>

ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ (አሰፋ ሀይሉ)

የሚሽከረከሩ የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች!

( – ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ)
አሰፋ ሀይሉ

‹‹ፖሊሲያችንን እስካፈጸመ ድረስ ገበሬንም አምጥተን ትምህርት ሚኒስትር እናደርጋለን›› ሲል በመሃይማዊ ድፍረት ከተናገረው መለስ ዜናዊ – ወደ ሥልጣን በወጣ ማግሥት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሰብስቦ – ‹‹ማንም ሰው የትኛውንም ዓይነት ሹመት መወጣት ይችላል!›› ሲል በቴሌቪዥን እስከተደመጠው እስከ አብይ አህመድ ድረስ – ኢትዮጵያ በወጉ ብስለትንና አንጋፋ የሙያ ልምድን በተላበሱ ሰዎቿ እንዳትመራ አወላግዶ የሚያስኬዳት በፊት ለፊትና በድፍረት እየታወጀ የሚቀጥል ኃይለኛ ፀረ-ዕውቀት፣ ፀረ-ሙያ፣ ፀረ-ፕሮፌሽናሊዝም የመንግሥት ፖሊሲ አለ፡፡ በተቋማት ደረጃ ብዙ ነገራችን እንዳልነበር ሆኖ የወደመውም በዚህ ዓይነቱ ኢህአዴጋዊ የአላዋቂዎች ፍልስፍና ሳቢያ ነው፡፡
በመንግሥት አመራር ውስጥ ሙያዊ ህይወት ገደል መግባቱ የብዙ ሀገራዊ ውድቀታችን ምንጭ ነው፡፡ ዛሬ የአንድ ትልቅ ፕሮፌሽንን የሚጠይቅ ተቋምን መምራት ያለበት ሰው ቀርቶ – ሌላ የኢህአዴግ ዲግሪዎች የተለጣጠፈለት ለሙያው ባዕድ የሆነ ተላላፊ የፓርቲ አስፈጻሚ ወንበሩ ላይ በጊዜያዊነት ጉብ ይላል፡፡
ጉብ ብሎም ለዘለቄታው ቢቀጥል እኮ የሆነ በቆይታ ሊማርና ሊያዳብር የሚችለው ስትራቴጂክ ዕውቀትና ልምድ፣ ራዕይና ክህሎት እኮ ይኖራል መቼም ሰው እስከሆነ ድረስ፡፡ ይሄ ግን በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ አይታሰብም፡፡ ሥልጣን እንደ ጉልቻ ከአንዱ አላዋቂ ሰው ወደ ሌላው ሰው ያለማቋረጥ ይሽከረከራል፡፡ በዓለም ታሪክ እጅግ አሳፋሪ ሆኖ መገኘት ምንም መስሎ በማይሰማው በኢህአዴግ ዘመን ነው የህግ ሙያ የሌለውን ሰው – የፍትህ ሚኒስቴር አድርጎ ሾሞት ያየነው፡፡
የፕሮፌሽናሊዝም ሞት የሀገራችንን የመንግሥት ሥርዓት ክሽፈት አንዱ ማሳያው ነው፡፡ በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ሙያ እና የሙያዊ ዕውቀት አስፈላጊነት ገደል ገብቷል፡፡ በበረሃ ትግል (ጦርነት) ላይ ለበርካታ ዓመታት በመሠማራታቸው የተነሳ ከምንም ዓይነት የረባ ዘመናዊ ትምህርትም ሆነ ሙያዊ ዕውቀት ርቀው የቆዩት የህወኀት አባላትና መሪዎች የሀገሪቱን ሥልጣን ለመቆጣጠር የግድ ‹‹ሙያ›› እና ‹‹ሙያዊ ህይወት›› አላስፈላጊ አድርገው መቁጠርን እንደ መንግሥት መመሪያ አድርገው መተግበር ነበረባቸው፡፡ ያደረጉት እና እስካሁንም የቀጠለው ይሄው ነው፡፡
በአንድ መስክ አንቱታ ደረጃ ከደረሰ ሙያዊ ልህቀት አሊያም የዳበረ የዕውቀትና የሥራ ልምድ በሙያው ዘርፍ ከተላበሰ አንጋፋ ዜጋ ይልቅ – በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ – ከምንም ነገር በላይ የፓርቲው አባልነትና ጋሻጃግሬነት፣ ታማኝነትና አደግዳጊነት ትልቁ የሥልጣንና የመሪነት መስፈርት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት መንኮታኮት ሀ ብሎ የጀመረው በዚህ ዓይነቱ የክሽፈት እንድርድሮሽ ነው፡፡
የሀገራችንን ተቋማት ያውሸለሸላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ቦታ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን – ኢትዮጵያን የሚመራው መንግሥት የዕውቀት-ፀር እና የሙያ-ፀር ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ነው፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ትልልቅ ሀገራዊ ፋይዳዎችን ሊያበረክቱ ይችሉ የነበሩ ግዙፍ ሀገራዊ ተቋማት ተውሸልሽለው የቀሩት በየዘርፉ በሳል የህይወት ልምድና ዕውቀትን ባካበቱ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የሚመራ ተቋም እንዳይኖር በመደረጉ ነው፡፡
