ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ፣ (አፋብን) ውስጥ ተሰጥቷቸው የነበረውን የፖሊት ቢሮ አባልነት ቦታ እንደማይቀበሉ አሳወቁ

ታዋቂው ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ፣ በቅርቡ ውህደት ፈጥሮ በተመሰረተው “የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ” (አፋብን) ውስጥ ተሰጥቷቸው የነበረውን የፖሊት ቢሮ አባልነት ቦታ እንደማይቀበሉ እና በምትካቸው ሌላ ሰው እንዲተካ ጠየቁ።

አርበኛ እስክንድር ይህንን ያስታወቁት ዛሬ ጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ለንቅናቄው ፖሊት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው ላይ የድርጅቱን መመስረት “በደስታ እንደተቀበሉት” የገለጹት አቶ እስክንድር፣ የታሪካዊው ድርጅት አካል በመሆናቸው ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ሆኖም ግን፣ በአዲሱ የውህድ ድርጅት ውስጥ በአመራርነት (በፖሊት ቢሮ አባልነት) የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው በግልጽ አስቀምጠዋል። “በአዲሱ ውህድ ድርጅታችን ውስጥ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኜ መሥራት እንደማልችል ታውቆ፣ በተመደብኹበት ቦታ ላይ ሌላ ሰው እንዲተካ አሳስባለኹ” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ከአመራርነት ለመልቀቅ ቢወስኑም፣ ከትግሉ እንደማይለዩ አቶ እስክንድር አረጋግጠዋል። “እንደ ተራ የድርጅት አባልነቴ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምቀጥል እና የሚጠበቁብኝን ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች በሙሉ እንደምፈፅም አረጋግጣለኹ” ሲሉ ለንቅናቄው ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

በመጨረሻም አዲሱ አመራር የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በስኬት እንዲወጣ ልባዊ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች መካከል ሲደረግ የነበረውን የውህደት ሂደት ተከትሎ የተመሰረተ ሲሆን፣ አቶ እስክንድር ነጋ በዚህ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ከአመራርነት ለመገለል የወሰኑበትን ዝርዝር ምክንያት በደብዳቤው ላይ አልጠቀሱም።

የታላቁ አርበኛ እስክንድር ደብዳቤ

ለአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ፖሊት ቢ

ጥር 12፣ 2018 ዓ.ም

በቅድሚያ፣ በአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ምስረታ የተሰማኝን ደስታ መግለፅ እወዳለኹ። የዚህ ታሪካዊ ድርጅት ምስረታ አካል በመሆኔ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።

በአዲሱ ውህድ ድርጅታችን ውስጥ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኜ መሥራት እንደማልችል ታውቆ፣ በተመደብኹበት ቦታ ላይ ሌላ ሰው እንዲተካ አሳስባለኹ።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተራ የድርጅት አባልነቴ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምቀጥል እና የሚጠበቁብኝን ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች በሙሉ እንደምፈፅም በዚህ አጋጣሚ አረጋግጣለኹ።

በመጨረሻም፣ ድርጅታችን አፋብን እና አዲሱ አመራር የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በሰኬት እንዲወጡ ልባዊ እና ጓዳዊ ምኞቴን እገልፃለሁ።

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር ፣
እስክንድር ነጋ።
ጥር 12፣ 2018 ዓ.ም።

ጋሻ ሚዲያ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.