>

ታላቁ ስላቅ¡¡¡:- "በኢንተርኔት የቪዲዮ ንግግር በበቂ ሁኔታ ማድረግ አልቻልኩም!" የአቶ ጃዋር አቤቱታ (የትነበርክ ታደለ)

ታላቁ ስላቅ¡¡¡:-

በኢንተርኔት የቪዲዮ ንግግር በበቂ ሁኔታ ማድረግ አልቻልኩም!የአቶ ጃዋር አቤቱታ
የትነበርክ ታደለ

* … ጃዋር መሀመድ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ሳለ “…አሜሪካን ሀገር ካሉት ሚስቴና ልጄ ጋር በኢንተርኔት የቪዲዮ ንግግር በበቂ ሁኔታ እየተገናኘሁ አይደለም!” የሚለውን አቤቱታውን ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ስሰማ መጀመርያ በከባድ ድንጋጤ  ተመታሁ፣ ቆይቼ ሆዴን እስኪያመኝ ከት ከት ብዬ እንደ እብድ ሳቅሁ፤ ማሽላ ሲያር… ይሉት አይነት ሳቅ! 


…..እየቆየሁ ግን የነአንዷለም አራጌ የነ እስክንድር ነጋ ያለምንም ጥፋት ለሀገር ካላቸው ሀሳብ የተነሳ ወህኒ ተወርውረው መከራና ስቃይ ተፈራርቆባቸው በመጨረሻም አሳሪዎቻቸው የሰው ልጅ ላይ ያደረሱት ግፍና የሰሩት ሀጢያት አሳዷቸው ወደ ቁም እስር ገብተው እነሱ ከእስር ሲፈቱ የነበራቸው የተጎሳቆለ መልካቸው ከፊቴ ላይ ተደቅኖ ለደቂቃዎች አስተከዘኝ።
እነዚህ ሰዎች ለህዝብ እና ለእውነት እንዲሁም ለሰላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲ እውን መሆን የደረሰባቸውን ግፍ ሳስበውና ዛሬ በወንጀል ተጠርጥረው በፍትህ ፊት የሚቆሙት እነ ጃዋር መሀመድ ጥያቄያቸው ሁሉ እንኳን በእስር ላይ ያለ ይቅርና በነጻነት የሚንቀሳቀሰው ዜጋ እንኳ የማያገኘውን “በኢንተርኔት ማውራት አልቻልንም” ጥያቄ ስሰማ አንድም “የፍትህ ሂደቱ እውን በዚህ ደረጃ ዴሞክራሲያዊነትን ተላበሰ?” የሚል ጥያቄ ሲያጭርብኝ፣ አንድም ደግሞ እነ ጃዋር መሀመድ ከህዝብና ከሀገር ፍላጎት አግልለው ራሳቸውን የሰቀሉበት የትምክህት ማማ እነዚህ ሰዎች በእውነትም ራሳቸውን እንደ መንግስት እና ዝንቡን እንደማያባርሩት እንደ ጎሳ መሪ መቁጠራቸው ፍንትው ብሎ ይታየኛል።
Filed in: Amharic