>
5:16 pm - Monday May 24, 3362

እስክንድር እና የአሸባሪነት ክሱ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

እስክንድር እና የአሸባሪነት ክሱ

  ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ


የዶ/ር አብይ አስተዳደር በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለመደገፍም ይሁን ለመቃወም ግራ የሚያጋባ ስርዓት ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አብዛኛው ኢትዬጲያውያን ድጋፉን ለግሶት ነበር ምክንያቱም ከነበረው አስከፊ ስርዓት ጋር ሲነፃፀር በርካታ ማሻሻያዎች ተወስደው ነበርና፡፡ እውነት እና ንጋት እያደረ ይጠራል ነውና ቢሂሉ፤ ቀን ቀንን እየወለደ ሲመጣ ግን የስርዓቱ ትክክለኛ ገፅታ እየለየለት መጣ፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳፍሩ ድርጊቶችን ከስርዓቱ አይተናል፤ የመሪዎችን የወረደ ብቃት ገምግመናል፤ የስብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል አስተናግደናል፤ስርዓቱ ለኢትዬጲያ እንደማይመጥን ተረድተናል፡፡

ዛሬ ደግሞ የእስክንድር ነጋን የአሸባሪነት ክስ ሰምተናል፡፡ እስክንድር ነጋ ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና ያለው፣ አስተዋይ እና ሀገር ወዳድ  ኢትዬጲያዊ ነው፡፡  እስክንድር ጊዜውን፣ ዕውቀቴን፣ ንብረቱን ሳይሄን ማንነቱን ለኢትዬጲያ የሰጠ የቁርጥ ቀን ጀግና ነው፡፡ እስክንድር  ካለው ትጋት፣ ቅንነት እና ሀገር ወዳድነት አንፃር መንግስት ሊጠቀምበት ሲገባ በሀሰት ክስ መወንጀል አግባብ አይደለም፡፡ እስክንድር ነጋ የመንፈሳዊ እና የሞራል ልዕቀቱ እውነትኛ ከሆነ መንፈሳዊ መሪ ጋር የሚወዳድር ታላቅ አንጋፋ ሰው ነው፡፡ 

ይህን ሰው በሽብር ከስ መክሰስ ለገዥው መንግስት ከፖለቲካ ትርፉ ይልቅ ፖለቲካዊ ኪሳራው ያመዝናል፡፡ በፍትህ ዙሪያ ስርዓቱ እንዳልተለወጠና ሊለወጥ እንደማይፈልግ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡   

በሀሰት ክስ አዙሪት ውስጥ ተጠምደን፤ የሚሰነፍጥ እውነትን እየሸሸን፣ በተሻለ ሀሳብ የሚሞግቱንን እየወነጀልን እስከመቸ እንደምንጓዝ አላውቅም፡፡ ዳሩ ግን የሀሰት ከሳሾችን የብረት መወርወሪያ የሚሰብር ብርቱና ኃያል እግዚአብሄር በሰማይ አለ፤ እሱም ይፈርዳል፡፡ እኛም ባሪያዎቹ ዝም አንልም ኢ- ፍትሀዊ ድርጊትን እናወግዛለን፣ እንታገላለን፡፡

Filed in: Amharic