>

መማሩንስ እንማራለን፤ እንኳን ገዳን የፈረንጁንስ እንማር የለ፤ ግን ...? (ያሬድ ሀይለማርያም)

መማሩንስ እንማራለን፤ እንኳን ገዳን የፈረንጁንስ እንማር የለ፤ ግን …?

ያሬድ ሀይለማርያም

* … ለምን በአዲስ አበባ ብቻ? በመላ አገሪቱስ ለምን አይሰጥም? አዲስ አበቤ ከገዳ የምታገኘውን ልዩ ጥቅም ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አዋሳ፣ አሶሳስ ይጠላባቸዋል ወይ? ገዳ በትምህርት እንዲሰጥ የተጠናስ ከሆነ ጥናቱን ያጠናው ማን ነው? ብልጽግና ወይስ የትምህርት ሚኒስትር? ወይስ ሌላ አካል? ገዳስ ከሌሎቹ የአገሪቱ ባህላዊ ሥርዓቶች ለምን በልዩ ሁኔታ ተመረጠ?
ጎበዝ መማር ምን ይከፋል? ገዳን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸውን እሴቶቻችንን መማር ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። እኔ እድሉን ካገኘሁ ገዳን ጨምሮ የበርካታ የአገራችን ብሔሮችን ባህል፣ ወግ እና ሥርዓት እማራለሁ፤ እመራመራለሁ፤ ጎጂና ጠቃሚውን ለይቼ አወጣለሁ። ጎጂዎቹ እንዲወገዱ፤ ጠቃሚዎቹ እንዲበለጽጉም ጥረት አደርጋለሁ። መማር እና ማወቅ ምን ይከፋል? ነገሩ የሚበላሸው ካድሬ ሲይዘው ብቻ ነው። ካድሬነት እና እውቀት ለየቅል ናቸው። የካድሬ ነገር እንደምታውቁት ውስጡ እውቀት የለውም። ካድሬ የተወረወረለትን ትኩስ አሎሎ ሁሉ ቶሎ ብሎ እንጁን እንዳይፈጀው ወደ ሕዝብ ስለሚወረውር ከካድሬ የመጣን ነገር ሕዝብ ሁሌም በጥርጣሬ እና በጫና መልክ ነው የሚያየው። በእርግጥም ካድሬ ትኩሱን አሎሎ ወርውሮ ዝም አይልም። አሎሎውን አላቅፍ ያለው ላይ ጡንቻውንም ያሳያል። ለዚህም ነው ስርዓት ቢለዋወጥም የካድሬዎች ባህሪ የማይቀየረው።
እና ምን ለማለት ነው፤ ነገርየው በምሁራን ጥናት ተደርጎበታል ወይ? ገዳን ለአዲስ አበቤ ማስተማር ከፖለቲካ ፍጆታ ባለፈ ያለው ፋይዳ በጥናት ተደግፏል ወይ? ወይስ የኦዴፓ-ብልጽግና የፖለቲካ ማሻቀጫ ብቻ ሆኖ ነው የቀረበው? ከፖለቲካ የዘለለ በማህበረሰቡ ስነ ልቦና እና ባህል ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ጥናት ካለ ለምን በአዲስ አበባ ብቻ? በመላ አገሪቱስ ለምን አይሰጥም? አዲስ አበቤ ከገዳ የምታገኘውን ልዩ ጥቅም ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አዋሳ፣ አሶሳስ ይጠላባቸዋል ወይ? ገዳ በትምህርት እንዲሰጥ የተጠናስ ከሆነ ጥናቱን ያጠናው ማን ነው? ብልጽግና ወይስ የትምህርት ሚኒስትር? ወይስ ሌላ አካል? ገዳስ ከሌሎቹ የአገሪቱ ባህላዊ ሥርዓቶች ለምን በልዩ ሁኔታ ተመረጠ?
ሌላው አብሮ መነሳት ያለበት ጥያቄ የገዳ ሥርዓትን የሚመለከተው ትምህርት በራሱ በኦሮሚያ ክልል እስከ አሁን ሲሰጥ ቆይቷል ወይ? ከተሰጠ ምን ጥቅም እና ትርፍ አስገኘ? በእነማን ላይ የባህሪ ለውጥ አመጣ? እነማን የገዳን ትምህርት በመከታተላቸው ምን አደረጉ? ለተጀመረው የለውጥ መነቃቃት ምን አስተዋጾ አበረከተ? ስንት አመትስ በክልሉ ውስጥ እንደ ትምህርት ተሰጠ? የሚለኩ ውጤቶችን አስገኝቷልስ ወይ? ገዳ ሥርአት እንደሚባለው፤ አቃፊ፣ ደጋፊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ መቻቻልን እና ፍቅርን የሚያጸና፣ ሰላምን የሚያጎናጽፍ ከሆነ ለምን ኦሮሚያ ክልል ጥሩ ማሳያ መሆን አቃተው? እነዚህን ትሩፋቶችስ ማን ይጠላል? ግን እነዚህ ሥርዓቱ መገለጫ ተደርገው የሚነገሩት የማህበረሰብ ባህሪያት ለምን የገዳ ባለቤት በሆነው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጎልቶ ሊወጣ አልቻለም? የገዳ አባቶች እንዴት እነዚህን ድንቅ እሴቶች በማህበረሰባቸው ውስጥ በተለይም በወጣቱ አዕምሮ ማስረጽ ተሳናቸው? በክልሉ ውስጥ ውጤቱ በተግባር ያልታየን ነገር ለባህሉ ባዳ በሆነው እና በጎራማይሌ እሴቶች የተጠለፈውን አዲስ አበቤ ላይ ማስረጽስ ይቻላልስ ወይ? ይሄስ በቅጡ ተጠንቷል ወይ?
በአጭሩ የገዳ ሥርዓት እንደ ትምህርት በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም በመላ አገሪቱ ቢሰጥ አልቃወም። መማርም እፈልጋለሁ። ነገር ግን ከላይ ያሉት ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ። በደመነፍስ የሚደረጉ እርምጃዎች የጊዜ እና የገንዘብ ዋጋ ካስከፈሉ በኋላ የውሃ ሽታ ሆነው ሊቀሩ ይችላሉ። ከወጋጎዳ መማር ይበጃል። አገር በእውቀት እና በጥበብ ስትመራ መንገዳችን ሁሉ የብርሃን ይሆናል። ዛሬም አገር በካድሬዎች ቅዠት ብቻ የምትመራ ከሆነ ደግሞ ያው የተለመደውን ሰለሜ ሰለሜ ዳንስ እየደነስን በአገዛዝ አዙሪት ውስጥ ስንሽከረከር እንቆያለን። የዞረበት ትውልድ አልፎ በዞረበት ትውልድ የመተካቱ ሂደትም እንዲሁ ይቀጥላል።
ስለ ገዳ መማርና ማወቅ ግን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ባይሆን ‘አገራዊ ባህሎች’ ወይም ‘አገር በቀል የማህበረሰብ ሥርዓቶች’ የሚል የትምህርት ዘርፍ ከፍቶ እና በቂ ጥናት አድርጎ፤ ገዳ፣ ጨምበለላ፣ እና ሌሎች የማህበረሰብ ትውፊት እና ባህሎች በአገር ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ እንዲሰጡ ቢደረግ ትውልዱም አገሩን በደንብ ያውቃላት፣ ከመደናበርም ይወጣል፣ አገርም ታተርፋለች።
Filed in: Amharic