>
7:17 pm - Tuesday June 6, 2023

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ባቀረበው ጽሁፍ  ላይ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በ ‘ብሄራዊ መግባባት ውይይት መድረክ’ ላይ ባቀረበው ጽሁፍ  ላይ አጭር አስተያየት

አበጋዝ ወንድሙ


ፕሮፌሰር መረራ  ‘በኢትዮጵያ የሀገረመንግስት ግንባታ የታሪክ ዳራ: በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣ ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን እድሎች በብሔራዊ መግባባት መነጽር ሲታይ የሚል ጽሁፍ  በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዘጋጅነት የተካሄደው ብሄራዊ መግባባት ውይይት መድረክ ላይ አቅርቦ ነበር

በጽሁፉ ላይ ያሉኝን አንዳንድ አስተያየቶች ከመሰንዘሬ በፊት፣ ሀገር ቤት  ውስጥ የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ እንዲህ ያለ ግልጽ ውይይት መደረግ መቻሉ፣ በኔ አስተያየት በራሱ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን እገነዘባለሁ።

 በተለይ ደግሞ በሀሰትም ሆነ በእውነተኛ ታሪክ /ትርክት ላይ ተመስርቶና ጎራ ለይቶሌላኛው ወገን’ ተብሎ በተፈረጀው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ማስተናገድ እየተለመደ የመጣበት ወቅት በመሆኑ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅተናል የሚሉ ልሂቃን፣ አለን የሚሉዋቸውን ሃሳቦች አቅርበው እርስ በእርስ የሚሟገቱባቸው መድረክ መኖሩ፣ በሀገሪቱ የሰፈነውን ውጥረት ለማርገብ ሚና ይኖረዋል ብዬ ስለማስብም ነው ትልቅ ፋይዳ አለው የምለው።

ይሄን እንደ መግቢያ ካልኩኝ በዃላ ወደ ፕሮፌሰር መረራ ጽሑፍ ስመለስ፣ ጽሁፉን የሚጀምረው አሻሚ በሚመስል መልኩ በሚያቀርበው የሀገራችን ታሪክ ነው፣ እሱምአንዳንዱ ታሪክ ሲለው ሌላው  ደግሞ ተረት አድርጎ የሚወስደውበሚል በደምሳሳው አልፎ፣የዛሬይቱ‘ ‘ሰፊዋየሚል ቅጽል በመጨመር ኢትዮጵያ የተፈጠረችው 2ኛው 19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽነው ወደሚል መደምደሚያ በመድረስ ነው።

 ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እንደሚገኙ ሌሎች ሃገራት የራሷ የሆነ የአመሰራረት ታሪክ ( በእንግሊዝኛ Founding myth or National myth) እንዳላት ግልጽ ሲሆን ይሄ የአመሰራረት ታሪክ ከመልክዐምድር መስፋት ወይንም መጥበብ ወይንም በታሪክ ሂደት በሚካሄድ መስፋፋትና ሌሎች ብሄረሰቦችን በማካተት የሚያካሂደው እንቅስቃሴ የሚወስኑትም አይደለም። 

ብዙውን ጊዜ ፖለቲከኞች ታሪክን፣ ሊያራምዱ ለሚፈልጉት ፖለቲካ፣ ጥገኛ በማድረግ ሊጠቀሙበት ስለሚሞክሩ፣ ያለፈ ታሪክን አስመልክቶ ስምምነት ላይ ለመድረስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ታሪክን አስመልክቶ በታሪክ ምሁራንም በኩል ቢሆን ፣መሰረታዊ ታሪክ በሚባለው ላይ አጠቃላይ ስምምነት ቢኖርም፣ አዲስ ግኝት በተገኘ ቁጥር የሚታደስና የሚጎለብት፣ ታሪክና የታሪክ መስክም፣ ግዑዝ ሳይሆን ህያው የሆነ እንደሆነ የሚታመን ነውና፣ እሱን ለባለሙያዎቹ መተው የተሻለ ይመስለኛል።

አሁን ላይ ያለው የሀገራችን ችግር ባለፍናቸው የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የትኛው አጼ የበለጠ ጨካኝ ነበር አልነበር ላይ ያውጠነጠነ ሳይሆን(መሆንም የለበትም) ፣ዛሬ ላይ ሆነን የገጠሙንን ችግሮች እንዴት አድርገን በጋራ ታግለን በጋራ ልንወጣቸው እንችላለን የሚለው ነው።

