ቀደም ብለን ይህን ብለን ነበር ዛሬስ ታሪክ ራሱን አልደገመም ትላላችሁ…???
ያሬድ ጥበቡ
* ኢትዮጵያችን ያለችበት ሁኔታ ለብዙዎች የጭንቀት ምክንያት ሆኗል፤ ማለቂያችን ምን ይሆን በሚል…!!!
ለእኔ ዛሬ ላይ ካለኝ የተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ በመነሳት ስድስት የተለያዩ ውጤቶች ሊያጋጥሙን ይችሉ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ።
1) ሥርአቱ ቀውሱን አሸንፎ ይደላደላል
2) ቀውሱ አሸናፊም ተሸናፊም ሳይኖረው ለረጅም ጊዜ በመቀጠል፣ ሃገሪቱ ረጅም ውጥረት ውስጥ ልትገባ ትችላለች
3) የህዝባዊ እምቢተኝነቱ አሸንፎ ከሁሉም የተውጣጣ ብሄራዊ የሽግግርና እርቅ መንግስት ይመሰረታል
4) ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ሃይሎች በህዝባዊ ድጋፋቸው እየተማመኑ ሄደው፣ የወያኔን የበላይነት እምቢተኛ በመሆን ኢህአዴግ ራሱን አርሞና፣ ነፃ የምርጫ ቦርድና ፍትሃዊና ርቱአዊ ምርጫ የሚቀበል ፓርቲ እንዲሆን በማስገደድ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ የምንሸጋገርበት እድል ሊፈጠር ይችላል።
5) ህወሐት ኢህአዴግ ላይ ያለውን የበላይነት ማስጠበቅ ሲያቅተው፣ የመከላከያ ጄኔራሎችን ከፊት አስቀምጦ የመንግስት ግልበጣ ሊያካሂድ ይችላል
6) አሜሪካ የፀጥታ ሁኔታው ስጋት ላይ ጥሎኛል ብላ ካመነችና፣ ጦሩን ሊያስተባብር የሚችል ወታደራዊ/ደህንነት መሪ ካገኘች ወይም ካላት መፈንቅለ መንግስት ልታካሂድ ትችላለች ።
ዛሬ ለኔ የሚታዩኝ አደጋዎችና እድሎች እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ናቸው ። ኢትዮጵያችን ያለችበት ሁኔታ በብዙ አደጋና ያንኑ በሚመጥን ተስፋ ውስጥ በመሆኑ፣ እነዚህ ሁኔታዎች በአፋጣኝ ተለዋዋጭነት ሊያሳዩ ይችላሉ ። ዛሬ ይሆናል ብለን የተነበይነው በብርሃን ፍጥነት ሊኮሰምንና ሊጠፋ ይችላል ። ዛሬ የህዝብ ወዳጅ ነው ብለን ተስፋ የጣልንበት በብርሃን ፍጥነት ተቀይሮ ሊያድር ይችላል ።
በቁጥር አንድ ያስቀመጥኩት ሥርአቱ አሸናፊ ሆኖ በቶሎ የመደላደሉ እድል እጅግ በጣም ደካማው አማራጭ ይመስለኛል ። በኦሮሞ ክልል የአስር ወራት ህዝባዊ እምቢተኝነት የተገነዘብነው ነገር ቢኖር፣ መንግስት የህዝቡን ተቃውሞ በጥገናም ሆነ በአመፅ መደምሰስ እንዳልቻለ ነው ። ኦሮሚያን በወታደራዊ ቀጣና ከፋፍሎ የሽብር አገዛዝ የጫነበት ቢሆንም፣ ይበልጥ ከህዝቡ እየተነጠለ እንጂ እየተደላደለ መሄድ አልቻለም ። ይባስ ብሎም በአማራ ክልል ወደተነሳ ህዝባዊ እምቢተኝነት ረመጥ ውስጥ ጨምሮታል ። በተለይ በጎንደርና ጎጃም የተነሱት እንቅስቃሴዎች ስርአቱ ጥገና ሊሰጥ ወይም ሊያደርግ በማይችልበት የወልቃይት ጠገዴ ማንነት ጥያቄ ጋር ስለተቆላለፈ፣ ለሥርአቱ ፋታ ባለመስጠት እየጠነከረ የሚሄድ ተቃውሞ የመሆን እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው ። ይህ የአማራ ክልል ህዝባዊ እምቢተኝነት ዛሬ ያፈነውን የድርጅትና አመራር ችግሮች ተወጥቶ ባልገመትነው ፍጥነት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው ። ስለሆነም፣ ሥርአቱ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳበትን ተቃውሞዎች አሸንፎ በቶሎ ይደላደላል ለማለት አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አይችልም ። በቶሎ ለመደላደል ከፍተኛ አመፅ መጠቀም ስለሚገደድ፣ ዛሬ ያለውን የሰራዊት ተዋፅኦ በሆነ ተአምር ካልቀየረ በቀር፣ አብዛኛው ዝቅተኛ መኮንንና ወታደር አማራና ኦሮሞ የሆነ ሰራዊት በራሱ ህዝብ ላይ ከፍተኛ አመፅ እያካሄደ ይቀጥላል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው፣ እንዲያውም አይቻልም ።
