽቀት በቅጡ ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚህ የሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ ሆነን የምነገነባው ሊጸና፣ የምንተክለው ሊጸድቅ፣ የምንወልደው ሊባረክ አይችልም፡፡ እናም የዚህ ክፋት ምንጩን፣ የጭካኔውን ሥር ለማወቅ፣ አውቆም መፍትሔውን ለመጠቆም ሁላችንም- መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ተቋማቶቻችን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ፖለቲከኞቻችን፣ ማኅበረሰባችን… ወዘተ.  ቆም ብለን ማሰብ፣ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

 

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!

Filed in: Amharic