>

ፖለቲካ እና መንፈሳዊነት፤ መንፈሳዊ ፖለቲከኝነት (ያሬድ ሀይለማርያም)

ፖለቲካ እና መንፈሳዊነት፤ መንፈሳዊ ፖለቲከኝነት

ያሬድ ሀይለማርያም
የአገራችን ፖለቲካ ጤና ካጣ ቢሰነባብትም ፖለቲካውን በሚዘውሩት ሰዎች አካባቢ ግን አንድ ያልተለመደ ነገር ይስተዋላል። ፖለቲካን እና መንፈሳዊነትን አጣምሮ ለመሄድ መሞከር፤ መንፈሳዊ ፖለቲካ (Spiritual politics)። ይሄ አይነት የፖለቲካ አመራርን ከመንፈሳዊ አድራጎቶች ጋር አጣምሮ ለማስኬድ መቻል ኃይማኖተኛነት በጠነከረበት ቦታ ሁሉ የብዙዎችን ቀልብ የሚስበውን ያህል ጥቂት እርቆ አሳቢዎችን ደግሞ ግራ ያጋባል። በዚህ አይነቱ የፖለቲካ መንፈሳዊነት ውስጥ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ሁለቱ፤ ፖለቲካ እና መንፈሳዊነት አብረው ይሄዳልሁ ወይ የሚል ነው። የጥያቄውም መነሻ ኃይማኖት እና መንግስት የተለያዩ ናቸው ከሚል ይመስለኛል።
የተለያዩ ምሁራን ሃሳቡን ሲተቹ መንፈሳዊነት ከኃይማኖት ይለያል። በእርግጥ ኃይማኖት የመንፈሳዊነት ምንጭ ቢሆንም ድርጅታዊ ቅርጽ እና ውክልና ያለው ነገር ነው። መንፈሳዊነት ግን ከሞራል ወይም ከመንፈስ ልዕልና ጋር የተያያዘ ስለሆነ ከኃይማኖት ውስጥ ቢመነጭም ማጠንጠኛው ድርጅት ሳይሆን የመንፈስ ወይም የሞራል ልዕልናው ብቻ ነው።
ከዚህም ተነስተው ፖለቲካ እና መንፈሳዊነት አይጋጩም። ፖለቲካን በመንፈስ ልዕልና መምራት ይቻላል ይላሉ። ነገር ግን መንፈሳዊ ልዕልናው ከዚህ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ሲያሟላ ብቻ ነው ከፖለቲካ ጋር ተሰናስኖ ፍሬ የሚያፈራው። እነዚህ ለጥሩ መንፈሳዊ የፖለቲካ ምሪት ዋና ግብዓት የሆኑትን ነገሮ መላበስ እውነተኛ ፖለቲከኛ ያደርጋል። ከዛ መለስ ያለው መዳከር ግን ትርፉ መላላጥ ብቻ ነው። እስኪ እነዚህን ሃሳቦች አንድ በአንድ እያየን መንፈሳዊ ፖለቲከኞቻችንን እንፈትሽ፤
፩ኛ/ ለአንድ ሕዝብን እና አገርን ለሚጠቅም ነገር ለመሥራት ያለ ቁርጠኝነት (Courage in standing up to special interests of the public)
፪ኛ/ ታማኝነት እና ጠንካራ ወይም የማይናወጽ የመንፈስ ልዕልና፤ የተናገሩትን ነገር በሥራ ላይ የማዋል ጽናት (Honesty and integrity—“walking the talk”)
፫ኛ/ እራስን ከማዋደድ ወይም ከማስቀደም አባዜ ነጻ መሆን እና ሌሎችን በተጽእኖ ስር አድርጎ እና ከሁሉም ጎልቶ እኔ ብቻ ልታይ አለማለት፤ (Lack of ego-inflation and manipulation of others)
፫ኛ/ ሚዛናዊነት እና ለፍትህ መቆርቆር (Fairness and justice)
፬ኛ/ ከአመጽ ወይም አላስፈላጊ ጉልበተኝነት መጽዳት እና ሰላማዊ መንገዶችን መምረጥ (Non-violence and peaceful means)
፭ኛ/ ለተጎዱ እና ለተገፉ ሰዎች ተቆርቋሪ ሆኖ መቆም (Compassion for the disadvantaged)
፮ኛ/ የግል ጥቅምን ከማሳደድ ይልቅ ለሌሎች፣ ለሕዝብ እና ለሃገር ጥቅም መስራት እና እራስን አሳልፎ መስጠት (Serving the good of the whole, rather than personal interests)
