>
5:13 pm - Sunday April 19, 0387

"ኢትዮጵያ እየፈራረሰች ነውን?" (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

“ኢትዮጵያ እየፈራረሰች ነውን?”

ቴዎድሮስ ሀይለማርያም

ርዕሱን የወሰድኩት የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ካዘጋጀው “Is Ethiopia Breaking Apart?” ከሚለው ፕሮግራም  ነው። ይህ አስደንጋጭ ጥያቄ የሀገራችን ህልውና ክፉኛ አጠራጣሪ ከነበረበት ከ1980ዎቹ መባቻ በኋላ በድጋሚ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ መነጋገሪያ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡
በ1983 ዓ.ም ሀገራችን በወያኔ ፣ ሻዕቢያና ኦነግ እጅ ወድቃ ያለርህራሄ ስትበለት ፣ የህወሃት – ኢህአዴግ አገዛዝ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንንና ግዛቶቻችንን በማናለብኝነት እያሳለፈ ሲሰጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በአቅመ ቢስነት ለመቀበል ተገድዷል፡፡ ከናካቴው ሀገር አፍራሹ ህወሃት ‹‹ይህቺን ሀገር›› ከመበታተን ያዳንኳት እኔ ነኝ ብሎ ለመሳለቅ በቅቷል፡፡
ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ዛሬም ኢትዮጵያውያን በብዙ መስዋዕትነት ሰው በላውን የህወሃት ቡድን ወደ ዋሻው እንዲፈረጥጥ ካደረገ  በኋላ የሀገራቸውን እጣፈንታ ለምድራዊ ይሁን ሰማያዊ ኃይል ለመተው የመረጡ ይመስላል፡፡
*   *    *
   ሀገራችን ከመበታተን አፋፍ ላይ ናት !
ከእንግዲህ ልንሸሸው የማንችለው አንድ ያገጠጠ ሀቅ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በሚያስፈራ የመበታተን አፋፍ ላይ ቆማለች፡፡  ቢያንስ ዓለም ያመነባቸውን ሶስት ቁልፍና ተያያዥ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሀ. ሥርዓት አልበኝነት  
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዘመነ መሣፍንት ወዲህ ያልታየ ጥልቅ ሀገራዊ ክፍፍል ሰፍኗል፡፡ ደካማና ያልተረጋጋ የፖለቲካ ማዕከል ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት በመላው ሀገሪቱ ሥልጣኑን መዘርጋት ፣ መሰረታዊ ህግና ሥርዓት ማስከበር ፣ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አቅቶታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሚታዩት ከማዕከላዊ መንግሥቱ የራቁና በተቀናቃኝነት የተሰለፉ ሥርዓት አልበኛ ቡድኖች ፣ ኃይሎችና አሰላለፎች  መካከል በሀገሪቱ ህልውና ላይ ግንባር ቀደም አደጋ የደቀነው  ህወሃት ነው፡፡ ህወሃት ለማዕከላዊ መንግሥቱ እውቅና ከመንፈግና በትግራይ ‹‹በዲፋክቶ›› ሉዓላዊነት ከመግዛት አልፎ ወደ ‹‹ህጋዊ›› መንግሥትነት የሚሸጋገርበት ህዝባዊ ውሳኔ ለማድረግ ጥቂት ቀናት ይቀሩታል፡፡
ጠ/ሚ አብይ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም!›› ይላሉ፡፡ እሰይ ! ጠላቷ ይፍረስ ! ግን ሀገር በጉልበተኞች እንዳትፈርስ ለማዳን ምን እየሰሩ ነው? መንግሥት የህወሃትን ህገ ወጥ ህዝበ ውሳኔ ለማስቆም በግልፅ የሚወስደው እርምጃ የለም፡፡ ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ጣጣ ለመመከት አንዳችም ነገር ሲያደርግ አይታይም፡፡  ለህዝብ ያቀረበው ሀገር አድን እቅድም ሆነ ጥሪ የለም፡፡ ይህ የንቀት አካሄድ መዳረሻው ምንድነው?
ለ. መረን የለቀቀ አመፅ 
