ተልእኮና ትእዛዝ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ‹‹የቤተ ክርስቲያን መምህራን›› እና ‹‹አንቂዎች››
ከይኄይስ እውነቱ
ከዚህ ቀደም ባንድ መጣጥፌ ርጉም ዐቢይ አለቃ የሆነበት ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ መለያዎች ከሆኑት ጠባያቱ አንዱና ዋነኛው ሕዝብ የሚወዳቸውና ላገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ሰዎችን ማምከን እንደሆነ ገልጬአለሁ፡፡ ቊጥራቸው ቀላል የማይባሉ መንፈሳዊውም ሆነ ዓለማዊው ትምህርት የቀሰሙ ‹ፊደል ቆጣሪዎች›› ባመዛኙ ለከርሣቸው በመገዛት በዚህ የምክነት ወጥመድ ውስጥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ገብተዋል፡፡ በጣት የሚቆጠሩቱ በተመደቡበት ተቋማት ለአገዛዙ መሣሪያ ሆነውበስማቸው ብዙ ጥፋት ከፈጸሙ በኋላ ለመሸሽ የሞከሩ አሉ፡፡ በምርጫ ይሁን በአድርባይነት ወይም አልጠግብ ባይነት (ለከት ያጣ ስግብግብነት) ተጠናውቶአቸው እየተርመጠመጡ ያሉና በመሸጦነት የቀጠሉም አሉ፡፡ ደጋግሜ እንዳልሁት መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዕውቀት ለእውነትና ለጠቅላላው በጎነት እስካልዋለ ድረስ ከክህደት (አገርን፣ ሕዝብን) እና ድንቊርና ልዩነት የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ሕይወት መምራት ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብና ላገር ማፈሪያ መሆን ነው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያን የገጠማት ዘርፈ-ብዙና ፈርጀ-ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ አንዳንዱ በማን አለብኝነት ‹ዝኆን ነን እንሰብራለን› እየተባለ በፉከራ በቀረርቶ የሚፈጸም ግዙፍ ጥፋት ሲሆን፣ ከፊሉ ደግሞ በተጠና መልኩ ሕዝብ ያምንባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን መሣሪያ በማድረግ በረቀቀ መልኩ የሚፈጸም ጥፋት ነው፡፡ የሚገርመው እንቆቅልሽ ግን እነዚህ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የሚሰማሩ ግለሰቦችን ማጋለጡ ባንድ ጊዜ ጣዕምና ምሬትን አዝሎ ፋሺስታዊውን አገዛዝ የሚጠቅም መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለአገዛዙ በመሥራታቸውም ሆነ በመጋለጣቸው (ከሕዝብ እንዲነጠሉ በማድረጉ) ተጠቃሚው አገዛዙ መሆኑ በእጅጉ ያማል፡፡ ዝም ማለቱ ደግሞ የበለጠ ጎጂ ነው፡፡ በመሆኑም ‹ስለ ጽዮን ዝም አንልም› ብለን ወደ ጽሑፋችን እንገባለን፡፡
በዚህ ጽሑፍ የምናነሳቸው (በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ሕይወት የተሰማሩ) ‹ታዋቂ፣ አንቱ የተባሉና ተጽእኖ ሊፈጥሩ› የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መምህርነትና ሰባኪነት የተሰለፉት የጠመመውን ለማቅናት÷ የጎደለውን ለመሙላት÷ ምእመናንን ለንስሓ ለማብቃት የሚተጉ ይመስላል፡፡ ባንደበተ ርቱዕነት÷ በተሸከሙት ማዕርግ÷ በያዙትም ዕውቀትየሚታሙ ባለመሆናቸው ብዙዎች አይጠረጥሩአቸውም፡፡ በአገዛዙ የሚጎነጎነው ሴራና ደባ የገባው ኧረ ባካችሁ እነዚህ ‹የቤተ ክርስቲያን ናቸው› ያልናቸው ‹መምህራን/ሰባክያን› ለአገዛዙ መሸጦዎች ሆነዋልና እናስተውል ብሎ ሲናገር፣ አእላፍ መንጋ ተከታዮችን በማበጀታቸው ከስም ማጥፋት ጀምሮ ድንጋይ ለመጫን ሲሯሯጡ ስናይ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት እንደተናገረው ክቡሩ ሰው ግዕዛን ከሌላቸው እንስሳት በታች መሆኑ ያሳዝነናል ብሎም ያበሳጨናል፡፡
