>
5:18 pm - Monday June 16, 8200

አዳነች-አስናቀች! (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

አዳነች-አስናቀች!

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

አዲስዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች የእውነትን በር ከፈተች! ቃል በተግባር ከተደገፈ ወይዘሮ አዳነች ጠቅላይ ሚኒስትሩንም፣ አገሪቱንም፣ ብልጽግናንም አድናለች፤ አዳነች ለወላጆቿ ምስጋና ይድረሳቸውና!  ይህ እውነት ሆኖ ከያዘ ስም ወደተግባር ይመራል የሚባለውም እውነት ይሆናል፤ በከፈትሽው መንገድ ምሪበት! ተባረኪ!
የሚመርር ቢሆንም እውነትን መቀበልና ስሕተትንም ሆነ ጥፋትን ከመሸፋፈንና ከማድበስበስ ይልቅ ፊት-ለፊት መጋፈጡ ወንድነት ነው፤ ለወይዘሮ አዳነች ስል ወንድነት ማለቱን በመሻር ሴትነት እለዋለሁ! ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ሲሆን የተደረገውን ጥፋት የማረሙ ሁኔታ እንዲሁ በይፋ እንድናውቀወ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፤ ይህ ጥፋት ማዘጋጃ ቤቱን ሳያበላሽ፣ ብልጽግናን ሳያበላሽ፣ አገሩን ሳያበላሽ፣ አገሩ በብልሽት ሳይፈርስ ወይዘሮ አዳነች ቁልቁለት የጀመረውን የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ወደዳገት እንደምታወጣው እንጠባበቃለን፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢዜማ እንደፖሊቲካ ቡድንም ሆነ እንደየነቃ ዜጋ ያቀረበው ጥናትና ያጋለጠው ጥፋት በአሉባልታ ብቻ የሚንጫጩትን የፖሊቲካ የሚያስተምር በመሆኑ የሚያስመሰግነው ይሆናል፡፡
ለወይዘሮ አዳነች ከመጽሐፈ ምሳሌ በአሥራ አንድና በአሥራ ሁለት ምዕራፎች ላይ የሚገኙ አንቀጾችን ልጥቀስላት፡–
አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው
መልካም መክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል፤ ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው፤
ሥልጣን ላይ ያሉ ሁሉ በሰሎሞን ምክር ቢመሩ ጠቃሚዎች ይሆናሉ፤ አደራ ከመብላት ይድናሉ፡፡
ወይዘሮ አዳነችን ይበልጥ የማመሰግናት የከንቲባነቱን ወንበር ስትለቅ ሳትማስን የቀረች እንደሆነ ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቃት!
Filed in: Amharic