ባለፉት ሁለት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ግጭት ፣  ሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊቶች መቆሚያ አጥተዋል፡፡ ማዕከላዊውና ክልላዊ መንግሥታት ህግና ሥርዓት ማስከበር አለመቻል ብቻ ሳይሆን በሽብር ፣ በዘር ማፅዳትና ዘር ማጥፋት ድርጊቶች ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተሳታፊዎች መሆናቸው ችግሩን ከባድና ውስብስብ  አድርጎታል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል ተደጋግሞ የተከሰተው መንግሥታዊ ከለላና ድጋፍ ያለው የዘር ማጥፋት ድርጊት የሀገሪቱን ታሪካዊና ማህበራዊ ድሮች ክፉኛ እየበጣጠሰ በቀላሉ የማይጠገንበት ደረጃ አድርሶታል፡፡ በቅርቡ በሃጫሉ ግድያ ሰበብ የተፈፀመው ሩዋንዳንና ሶሪያን የሚያስታውስ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊት ሀገሪቱ ምን ያህል በሰላላ ድር እንደተያዘች ያረጋግጣል።
እዚህም ላይ ማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልል መንግሥት ሊያደርጉ ከሚገባቸው ትንሹ የሆነውን የዘር ማጥፋት ድርጊቱን በግልፅ ለማውገዝ እንኳን አቅምና ፈቃደኝነት አልታየባቸውም፡፡ በእውቀትም በቸልተኝነትም የጥቃቱ ተባባሪ የሆነው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች ድርጊቱን በስሙ ጠርተው ለማውገዝ እንኳን ሰብአዊነት አጥተዋል፡፡
ሐ. ወረርሽኝና ችጋር
መንግሥት ከስድስት ወር በፊት የኮሮና ዓለማቀፍ ወረርሽኝን ለመከላከል የጀመረው ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ከመምጣት ይልቅ በግልፅ መዳከሙ ይታያል፡፡ ግራ የተጋባና የመጣውን በፀጋ ለመቀበል የወሰነም ይመስላል፡፡ ጥቂት ሳምንታት በቀሩት አዲስ ዓመት ትምህርት እከፍታለሁ ሲል እንዴት ምን ዝግጅት እንዳደረገ ሚኒስትሮቹም እንኳን እንደማያውቁ እየታዘብን ነው፡፡
በተቃራኒው ወረርሽኙ በመላ ሀገሪቱ እንደ ቋያ እሳት እየተስፋፋ ነው፡፡ የጤና ጥበቃ እለታዊ ዘገባዎች የአሃዝ ጭማሪዎች ሆነዋል፡፡ ህዝብም ወደ ተለመደው አኗኗሩ ተመልሷል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን ከሚያስከትለው ከፍተኛ የህይወት ኪሳራ በተጓዳኝ በቤተሰቦችና ማህበረሰቦች ላይ የሚያደርሰው የምጣኔ ሀብት ድቀት ሲታከልበት  የሀገራችን እጣፈንታ ፅኑ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ መገመት አያዳግትም፡፡
**      **     **
                  ምን ይበጃል?
‹‹እውን ሀገራችን እየፈራረሰች ነውን ?›› የሚለውን እጅግ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ልንጋፈጠው አልቻልንም። በየዋህነትም ይሁን በብልጣብልጥነት ‹‹ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል!›› ፣ ‹‹ዘረኝነት ይጠፋል!›› ፣ ‹‹ሀገራችን አትፈርስም!›› የሚሉት አነጋገሮች ከማስተባበያነት ወይም ከመልካም ምኞት መግለጫነት አያልፉም፡፡
በዚህ ጉዳይ ግንባር ቀደም ሃላፊነት ያለበት ማዕከላዊ መንግሥት መጠየቅ አለበት፡፡ የአብይ መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነትን ከማስከበር ይልቅ ሀገር በጉልበተኞች ስትፈርስ ፣ የንፁሃን አንገት በሜንጫ ሲቀነጠስ ቆሞ መመልከት ከቀጠለ እህል ውሃው አብሮ ያከትማል፡፡
በተለይም መንግሥት ልክ ወያኔ-ኢህአዴግ በ1980ዎቹ መጀመሪያ እንዳደረገው የትግራይ ክልልን ሀገር አፍራሽ ‹‹ምርጫ›› እጁን አጣጥፎ መመልከት ከቀጠለና በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን ያማከለ ግልፅ አቋም በአስቸኳይ ካልወሰደ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብስ አሁንም እንደ 1980ዎቹ ሀገሩ ስትፈራርስ በዝምታ መመልከቱን ይቀጥላል? ሀገርን የሚያክል ነገር በባዶ መፎክርና በግለሰቦች ትክለ ስብእና ተማምኖ ይተዋል? ወይስ የመጣውን የህላዌ አደጋ በመገንዘብ መንግሥት ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ይጠይቃል? ራሱም የመፍትሄው አካል ይሆናል?
በብርሃን ፍጥነት ሊመለሱ የሚገባቸው በርካታ ግዙፍ ጥያቄዎች አሉ!
Filed in: Amharic