>

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አማራዎች ላይ በኦነግ ታጣቂዎች ግድያ ተፈፀመባቸው !!! (አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ)

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አማራዎች ላይ በኦነግ ታጣቂዎች ግድያ ተፈፀመባቸው !!!

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

 ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ዞን የደረሰን መረጃ እንዳመለከተው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ በሚገኙ አማራዎች ላይ በኦነግ ታጣቂዎችና ቄሮዎች “ነፍጠኛ” የሚል የጅምላ ስም በተሠጣቸው የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ግድያ፣ ማሳደድ፣ መደፈርና ማፈናቀል ተፈፅሟል።
ባሳለፍናቸው ሶስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በአካባቢው ባሉ በታጠቁ የኦነግ ሸኔ አባላት አሰቃቂ ግድያ የተፈፀመባቸው ወጣቶችን አስከሬን ማንሳት አለመቻሉን ከግድያው ያመለጠ በምስራቅ ጎጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ ነዋሪ ተናግሯል።
ከምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ዞን ለስራ ከሄዱት መካከል ከሰሞኑ ብቻ 12 የአማራ ወጣቶች በአሰቃቂ መልኩ በጥይት ተገድለዋል።
ግድያውና ማሳደዱ የሚፈፀመው በኦነግ ታጣቂዎችና ተባባሪዎቻቸው በሆኑት በአካባቢው ቄሮዎች ሲሆን መከላከያና የፀጥታ አካሉም እየታደጋቸው እንዳልሆነ የገለፁት ምንጮች ከአካባቢው ለመሸሽ እየሞከሩ ቢሆንም በየመንገዱ ጥቃት እያጋጠማቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የፌደራል እና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በየጫካው የተበተኑትን ወጣቶች እንዲታደጓቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የሟች ቤተሰቦችም የልጆቻቸውን የመገደል መርዶ ተነግሯቸው በከፍተኛ ሀዘን ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዘርና ሀይማኖት ተኮር ጥቃት እንዲቆም ሲሉ በባሶ ሊበን ወረዳ በላም ገጅ ታዳጊ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ዛሬ ነሀሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
የላም ገጅ ታዳጊ ከተማ ነዋሪዎች በዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ዞን በአማራ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት እንዲቆም፣በበርሀ የተበተኑትን መታደግ እንዲቻል፣የተገደሉትም አስከሬናቸው እንዲነሳ እንዲሁም የቆሰሉትም ተገቢ ህክምና እንዲደረግላቸው የክልሉን መንግስት ጠይቀዋል።
የአማራ ሚዲያ ማዕከል ለኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አመራር ለሆኑት ለአቶ ሞገስና ለሆሮ ጉድሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ለአቶ ብርሀኑ የደወለ ቢሆንም “የደረሰን መረጃ የለም ” የሚል ምላሽ ሰጠው እንደሚያጣሩት ነው የተናገሩት።
አቶ ብርሀኑ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካውን አካባቢው የሚያስተዳድረው የፌደራል መንግስት መሆኑንም ገልፀዋል።
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት በአዲስ አበባ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ በመቶዎች በሚቆጠሩ ንፁሀን ላይ ነፍጠኛን በለው በሚል ዘር እና ሀይማኖት ተኮር ጥቃት መፈፀሙ ይታወሳል።
ከግድያ ካመለጠና ከሟች ቤተሰቦች ጋር የተደረገውን ቆይታ በአሚማ ዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።
Filed in: Amharic