ሁለተኛው አማራጭ ቀውሱ ለረጅም ወራት የመቀጠሉ ጉዳይ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ሲሆን፣ ሃገራችንን የበለጠ የሚያዳክማትና፣ ላልተጠበቁ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ቀውሶች ውስጥ ሊያስገባን የሚችል ይመስለኛል ። ወያኔ የበላይነቱን ለመጨበጥ በሚያደርገው ትግል፣ ሁለተኛ ደረጃና ኮሌጅ የጨረሱ የትግራይ ልጆችን ለመከላከያ ሀይሉ በእጩ መኮንንነት በመመልመል፣ መጠነ ሰፊ የወታደር ምልመላ በደቡብና ሱማሌ ክልሎች በማካሄድ፣ በኦሮሞ ፍርሃትና አማራ ጥላቻ ላይ የተማከለ አዲስ ሰራዊት ወደመገንባት ሊሸጋገር ይችላል ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሱማሌ ክልል ያገኘውን ከበሬታና ማንቆለጳጰስ ማየት ነው ። ይህንንም ስራ በፍፁም ህቡእነት ትግራይ ውስጥ ሊያከናውን ይችላል፣ ምናልባትም ይህ ስራ ተጀምሮ ሊሆን ይችላል ። ይህን አዲስ ሰራዊት መገንባቱን ሲተማመን፣ በመከላከያ ሀይሉ ውስጥ ያሉትን ኦሮሞዎችና አማሮች ሊያባርር ይችላል ። በምርጫ 97 ማግስት የወሰዳቸውን ተመሳሳይ እርምጃዎች ማጤን ተገቢ ነው ። ከዚህ ይሰውረን በሉ ። ወይም እዚህ ውስጥ ላለመነከር ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ዛሬውኑ እናድርግ ። አንዱ መደረግ የሚገባው ጉዳይ የመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያሉት መኮንኖች ይህን ነቅተው እንዲጠብቁና እንዲያከሽፉ ዓይናቸውን መግለጥ ነው ።
በሶስተኛ አማራጭነት ያቀረብኩት ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በብሄራዊ የሽግግር መንግስት ብሎም ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ የመግባታችን እድል እጅግ ተመራጩ አማራጭ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ሆነን የህዝባዊ እምቢተኝነቱን የአመራርና ድርጅት አቅም ስናይ፣ ይህ የመሆን እድሉ የቀጨጨ መስሎ ይሰማኛል ። ግን ማን ያውቃል፣ እምቢተኞቹም ድክመቱ ታይቷቸው ይህን ችግር ለመቅረፍ እየሰሩ እንደሆን? ማን ያውቃል የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ? የጎንደሩና ጎጃም እምቢተኝነት ከብአዴን፣ መላ አማራ ህዝብ ደርጅት፣ ቤተ አማራና ምናልባትም ግንቦት ሰባት ጋር ተቆላልፎና፣ ዛሬ የሚታይበትን የአመራርና ድርጅት ድክመት በአፋጣኝ መፍታት ቢችል? ይህም እውን ቢሆንና፣ ማእከላዊ መንግስቱ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ በማስገደድ፣ የብሄራዊ እርቅ መንግስት ብሎም ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ የምንሸጋገርበትን እድል ቢከፍትልንስ? ከላይ እንዳልኩት የመሆን እድሉ ጠባብ ነው እንጂ ሊመረጥ የሚገባው ይመስለኛል ።
