>
10:41 am - Thursday March 30, 2023

ልቦናህን ከጨፈንክ ጨፈንክ ነው!  (በድሉ ዋቅጅራ)

ልቦናህን ከጨፈንክ ጨፈንክ ነው! 

(በድሉ ዋቅጅራ)

* …አድሏዊነት ሲጫንህ፣ ልቦናህን ስትጨፍን እንዲህ ነው፡፡ የተሰረቀው ሳይሆን፣ ሌባን ሌባ ያለው ላይ ትፈርዳለህ፡፡ ህዝብን የሚከፋፍል፣ አደገኛ ንግግር ያደረገውን ትተህ፣ ንግግሩን ያሰራጨው ላይ ጥናት ታደርጋለህ!
 
1985 – ጎርጎራ
ጎርጎራ ሳስተምር አንድ መምህር የሌላውን 50 ብር ወሰደበት፡፡ ሁለቱም ጓደኞቻችን ናቸው፡፡ አብረው ነው የሚኖሩት፡፡ ወሳጅ ቀድሞ ወጥቷል፡፡ ባለገንዘቡ ሲነሳ ገንዘቡ የለም፤ አበደ፡፡ ወደ ጎርጎራ መዝናኛ ክበብ ሲሄድ፣ አጅሬ ቁርሱን ምላስ- ሰንበር በልቶ፣ በረንዳ ላይ ከጥርሱ ውስጥ የተራረፈ ስጋና ፈርስ በስቴኪኒ እየቃረመ፣ ማኪያቶውን ይጠጣል፡፡
‹‹አንተ ሌባ! ገንዘቤን አምጣ››
አስተናጋጆች፣ እንግዶች ገላገሉዋቸው፡፡
ጉዳዩ እኛ ዘንድ ደረሰ፡፡
‹‹በሉ ታረቁ››
‹‹አልታረቅም፣ ድብን ብል አልታረቅም፡፡›› ወሳጅ፡፡
‹‹ለምን;›› እኛ (ሽማግሌዎቹ)
‹‹እንዴ! በሰው ፊት ሌባ ብሎ ይሰድበኛል? አልታረቅም!››
እኛ ወደ ባለገንዘቡ ዞር አልንና. .
‹‹ስማ፣ ጓደኛህ ነው፡፡ አብራችሁ ክፉና ደግ አሳልፋችኋል፡፡ ምን ቢሰርቅህ፣ በሰው ፊት መሳደብ አልነበረብህም፤ በል ይቅርታ ጠይቀው፡፡››
.
2012 አዲስ አበባ
አቶ ታዬ ደንደአ ስለሰሞኑ የኦሮምያ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ ንግግር በአንድ የራዲዮ ጣቢያ ይጠየቃሉ፡፡
ጋዜጠኛ – ‹‹ስለአቶ ሽመልስ ንግግር ያሎት አስተያየት ምንድነው? የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲ አቋም ነው ወይ?››
አቶ ታዬ – ‹‹ዋናው ጉዳይ ንግግሩ አሁን ለምን ተለቀቀ የሚለው ነው፡፡ ፕርቲው በሰሞኑ በሚያደርገው ስብሰባ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ ይህን ያደረጉትን ዝም ብለን አናልፍም፡፡ የፓርቲው አቋም ነው ግን ለማለት ያስቸግራል፡፡›› (ቃል በቃል ሳይሆን ሀሳቡ የተወሰደ ነው)
.
አድሏዊነት ሲጫንህ፣ ልቦናህን ስትጨፍን እንዲህ ነው፡፡ የተሰረቀው ሳይሆን፣ ሌባን ሌባ ያለው ላይ ትፈርዳለህ፡፡ ህዝብን የሚከፋፍል፣ አደገኛ ንግግር ያደረገውን ትተህ፣ ንግግሩን ያሰራጨው ላይ ጥናት ታደርጋለህ፡፡
.
የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲም ሆነ፣ አቶ ሽመልስ በግልጽ ስለሰማነው ንግግር በግልጽ ወጥተው ይናገራሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ አላደረጉም፡፡ እንዲህ አይነቱ ዝምታ ቀስ በቀስ ወደነበርንበት እንዳይመልሰን እፈራለሁ፡፡
Filed in: Amharic