ይህ ከጥልቅ መሀይምነት አስተሳሰብ የመነጨ የጨዋ ድፍረት የተጀመረው በእርግጥ ዛሬ ላይ አይደለም፡፡ ሁሉን-አድራጊ-ፈጣሪ ለመሆን ይዳዳቸው በነበሩ በዘመነ ደርግ ወታደራዊ ባለሥልጣናትና የኢሠፓ ሹመኞች ጀምሮ ነው፡፡ ቢሆንም – ህወኀት-ኢህአዴግ ግን በአላዋቂዎች፣ እና እንደ ሲራራ ነጋዴ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚዘዋወሩ ዘዋሪ ባለሥልጣናቱ – ሀገርና ተቋማትን በባዕድ ዘዋሪ ሰዎች መምራትን – ከፍተኛው ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡
ይህን ረዥም ትንታኔና ጊዜ የሚፈጅ አብይ ርዕሰ ጉዳይ ለጊዜው ተወት አድርገን የዘመኑን ኢህአዴጋዊ የዘዋሪዎች ሥልጣን ለማየት የፓርቲው የሥልጣን አሞሮች – እንዴት እንደ ፌንጣ ወይ እንደ ጉሬዛ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የማይገናኝ ቦታ እየዘለሉ እንደሚኖሩ – ለማየት በዚህች ሁለት ዓመት ብቻ በሀገራችን ከተስተናገዱ ተሿሚዎች ቀበላሉ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ ሀገሪቱ የሥልጣን አሞሮች ከዚህ የተሻለ ማሳያ ማስረጃም የለም፡፡ ጥቂቶቹን ስመኞች እንያቸው፡፡
አዳነች አቤቤ፡- መጀመሪያ የጉምሩክ ባለሥልጣን ነበረች፣ ቀጥሎ ጠቅላይ አቃቤ ህግ (ማለትም የፍትህ ሚኒስትር) ሆነች፣ አሁን ደሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ፡፡ እግዚአብሔር ያሳየን እስቲ፡፡ ጉምሩክን ለመምራት ስለጉምሩኩ ዝርዝርና አጠቃላይ አሠራር ጥልቅ ግንዛቤው ያለው ሰው – ኬሪሩን (ማለትም ሙያዊ ህይወቱን) በዚያ ዘርፍ ያሰማራ ሰው አያስፈልግም ወይ ለመሆኑ? ጉምሩክን ባለሥልጣን በወጉ ሳይመራስ እንዴት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር? ፍትህን በሚገባ ሳያስከብሩስ ደሞ እሱን እርግፍ አድርጎ ወደ ከንቲባነት? ከኢኮኖሚ ወደ ህግ፣ ከህግ ወደ አስተዳደር፣ ከአስተዳደር ወደ ብሄር ፖለቲካ፡፡ መገለባበጥ ነው እንደጉድ፡፡
ግን ይሄ የአዳነች አቤቤ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የምናወራው ስለእሷ ብቻም አይደለም፡፡ አጠቃላይ ኢህአዴግን የተጣባው የመገለባበጥ አባዜ ነው፡፡ ጉልቻው ያለማቋረጥ ይቀያየራል፡፡ ተቋማት ተቋማቱን የሚያውቅም፣ በትክክል እንደቃሉ ‹‹የሚመራ››ም መሪ የላቸውም፡፡ በሀገራችን በዘርፉ ሙያው ያካበተ ልምድና ዕውቀት ያለው መሪ ሳይሆን ያለው – ከአውቶብስ እንደሚወርዱና እንደሚሳፈሩ መንገደኞች – በፍጥነት ከአንዱ ተቋም ወደሌላ የማይገናኝ ተቋም እየተንቀዠቀዠ የሚሳፈር – የሥልጣን መንገደኛ ነው ያለው፡፡
አሞሮቹ በሀገሪቱ ሥልጣኖች ዙሪያ ሥጋ እንዳዩ አሞሮች እያንዣበቡ ይኖራሉ፡፡ ያገኙትንና የደረሳቸውን ሥልጣን እያነሱ መብረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ድጋሚ ደግሞ ያርፉና ሌላ የሥልጣን ሥጋ ይወረወርላቸዋል፡፡ እንዲያ እንዲያ እያሉ የሥልጣን አሞሮቹ ዓላማ-የለሽ የሥልጣን በረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሀገር፣ ተቋም፣ ሙያ (ፕሮፌሽናሊዝም)፣ የማይቋረጥና በፅናት የሚተጋ ሀገራዊ ራዕይ፣ ዕውቀትና ባለዕውቀቶች – በእነዚህ ሁሉ የፓርቲው የሥልጣን ሻሞዎች ውስጥ – አንዳች ቦታ የላቸውም፡፡ ስለዚህ አሳዛኛ ነገር ነው የምናወራው፡፡ ስለ አዳነች አቤቤ አይደለም፡፡ ስለ ሁሉም ነገራችን ነው፡፡ ስለ ሁሉም ነው፡፡
ለማ መገርሳ፡- በመጀመሪያ ወታደር ነበር፣ ቀጥሎ የደህንነት ሹም ሆነ፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ሆነ፣ ቀጥሎ የፌዴሬሽን ምክርቤት አባል፣ ቀጥሎ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ አሁን ከጨዋታ ውጪ፡፡
