>

ታሪክ የፖለቲካ ማሳለጫ መሣርያ ሲሆን....?!? (እውነት ሚድያ)

ታሪክ የፖለቲካ ማሳለጫ መሣርያ ሲሆን….?!?

እውነት ሚድያ
✍️ ስለ አንዲት አገር እጅግ የተራራቁና የተጣረሱ ‹‹ታሪኮች›› ሲጻፉ ይውላሉ፣ ያድራሉ፤ በተለያዩ አካላት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች፡፡ ይህ ትውልድም ሁሉን በጨረፍታ እያነበበና እየሰማ የትኛውን ማመን እንዳለበት ግራ ተጋብቷል፤ በመስቀልኛ ቦታ ላይ ቆሞ ወዴት መታጠፍ እንዳለበት በማለም ላይ ነው፡፡ 
✍️ ታሪካችን ግን የመገናኛ፣ የመነጋገርያና የመግባቢያ ዐውድ እንጂ የእርስ በርስ መናቆርያ (የጦርነት) ሜዳ መሆን አልነበረበትም!
✍️ በተለይ ታሪክ የፖለቲካ መሣርያ ሲሆን ደግሞ ‹‹ለታመመ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት›› የሚለው ብያኔው ቀርቶ አሁን እንደምናስተውለው ለአእምሮ መታወክ ዋናው መንሥኤ መሆኑ አይቀርም! 
✍️ ታሪክን በታሪክነቱ ብቻ ሲረዱት እንጂ በፖለቲካ መነጽር ካዩት ምንጊዜም መዛባቱ አይቀሬ ነው፤ የታሪክ ትልቁ ፈተናም አማናዊ ክስተቱ (Objectivit Reality) ሣይሆን መፈክራዊ ትንታኔው (Subjective Analysis) ነውና!   
✍️ እናም አንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ የተወሳሰበና ውጣ ውረድ የበዛበት ታሪክ ያለው ማኅበረሰብ ታሪክን መማር ያለበት መልካም ታሪክ ራሱን ሊደግም ሲል ለማበረታታት፣ መጥፎዉን ደግሞ ለማረቅና ለማራቅ መሆን አለበት!
 
““““`
ታሪክና ብያኔው ከሳይንስ ዘርፍነቱ ይልቅ የፖለቲካ ማሳለጫ መሣሪያ መደረግ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመጡት የኢትዮጵያ መሪዎች ከጦር መሣርያ ባልተናነሰ ሁኔታ ታሪክን በተንሻፈፈ ትርክት በመጻፍና በመናገር ትውልዱን ጠፍንገው ወደሚፈልጉበት ርዕዮተ ዓለም የሚጠመዝዙባቸው ክስተቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ እናም አንዱ እውነት በተለያዩ የሐሰት ቅላጼዎች እንዲጻፍ ሰፊ በር ተከፍቷል፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገር ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት ከፍተኛ ሥጋት እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ በሀገራችን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ቀጣይነት ያለውና ሁለንተናዊ የሆነ እድገት እንዲመጣ ከተፈለገ ከራሳችን ታሪክ ጋር ከመታረቅ በላይ ብልህነት ያለ አይመስልም፡፡
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ ተናጠላዊ ማንነታቸውን የሚያንጸባርቁ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ አሏቸው፡፡ የባህላቸውና የቋንቋቸው ብዛት ግን አንድነታቸውን የሚንድ ሳይሆን ጌጥ ሆኖ የሚያሸበርቃቸው ነው፡፡ በታሪክ ረገድም የሚለያያቸው መገለጫ እንዳለ ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው፣ እንደ ጽኑ ሰንሰለትም የሚያስተሳስራቸው ሞልቷል፡፡ ማንነታቸው ደግሞ ዝቅ ሲል ከሚገኙበት ብሔረሰብና አካባቢ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታዎች የሚቀዳ ነው፡፡ እንግዲህ የአንድን ሰው  ማንነት የሚቀርጹት የእነዚህ ገጽታዎች ሁሉ ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡
