አርበኛ ጌራወርቅ ወርቁ
በቅድሚያ፣ የእራሱን ቤት እያነደደ፣ ነዲዱን በመሞቅ ከሚጨፍረዉ ወገን እንዳይደለን ይታወቅልን።
የእኛ አላማ የአማራን ህልዉና ማስጠበቅ እና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ማቆም ነበር፤ ነገር ግን የወንበር አንካሳዎቹ አካሄዳችን ሁሉ ወደ ቁልቁለቱ አድርገዉብናል። የታየንን እና የምናዉቀዉን እንዳንናገርም “እሻ” ባዩ በዝቷል። ብርሃነ መስቀል ረዳ ወተት እያጠጣ ባሳደገዉ ኢህአፓ መነከሱን ባናጣዉም፤ አብርሃም ተወልደ በወለደዉ ሻቢያ መበላቱን ባንስተዉም፤ በእፉኝቶቹ አሳበን ባርነትን ልንለማመደዉ ግን አንችልም፤ ስለሆነም ያለመሳቀቅ ለህዝባችን የሚበጀዉን ብቻ እናደርጋለን።
አካሄዳችን ቆም ተብሎ መገምገም አለበት፤ ጉዟችን ካለፈዉም ሆነ ካለዉ በከፋዉ ሆኗል። የያዝነዉ መንገድም አማራን የሚታደግ እና ሀገር የሚያቆም ሳይሆን፣ አማራን የሚበታትን እና ሀገር የሚያፈርስ እየሆነ መጥቷል፤ መጓዝ ካለብን በርዕዮተ ዓለም እና በፖለቲካዉ መስመር መሆን አለበት፤ ከዚያ ባለፈ፣ በኢምፕሪሲስትነት ወይንም ደግሞ በአቦ ሰጠኝነት የሚደረግ ጉዞ መዳረሻዉ ገደል ነዉ፤ ህዝባዊ ድርጅት በግለሰብ ስሜት የሚመራ ከሆነም ርዮተ ፖለቲካዊ ችግር ይወልዳል፤ እዳፊዉም ለህዝብ ይተርፋል፤ ወዳጅ ሲበጅም ሆነ ጠላት ሲፈረጅ ደግሞ በመርህ እና በሁኔታ ትንተና ሊሆን ግድ ነዉ፤ ካልሆነ ግን ወዳጅ ባሉት መጥፋት፣ ጠላት ባሉት መናቅ ይመጣል፤ ቢያንስ ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገ፣ የሚባሉ ማያወችን፣ ከመተቃቀፍም ሆነ ከመኮራረፍ በፊት ተንትኖ ማየት ያስፈልጋል።
በመሆኑም፥ አሁን በአለዉ ነባራዊ እዉነት፥ ህወሓት ለአማራዉ አጋር ትሆናለች ወይንስ ፈተና? የሚለዉን በጥኋት አዕምሮ፣ በተዉጣጣ የተተነተነ ሀሳብ ማየቱ ተገቢ ይሆናል።
ህወሓትን “በፖለቲካዉ አለም፣ ዘላቂ ወዳጅነትም ሆነ ጠላትነት የለም” በሚል ‘ Cognitive dissonance ‘ ከአማራዉ ትግል ጋር ልታዋድዳት የምትችል ፍጥረት አይደለችም። ከብዙዉ በጥቂቱ ምክናያት ብናነሳ፦
ሀ. ህወሓት የህዝብ ወንጀለኛ ናት፤ ካለፈ ሀፂያቷም ሆነ ወንጀሏ ትንፃ ቢባል እንኳ፣ ስልጣኑ የግለሰቦች ሳይሆን የአማራ ህዝብ፣ አለፍ ሲልም የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ።
