>

ከ«ፉክክር ቤት» ወደ «ዐፄ በጉልበቱ»? (በፍቃዱ ኃይሉ -ዶይቸ ቬለ )

ከ«ፉክክር ቤት» ወደ «ዐፄ በጉልበቱ»?

በፍቃዱ ኃይሉ (DW)

‘ዴስቲኒ ኢትዮጵያ’ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የፖለቲካ መሪዎችን አሰባስቦ በማነጋገር ‘አራቱ ሲናሪዮዎች’ ብሎ የሰየማቸው አማራጮችን ማውጣት ችሎ ነበር። የፖለቲካ መሪዎቹ ተሰባስበው የበየኗቸው አራት ቢሆኖች ውስጥ ለሁሉም ተስማሚ የሚሉትን ‘ንጋት’ የሚል ሥም አውጥተውለት ነበር። መሆን የለባቸውም ነገር ግን ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸው ደግሞ ‘የፉክክር ቤት’፣ ‘ዐፄ በጉልበቱ’ እና ‘ሰባራ ወንበር’ የሚል ሥያሜ የሰጧቸውን ነበር። እንደ ተረቱ ‘የፈሩት ይደርሳል’ እንዲሉ፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካሔድ ‘ንጋት’ ከተባለው በቀር ሦስቱንም መሆን የሌለባቸው ሒደቶችን እያስተናገደ ነው። ለመሆኑ የሰሞኑን ፖለቲካዊ አዝማሚያ ወዴት ያደርሰን ይሆን?
መካሪዎቹ
የፖለቲካ ለውጡ ከጀመረ በኋላ የተዘጋጀው ‘የሲናሪዮ’ ምክክር ላይ ዛሬ ለእስር የተዳረጉት ጃዋር መሐመድ እና እስክንድር ነጋ ተጠይቀው ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ሰምቻለሁ። የምክክሩ ተሳታፊዎች በሒደቱ በጣም ደስተኞች የነበሩ ከመሆኑም በላይ የሰከነ ፖለቲካ እንዲጫወቱ እንደገፋፋቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ነገር ግን ምክክሩ ወደ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መዝለቅ አልቻለም ነበር። እንዳስተዋልነው የፖለቲካ ለውጡን በተመለከተ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዒላማ የሚያደርጉት የጋራ ‘ንጋት’ የላቸውም። የተለያዩ ዒላማዎችን እያሰቡ በተለያየ መንገድ ሲጓተቱ ከርመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም፣ ፓርቲያቸውን ወክሎ የተሳተፈ ቢኖርም፣ በዚህ የሲናሪዮ መሰናዶ ምክክር አልተገኙም ነበር። ይህንን በማሰብ ይመስላል አንድ የምክክሩ ተሳታፊ በቀልድ መልክ “ከአሳሪዎቹም፣ ከታሳሪዎቹም መካከል ሒደቱ ላይ የተሳተፉ የሉበትም” ብለው ያሉኝ።
ያልተመከረበት ለውጥ
ኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ አስተናግዳለች። ነገር ግን ለውጡ ወዴት ለመድረስ እንደሆነ በቅጡ አልተመከረበትም። ይህ ያልተመከረበት የኢትዮጵያ ለውጥ መጀመሪያ ያስኮረፈው የቀድሞ ተቃዋሚዎችን ነበር። በርግጥ እነዚህ የቀድሞ ተቃዋሚዎች፣ የጠላቴ ጠላት ለኔ ወዳጄ ነው በሚል መርሕ ለለውጡ መሪዎች ቀዳሚ ድጋፍ ሰጪ ነበሩ። ሆኖም ቀስ በቀስ እየተኳረፉ መጡ። እንደምሳሌ ያክል ሟቹ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ (የቀድሞው እስረኛ) እና እስረኛው ጃዋር መሐመድ (የቀድሞው ስደተኛ) ተጠቃሽ ናቸው። ሁለቱም የለውጡ ተስፈኞች በሆኑበት ፍጥነት እጅግ ጎልቶ የሚታይ ቅሬታ እና ኩርፊያ አሳይተው ነበር። በሁለቱም ሰዎች ንግግሮች ስንሰማ የነበረው ለውጡ በጠበቁት ወይም በሚፈልጉት መልኩ እየሔደ እንዳልነበር ነው። በዚህ መልኩ የዚያኛው ተቃዋሚ ዕጣ በሞት፣ የዚህኛው ተቃዋሚ ዕጣ በእስር ተቋጨ ወይም የተቋጨ መሰለ።
እነዚህ ሁለት ጉልህ የታሪክ ገጽታ አካል ስለሆኑ ጠቀስኳቸው እንጂ የብዙዎች ታሪክ ነው። ለዚህ ተወቃሹ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲወተወት የነበረው ፍኖተ ካርታ (roadmap) አለመኖር አንዱ ሲሆን፣ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ አለመኖሩ ሌላኛው ነው። የፍኖተ ካርታው አለመኖር የተለያዩ ወገኖች አንድ ላይ መክረው የጋራ ‘ንጋት’ የሚሉትን ግብ ቀርፀው፣ ይህ ባይቻል እንኳ የለውጡ ግብ እና አካሔድ ምን መሆን አለበት የሚሉት ላይ ተስማምተው ለጋራ ግብ ቢያንስ በአንድ የአጨዋወት ሕግ የሚሳተፉበትን ዕድል አሳጥቷል። የሽግግር ጊዜ ፍትሕ አለመኖሩ ደግሞ የቀድሞ ጉዳተኞች እና ታጋዮች ለጉዳታቸው ካሣ ሳያገኙ፣ ለትግላቸው ዕውቅና ሳይሰጣቸው፣ ለበደላቸው ፍትሕ ሳያገኙ፣ በሕይወታቸው ለውጥ ሳያዩ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል። ይባስ ብሎ የቀድሞ አጥፊዎች የሞራል የበላይ ሆነው የሚታዩበት ጊዜ የእግር እሳት ሆኖባቸዋል። ይህ በከፍተኛ ተስፋ የተጀመረውን ለውጥ፣ በከፍተኛ ቁጭት እና ቁጣ እንዲቋጭ እየነዳው ነው።
