>

አቶ ልደቱ አያሌው ለፍርድ ቤት ያቀረበው የህግ መከራከሪያ ነጥብና የፍትህ ስርዓቱን ውድቀት ያሳየበት ንግግር !! (ሰው መሆን በፍቃዱ)

አቶ ልደቱ አያሌው ለፍርድ ቤት ያቀረበው የህግ መከራከሪያ ነጥብና የፍትህ ስርዓቱን ውድቀት ያሳየበት  ንግግር !!

ሰው መሆን በፍቃዱ

ክቡር ፍርድ ቤት፤ ለመጀመሪያ ቀን በዚህ ችሎት ላይ ስገኝ ከችሎቱ ጀርባ የተፃፈውንና “ተልዕኳችን የህግ የበላይነትን በማስከበር አርዓያ መሆን ነው ” የሚለውን ሳነብ እና ከአሁን ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከስሼ ነፃ ያወጡኝ ፍርድ ቤቶች በመሆናቸው እውነተኛ ፍትህ ከዚህ ችሎት አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡
ዛሬ ግን በዚህ ችሎት ፊት የተገኘሁት ህጋዊ ግዴታዬን ለመወጣትና ለችሎቱ ያለኝን አክብሮት ለመግለፅ እንጂ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ በማድረግ አይደለም፡፡
ክቡር ፍርድ ቤት፤ ይህንን ማለት የተገደድኩት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡-
1ኛ. ለፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠው በምርመራ ሂደቱ ላይ ያሉት ለውጦች በዳኞች እየተመዘኑ ቢሆንም እስካሁን በቀረብኩባቸው አራት ችሎቶች ጉዳዩን ያዩት አራት የተለያዩ ዳኞች በመሆናቸው ምንም ዓይነት የምርመራ ውጤት ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ተከታታይ የጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠብኝ ያለው ከህጉ መንፈስ ውጭ በመሆኑ፣
2ኛ- ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ቀጠሮ እንዳለኝ፣ በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ የልብ ህመም ታማሚ እንደሆንኩ፣ ከህመሜ ጋር በተያያዘም በኮቪድ 19 ቫይረስ ብጠቃ ህይወቴ አደጋ ውስጥ ሊዎድቅ እንደሚችል የህክምና መረጃ አቅርቤ እያለና በፖሊስ የቀረበብኝ ክስ የዋስትና መብት የማያስከለክል ሆኖ እያለ ያለ አግባብ የዋስ መብት ተከልክያለሁ፡፡
ክቡር ፍርድ ቤት ከምገኝበት አሳሳቢ የጤና ችግር በእስር ላይ ከምገኝበት ለኮሮና እጅግ ተጋላጭ የሆነ እስር ቤት አንፃር የተከለከልኩት የዋስትና መብት ሳይሆን የሰው ልጅ መሰረቴዊ መብት የሆነውን በህይወት የመኖር መብቴን ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ገና ወንጀለኛ ተብዬ ሳይፈረድብኝ የሞት ፍርድ እንደተፈረደብኝ መሆኔን ነው፣
3ኛ- በዚኅ በተከበረው ፍርድ ቤት ፊት አሁን እየተከራከርን ያለነው አንድ መንግስት እና አንድ ዜጋ አይደለንም፡፡ በህጉ መሰረት ከሳሽና ተከሳሽ ነን፡፡ ክቡር ፍርድ ቤቱ ለከሳሽና ለተከሳሽ መብት መከበር እኩል መቆም ሲገባው ሁል ጊዜ የከሳሽን ምክንያታዊ ያልሆነ ጥያቄ እየተቀበለ፣ በተቃራኒው ደግሞ የእኔን በመረጃ የተደገፈ ጥያቄ ውድቅ እያደረገ አድሏዊነት እየፈፀመብኝ በመሆኑ፣
4ኛ- በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስናይም ፍትህ እየተሰጠ ያለው ከችሎት አደባባይ ሳይሆን ከ4ኪሎ ቤተ-መንግስት መሆኑን እያየን ነው፡፡ በወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በእስር ላይ የምንገኘው ዜጎች በብዙ ሺዎች የምንቆጠር ሆኖ እያለ፣ ልክ ሁላችንም አንድ ዓይነት ወንጀል እንደሰራንና ጉዳያችን በአንድ ዳኛና ችሎት ብቻ እየታየ እንደሆነ ሁላችንም የዋስ መብት ተነፍገን በተደራራቢ የጊዜ ቀጠሮ መብታችን በጅምላ እየተጣሰ ነው፡፡
ክቡር ፍርድ ቤት፣ እኛ ፍትህ የምንጠብቀ ው ከፍርድ ቤት እንጂ ከሳሻችን ከሆነው የ4ኪሎ መንግስት አይደለም፡፡ የ4ኪሎ መንግስት ሃላፊነት ህግ ማስፈፀም ነው እንጂ ህግ መተርጎም አይደለም፡፡ ክብር ፍርድ ቤት፣ በአጠቃላይ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አራት ነጥቦች የሚያሳዩት የህግ ሳይሆን የፖለቲካ እስረኞች መሆናችንን ነው፡፡
 አሁን በመጨረሻ ፖሊስ ” የሽግግር መንግስት ጥያቄ በማቅረብ መንግስትን የመገልበጥ ሙከራ አድርጓል ” በሚል ክስ ሲያቀርብብኝ መታየቱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።
በዚህ ሁኔታ እውነተኛ ፍትህ ይገኛል ብዬ ስለማልጠብቅ በጊዜ ቀጠሮ እየተመላለስኩ እኔና ጠበቃዬ አጉል ከምንጉላላ፣ ባለሁበት ሆኜ ውሳኔያችሁን መጠበቅ ምርጫዬ ነው!
Filed in: Amharic