አብይ (አብዮት) አህመድ፡- መጀመሪያ ወታደር፣ ቀጥሎ የደህንነት ሹም (የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር) ፣ ቀጥሎ የሳይንስና የመረጃ ዳይሬክተር፣ የቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የአጋሮ ተመራጭ የፓርላማ አባል፣ የኦሮሚያ ክልል ቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኦህዴድ ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ ደሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡
ሽፈራው ሽጉጤ፡- መጀመሪያ መምህር፣ ከዚያ ከሲቪል ሰርቪስ በአካውንቲንግ ሲመረቅ ኦዲተር፣ ቀጥሎ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት፣ ቀጥሎ የትምህርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ከጨዋታ ውጪ፡፡
ደመቀ መኮንን ሀሰን፡- መጀመሪያ የባዮሎጂ መምህር፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት፣ ቀጥሎ የፓርላማ አባል፣ ቀጥሎ የትምህርት ሚኒስትር፣ የብአዴን ሊቀመንበር፣ ለ7 ዓመት ደሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡
አምባቸው መኮንን፡- መጀመሪያ ታጋይ፣ ከዚያ በርቀት ትምህርት ሃይስኩልን፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከደቡብ ኮሪያና ከእንግሊዝ ዲግሪዎችን አገኙ፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ ቀጥሎ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ቀጥሎ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ዋና ዳይሬክተር፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማት አማካሪ፣ በመጨረሻም የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት፡፡
ታከለ ኡማ፡- ሃይስኩል ከአምቦ፣ በመጀመሪያ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ቀጥሎ በኢንቫይሮመንታል ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል፣ ቀጥሎ የሱሉልታ ከንቲባ፣ ቀጥሎ የሆለታ ከንቲባ፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ አሁን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር፡፡
ሽመልስ አብዲሳ፡- ከጊንጪና ከአምቦ የመጀመሪያና ሃይስኩል ትምህርቱን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍናና በሂውማንራይትስ፣ ከዩኒሳ በሊደርሺፕ ዲግሪዎች አግኝቷል፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ ቀጥሎ ደሞ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣ ከዚያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ቀጥሎ የኦህዴድና የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ አሁን ደሞ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት፡፡
አይሻ መሀመድ፡- በሲቪል ኢንጂነሪንግና ሊደርሺፕ ዲግሪዎችን አግኝታለች፣ ቀጥሎ የአፋር ፓርቲ (አብዲፓ) አባልና አመራር፣ ቀጥሎ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ደሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ለ10 ወር የመከላከያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ደሞ ድጋሚ የከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ሚኒስትር፡፡
ሲራጅ ፈጌሳ፡- የደኢህዴን ምክትል ሊቀመንበር፣ ቀጥሎ የመከላከያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ፣ ቀጥሎ የትራንስፖርት ሚኒስትር፡፡