ባንፃሩም ዓለማዊውን ዕውቀትና በትምህርት የሚገኝ ከፍተኛ ማዕርግ ይዘው፣ ላገር ዕድገትና ልማት የሚጨነቁና የሚያስቡ መስለው አገርን ከሚያፈርሱት የጥፋት ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሠሩ የምናገኛቸውም አሉ፤ እንደ ዳኛቸውአሰፋ (ዶ/ር)፣ የአአዩ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) – ተልእኮ ተሰጥቶት አአዩን እያፈረሰ ያለ እና ‹‹የምክክር ኮሚሽን›› እየተባለ የሚጠራውን የማጭበርበሪያ አካል የሚመራው ሰው ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
አንዳንዱ አጭበርባሪ ደግሞ እምነትን ወይም ሞያን ታኮ የሰዎችን የግልም ሆነ ሙያዊ ሕይወት ለማነቃቃት፣ ለማበረታታት፣ አዎንታዊ በሆነ መልኩ አስተሳሰብን ለመቀየር፣ በጎ ለውጥን ለማምጣት በሚመስል በማር የተለወሰ መርዛማ ንግግር (so-called motivational speech) ባገኘበት መድረክ ሁሉ እየጮኸ ሕዝብን በማደንዘዝ ለፋሺስታዊ ጐሣ አገዛዞች የሚያመቻች አለ፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ መልኩ የተሰማሩ ራሳቸውን ‹የኅብረተሰብ አንቂ› ብለው የሰየሙ ግለሰቦች አብዛኞቹ እምነትም ሆነ ሞያ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ለመታለል የተዘጋጀ በቂ የኅብረተሰብ ክፍል አለና፡፡
አንዳንዶች ደግሞ በ‹ጎበዞቹ› ቦታ ተደብቀው፣ ለሆዳቸውተገዝተው ከወዲሁ በሥልጣን ሰክረው፣ በኢትዮጵያ የዘረኝነትንአገዛዝ ካቆመ ወያኔ/ሕዋሓት ጋር ኅብረት ፈጥረው፣ ጊዜ ጠብቆ ከሚያጠፋቸው ከርጉም ዐቢይ የሚገኝ ፍርፋሪ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ የዐምሐራ ሕዝብ ዕባጮች ናቸው፡፡ የሕዝብን ህልውናና የአገርን አንድነት ለማስጠበቅ እየተዋደቁ በሚገኙ ፋኖዎች ሕይወት እየቆመሩ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን ‹የምውታን ስብስብ› ለሆነው የአፍሪቃ ኅብረት (በትእዛዝ ጦማር አዘጋጅተው)የአዞ እምባ ሲያነቡ ተስተውለዋል፡፡ በዚህም መሸጦነታቸውን በይፋ አስመስክረዋል፡፡ ከውስጥና ከውጭ ተቀናጅተው የፋሺስቶቹ ተልእኮና ትእዛዝ ፈጻሚ በመሆን የሕዝብን ሰቆቃና የነፃነትን ቀን እያራዘሙ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህን ከሃዲ ባንዳዎች ማንነት አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው በመሆኑ በስማቸው (ዘመነ ካሤ ከነ ጭፍራው፣ ዐሥረስ ማረ ከነ ጭፍራው፣ መዓዛ መሐመድከነ ግብር አበሮቿ) እንጠራቸዋለን፡፡