በሌላ አነጋገር  ዛሬ ሀገራችን ላይ ፈጦ ያለው ችግርና የምክክር መድረኩም አላማ የታሪካችን እርዝማኔ ወንም ማጠር ሳይሆን፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመፍጠር ምን ማድረግ አለብን፣ ከገባንበት የፖለቲካ ቅርቃርስ እንዴት እንውጣ  የሚለው ነው።ይህም ከፕሮፌሰር መረራ አስተሳሰብ በተቃራኒ በአጼዎቹ ዘመን( ልጅ ኢያሱም ቢሆኑ!) የሚታሰብ ስላልነበር፣ውይይታችን 1966 አብዮት ጀምሮ እስከአሁን ባለው ላይ ቢያተኩር የተሻለ መግባባት ላይ መድረስ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። 

ዛሬ ተፈብርኮ እንደሚወራው 1966 አብዮት የጨነገፈው ኢህአፓና መኢሶን እርስ በርስስለ ተጨራረሱ’ ሳይሆን የሁለቱ ለጋ ድርጅቶችን እርስ በርስ አለመግባባትና መናቆርን ተጠቅሞ፣ ደርግ የሁለቱንም ድርጅት አባላትና መሪዎች ጨፍጭፎና ድርጅታቸውን አፈራርሶ ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት በመመስረቱ ነው።

አብዮቱ ይክሽፍ እንጂ፣ መረራ እንዳለው የጭሰኝነትን ስርዓት ያስወገደውና የባላባት ስርዓቱን የኢኮኖሚ መሰረት የናደው የመሬት አዋጅ መታወጅ ፣ የብሄረሰቦችና የሃይማኖት እኩልነት እውቅና ማግኘትና በሀገሪቱ ህገመንግስት መካተትና፣ አንድ አንድ ሌሎቹም አዋጆች  የአብዮቱ ትሩፋቶች ናቸው።

የነዚህ ትሩፋቶች መኖር እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ፣ በዋናነት የደርግ ህብረብሄራዊ ድርጅቶችን ማፈራረስና አምባገነናዊ ስርዓት መንሰራፋትም ነው ለብሄራዊ ንቅናቄ ድርጅቶች በር በመክፈት ህወሃት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ያደረገው። ህወሃት/ኢህአዴግ ደርግን ከስልጣን አውርዶ በገዛባቸው 27 ዓመታት  ሙሉ ሀገሪቱን በፖለቲካ መስክ ሲከፋፍልና ቅራኔዎችን ሲያራግብ የከረመ ድርጅት ነው። 

መረራ እንዳለውም ይሄ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል ጭምብል ያደረገ ድርጅት 27 ዓመት ሙሉ ሀገሪቱን በፖለቲካ መስክ ሲከፋፍል በመክረሙም አሁን ላለንበት የፖለቲካ ኪሳራና ውድቀት ዳርጎናል።

አንዳንዶች እንደሚሉትና እንደሚመስላቸው ህውሃት ይሄንን ያደረገውና እንዲያደርግም የተገደደው የተለየ ክፋት ስለነበረው ሳይሆን፣ የተከተለው የብሄር ፖለቲካ አመክንዮ ያመጣበት ጣጣ በመሆኑ ነው። ለወደፊትም ቢሆን ራሳችንን በብሄር ፖለቲካ አጥር ውስጥ ብቻ ወስነን የምንቀሳቀስ ከሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ ያደርግ የነበረውን፣ በፈረቃ ከማድረግ ውጭ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ሀገር የመገንባት ህልማችን መና ሆኖ እንደሚቀር አያጠራጥርም።  

በኔ ግምት ሀገራችን ገጥሟት ያለውን ችግር ለመወጣትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመመስረት፣ በቀድሞው ታሪካችን ላይ ከመነታረክ ይልቅ፣ የሀገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴና ትግል ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የህዝቦቿን መሰረታዊ ችግር ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ መፈለጉ ላይ መሆን ያለበት ይመስለኛል።

የብሄራዊ መግባባት ውይይት መድረክ ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችም እኔ እሻል፣ እኔ እበልጥ ከሚል ንትርክ ወጣ ባለ መልኩ ሃገራዊ ችግሮች ላይ ተወያይተው የተወሰነ መግባባት ላይ መድረስ ቢችሉ፣ ህብረተሰቡ ላይ ተስፋ ሊያጭሩ ይችላሉና ትኩረታቸውን  እሱ ላይ ቢያደርጉ ይመከራል።

በትክክል ባላስታውሰውም በአንድ ወቅት ዮሃንስ አድማሱ

 እራቤ ጥማቴ እርዛቴ ሶስቱ

 ይቀጠቅጡኛል ባንድ እየዶለቱ 

በሚል የዛሬ ሃምሳ ዓመት ግድም የህዝባችንን መሰረታዊ ችግር አስመልክቶ የገጠመው የዛሬውም የህዝባችንና የሀገራችን መሰረታዊ ችግር መሆኑን ተገንዝበን ለመፍትሄው ብንረባረብ ያማረ ታሪክ መስራት እንችላለን።

 

 

Filed in: Amharic