፯ኛ/ ለተቀናቃኝ፣ ለተፎካካሪ ወይም ደጋፊህ ላልሆነ ሰው ወይም አካል ተገቢውን ክብር እና ትህትና ማሳየት (Respect and civility for opponents)
፰ኛ/ ከሌሎች ጋር ተባብሮ እና አጋርነት ፈጥሮ የመስራት ፍላጎት እና ክህሎት (Collaboration and partnership)
፱ኛ/ በአንድ ጉዳይ ላይ ሙሉ የሆነ ነገሮችን የመረዳት ወይም የተሟላ ግንዛቤ የመያዝ ክህሎት እና በነገሮች መካከል ያለውን ቁርኝት እና ትስስር በሚገባ መረዳት (Whole systems thinking—understanding how everything is interconnected)
፲ኛ/ ነገሮችን ፈጥኖ የመረዳት እና እራስን በትክክለኛውም መንገድ የመምራት ክህሎት (Reliance on intuition and inner guidance)
፲፩ኛ/ ከፍ ባላ ኃያል አምላክ፣ መንፈስ ወይም ምድራዊ ኃይል ላይ እምነት መኖር (Faith in a Higher Power—God, Spirit, the Universe, etc.)
እንግዲህ እነዚህን ለመንፈሳዊ ፖለቲከኛነት ወይም በመንፈስ ለተመራ ፖለቲካ መገለጫ የሆኑ ሃሳቦችን ይዛችው ከጠቅላይ እስከ ምንዝር ያሉ የወቅቱ ፖለቲከኞቻችንን የመመዘኑን ነገር ለእናንተ ልተው።
ለእኔ አንድ እየተምታታብኝ ያለ ነገር ስላለ እሱን ጠቆም አድርጌ ላብቃ። በእኔ ትዝብት መንፈሳዊነት እና ፖለቲካ እጅግ እየተምታቱ ይመስለኛል። ፖለቲከኞቻችን መንፈሳዊ ለመሆን የሚደክሙበት፣ የሚታትሩበት እና ፎቶ እየተነሱ የሚያጋሩበት ወቅት እና ሁኔታ ይህን እንዲል አስገድዶኛል። ትህትናቸውን አደንቃለሁ። ዝቅ ዝቅ ማለታቸውንም በበጎ አየዋለሁ። ነገር ግን የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ውሳኔ የሚፈልጉ ቦታዎች ላይ ሲደርሱ ፍጹም መንፈሳዊ መምሰል፤ መንፈሳዊነት በሚያስፈልግበት ቦታ እና ወቅት ላይ ደግሞ ልበ ደንዳና መስለው ፖለቲከኛ ብቻ ለመሆን መጣር ግራ ያጋባል።
ድሆች ከኖሩበት ቤት በግፍ ሲፈናቀሉ፣ ንጹሃን ዜጎች በጠራራ ጸሓይ በወሮበሎች ሲታረዱ፣ ሰዎች እድሜያቸውን ሙሉ ለፍተው፣ ጥረው ግረው ያፈሩት ሃብት በዘራፊዎች ሲዘረፍ እና ሲወድም፣ አሥር ሺዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው መዳ ላይ ሲወድቁና የአውሬ ሲሳይ ሲሆኑ፣ በሙሰኛ ሹማምንት የዜጎች ቤት እና መሬት ሲዘረፍ እና ሲወረር፣ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ብቻ ማንቁርታቸውን ተይዘው በማጎሪያ ቤት ሲጣሉ እና ሌሎች ተመሳሳይ ግፉች ሲፈጸሙ የማይታይ መንፈሳዊ ፖለቲከኛነት በአዘቦት ጊዜ ጫማ በሚያስጠርግ ትህትና ሊካካስ ይችላል ወይ? ለአንድ ቀን ዳቦ በነጻ በማደል ሊወራረድ ይችላል ወይ? በጉርሻ እና በስብከት ሊሞላ ይችላል ወይ?
ይህ የመንፈሳዊ ፖለቲካ ጸበል ጻዲቅ ትላንት በአደባባይ በዘራቸው እና በኃይማኖታቸው ምክንያት የታረዱትን ወገኖች እና ቤት ንብረታችው ወድሞ በየአድባራቱ የተጠለሉ ወገኖችን፣ ቤታቸው ፈርሶባቸው በየመንገዱ ከነልጆቻቸው የተጣሉ ወገኖቻች እና ፍትህ አጥተው የመንግስት ያለህ የሚሉ ዜጎችን ያዳርስ ይሆን? ትዝብቱን ለእናንተ እተዋለሁ፤ ጠየቅላዩን ትህትና አደንቃለሁ፤ የተምታታውን መንፈሳዊ ፖለቲከኝነት መልክ እንዲይዝ አሳስባለሁ።
Filed in: Amharic