>

የንጉስ ምኒልክ የአርሲና የሐርር ጦርነቶች...!!!  (ዝክረ ነገር)

የንጉስ ምኒልክ የአርሲና የሐርር ጦርነቶች…!!!

 ዝክረ ነገር

አፄ ዮሐንስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ በመሆናቸው ራስ አዳልን “ንጉሥ ተክለሃይማኖት” ብለው የጎጃምና የከፋ ንጉሥ አድርገው ሾሙ። የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጦር መሪ ራስ ደረሰ ጅማንና ከፋን ተቆጣጥሮ ማስገበርም ጀመረ። ከዚህ የምንረዳው አንዳንድ የኦሮሞ ክፍሎች ከአፄ ምኒልክም በፊት ለጎጃሙ ንጉስ መገበር ጀምረው እንደነበር ነው።
ራስ ጎበና ዳጬ የምኒልክን ጦር እየመራ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እያስገበረው ወደ ነበረው የኦሮሞ ግዛት ሲመጣ የኦሮሞ ግዛት ባላባቶች ለማን እንደሚገብሩ ግራ ተጋቡ። በራስ ጎበና የሚመራው የሸዋ ጦር ማጥቃት ሲሰነዝር ጥቃቱን መቋቋም ያልቻሉት የጎጃሙ ራስ ደረሰ ከጅማና ከከፋ የሰበሰቡትን ግብር የዝሆን ጥርስ ጨምሮ በቅጡ ሳይሰበስቡ ሸሹ።
በዚህም ምክንያት እረኞችና አዝማሪዎች
እንግዲህ ጎጃሞች በምን ይስቃሉ
ጥርሳቸውን ሊሙ ትተውት ሄዱ አሉ። ብለው ተሳለቁ።
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በሊሙ ጦርነት የጦር መሪያቸው ተሸንፎ ግዛታቸውን መነጠቃቸው አበሳጫቸው። ውርደትም አድርገው ቆጠሩት። ሽንፈት በፈጠረው ንዴት ውስጥ ሆነውም ለንጉስ ምኒልክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉላቸው።
“ምነው እርስዎ እኔን ሁልጊዜ ያዋርዱኛል። ከዚህ ቀድሞ በኃይል መጥተው አገሬን ጎጃምን አጥፍተውት ሄዱ። አሁን ደግሞ ያቀናሁትን የኦሮሞ አገር እያጠፉ ሹም ሽር አደረጉበት። ከእንግዲህ ወዲህ መጣሁ አይሂዱ፤ ከጉድሩና ከሖሮ ከጅማና ከጨሊያ በወደዱት አገር የጠራ ሜዳ ይዘው ይቆዩኝ። ይህንንም ቃል በደብዳቤ አለመላኬ ደብዳቤውን ብቻውን ( ብቻዎትን) አይተው ቀደው ጥለው፣ ሰምተው እንዳልሰማ ሆነው ሸሽተው ይሄዳሉ። በቃል የሆነ እንደሆነ ግን አሽከርዎችዎ ይታዘቡዎታልና በቃል መላኬ ለዚህ ነው”
የንጉስ ተክለ ሃይማኖትን መልዕክት እንደሰሙ ንጉስ ምኒልክም በመልዕክተኛ ምላሻቸውን ሰደዱ።
” እኔ ለአንተ ጦርነት ሰግቼ ሸሽቼ አልሄድም ፤ ግን ከኔ ጋር ለመዋጋት ከአፄ ዮሐንስ ፈቃድ አግኝተህ እንደ ሆነ ፈቃድ ማግኘትህን በደብዳቤ እንድትልክብኝ ነው እንጂ ለጦርነቱስ እዚያው አገርህ ደረቤ ሜዳ ላይም ቢሆን እመጣልሃለሁና አንተን መንገድ አይምታህ ፤ ይህንም በደብዳቤ አለመላኬ አንተ ደብዳቤውን ስትጠላው አይቼ ነው”
መናናቅ ከሚታይበት የመልዕክት ልውውጥ በኋላ በግንቦት 29 ቀን 1874 ዓ.ም ሆሮ ጉድሮ በእምባቦ ሜዳ ጦርነት ገጠሙ። የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ጦር የሸዋ ፈረሰኞችና የወሎ ጦረኞችን መቋቋም አቅቶት ተሸነፈ። ንጉስ ተክለ ሃይማኖትም ተማረኩ። ይህ ድል የንጉስ ምኒልክን ወደ ፊት ንጉሰ ነገስት መሆን የወሰነ ነው ይባልለታል። ከዚህ በኋላ ነው የጂማው አባጂፋርን ጨምሮ ሌሎቹ የጊቤ ነገሥታት የንጉሥ ምኒልክን የበላይነት የተቀበሉት።
ምኒልክ በከፋ
የምኒልክ ጦር የከፋውን ንጉስ ለማስገበር ተንቀሳቀሰ:: አብዛኛውየተንቀሳቀሰው የሸዋ ጦር ነው:: የጅማው አባ ጅፋር ለማንም አልወግንም አለ:: ግን ደግሞ ለምኒልክ ቀድሞ ገብሮ ስለነበር ባይሆን ብዙ ዋጋየማያስከፍላችሁን መንገድ ልጠቁማችሁ ብሎ መረጃ ለሸዋ ጦር ሰጠ:: የሸዋ ጦር ከብዙ መስዋዕትነት በሁዋላ የከፋውን ንጉስ ማረከው::
