>
5:18 pm - Sunday June 14, 2020

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !

 
አዲስ አበባ በራሷ ግዛተ-መሬት ላይ የፌዴራል /ክልልነት/ መብት ሊረጋገጥላት ይገባል!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በመመዘኛዎቹ ላይ በኢትዮጵያ ተፃራሪ አቋም ባላቸው ልሂቃን ዘንድ ስምምነት ላይ ሊደርስ ቢችል፣ ፌዴራላዊ የመንግስት አደረጃጀት የፖለቲካ አለመግባባት መንስኤ ሊሆን የሚችል አልነበረም፡፡ ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ዋነኛ መገለጫ ሊሆን የበቃው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ሊግባቡ ያልቻሉበትም ምክንያት በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት የግንባታ ታሪክ ላይ ልዩነታቸውን ማጥበብ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ትውልድ ደግሞ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1940ዎቹ ዓመታት ተወልዶ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለዩኒቨርስቲ ደረጃ የደረሰው ትውልድ ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ1960ዎቹ ሁኔታ ደግሞ አለም በሁለት ተፃራሪ የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጎራዎች ፉክክር ተቀስፋ ተይዛ የነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ በ1960ዎቹ ለጉልምስና ከደረሰው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ነው ባይባልም ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ አለኝ ብሎ ያቀነቅን የነበረው የትውልዱን የአመራር ሚና የተጫወተው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተምህሮ የተቀበለው ነበር፡፡
ይሁንና የዚህ የ1960ዎቹ የተማሪ አብዮተኞች እና የነሱ ከፊል ውጤት ሆነው ያቆጠቆጡት የነገድ ድርጅት መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በተፃረረና ባልተገናዘበ ሁኔታ የሶቭየት ሕብረትን የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የስታሊንን “የብሔርና የቅኝ ግዛት ጥያቄ” መጽሐፍ ቃል በቃል በመገልበጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ችግር “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች መስተጋብር ነው” የሚል የሐሰት የታሪክ ትርክት ይዘው ተነሱ፡፡ እነዚህ ከተማሪ አብዮተኝነት ወደ ነገድ ድርጅትነት የተሸጋገሩት ከደርግ መንግስት ጋር ለ17 አመት ጦርነት አድርገው በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያላሰለሰ ድጋፍ በ1983 በኢትዮጵያ ጦር ላይ ድል ሊቀዳጁ በቁ፡፡ አነዚህ ሃይሎች በተጠናወታቸው “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች” የሃሰት ትርክት ውጤት የሆነውን የመገንጠል መብት ሕገ መንግስታዊ መብት ያደረገ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ቋንቋን መሰረት ያደረገ መንግስታዊ የፌዴራል አወቃቀር በኢትዮጵያ ላይ አነበሩ፡፡
በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የጐሳና የዘረኝነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት የመንግስት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አደረጃጀት አይነተኛ መገለጫ ከመሆን አልፎ ይኸው አይነት አደረጃጀት  ወደ እምነት ተቋማት ሳይቀር ዘልቆ እንዲገባ ተደረገ፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ በማይታወቅ ሁኔታ በተረኝነት መንፈስ የተቃኘ ተቋማዊ/መንግስታዊ ሙስና እና የፍትህ መዛባት የስርዓት መገለጫ ሊሆን በቃ፡፡ ከህዝቡ ታሪካዊ አሰራር ጋር ባልተገናዘቡ የክልል አደረጃጀቶች ምክንያት በሃገራችን እንግዳ በሆነ መልኩ ማንነትን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲበራከቱ፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው በፌዴራል መንግስቱና በክልል መንግስታት መካከል የሃላፊነትና የተጠያቂነት ጉዳይ አሻሚ በማድረግ፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ስሜት እንዲላሽቅ በምትኩ ጠባብና ክልላዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝም ስርዓት ችግር ብሔረሰብን ዋነኛው የፌዴራል ስርዓቱና የአገር መንግስት ግንባታ መሰረት ማድረጉ ነው፡፡
እዛው ተወልዶ ያደገውና ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንድ ብሔረሰብን እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሠረት አድርጎ በተዋቀረ ክልል ውስጥ አስገብቶ እንዲተዳደር ማድረግ  ፍትሃዊነት የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄ ከራሴ ውጭ በኔ እጣ ሌላ ሊወስንብኝ አይገባም የሚል ነው፡፡ አዲስ አባባ በኦሮሚያ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ በመገኘቷ ብቻ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት የመብት መብለጫ፣ ለተፈጠረ ውጥንቅጥ ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብን መብት ማሳነሻ ማድረግ በምንም መመዘኛ ተገቢነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡
የኢፌድሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 69 “የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው ቢታወቅም የህወሓት እና የኦነግ በሆነው ሕገ መንግስት ውስጥ “በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ይኖረዋል” በሚል መካተቱ ችግሩን ሆን ተብሎ እንዲወሳሰብ አድርጎታል፡፡
በ1989 የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር ሲደነገግ፣ በሕገ መንግስቱም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜ አዲስ አበባ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ቻርተሩን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቂ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጽደቅ ሂደቱ በደባ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ እና እንደ ካንቤራ የፌዴራል መንግስት ግዛት ናት የሚል የሕግ አንቀጽ የለም፡፡ ይህ አይደለም እንዳይባል በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ጉዳይ በአዲስ አበባ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈፀመ ወይም የተከናወነ የሕግ ጥሰት ግን ልክ የፌዴራል መንግስት ይዞታ አንደሆነችው ዋሽንግተን የመዳኘት ስልጣንን ለፌዴራል መንግስቱ ይሆን ዘንድ በሕግ ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ ማለትም በተግባር የፌዴራል መንግስቱ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የራሱ ግዛት አድርጓቸዋል፡፡
ሕገ መንግስቱ አዲስ አበባ እራሱን የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን የሰጠው መሆኑ ከላይ የተጠቀሰው የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ለመዳኘት ከተሰጠው ስልጣን ጋር ሲዳመር አዲስ አበባ ልክ እንደ ዋሽንግተን የፌዴራል ግዛት እንደሆነች ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተጨባጭ ግን አዲስ አበባ ከተማ የተተወላት የከተማ ነክ አስተደደርና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመዳኘት ስልጣን ነው፡፡ ማለትም ስለ ዳኘነት ሲሆን መሬቱ የፌዴራል መንግስት፣ ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲሆን የከተማ መስተዳድሩ ሆኗል፡፡
አዲስ አበባ ራሷን የማስተዳደር መብት በሕገ መንግስቱ የታወቀ ቢሆንም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ውክልና የላትም፡፡ ሕገ መንግስቱ ከሚደነገገው ውጭ ስትደዳደር የቆየችው በህወሓት/ኢህአዴግ፣ አሁን ደግሞ በኦህዴድ/ብልጽግና ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የክልል ፓርቲዎች አሉ /ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ወዘተ…/ አዲስ አበባ ላይ ግን የሚወክላት የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ገዥ ፓርቲዎች ፍላጎታቸውን የሚጭኑባት ከተማ ናት፡፡ ቀደም ሲል ህወሓት/ኢህአዴግ አሁን ደግሞ ኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ማስተዳደሩን ቀጥሎበታል፡፡ ይህ ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ፍፁም የሚጥስ ነው፡፡
አዲስ አበባን እንዲመራ የሚመደበው በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከነበሩ ወይም ካሉ የክልል ገዢ ፓርቲዎች እንጂ በከተማው ሕዝብ ነፃ ምርጫ አልነበረም፡፡ አሁንም አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ቀደም ሲል ከሁለቱ ክልሎች /ትግራይ፣ ኦሮሚያ/ አሁን ከ “ለውጡ” ወዲህ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል በሚመጡ ተሹዋሚዎች እንድትደዳደር መደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎት እንዳይከበር ያደረገ የፖለቲካ ደባ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከ7 ሚሊዮን የሚልቀውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በግብር መልክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመንግስት ካዝና የሚያስገባውን ነዋሪ የፖለቲካ ባይተዋር ያደረገ እና በእጣ ፋንታው ላይ  እንዳይወስን ያደረገ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡ የአሜሪካን አብዮት እንደቀሰቀሰው /Taxation with out political Representation/ እንደሚለው መፈክር ሰርቶ ግብሩን እየገበረ የፖለቲካ ባይተዋር በማድረግ በእጣ ፋንታው ላይ እንዳይወስን አድርጎታል፡፡ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ የፖለቲካ አካሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ በግልጽ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 49 እና አንቀጽ 89 ይጥሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ትልቁ ወለፈንዲ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው፡፡ በአንቀጽ 69 መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ እና የከተማው ነዋሪ ሕዝብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ይኖረዋል ሲል ደንግጓል፡፡ ማለትም አዲስ አበባ የተወላጆቿና እና የሁሉም ከ80 በላይ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በባለቤትነት የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ የአዲስ አበባን አስተዳደር ስንት አማራ፣ ስንት ኦሮሞ፣ ስንት ትግሬ፣ ስንት ጉራጌ፣ ስንት ወላይታ፣ ስንት ሱማሌ፣ ስንት አደሬ፣ ስንት ጋምቤላ፣ ስንት ቤንሻንጉል፣ ስንት ማኦ ወዘተ… እንደሚኖሩባት በተጨባጭ የተረጋገጠ ስታስቲክ ስለሌለ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ሊሰጥ የሚችለው ከሕገመንግስቱ መንፈስ ውጭ ለመላ ቋሚ ነዋሪዎቿ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባን ከተማ ባለቤትነት በተመለከተ እንደ ሌሎች የፌዴራል መንግስት ዋና ከተማዎች እንደሆኑት እንደ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ቪየና እና ብራስልስ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ ያልሆኑ፣ በኢትዮጵያም ከ1983 ሰኔ ወር ጀምሮ ህገ መንግስቱ ተግባራዊ እስከ ተደረገበት 1987 ነሐሴ ወር ድረስ ክልል 14 ተብላ የክልልነት ደረጃ የተሰጠበትን ሁኔታ መልሶ ተግባራዊ ማድረግ  ፍትሃዊ እና የነዋሪዎቿን ሕጋዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡
አዲስ አበባ እንደ ፌዴራል መንግስት ርዕሰ ከተማነቷ የግዛተ-መሬቷ ባለቤትነትን ለፌዴራል መንግስቱ ሳይሆን በሽግግር ወቅት እንደነበረው በፌዴራል አድያምነት /በክልልነት/ ደረጃ እንደገና እንድትዋቀር ባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ለከተማዋ ሕዝብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ከሀገራችን ዘመናዊ የታሪክ ጅማሮ ጋር የተሰናሰለ እድሜ ያላት አዲስ አበባ ከተማ፣ በመልክ-ዕምድር አቀማመጧ የሀገሪቱ እምብርት ላይ መገኘቷ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋን የጎላ አድርጓታል፡፡ ይህ ሁኔታዋ ለሀገራችን ዜጎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለመስጥ የሚያስችል አቅም ያላት ከተማ እንድትሆን ሰፊ እድል ሰጥቷታል፡፡ ነገር ግን ከተማዋ ያላትን ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም አሟጣ በመጠቀም ለነዋሪዎቿ ተስፋ መሆን እንዳትችል በሀገራቸን የነበሩ እና ያሉት ገዢዎች አተያይ እና የአመራር ፈሊጥ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ጎሳን መሠረት ያደረገው የባለፉት 30 ዓመታት የሀገራችን ፖለቲካን ያነበረው ስርዓት የአዲስ አበባ ከተማን ህልውና የበለጠ ተፈታትኖታል፤ ከባድ አደጋንም የፈጠረ ሆኗል፡፡
አዲስ አበባ የሀገራችን ርዕሰ መዲና ከመሆኗ ባሻገር፣ የአፍሪካ ህብረት እና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌትና መናኸሪያ፣ የትላልቅ አለም አቀፍ ተቋማት መታደሚያ ናት፡፡ የሀገራችን 65%            ምጣኔ-ኃብት በአንበሳ ድርሻነት ይዛለች፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቤተ-እምነቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተቻችለው የሚኖሩባት የአብሮነት መገለጫ ከተማ ስትሆን፣ የታሪካችን መገለጫ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርስ እና ትውፊት የተመዘገበባት፣ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ሕብር ፈጥረው በነጻነት የሚንጸባረቁባት የኢትዮጵያ ብዝሃነት ማሳያ ፈርጥ ናት፡፡
ከተማችን አዲስ አበባ ባለፉት 3 አስርት አመታት ሲመሯት የነበሩት ሁሉ ምን ልጠቀምባት እንጂ ምን ላድርግላት የሚል ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለመሆኑ ችግሮቿን የተወሳሰቡ አደርጎታል፡፡ እንደ ፓርቲያችን እምነት፣ ለዚህ ችግር በዋነኝነት ያጋለጣት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አስተዳድር ተሰይሞ ሊያስተዳድራት አለመቻሉ ጉልህ ስፍራ ይይዛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት ግለሰቦች በአብዛኛው የከተማውን ነዋሪ ስነ ልቦና በቅጡ ያልተረዱ፣ ራዕይ አልባ የሆኑ እና ከፍተኛ የብቃት ጉድለት የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ (በአሁኑ አጠራር ክልል) እንድትሆን መሆኑ እውነተኛ ፌዴራላዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ለማንበር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል፤ በመሆኑም አዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖረው በላቀ መንገድ መታገል አስፈላጊ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ላለፉት ዘመናት በተለይም የህወሃት/ኢህአዴግ ስልጣን ዘመን ጀምሮ በመረጠው የመተዳደር መብቱን ተነፍጎ፣ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦህዴድ በውክልና ተቀብሎ አስተዳድራለሁ በሚል የተረኝነት፣ የሙስና፣ የባህል በአጠቃላይ የዘረኝነት ሰለባ ሆናል፡፡ የተረኛነት ስሜት ነቀርሳ የሆነበት ኦህዴድ/ብልጽግና የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ከመቀየር ጀምሮ ተጠንቶ የከተማው ሕዝብ ባልመከረበት የትምህርት ስርዓት ውስጥ ረጅም እጁን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመስደድ፣ የከተማውን መሬት በማስወረር እና ነዋሪው ጥሮ ግሮ ቆጥቦ የሰራውን ቤት አንዴ ለኦሮሚያ የመንግስት ሰራተኞች በሚል ሌላ ጊዜ ደግሞ የተለየ ምክንያት በመስጠት እየዘረፈ  መሆኑ የከተማዋን ነዋሪ በደል ጫፍ አድርሶታል፡፡