ኅብረተሰባችን እንደዚህ ዓይነቱ የግብረ ገብና መልካም ሥነ ምግባር ድቀትና መበስበስ ላይ (spiritual and ethical decadence) ያደረሰው ምክንያት ምን እንደሆነ ራሱን ችሎ እውነተኛ በሆኑ በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ጠበብቶች ሊጠና የሚገባው ይመስለኛል፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ከአገዛዙ የሚሰጡ ተልእኮና ትእዛዝ በምን መልኩ በረቀቀ ሁናቴ እንደሚፈጸሙ ማሳያ የሚሆኑ አንድ/ሁለት ጉዳዮችን ላንሳ፡፡
1ኛ/ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ሴሌብሪቲ መምህራን እና ሰባክያን› በማኅበራዊው ሚዲያ በአንድ ዓይነት ርእሰ ጉዳይ ለምእመናን/ለሕዝብ መልእክት ሲተላለፍ እንሰማለን፡፡ የመልእክቱ ወይም ‹የምክሩ› ርእስ እንደሚከተለው ቀርቧል፤
‹‹ዝም ማለት ልመዱ›› (ዲ/ን ሄኖክ)
‹‹ዝም ስትሉ ሁሉም ይሳካል›› (ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን)
‹‹ዝም ማለትን ልመዱ›› (መጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ)
ይህ መልእክት በርእስነትም ሆነ በይዘት ደረጃ እነዚህን ግለሰቦች የማይወክልና ዝግጅቱ በስማቸው የተቀነባበረ ከሆነ የማስተባበል መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ በዚህ አስተያት አቅራቢ ዕውቀት እስካሁን አይመለከተንም የሚል ማስተባበያ አላየሁም፡፡ የኔ ትኩረት የመልእክቱ ይዘት ትክክል ነው/አይደለም የሚለው ላይ አይደለም፡፡ሐሳብን (መንፈሳዊም ይሁን ሥጋዊ) በነፃነት የማስተላለፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ተፈጥሮአዊ ሥጦታ ማንም የሚፈቅደው ወይም የሚከለክለው ጉዳይ አለመሆኑን በመዘንጋትም አይደለም (በርግጥ ‹ለጋራ ጥቅምና ደኅንነት› በሚል በዓለማዊ ሕግ የሚደረጉ ገደቦች እንዳሉ ይታወቃል)፡፡ የኃይለ ቃሉ ምርጫ፣ የርእሱ ወጥነት፣ የሐሳቡ መደጋገም፣ የመልእክት አስተላላፊዎቹ ማንነት፣ ከይዘቱ ይልቅ ኃይለ ቃሉ ለሕዝብ የሚያስተላልፈው አንደምታ (‹‹ዝም በሉ››) መልክ (pattern) ያለው መሆኑ ከአንድ የተደራጀ አካል የተሰጠ ተልእኮና ትእዛዝ መሆኑ ከጥርጣሬ በላይ የሚያሳምን ነው፡፡
ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተባለ ክቡሩ የሰው ልጅ በእምነቱና በነገድ ማንነቱ፣ አገርና ቤተ ክርስቲያን ከነ መልካም ዕሤቶቻቸውና ቅርሳቸው እየፈረሱ ያሉበት ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ውስጥ መኖራችን የሚታወቅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ግዙፍ ጥፋት በሚፈጸምበት አገር የአገሩ ባለቤት የሆነ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ ‹አገር› የተሰኘች የኢኦተቤክ ምእናን በተለይ እንዴት ነው ‹ዝም› የምንለው? ዝምታ ‹ወርቅ› የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ‹ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል› የሚለው ብሂልም የኛው ነው፡፡ ቅፅረ ኢያሪኮ ‹በጩኸት› መፍረሱን አንዘንጋ፡፡ የዘረኛነት፣ የበደል፣ የግፍ፣ የርኵሰት፣ የነውረኛነት ወዘተ. ቅፅር በዝምታ ሳይሆን በጩኸት