ለ. ብዙዉ ፍላጎቷ የአማራ የሆነዉ ስለሆነ፤ ከማይዳሰሰዉ ብዙዉ ፍላጎቷ፣ የሚዳሰሰዉን ጥቂት ብናወሳ፣ ህወሓት ከራያ፣ ጠለምት እና ወልቃይት ወሰኖቻችን ጋር በተያያዘ የማይታረቅ ‘የእኔ’ ባይ ፍላጎት አላት፤ ይሄን እዉነት እያወቅህ አብሬያት ልጎዝ ብትል ግን እስኪመቻት ወይ ደግሞ ገዢ ቦታ እስክታመቻች ብቻ ይሆናል፤ የተመቻት እና ቦታ የያዘች ጊዜ ግን ፏጭራ ማድማት ብቻ ሳይሆን ነክሳ ትበላሀለች፤ ያንተ የሆነዉንም ትወስዳለች።
ሐ. ሀይል ስለምትበትንብህ፤ ህወሓትን በታሪካዊ ጠላትነት የሚፈርጀዉ እና የማያምነዉ የእራስ አካል እልፍ ነዉ፤ ይሄ ሀቅ ባለበት ዘሎ መተቃቀፉ፣ ከጀርባ የሚያኮርፉ የእራስ ሀይሎችን ያሳጣል፤ በእሩቅ ያለዉን በመመኜት የእጅን መጣል ደግሞ ታሪካዊም ሆነ ርዮተ ፖለቲካዊ ድጋፍ የለዉም።
መ. ያልተቋጩ ጉዳዮች ስላሉ፤ ከብዙ ያልተቋጨዉ ጉዳያችን መካከል አንዱ የሆነዉን የክስ ጉዳይ ብናይ፥ በኢትዮ ህወሓቱ ጦርነት፣ ህወሓት “ጀኖሳይድ” ተፈፅሞብኛል የሚል ክስ አላት፤ ከተከሳሾቹ መካከልም፣ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ አንዱ ነዉ፤ ስለሆነም ይሄ እድፍ ባለበት ሁኔታ የሚደረግ ከፊል መላላስ፣ ነገን ካለማየት የሚደረግ የስካር ጨዋታ ነዉ።
ሠ. ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ጥቅሟ ሲሰላ ከዜሮ በታች በመሆኑ፤ ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በትግራይ ህዝብ ተፈትና የወደቀች፣ ይሄንን ታደርግልኛለች ከምትለዉ ታደርግብኛለች የምትለዉ የሚበዛ፣ እንኳን ለሌላ ለእራሷ መሆን ያቃታት፣ በሀሳብም ሆነ በቁስ የዛለች፣ አቅም የሌላት የስጋት ድርጅት ናት፤ ስለሆነም ከአጋርነት የጥቅም ስሌት አኳያ አጋር መሆን አትችልም።
ረ.
ሰ.
ጰ. ብዙ ዝርዝር የመሆን ምክናያቶች እንዳሉ ሆነዉ፣ ገዢዉ እና ዋናዉ ምክናያት ደግሞ፣ ትግላዊ ተቃርኖዉ ነዉ፤ ህወሓት የምትታገለዉ፣ ስርዓት ለመቀየር ሳይሆን ሀገሮችን ለማዋለድ ወይንም ደግሞ ሀገር ለማፍረስ ነዉ፤ የእኛ ትግል ደግሞ ስርዓት ለመቀየር እንጂ ሀገር ለመሆን ወይንም ደግሞ ሀገር ለማፍረስ አይደለም።
ስለሆነም ከህወሓት ጋር የሚያጣብቀን፣ ወታደራዊ አፈጣጠርም ሆነ ፖለቲካዊ ዳሀራ የለንም፤ እዉነታዉን በመቃረን የሚደረግን መርህ አልባ እና ጥቅም አልባ ግንኙነትም እናወግዛለን፤ ከመጪዉ ታሪካዊ ተጠየቅ ለመዳንም፣ እንደ ጲላጦስ እጃችን ከደሙ ታጥበናል፤ ይሄንን ሰፊዉ ህዝባችን እና ለፍቶ አዳሪዉ ጦራችን ይወቅልን።
“ከሰላምታ ጋር”
አርበኛ ጌራወርቅ ወርቁ

