ኩሩው የከፋ ጀግና ንጉስ ቀንጥሎኝ ብማረክም በመናኛ ገመድ አልታሰርም ራሴ ባሰራሁት የብር ሰንሰለት ነው መታሰር ያለብኝ አለ:: ምኒልክ ይሁንልህ ብለው በብር ሰንሰለት አስረው ምርኮኛቸው አደረጉት::
ንጉስ ምኒሊክ አሸንፎም ይሁን በድርድር አሳምኖ የያዛቸው ግዛቶች ላይ ሥልጣኑን ለማጠናከር ይጠቀምባቸው ከነበሩ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ከተለያየ ጎሳ የመጡ ኢትዮጵያኖች ተቀላቅለው እንዲኖሩ ማድረግ ነበር። በርካታ የደቡብ አካባቢ ነዋሪዎችን ወደ ሸዋ አምጥቶ አስፍረዋል። የሸዋና የሌላ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች ደግሞ በደቡብ እንዲሰፍሩ አድርገዋል።
የአርሲ ጦርነትና ንጉሥ ምኒልክ
ንገሥ ምኒልክ ከጦርነት ይልቅ ነገሮችን በንግግር ለመጨረስ በማሰብ መልዕክተኞችን ወደ አርሲ ባላባቶች ላኩ። ለአርሲ ባላባቶች እንዲህ ብለው እንዲነግሯቸው በመልዕክተኞቻቸው በኩል መልዕክት ላኩ ” የኔን የበላይነት እስከተቀበላችሁ ድረስ በውስጥ አስተዳደራችሁ አልገባም!”
ከአርሲ ባላባቶች ውስጥ ሱፋ ኩሶና ዳሙ ኡሱ የተባሉት ባላባቶች ንጉሥ ምኒልክ በመልዕክተኛ ቡላኩት ሃሳብ ተስማሙ። ነገር ግን ሌሎች የአርሲ ባላባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ” የኔን የበላይነት እስከተቀበላችሁ ድረስ በውስጥ አስተዳደራችሁ አልገባም!” የሚለውን አንቀበልም በማለት ጦርነትን መረጡ። ይህም በአርሲ ባላባቶች መካከል መከፋፈልን ፈጠረ። ይህንን የአርሲዎች መከፋፈል ተጠቅሞም የሸዋ ጦር የአርሲን ጦር ድል አደረገ። አርሲም የማታ ማታ ለንጉስ ምኒልክ ገበረች።
የሐረር ጦርነትና ምኒልክ
ሐረርን ግብፆች ለእስር አመታት አስተዳድረዋታል። በ1877 ግብፆች ሐረርን ለቀው ሲወጡ አሚር አብዱላሂን ወደ ስልጣን መልሰው ነበር የሄዱት። አሚር አብዱላሂም እስልምናን ማስፋፋትና ማጠናከር ጀመረ። በሐረር አካባቢ የሚኖሩ ኦሮሞዎችንም ማስገበር ጀመረ። አሚር አብዱላሂ በሐረር ይኖሩ የነበሩ ክርስትያኖችን ማሳደድ ጀመረ። አብዛኞቹ ኦሮሞ የሆኑ ክርስትያኖች ወደ ሸዋ ተሰደዱ። ከተሰደዱት አንዳንዶቹም የምኒልክን ጦር ተቀላቀሉ።
በ1878 ዓ.ም ኤሚር አብዱላሂ አዲስ አይነት የገንዘብ ሥርዓት መከተል ጀመረ። አዲሱ የገንዘብ ስርዓት ለብዝበዛ ስላጋለጣቸው በርካታ ኦሮሞዎች አመፁ። አሚር አብዱላሂ በሚያደርገው ነገር ቢበሳጩም ንጉስ ምኒልክ በትዕግስት ነገሮችን ማለፍ መረጡ። ነገር ግን ሐረርን አልፎ ይመጣላቸው የነበረው የጦር መሳሪያ በአሚር አብዱላሂ ትዕዛዝ ሲቋረጥ ንጉስ ምኒልክ ጦራቸውን ማዝመት እንዳለባቸው ወሰኑ።
ንጉስ ምኒልክ ጦራቸውን ጨለንቆ ላይ ካሰፈሩ በኋላ ነገሩን በሰላም ለመጨረስ በማሰብ መልዕክተኞች ላኩ። ” ለጅማው አባ ጅፋር የሰጠሁትን አይነት የግዛት ነፃነት ለአንተም እሰጥሃለው” በማለት። አሚር አብዱላሂ የምኒልክን ሃሳብ አልቀበልም አለ። ታህሳስ 29 ቀን 1879 ዓ.ም በእለተ ገናም አሚር አብዱላሂ በምኒልክ ጦር ላይ ጦርነት ከፈተ። አሚር አብደላሂ ቀኑን የመረጠው ዕለቱ ገና በመሆኑ የምኒልክ ጦር ተዘጋጅቶ አይጠብቀኝም በሚል ነበር፤ ምኒልክ ግን ወታደሮቻቸውን አዘጋጅተው ነበር የጠበቁት። በስተመጨረሻም ጦርነቱ በንጉስ ምኒልክ አሸናፊነት ተደመደመ።
Filed in: Amharic