ዛሬ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞካራሲ ፓርቲ ይህንን የዘመናት የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መብቱን የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ መድረሱን ተገንዝቧል፡፡ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍትህ ማግኘት የሚቻለው የከተማው ነዋሪ እራሱ የመረጠው ስርዓት ሲዘረጋ መሆኑን በቅርቡ ተረድቷል፡፡ አሁን እየደረሰበት ያለው ግፍ መነሻው ለህዝብ ተጠያቂነት ያለው ትክክለኛ አስተዳደር አለመኖሩና ይህንን ተገን በማድረግ ወደ ዝርፊያ የገቡና ለዚሁ ሁኔታ እንዲያመቻቸው ብቻ የሚሰሩ የውክልና መሪዎች በመሆናቸው ከእነዚህ አስተዳደር ውጭ እንዲሆን ለማስቻል ዴሞክራሲን ለማስፈን እንዲረዳ ነው፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ እንድትሆን ብዙ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበረ ያምናል፡፡ ይህ የከተማው ነዋሪ ጥያቄም፣ ፓርቲው እንዲመሠረት ገፊ ምክንያት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ትላንት ዜጎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ ወደላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩን በማብሰር የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ችግር አስጨንቋቸው እና እንቅልፍ ነስቷቸው ለነበሩ ዜጎች ሁላ ይህ የናንተ የትላንትና የትግል ጥያቄ በመሆኑ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቹሃል፡፡ የዜጎች በደልና ጭቆና እንዳንገበገባቹህ እናምናለን፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ በጋራ እንድንቀሳቀስ እንጠይቃለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የከተማችንን ነዋሪ የሚመጥን አስተዳደር እንዲዘረጋ የሚያደርገው ጥረት፣ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥያቄ በላይ እንደሆነ ያምናል፡፡ በመሆኑም በአገራችን የምትገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለከተማው ነዋሪ የራሱን ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲመሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንድታደርጉለት፤ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦችም የሚመሠረተው አስተዳደር የሚያስፈልገውን ድጋፍና አወቃቀር በአግባቡ እንዲይዝ መልክ ለማስያዝ የሚረዳ ልምዳችሁን፣ እውቀታችሁን እንዲሁም ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማችሁን እንድታበረክቱ ጭምር አደራ ይላል፡፡
በዋነኝነት የአዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር ባለቤት ሁሉም የከተማው ነዋሪ እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በማድረግ የፌዴራል መንግስት ጥያቄውን እንዲቀበልና በሀገሪቱ አሁን ባለው ስርዓት መሠረት ህዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡ ይህንንም ጥያቄ እውን ለማድረግ እና በሕጉ አግባብ እንዲስተናገድ ለማድረግ የተከማው ነዋሪ የስምምነት ፊርማ የማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ጥሪውም በነዋሪ ሕዝቧ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማስረገጥ ድጋፉን በፊርማ የሚያቀርብበት የአሰራር ዘዴ ይቀይሳል፡፡
በመጨረሻም ይህንን የጳጉሜ ሣምንት በግፍ ለታሰሩ የፓርቲያችን መሪ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች በግፍ ከታሰሩበት እንዲፈቱ በተለያዩ መንገድ ግፊት ለምታደርጉ ወገኖች ምስጋናችንን እያቀረብን፣ መንግስት በማን አለብኝነት ያለ ኃጢያታቸው አስሯቸው የሚገኙ ንፁሃን መሪዎቻችንን እና አባላቶቻችንን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
መጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ ከኮሮና ስጋት ተላቀን በሰላም ወጥተን የምንገባበት፣ ለሀገራችን ዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት፣ለተበደሉ ፍትህ የሚሰፍንበት፣ ዲሞክራሲ የሚያብብበት እንዲሆን እንመኛለን፤ ለብሔራዊ መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ወገኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስምምነት ላይ የሚያደርስ ተጨባጭ ስራዎች የምናከናውንበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞቱን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገልጻል፡፡
ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!
ጳጉሜ 3/2012 ዓ.ም
Filed in: Amharic