>

የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫን እንደታዘብኩት  (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫን እንደታዘብኩት

 ብርሀኑ ተክለያሬድ

በኦሮሚያ ክልል ሐይማኖትንና ብሔርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ከተካሄደ ከ58 ቀናት በኋላ ዛሬ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው መዘግየት ያዘኑና የተከፉ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን እንዳሉ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶሱ የሌሎችን መግለጫ ተከትሎ ነው መግለጫ ያወጣው የሚል ግምት የሰነዘሩም አልጠፉም።(ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን ደረጃ መግለጫ ለመስጠት ተወስኖ መግለጫውን በማዘጋጀትና ቀን በመቁረጥ ላይ ውይይት እንደነበረ ስለማውቅ ይህኛው ግምት ክሹፍ ለመሆኑ ምስክር ነኝ)
የመግለጫው ይዘት ምንድነው?
መግለጫው ከሰኔ 23 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኦርቶዶክሳውያን ላይ በአክራሪዎች፣በመንግስት ሹማምንትና የፀጥታ አካላት ጭምር የደረሰውን አሰቃቂ ግድያና ማፈናቀል የዳሰሰ፣ችግሮችን የዘረዘረና መፍትሄዎችንም የጠቆመ፣ለተጎዱ ኦርቶዶክሳውያን አባታዊ ማበርታትን የለገሰና በጊዜያዊነትም ሆነ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ አቅጣጫ ያስቀመጠና ከእስካሁኖቹ በይዘቱ ጠንከር ያለና የተለየም ነው።
ከእስካሁኖቹ መግለጫዎች በምን ይለያል?
 
   *ድርጊቱን በስሙ የጠራ መግለጹ…
እስካሁን እንዲህ መሰል ተግባራት ሲጠሩበት ከነበረው “ግጭት፣ጉዳት፣ ወዘተ..”ከሚሉት ቃላት ወጥቶ ድርጊቱ “ኦርቶዶክሳውያንን የማፅዳት ተግባር” መሆኑን አስረግጦ ገልጿል። ይህም የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ተከትሎ የተደረገ ይሁን እንጂ ነገር ግን “የመንግስትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነትና የብሄር ፅንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ሀይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈፀሙት ስልታዊና አረመኔያዊ ጥቃት” መሆኑን በመግለፅ ኢላማውም ኦርቶዶክሳውያንን ያደረገ መሆኑን አስገንዝቧል።
      *ቀደምት ጥቃቶችንም የዳሰሰ ነው!
በመግለጫው ከሰኔ 22 ምሽት ጀምሮ የነበረውን ብቻ ሳይሆን በጥቅምት ወርና  (በጃዋር ምናባዊ መከበብ ወቅት) በጥር ወር የጥምቀት በአል ወቅትም የደረሱ ጥቃቶችን ያስታወሰና እስከዛሬ ድረስም ፍትህ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንና አሁንም መንግስት እስካሁን ያደረገውን ጉዳዩን ለህዝብ እንዲገልፅና ትክክለኛ ፍትህ እንዲያሰፍን ያሳሰበ ነው።
   *የችግሩን አስኳል በአግባቡ የተረዳና የገለፀ ነው!
በሀገራችን ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮችና ኩርፊያዎች ሁሉ ቤተክርስቲያንንና ምእመናንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲፈፀሙ “ጊዜው የሽግግር ነው በሽግግር ወቅት ከዚህም በላይ ብዙ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ” እየተባለ ሲታለፍ የነበረ ቢሆንም ይህ መግለጫ ግን ችግሩ የሽግግር ጊዜ ሙቀት እንዳልሆነ በመግለፅና ምክንያቱንም ይፋ በማድረግ የማልበሻ መጋረጃውን ለመጨረሻ ጊዜ የቀደደው÷
“ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው፣ “በሽግግር ላይ የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾኑ፣ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ተርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረና በተደራጀ ስልት የሚፈፀሙ ኦርቶዶክሳውያንን የማፅዳት እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያናችን ትገነዘባለች፡፡ በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚሁ ከቀጠለም የከፋ ፍፃሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች”በማለት ነው።
 *በጥናት ላይ የተመሰረተና በማስረጃ የተደገፈ ነው!
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትንና በርካታ የብዙኃን መገናኛዎችን ጨምሮ 260 ያኽል ልኡካን የተሳተፉበትና ስድስት አህጉረ ስብከትንና 25 ወረዳዎችን የሸፈነ የጉብኝት ጉዞ ተደርጎ ከተጎጂዎች የተወሰደ ቃል፣በቦታው ተገኝቶ ጉዳቱንና ውድመቱን ከዳሰሰ ቡድን የተገኙ የቪድዮና የፎቶ ማስረጃዎችን፣ ከመንግስት አካላት የተገለፀ ሪፖርትንና ሌሎችንም አካትቶ የተዘጋጀና በቀጣይ በሚደረጉ ጥናቶችም እያደገ የሚሄድ መሆኑ የተገለፀበት ነው።
 
መግለጫው ምን ጎድሎታል?
በኔ እምነት እስከዛሬ ድረስ ለሰማእታቱ ይፋዊ የሀዘን ቀን አለመታወጁና በስርዓተ ቤተክርስቲያን የፍትሐት ፀሎት ያልተደረገላቸው መሆኑን በመረዳት “እለተ ሰማእታት” አውጆ ይፋዊ የሀዘንና የፍትሀት ቀን በመላው ዓለም መታወጅ ነበረበት ባይ ነኝ።
በመጨረሻም
ከጥቃቱ እለት ጀምሮ እንቅልፍ አጥታችሁ ጉዳዩን ስትከታተሉ የነበራችሁ ዛሬም ይህን መግለጫ በማዘጋጀት የደከማችሁ አባቶችና ወንድሞች፣ማህበራትና ህብረቶች አቢይና ንኡስ ኮሚቴዎች አምላከ ሰማእታት ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በጉዳዩ እስከፍፃሜ እንድትደርሱም  አፍጣኒተ ረድኤት ድንግል ትቁምላችሁ።
ወፀልዩ ሊተ
Filed in: Amharic