“ከድጡ ወደ ማጡ”
ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ ሳለሁ ልደቱ አያሌው በኦሮሚያ ፖሊስ በዚህ ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ ተገኝቶባቸዋል በሚል ክስ ለመመሥረት እንዳስራቸው ይፈቀድልኝ ብሎ ፍርድ ቤት እንዳቀረባቸው ሰምቻለሁ። በጣም ተስፋ አስቆራጭ ጉዳይ ነበር። ፖሊስ የጠቀሰውን ጽሑፍ ከመታሰራቸው በፊት አግኝቼ አንብቤው ነበር። ‘የለውጡ ሒዷት ተቀልብሷል፤ የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት’ ከሚል ምክረ ሐሳብ ያለፈ ለወንጀልነት የሚያበቃ ምሥጢር የለውም። ይልቁንም የፖሊስ ክስ የጽሑፋቸውን እውነትነት የሚያረጋግጥ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
የዐቢይ አሕመድ መንግሥት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን አራዝሞታል። መራዘሙ ባያጣላም የሚካሔድበት ጊዜ አለመታወቁ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል። ፖለቲካዊ ኩርፊያዎች ላይ ነዳጅ አርከፍክፏል። ፖለቲካዊ ነውጦችን ተከትሎ መንግሥቱ የሚዲያ ተቋሞች ዘግቷል፣ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ አመራሮችን አስሯል። አንዳንዶቹ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን ከነውጥ ጋር ያገናኘውን የመንግሥትን የእስር ሰበብ ለማመን እንደ ልደቱ አያሌው ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በፍፁም የማይጠረጠሩ ሰዎችን አግበስብሶ እስር ቤት አኑሯቸዋል። ይህ “የፉክክር ቤት” ሆኖ የከረመውን አገር ወደ “ዐፄ በጉልበቱ” እያሸጋገረው ይሆን ብሎ መጠርጠርን ቀላል ያደርገዋል። ልደቱ አያሌውም ይሁን ሌሎቹ ለእስር የተዳረጉትን የፖለቲካ አመራሮች የሚያመሳስላቸው ለምርጫው መራዘም እውቅና መስጠት ያልፈለጉ፣ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ እምነት የሌላቸው እና የሽግግር መንግሥት፣ ወይም ተመሳሳይ አማራጭ የጠቆሙ መሆናቸው ብቻ ነው።
ጉዞ ወደ ዐፄ በጉልበቱ
ያለፉት ሁለት ዓመታት ክልሎች መካከል ፉክክሩ ያየለበት፣ ማዕከላዊው መንግሥት አቅመ ቢስ ሆኖ፣ ከላይ ከተዘረዘሩት መካከል ‘ሰባራ ወንበር’ መስሎ ነበር። ትዕይንቱ ኢትዮጵያን የክልላዊ መንግሥታት “የፉክክር ቤት”፣ የፌዴራሉን መንግሥት “ሰባራ ወንበር” አስመስሎት ነበር። በዚያ ላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የሚፈጥሩት ነውጥ ነበር። ይህ ሁኔታ የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ አንዳንዶችን “ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ አልተዘጋጀንምን?” ብለው እንዲጠይቁ፣ ሌሎች ደግሞ የፌዴራሉን መንግሥት “አምባገነን ሁንልን” ብለው አፍ አውጥተው እስኪለምኑ አደረሳቸው። አሁን ያለንበት ደረጃ በርግጥም አንዳንዶች የተለማመኑለት “ዐፄ በጉልበቱ” (የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት) ለመመሥረት የተመቻቸ ሁኔታ ላይ ነው።
ነገር ግን በተለይ አሻፈረኝ ብላ ለብቻዋ ለምርጫ እየተዘጋጀች ካለችው ትግራይ ክልል እና ፌዴራሉ መካከል ዛሬም ፉክክሩ አለ። ያለ ክልላዊ መንግሥታቱ ታዛዥነት ዛሬም የፌዴራሉ መንግሥት ወንበር ሰባራ ወንበር ነው። የሕዝብ ግፊት፣ የዴሞክራሲ ኃይሎች የተባበረ ጥረት ካልተጨመረበት የንጋት ተስፋ ግን ዛሬም እንደደበዘዘ ነው።
Filed in: Amharic