ይፈርሳል፡፡ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የአራት ቀን ሬሳ የነበረውን አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣ የሐዋርያቱ ድርሻ ከመቃብሩ ላይ ‹ደንጋዩን› ማንሣት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ውስጥ የሰው ልጆች ድርሻ አላቸው፡፡ ‹መጮኽ› አንዱ ድርሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀኬተኛ ሆነን ከሰማይ ‹መና› እንዲወርድልን አንጠብቅ፡፡ እንደ ሕዝብ በድነን ከምንገኝበት የፍርኀት፣ የድንዛዜ፣ ያለመተማመን፣ የልዩነት፣ የአድርባይነት፣ የከርሣምነት፣ ባጠቃላይ የጭቆና ‹መቃብር› ፈንቅለን ለመውጣት ከሚያስደነግጥ ዝምታ ተላቅቀን ቢያንስ እምቢ ብሎ መጮኽ የግድ ያስፈልጋል፡፡
በርእሰ መጻሕፍቱ ‹‹ስለ ጽዮን ዝም አልልም›› (ኢሳይያስ62÷1) የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ሊቃውንት አባቶች እንደሚያስተምሩን ጽዮን የሚለው ቃል የተለያዩ መንፈሳዊ ትርጕሞች አሉት፡፡ በዚህ ጽሑፍ ቃሉን የተጠቀምሁት ቤተ ክርስቲያን፣ አገርና አምባ መጠጊያ በሚለው ፍቺ ነው፡፡
የሰማያዊት ኢየሩሳሌም (መንግሥተ ሰማያት) ምሳሌ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጽዮን ናት፡፡ የኢኦተቤክ ‹አገር› ናት፡፡ እሷ ስትደፈር፣ አገልጋዮቿና ምእመኖቿ ሲገደሉ÷ ሲሳደዱ÷ ሲዋረዱ፣ ቤተ መቅደሷ ከነ ታሪኳና ቅርሶቿ ሲወድሙ ዝም አንልም፡፡ እንጮኸለን፡፡ እሷ በሥጋም በነፍስም አምባ መጠጊያችን ናትና፡፡ ከልደት እስከ ሞት በክብር ተቀብላ በክብር የምንሸኝባትና የምናርፍባት ቅድስት ስፍራ ናትና፡፡
ባንፃሩም ለእመቤታችን በዐሥራትነት፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በግብዝና የተሰጠች፣ ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኳት ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የሁላችን ሰፊ ‹መቅደሳችን› ‹ጽዮን› ናት፡፡ ተወልደን እትብታችን የሚቀበርባት፣ ድኸን ተጫውተንየምናድግባት፣ ተምረን÷ ተድረን ተኩለን÷ ወልደን ከብደንለማዕርግ የምንበቃባት፣ አርሰን ቆፍረን÷ ነግደን አትርፈንየምንከብርባት፣ብንደስት የምንቦርቅባት÷ ብናዝን ብንተክዝ የምንቆዝምባት፣ ብናረጅ የምንጦርባት፣ ዐረፍተ ዘመን ቢገታን በክብር የምንቀበርባት የጋራ ‹ቤታችን› ናት፡፡ አምባ መጠጊያችን ‹ጽዮን› ናት፡፡ ይህቺን ‹የጋራ ቤታችንን› ላፍርሳት የሚል የውስጥም ሆነ የውጭ ጣላት ሲመጣ እምቢ ብለን መጮኽ ግዴታችን ነው፡፡ ‹ስለ ጽዮን ዝም አንልም›፡፡
ያለንበት ጊዜ ግፍና በደልን እምቢ አሻፈረኝ በቃን የምንልበት እንጂ የ‹ዝምታ› ጊዜ አይደለም፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ያለ ቦታውናያለአግባብ መሣሪያ አድርጎ ጭቆናን እና ባርነትን ለመሸከም ዝም በሉ የምንባልበት አይደለም፡፡ ጊዜን ያልዋጀ የአገዛዞችን ድብቅ ተልእኮና ትእዛዝ የያዘ አደንዛዥ ‹መልእክት› ነው፡፡ ጥብዐቱ ካላችሁ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ያሉበትን ሁናቴ ያገናዘበ ትምህርትና ስብከት መስጠት