ይህ የአብሮነትም ሆነ የተናጠል ታሪክ ያለው ሕዝብ ደግሞ ባሳለፋቸው በርካታ ዘመናት ክፉ ደጉን አብሮ አሳልፏል፤ በርካታ ውጣ ውረዶችንም አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በመሰል ታሪካዊ ሂደት ዘመናትን ተሻግሮ የመጣው ሕዝብ ደግሞ መከተል ያለበት፡- ‹‹አንድ አንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ የተወሳሰበና ውጣ ውረድ የበዛበት ታሪክ ያለው ማኅበረሰብ ታሪክን መማር ያለበት መልካም ታሪክ ራሱን ሊደግም ሲል ለማበረታታት፣ መጥፎዉን ደግሞ ለማረቅና ለማራቅ መሆን አለበት›› የሚለውን የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌን ወርቃማ ምክር ነው፡፡
በእርግጥም የኢትዮጵያ ታሪክ ስላለፈው ክስተት በትክክል መግለጥ አለበት፤ ነገር ግን በጥናትና በቀና አእምሮ ላይ በመመርኮዝ እንጂ በፖለቲካ ጫና፣ በወገንተኝነት፣ አልያም በግል አመለካከት ተመሥርቶ መሆን የለበትም (Triulzi, 2002:287-288)፡፡ እንደዚሁም ታሪካችን የመገናኛ፣ የመነጋገርያና የመግባቢያ ዐውድ እንጂ የእርስ በርስ መናቆርያ (የጦርነት) ሜዳ መሆን የለበትም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ክፉ ደጉን በጋራ ስንቋደስ አብረን አሳልፈናል፤ አብረን በልተን ጠጥተናል፤ በጋብቻም ተሳስረን አንድ ቤተሰብ ሆነናል፡፡ እናም መለያየቱ ይበልጥ የሚጎዳው እኛኑ ነው፤ በአንድነታችን ጽናት ምክንያት ተሸንፈው የነበሩ ጠላቶቻችንን ደግሞ መናቆራችን ጮቤ ያስረግጣቸዋል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ብሂል ‘walii-galan, alaa galan’ ይባላል፤ ‹‹ሰው እርስ በርሱ ሲስማማ ብቻ በሰላም ውሎ ይገባል›› እንደማለት፡፡
ከየትኛውም ጎሣ እንወለድ፣ የትኛውንም ሃይማኖት እንከተል፣ ታሪክን በታሪክነቱ ለመረዳት ልንቸጋገር አልነበረብንም፤ ይህ የልዩነት ምክንያት መሆኑም ያሳዝናል፡፡ እንደ አገር ከሚለያዩንና ልዩነታችንን ከሚያጎሉ ክስተቶች ይልቅ አንድ የሚያደርጉንና የሚያስተሳስሩን ታሪካዊ መስተጋብሮች ሞልተውናል፡፡ በዘመኑ ወሬና አሉባልታ ምክንያት ይህ የአንድነታችን ሰንሰለት ፈጽሞ ሊላላ አይገባውም ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ በታሪክ ሂደት መጎዳቱን እያሰበ ሁሌ የሚያለቅስ (crying victim)፣ ሌላው ደግሞ ‹‹በአገር ሰላም ምን ታሟርታላችሁ?›› በሚል ምንም እንዳልተፈጠረ ተከናንቦ ከተኛ (denial) መችም ቢሆን ልንግባባ አንችልም፤ ያም በረድ ብሎ፣ ይህም ነቃ ብሎ ለጋራ የውይይት መድረክ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡
በተጨባጭ ማስረጃ እና በእውነት ሚዛን ሞግተው የሀሳብ ልዕልና ማግኘት ያቃታቸው አንዳንድ አካላት የአገሪቱን ነባራዊ የፖለቲካ አካሄድ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀምና በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም የሕዝቦቿን አንድነት ለመናድ አዲስ ስልት ቀይሰው በ ‹‹ታሪክ›› ስም በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡
