>
2:00 pm - Tuesday June 6, 2023

ይፋ የሆነው የአእምሮ ብልህነት (IQ)  ውጤት እና የኢትዮጵያ ደረጃ...!!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ይፋ የሆነው የአእምሮ ብልህነት (IQ)  ውጤት እና የኢትዮጵያ ደረጃ…!!! 

አቻምየለህ ታምሩ

የዘርፉ ምሑራን እንደሚሉት የአእምሮ ብልህነት (Intelligent Quotient / IQ) ማለት የአእምሮ እውቀት መጠንንና አንድን እውቀት የመገንዘብን ብቃት የሚያሳይ መለኪያ ነው። አንድ በወጣ  የIQ ሪፖርት ላይ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የIQ ደረጃ ከአለም ዝቅተኛ እና አንድ አገር ብቻ እንደሚበልጡ ያሳያል። ይህንን የIQ ደረጃችንን የሚያሳየውን ሪፖርት የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ግን ሲገረሙ ተመልክቻለሁ። በርግጥ እኔም ተገርሜያለሁ።
የኔና የሌሎች ሰዎች መገረም ግን ለየቅል ነው። ሌሎች ሰዎች የተገረሙት የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የIQ  ደረጃ ይህን ያህል በማሽቆልቆሉና አንድ አገር ብቻ በመብለጣችን ነው። እኔ ግን የተገረምሁት አንድ አገርም ቢሆን በመብለጣችን ነው። እንደ እኛ ያለ አእምሮ ያለው ሕዝብና አገር ከመጨረሻው  ሁለተኛ መውጣታችን በእጅጉ የሚያስገርም ነው። ከኛ የባሰ “ደደብ” አገርና እና  ሕዝብ አለ ወይ ያሰኛል።
–  በዓለም ታላላቅ መድረክ ሁሉ ልቀው በመገኘት ያስከበሩንን አክሊሉዎችን ያለ ፍርድ የረሸንን፤
-“የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ልዩነት የሌለው አንድ ቤተሰብ ነው” የሚል መርኅ ይዘው ከ14 ዓመታቸው ጀምረው በግፍ እስኪታረዱ ድረስ  ሁሉን ጎሳና ሃይማኖት እኩል እያሳደሩ ሥርዓት ፈጥረው ሲመሩን የነበሩና በዓለም መድረክ የተከበሩ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ትልቅ ሰው ለመባል የበቁ መሪያችንን ከታክሲ ነጂ እስከ ፕሮፌሰር ድረስ ተባብረን  “ሌባ! ሌባ!” እያልን እንዳይሆን አድርገን አዋርደን በጭቃኔ አፍነን የገድልን ፤ ጎሳና  ሃይማኖት ሳንለይ “እሰይ! ይበላቸው”  እያልን በግፍ መገደላቸውን ለማክበር  ለዘፈንና  ፈንጠዝያ አደባባይ የወጣን፤
–  የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ አገር ያለ ባሕር በር እንዲቀርንንና የባሕር በራችንን እንድናጣ ከዓለም በፊት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያመለከትን፤ ያገራችን ክፍል እንዲቆረስ በዱር በገደል የተንከራተትና   አገር  እንዲሆን  እጃችንን አውጥተን የመረጥን፤
–  ምጥቀተ- አዕምሮ ያለው መንግስት ያለን አልያም  ለምን የምንል የነገ ውጤቱን ዛሬ ላይ መረዳት የምንችል ህዝቦች ብንሆን ኖሮ አንቀፅ 39 በህገ መንግስቱ ባልተካፕባልተካተተ ነበር
ንቃተ- አዕምሮ ያለው አስተዳደር ቢኖረን ኖሮ የሚያጋጭ የጎሳ ፖለቲካ የህገ መንግስቱ ዋና አካል ባልሆነ ነበር።
–  “ኦሮሞ አይደላችሁም” ብለው የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሴትና የሁለት ሳምንት አራስ በሳንጃ  ያለ ርህራሄ የሚተረትር፤
– ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወይም አማራ ስለሆኑ ብቻ የ70 ዓመት ሽማግሌና የሶስት ዓመት ጨቅላ በዱልዱም የሚያርድ፤
– በዱልዱም ያረዱትን መቃብር የሚቆፍሩና እድሜ ልካቸውን ለፍተው በቋጠሩት ጥሪት የፈጠሩትን ሀብት ዶግ አመድ የሚያደርግ ትውልድ ያላት አገር፤ – – ይህ ሁሉ ሲሆን መለዮ ለብሰው ዝም ብለው የሚያዩና ባብዛኛው የድርጊቱ ተባባሪ የሆኑባት ምድር፤
–  እንኳን ለተፈጠሩበት አገር  ቀርቶ ለጠላት አገር እንኳን  ተባለ ቢባል በሚያስነውር አይነት  አገር ባላቸው ፈረንጆች ምድር እየኖሩ ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበትን ድሀ አገር ግን “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” የሚል ጉድ የተሸከመች አገር፤
– ይህ ሁሉ ሲሆን “የብልፅግና ፓርክ” እና “የቤተ መንግሥት እድሳት” እንደ አንገብጋቢ ጉዳይ በየሜዲያው ዋና ትኩረቱ አድርጎ ሲያስተጋባ የሚውል በመንግሥትነት የተሰየመ አገዛዝ ያላት አገርና እንዲህ አይነት አገዛዝ ተጭኖት ዝም ብሎ የሚያይ  ሕዝብ  የማሰቢያ አእምሮው ትንሽ ነው መባሉ ምኑ ነው የሚደንቅ?
*  እስኪ ከስር ከሚታዮት ፎቶዎች እንደ ሸረሪት ድር የተወሳሰበውን መንገድና በተወሳሰበ ግንድና ድንጋይ የተዘጋውን መንገድ እስተውሉ።
*  የተማሩ ሳጥናኤሎች ሜንጫ ያሸከሙትንና ጉግል ትራከር የተሸከመውን  ወጣት አወዳድሩ። እንዲህ እየኖርን፣ እንዲህ እየመራን፣ እንዲህ እያደረግን በምን መለኪያ ምጥቀተ-አዕምሯችን ከፍ ብሎ ይፈረጅ?
እንዲህ አይነት አገርና ሕዝብ ያለን እኛ ያለም ጉዶች እንዴት ብሎ  የማሰቢያ አእምሮ ደረጃችን አገርና መንግሥት ካላቸው ከኢኳቶሪያል ጊኒዎች ልንበልጥ ቻልን?  በእውነቱ  ኢኳቶሪያል ጊኒዎች እንዴት ብለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ  የባሱ “ደደቦች” ሊሆኑ ቻሉ?
Filed in: Amharic