የእውነተኛ መምህራንና ሰባክያን ኃላፊነት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነፃነትና መብቱ በዓላውያን አገዛዞች የተገፈፈበትን ሕዝብ እንዲያስመልስ አንደበትህን ዝጋ ሳይሆን አጥብቀህ ጩኽ የሚል መልእክት የምናሰማበት ጊዜ ነው፡፡ ዘመንን የመዋጀት አንዱ ትርጕም ይህ ይመስለኛል፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያትን ስምና ሥልጣን ተሸክመን እግዚአብሔር በደሙ ለዋጃት ‹ቤተ ክርስቲያን› መሰናከያ ደንጊያ ባንሆን መልካም ነው፡፡ ‹ስለ ጽዮን ዝምን አንልም›፡፡
ይህን ክፍል የምቋጨው በዚህ ዓይነቱ የምእምናንን/የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ የማስቀየር ተልእኮና ትዝዛዝ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሌሎችም ግለሰቦች መኖራቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሳልጠቅሰው የማላልፈው በአንድ ወቅት ካረፉ ጳጳስ በውርስ በሚልዮን የሚቆጠር ብር የወሰደ ‹መምህርም› ይገኝበታል፡፡ ከሌላም እምነት ተከታዮችም በርካታ መሸጦዎች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከእነዚህ መካከል ወዳጄነህ (ዶ/ር) የሚባለው ዘባራቂ፣ ‹ፓስተር› ዮናታን፣ ኢዩ ጩፋ የሚባሉ አጭበርባሪዎች ከ ‹ፕሮቴስታንት እምነት› ተከታዮች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከእስልምናውም እነ አሕመዲን ጀበልና ግብረ አበሮቹጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የኋለኞቹን በአጃቢነት ብጠቅሳቸውም በድርጊታቸው አምነውበት የሚንቀሳቀሱ የአገዛዙ ሰዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
2ኛ/ በቅርቡ በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) በሚታወቅበት ስሙ “I show speed” በመደበኛ ስሙ ዳረን ጄሰን ዋትኪንሰ ጁንየር የተባለ,አንድ ‹ታዋቂ አሜሪካዊ ዩቱበር› ዐዲስ አበባ እንደመጣ ተሰምቶ ነበር፡፡ ‹ታዋቂ› ያልሁት ለግልቡ ትውልድ ነው፡፡ ዓመፀኛና ጠማማ ትውልድ የሚገኝበት ዘመን ላይ ደርሰን ፊደል ቆጣሪውም ሆነ ሥራ ፈቱ ‹ዩቱበር› ሆኖ ተከታይ በማፍራት ገንዘብ መሰብሰብን ዋና መተዳደሪያ እያደረገው ይገኛል፡፡ ‹በሽታው› እንደ ወረርሽኝ በዓለም ተዛምቶ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ሆኑ ሠራተኞች ገንዘብ ያስገኛሉ ብለው ባመኑባቸው ግዙፍ ኩባንያዎች በፈጠሯቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ይህ ከወደ አሜሪካ የመጣው ወጣት በዐዲስ አበባ ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እና በመርካቶ ተገኝቶ ግርግር ፈጥሮ ሔዶአል፡፡ የተከታዮቹን ቊጥር የመጨመር ተልእኮውን ግን ያሳካ ይመስላል፡፡ የሚያሳዝነው የቅድስት ሥላሴ አስተዳዳሪና ካህናት እንግዳ ይመጣል ተቀበሉ ተብለው ቤተ ክህነቱን ከተቆጣጠሩት የርጉም ዐቢይ ቅጥረኛ ሥራ አስኪያጅ የታዘዙ ሲሆን፣ ሥራ አስኪያጁም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ቀጭን