በቁጥር አራት ያስቀመጥኩት ኢህአዴግ ውስጥ የሚደረግ የውስጠ ዴሞክራሲያዊና እርማት ንቅናቄ ድርጅቱን ከተነከረበት የማፊያና እብሪት መንገድ አውጥቶት ፣ ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር እድል ጠባብ ሲሆን፣ ተመራጭ የመሆን እድሉ ግን ከፍተኛ ነው ። ሃገራችን የማትወጣባቸው ቀውሶች ውስጥ ከምትዘፈቅ፣ ገዢው ፓርቲ ራሱን አርሞ፣ የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ህይወቱን አስፍቶ፣ የወያኔን የበላይነትና አፋኝ አሰራሮችን አስወግዶ፣ ነፃ የምርጫ ኮሚሽን ብሎም ፍትሃዊና ርቱአዊ ምርጫ እንዲደረግ ማድረግ ይችል ይሆናል ። ይህ አማራጭ የመሆን እድሉ ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ደካማ ቢመስልም፣ በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉት አመራሮችና ካድሬዎች ብአዴን ላይ በሚያደርጉት ጫናና፣ ህዘቡ ከውጪ የሚያደርገው እምቢተኝነት ተዳብለው ብአዴን ከወያኔ ቁጥጥር ነፃ ሊወጣ ከመቻል አልፎ፣ ኦህዴድና ደህዴድ አርአያነቱን ሊከተሉና፣ ወያኔ ከቁመቱ ጋር የሚመጣጠን ተሳትፎ ያለው የእህት ድርጅት እንዲሆን ሊያሰገድዱት ይችሉ ይሆናል ።
በቁጥር አራት የተቀመጠው አማራጭ መውደቅ፣ በቀጥታ ወደ አምስተኛው አማራጭ ይወስደን ይመስለኛል ። ወያኔ ከእህት ድርጅቶቹ የሚቀርብበትን የውስጣዊ ተሃድሶ አልቀበልም ከማለት አልፎ፣ ብቻውን በመቆም፣ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ በሚገኙ ጄኔራሎቹ አማካይነት መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂድ ይችላል ። ይህ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ይመስለኛል ። ለሃገራችን ግን ከፍተኛ አደጋ የሚደቅንና ባለፉት 25 አመታት ሲያላዝኑ የኖሩት “በታትነናት ነው የምንሄደው” የሚለውን ሟርት ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩበት፣ ሆኖም አማራውና ኦሮሞው በመፍጠር ላይ ባለው አዲስ የትግል ህብረት የሚከሽፍበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ።
በመጨረሻ ያየሁት አማራጭ አሜሪካ ራሷ በአመታት ስልጠናና ቀረቤታ በያዘቻቸው የጦር መኮንኖች አማካይነት መፈንቅለ መንግስት ልታካሂድ የምትችልበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል ። አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሃገሮች ሁሉ ተባርራ ለእግሯ እንኳ ማረፊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነው ። ኢትዮጵያን መልቀቅ አትፈልግም ። ስለሆነም፣ ኢህአዴግ ከውስጡ የመቅለጥ አደጋ እንዳለው ከተሰማት፣ የምትተማመንበት ተቃዋሚ ስለሌለ ራሷ ወደ መንግስት ግልበጣ ልትሰማራ የምትችል ይመስለኛል ። ለዚህ የሚሆኑ ተባባሪዎች ታጣለች ማለት ሞኝነት ይመስለኛል ። አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትየጵያ ብቸኛዋ የመረጋጋት ገነት ከመሆኗ ባሻገር የቻይና መንደርደሪያ ሆና እንዳትቀጥል የአሜሪካ ፍላጎት ይመስለኛል ። ስለሆነም፣ አሜሪካ የራሷን ጄኔራሎች ይዛ መፈንቅለ መንግስት ልታካሂድ ትችላለች ። ይህ አማራጭ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ባይሆንም፣ ስልጣን ላይ የሚወጡት ጄኔራሎች ግን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትንና ዴሞክራሲያዊ ተስፋን አዳብለው ከመጡ፣ በቁጥር 1, ፣ 2ና 5 ከቀረቡት አማራጮች የተሻለው ሊሆን ይችላል ። ምን ይመስላችኋል?
ቸር ይግጠመን