የአገሪቱ ቀደምት ታሪክ ከእነርሱ ዓላማና ፍላጎት ጋር አልገጥም ሲላቸው ያ ታሪክ ‹‹ተረት ተረት›› እንደሆነ ደጋግሞ በማስወራት ‹‹አዲስ ታሪክ መጻፍ አለበት›› ሲሉ ይደሰኩራሉ፡፡ ይህንኑም ‹‹አዲስ ታሪክ›› በራሳቸው ፍላጎትና ስሜት መሠረት ለመጻፍ ይፈልጋሉ፤ ‹‹ታሪክ›› ባይሆኑም ይህንን ርዕስ ይዘው የተሠራጩ የፕሮፖጋንዳ ጥንቅሮቻቸውም አሉ፡፡
እነዚህ የአዲሱ ‹‹ታሪክ›› ጸሐፊዎች ከወንዛቸው ባሻገር ያለውን ታሪክ ሁሉ ሀሰት ለማስባል ሲሉ ሌላ ወንዝ ተሻግረው ለመጻፍ የሞከሩት ‹‹ታሪክ›› እውነታውን በመካከሉ ጥለው እንዲነጉዱ አደረጋቸው፡፡ ስለዚህም ስለ አንዲት አገር እጅግ የተራራቁና የተጣረሱ ‹‹ታሪኮች›› ሲጻፉ ይውላሉ፣ ያድራሉ፤ በተለያዩ አካላት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች፡፡ ይህ ትውልድም ሁሉን በጨረፍታ እያነበበና እየሰማ የትኛውን ማመን እንዳለበት ግራ ተጋብቷል፤ በመስቀልኛ ቦታ ላይ ቆሞ ወዴት መታጠፍ እንዳለበት በማለም ላይ ነው፡፡
ታሪክ የፖለቲካ ዒላማ ማሳለጫ መሣርያ ሆነና ሁሉም ትውልዱን በ ‹‹ታሪክ›› ስም ወደየራሱ ጽንፍ ለመሳብ በሚያደርገው ፍልምያ የአገርን ታሪክ ‹‹ሁሉን በሚያስማማ መልኩ›› ማስተማርና መረዳዳት እጅግ ፈታኝ ሆኗል፡፡ ለዚህም ተጨባጭ ማሳያው በየዩኒቨርስቲዎቹ ያሉ የታሪክ ክፍለ ትምህርቶች (Departments) ነባራዊ ገጽታ ነው፡፡ የታሪክ ዘርፍ ክፍሎች ወይ የሚገባባቸው እያገኙ አይደሉም፤ አልያም ‹‹ታሪክ›› የሚባለውን ትምህርት ለማስተማር በሞከሩ ቁጥር በመምህራኑና ተማሪዎች፣ እንዲሁም በተማሪዎችና ተማሪዎች መካከል በተደጋጋሚ ተካርሮ ከሚነሳው ውዝግብ የተነሣ ለማቋረጥ የተገደዱባቸው ክስተቶችም ነበሩ፡፡
ሌላው ቀርቶ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እንኳን መንግሥት እስከ አሁን አገልግሎት ላይ የቆየውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተቀይሯል፤ ይልቁንም የታሪክ ማስተማርያ መጻሕፍቱን ገምግሞ ‹‹የፖለቲካ አስተሳሰቦች ተንጸባርቆባቸዋል፤ መታረም አለባቸው›› ሲል መግለጫ ሰጥቷል፤ በዚያው አግባብም የተከለሱ መጻሕፍትን ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በ2012 ዓ.ም መጀመርያ ላይ ‹‹ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መማርያ›› ተብሎ የተዘጋጀው የታሪክ ማስተማርያ ሞጁልም ከአዘጋጆቹ አመራረጥ፣ ከዝግጅቱ ሂደት፣ ከመረጃ ምንጭ አጠቃቀም፣ ከሙያዊ ሥነ ምግባርና ከጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲዎች እጅ አዙር የተዛባ ትርክት የተነሣ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ መንግሥትም ከሁሉም አቅጣጫዎች የጎረፉበትን ትችቶች ከግንዛቤ በማስገባት በሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ የታሪክ ክፍለ ትምህርት መምህራን ሞጁሉ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ (ውሳኔዎቻቸውን በቃለ ጉባኤ አስደግፈው እንዲልኩ)፣ ሞጁሉም በዚሁ አግባብ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት ለማስተማርያነት እንደሚፈቀድ ቃል ገብቶ ነበር፤ የተሰጡት የማስተካከያ አስተያየቶች በትክክል ተካትተው ጥቅም ላይ መዋላቸውን እስካሁን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፡፡ ይህን ሁሉ መዘዝ ያመጣው ሁሉም ታሪክን የፖለቲካ መሣርያ ለማድረግ  ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ታሪክ የፖለቲካ መሣርያ ሲሆን ደግሞ ‹‹ታሪክ ለታመመ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው፤ History is a medicine for a sick mind” (ሥርግው፣ 1972 ፣መግቢያ) የሚለው ቀርቶ አሁን እንደምናስተውለው ለአእምሮ መታወክ ዋናው መንሥኤ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
አቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ የተባሉት የታሪክ መምህር ‹‹ቀሠም›› ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለው ነበር፡-
‹‹የሚያጣላን ታሪክ ሳይሆን ስለ ታሪክ ያለን ዕይታ ነው። ያለፉ ሰዎች ሳይሆኑ እኛ ስላለፉ ሰዎች ያለን አመለካከት ነው …እያጣላን ያለው የፖለቲካ ታሪክ (History of Politics) ሳይሆን የታሪክ ፖለቲካ (The Politics of History) ነው…ያለፈ ታሪክ ፖለቲካ ሊሆን አይገባም። አሁን ያለው ፖለቲካ ስለ ታሪክ ያለው አመለካከትና ትርክርት እያፋጀን ነው…የተለያየ የፖለቲካ አመለካለከት ይዘን አብረን እንደምንኖረው ሁሉ የተለያየ ዓይነት የታሪክ ትርክት ይዘንም አብረን መኖር መቻል ነበረብን እንጂ ታሪክን የጦር ሜዳ ማድረግ አልነበረብንም፡፡ …ኢትዮጵያም የገጠማት ችግር የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ወይም የብሔር ዳራ ያላቸው ሰዎች የታሪክ ትርክታቸው መነጣጠሉ አይደለም። ዋናውና ትልቁ ዳኛ አገረ-መንግሥቱ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የታሪክ ትምህርት ክፍል (ዳኛ ብለን የመደብናቸው አካላት) እውነተኛ የታሪክ ዳኝነት መስጠት ሲያቅታቸው ነው ታሪክ የተበላሸው።››
በእርግጥም ባለፉት ጊዜያት ውስጥ የነበሩ አካሄዶች በሙሉ እንከን የለሽ ነበሩ የሚል አቋም አይኖርም፤ ይህ የሚሆነው የታሪክ ባለድርሻ አካላት ሰዎች ሳይሆኑ ‹‹መላእክት›› ሲሆኑ ብቻ ነውና፡፡ እንደዚያውም ደግሞ ሁሉም ክስተቶች ስህተት ነበሩ ለማለት ያስቸግራል፤ የክስተቱን መገምገሚያ ሚዛን ከጊዜው፣ ከቦታውና በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር መቃኘት የግድ ይላልና፡፡ ሀሰት ብዙ ትሆን ይሆናል እንጂ እውነት መችም ቢሆን አንዲት ናት፡፡ እውነት እንደ ሀሰት ብዙ ደጋፊዎች ባይኖሯትም ቅሉ የማታ የማታ ማሸነፏ ግን አይቀሬ ነው፡፡  እውነት ትቀጥን ይሆናል እንጂ መችም አትበጠስም! ስለዚህም ሁሉም ሰው በወሬ ነፋስ ከመወሰድ ይልቅ ታሪክ እንዴት መጤንና መጠናት እንዳለበት መገንዘብ ያሻዋል፤ ፖለቲካንና ታሪክንም መለየት ይጠበቅበታል፡፡ ታሪክን በታሪክነቱ ብቻ ሲረዱት እንጂ በፖለቲካ መነጽር ካዩት ምንጊዜም መዛባቱ አይቀሬ ነው፤ የታሪክ ትልቁ ፈተናም አማናዊ ክስተቱ (Objectivit Reality) ሣይሆን መፈክራዊ ትንታኔው (Subjective Analysis) ነውና!
አውነትን በመግለጥና ሐሰትን በማጋለጥ የሀገርን ሰላምና የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ እንትጋ!
Filed in: Amharic