ትእዛዝ እንደደረሰው ተሰምቷል፡፡ ይህንኑ ትእዛዝ ለካቴድራሉ ሲያወርድ እንደተለመደው ካህናት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰውና የመጾር መስቀል ይዘው አንድ አልቦ እግዚአብሔር የሆነ (atheist) ‹ተራ ዱርዬ› ተቀብለዋል፡፡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም እንዲዘል እንዲቦርቅ ተፈቅዶለታል፡፡ በየአገሩ እየዞረ የሚገኘው ይህ ወጣት ማን ጋብዞትና በምን ምክንያት እንደመጣ ግልጽ ባይሆንም በአገዛዙ በኩል ያጠፉትን አገር የ‹ገጽታ ግንባታ› ሥራ አካል ነው የሚል ሥላቅ ተሰምቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ‹ሴሌብሪቲ መምህራን› መካከል አንዱ የሆነው መሐእ. ‹ሰይፉ ሾው› በሚባለው ፕሮግራም ቀርቦ ለሃይማኖትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ መስሎ የሠራው ድራማ የአገዛዙ ተልእኮና ትእዛዝ ምን ያህል የታሰበበት መሆኑን ምእመናን ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዋረድ አንድ ተጨማሪ ነውር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሰይፉ የሚባለውም ግለሰብ አገዛዙ በፈለገ ጊዜ የሚጠቀምበት መሸጦ ነው፡፡ ለርጉም ዐቢይ ቅርብ የሆነው መምህር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪና ካህናትን ለመተቸት የሞራል ብቃት የለውም፡፡ እንደ አብዛኛው የቤተ ክህነቱ ሰዎች ሥልጣነ ክህነቱን ለገንዘብ መሰብሰቢያ÷ ለሀብት ማደራጃ አድርጎ እየተጠቀመ ያለ፣ ምእመኑም ከትምህርቱ ይልቅ ቀልዱን እና ‹ማዝናናቱን› ፈልጎ የሚሰበሰበው በርካታ ነው፡፡የአገዛዙን ትእዛዝና ተልእኮ ፈጻሚ ካህናት ጥቂት አይደሉም፡፡ ስማቸውንና ምን አደረጉ የሚለውን ለመዘርዘር ለጊዜው እታቀባለሁ፡፡ ሕፀፁ ለጊዜው የሃይማኖት አይደለም፡፡ ፈጻሚዎቹ ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ ከሰው ትችትና ነቀፋ ይልቅ እናገለግለዋለን ያላችሁትን የሰማይና ምድር ንጉሥ ፈርታችሁ ሕሊናችሁንታዳምጡ እንደሆነ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ምእመናንን መናቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ምን እየተደረገ እንደሆነ ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ የእናንተ ጊዜያዊ ትኩረት በጭፍን የሚከተላችሁና የሚያጨብጭብላችሁ መንጋ ጋር ነው፡፡ በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን ከእናንተም በማዕርግ ከፍ ያሉትን ለፋሺስቶች ያደሩትንየቤተ ክህነቱን ሹማምንት፣ ‹ሊቃነ ጳጳሳት› ያውቃቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ያዋረደውን ማንም ከፍ ሊያደርገው አይችልም፡፡ከዐላውያኑ ጋር የተርመጠመጠ ሁሉ ራሱንና ቤተ ክርስቲያኒቱን አዋርዷል፡፡
በመግቢያዬ እንደገለጽሁት ዝም በማለትም ሆነ በማጋለጡ ተጠቃሚው አገዛዙ ቢሆንም፣ እነዚህ መሸጦዎች ልብ የሚገዙ ከሆነ የማስጠንቀቂያ ደወል ስለሚሆናቸው ‹ስለ ጽዮን ዝም አንልም›፡፡