ወርቅነህ ገበየሁ፡- በህግ ተመርቋል፣ በተልዕኮ ተጨማሪ ዲግሪዎችን አግኝቷል፣ መጀመሪያ የፖሊስ ኮሚሽነር፣ ቀጥሎ ኮሚሽነርነቱን ትቶ የፓርላማ ተወዳዳሪ፣ ቀጥሎ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ቀጥሎ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር፣ ቀጥሎ የኢጋድ ዳይሬክተር፡፡
ተሾመ ቶጋ፡- የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ነው፣ መጀመሪያ የደኢህዴን አባልና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ቀጥሎ በሶስት የአረብ ሀገሮች አምባሳደር፣ ቀጥሎ የስፖርት ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የፓርላማ አፈጉባዔ፣ ቀጥሎ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር፣ አሁን በቻይና አምባሳደር፡፡
ሞቱማ መቃሳ፡- የኦህዴድ አባልና አመራር፣ ቀጥሎ የፓርላማ አባል፣ ቀጥሎ ለአጭር ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ድጋሚ ወደ ፓርላማ አባልነቱ ተመለሰ፡፡
ተመስገን ጥሩነህ፡- መጀመሪያ ወታደር፣ ቀጥሎ የብአዴን አባል፣ ቀጥሎ በኮምፒውተር ሳይንስና ሊደርሺፕ ዲግሪዎች አገኘ፣ ቀጥሎ የአማራ ክልል የፀጥታ አማካሪ፣ ቀጥሎ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ፣ ቀጥሎ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፤ ቀጥሎ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ቀጥሎ የደህንነት ሹም (የኢንሳ ኃላፊና ዋና ዳይሬክተር)፣ ቀጥሎ የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ቀጥሎ የመከላከያ መረጃ መምሪያዎች ኃላፊ፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፣ አሁን የአማራ ክልል ፕሬዚደንት፡፡
አባዱላ ገመዳ፡- መጀመሪያ ወታደር (ቀድሞ የደርግ ወታደር፣ በወያኔ ሲማረክ ታጋይ፣ በመከላከያ ኃላፊነቶች እስከ ሜጀር ጄነራል ማዕረግ)፣ በመቀጠልም የኦህዴድ መሥራችና አመራር አባል፣ ቀጥሎ ከቻይና ሚሊቴሪ ሊደርሺፕና በተልዕኮ በማኔጅመንት ዲግሪዎችን አገኘ፣ ቀጥሎ ሜጀር ጄነራልነቱን ውድቅ አድርጎ በአቶ በመተካት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት፣ ቀጥሎ የፓርላማ አፈጉባዔ፣ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፣ አሁን የጠቅላይ ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪና የደቡብ ሕዝቦች የበላይ ጠባቂ፡፡
ቴድሮስ አድሃኖም፡- የህክምና ዲግሪ አግኝቷል፣ ቀጥሎ የህወሃት አባል፣ ቀጥሎ የትግራይ ጤና ቢሮ ኃላፊ፣ ቀጥሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፡፡ ቢያንስ በስተመጨረሻ ለሙያው ወደሚቀርብ ሥልጣን ተመልሷልና ተመስገን ነው፡፡
ሥልጣኖች መገለባበጣቸው አላባራም፡፡ የሥልጣን አሞሮቹም መሽከርከራቸውን አላቆሙም፡፡ ሙያዊ ህይወትና አንጋፋ ልምድ ዜሮ ገብተዋል፡፡ የሥልጣን ሥጋዎች እንደ ቅርጫ ለባለዕድለኞች ይበተናሉ፡፡ ሀገር በዕውቀት፣ በልምድ፣ በያንዳንዱ ሙያ ራሱ ሙያው ባፈራቸው ዕውቅ ፕሮፌሽናሎች የምትመራ መሆኗ ቀርቶ – የኢህአዴግ የሥልጣን አሞሮች መጫወቻ ከሆነች ቆየች፡፡ ከገነት ዘውዴ እስከ አዳነች አቤቤ፡፡ እና ገና ወደፊትም፡፡
የመንግሥት ተቋማት ተረኛ ተጓዦችን የሚጭኑና የሚያራግፉ የጊዜያዊ መንገደኛ ተርሚናሎች ሆነዋል፡፡ አሞሮቹም መብረራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እኛም ለጉድ የፈጠረን ምድራውያን ወደነዚያው ሥልጣናት አንጋጠን ማላዘናችንን እንቀጥላለን፡፡ ሀገር የምትፈርሰው እንዲህ ነው፡፡
አሁን ነገሬን አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic