>

የኢትዮጵያ ወራት እና ስያሜያቸው...!!! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የኢትዮጵያ ወራት እና ስያሜያቸው…!!!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

 

በኢትዮጵያ የወራት ስሞች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ፤ እርስ በርስ የተወራረሱ ናቸው። አማርኛ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተስፋፋ የመጣ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠን፤ ቃላቶችን ከግዕዝ፣ ከኦሮምኛ፣ ከአፋር፣ ከአረብኛ፣ ከጣልያንኛ እና ካመቸው ወይም ህዝብ የተቀበለውን የራሱ እያደረገ እና እያደገ የመጣ ቋንቋ ነው። ከመስከረም እስከ ጳጉሜ ያሉትን የወራት ስያሜዎች ከመረመርን ደግሞ፤ የዚህን እውነት እንረዳለን…!
ወደ ኢትዮጵያ የወራት ስያሜዎች እና አመጣጣቸው ከመሄዳችን በፊት ግን፤ በአገራችን ካሉት ቋንቋዎች መካከል በኦሮምኛም፤ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የወራት ስሞች በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ ስያሜ እንደነበራቸው ማስታወስ እንወዳለን። እነዚህን ልዩ ልዩ ስያሜዎች ወደ አንድ መደበኛ ቃል ማምጣት በማስፈለጉ፤ በኦሮምኛ በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የወራት ስያሜዎች አንድ ላይ ሰብሰብ በማድረግ፤ የተሻለውንና በብዙዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የዋለውን ቃል በመምረጥ፤ አሁን በመደበኛ የኦሮምኛ ቃል ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።
ለምሳሌ – የመስከረም ወር “ፉልባና” ይባላል። ስያሜውን ያገኘው ከሜጫ ኦሮሞ ነው። የጥቅምት ወር አንኮሌሳ ይባላል – ከአርሲ እና የባሌ ኦሮሞ የተወሰደ ነው። ህዳር ሶስተኛ ወር ሲሆን አርሲ እና ባሌ ሰደሳ ወይም ሶስተኛ ይሉታል። ቃሉም ከዚያ የመጣ ነው። የታህሳስ ወር በቱለማ ኦሮሞዎች ዘንድ ሙዴ ይባላል። የጥር ወር አማጄ ማለት ሲሆን ስያሜውን ከአርሲ እና ከባሌ ኦሮሞ ነው ያገኘው። ጉራንላ ከቦረና ኦሮሞ የተወሰደ ሲሆን፤ የካቲት ወር ማለት ነው። መጋቢት ወር ቢቶሴሳ ይባላል፤ ስያሜውን ከአርሲና ባሌ ነው ያገኘው። የሚያዝያ ወር ኤልባ የሚባል ሲሆን፤ ከቱለማ ኦሮሞ የተወሰደ ቃል ነው። ከግንቦት ወር ጀምሮ ያሉት ወራት፤ በአርሲ በባሌ፣ በቦረና፣ በጉጂ በቱለማ ተመሳሳይ ትርጉም ስላላቸው ያለምንም ምርጫ ግንቦት – ጫምሳ፤ ሰኔ – ዋጣባጂ፤ ሃምሌ – አዶሌሳ፤ የነሃሴ ወር ደግሞ ሃጋያ ይባላል።
ይህን ያህል የኦሮምኛን ወራት የቃል አመጣጥ ካወቅን ይበቃናል። ነገር ግን እዚህ ላይ የብሄሮችን ቋንቋ ተወራራሽነት ለማሳየት እንድንችል፤ በሲዳማ እና በኦሮምኛ ውስጥ የሚገኙ ወራት መኖራቸውን እናስታውሳቹህ። ለምሳሌ ሳደሳ፣ አርፋሳ፣ አንኮሌሳ፣ አዶሌሳ… የመሳሰሉት የወራት ስሞች በሲዳማ እና በኦሮምኛ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ኩሼቲክ ወደ ሴማዊ ኢትዮጵያ በመሄድ፤ የአማርኛ ወራት ስያሜ ታሪካዊ አመጣጣቸውን ወይም ስለ ስነ-ውልደታቸው እንጨዋወታለን።
መስከረም – የመስከረም ወር አበቦች በየመስኩ የሚፈነዱበት፤ አደይ አበባ ምድሪቱን የሚያለብስበት ወር ነው። ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጪ፤ እጅግ ውብ የሆነ አገር ሲባል የሚሰሙት፤ ስለ ሮም እና ሮማውያን ነው። እናም ይህን በአበባ ያጌጠ መስክ – መስከ-ሮም ብለው ይጠሩታል። ይህን ለማረጋገጥ በተመሳሳይ መልኩ ረዥም እድሜ ያለውን የጉራጌ ሴማዊ ቋንቋ ማየቱ ይበቃል። በአብዛኛው የጉራጊኛ ቋንቋ መስከረምን…. መስከሮም ወይም መስከሮብ ይሉታል። አማርኛው ታዲያ ቃሉን ከርክሞ እና አስተካክሎ – መስከረም ብሎ ሰይሞታል።
ጥቅምት – በተለይ በገበሬው ዘንድ የጥቅምት ወር የሚታወቀው፤ ጥራጥሬ ተዘርቶ እሸት የሚያፈራበት ወር በመሆኑ ነው። ይህ ወር ከሌላው ወር በበለጠ፤ ለገበሬው እና ለከብቶቹ ጠቃሚ ወር ነው። በመሆኑም ጥቅም የሚሰጥ ጠቃሚት ወይም ጥቅምት ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነው።
ህዳር – ከመስከረም እና ከጥቅምት ወር በኋላ የሚመጣ ወር ነው። አንዳንዶች ህዳርን “ሃዳር” ከሚለው የግዕዝ ቃል ጋር በማዛመድ፤ “ከማደር” ጋር በማያያዝ – ታሪካዊ አመጣጡ ግዕዝ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ይጥራሉ። ሆኖም… የዚህ 3ኛ ወር ስያሜ የመጣው ባህር ተሻግሮ መሆኑ እውነት ነው። የህዳር ወርን… በግብጽ እና አረብ አገሮች፤ አቶር እና ሃቶር ሲሉት በእብራይጥ ደግሞ፤ አዳር በሚል ስያሜ ይታወቃል። በነገራቹህ ላይ ህዳር በግዕዝ ሲጻፍ ‘ኅ’ዳር ሲሆን፤ በትግርኛ ‘ሕዳር ነው። አማርኛው እንዳመቸው አድርጎ ሃሌታው ‘ሀ’ በመጠቀም ህዳር ይለዋል። የሆኖ ሆኖ የጥንት አባቶች የህዳር ወር ስያሜን ከጥንታዊው የባቢሎን ቋንቋ ወስደውታል። ይህ ካልሆነ ደግሞ በቸሃ ጉራጌ ህዳርን “ይዳር” ይለዋል። ስለዚህ ከውጭ ካላመጣነው ከራሳችን የጉራጌ ሴም ቋንቋ ተውሰነው ሊሆን ይችላል።
ታህሳስ – በግዕዝ ሐሰሰ ማለት፤ ተጓዘ ሄደ፤ ወይም አሰሰ እንደማለት ነው። የታህሳስ ወር ደግሞ ወታደሩም ነጋዴውም ከአገር ወዳገር የሚንቀሳቀስበት፤ የሚሄድበት፤ አገር የሚያስሥበት ወር ነው። ጉዞ ብሎ ተጓዘ እንደሚባለው… ሐሰሰ ብሎ ተሐሰሰ በመሆኑ፤ ተሃሰስ ወይም የጉዞ ወቅት ማለት በመሆኑ – ታህሳስ ቃሉን ያገኘው – ሀሰሰ ከሚለው ቃል መሆኑን መቀበል አይከብድም።
ጥር – በግዕዝ ጥሁር ማለት፤ ንጹህ ወይም ጥሩ ማለት ነው። የጥር ወር ሰብል ተሰብስቦ፤ ጥጋብ የሚመጣበት፤ ሰርግ እና ምላሽ፤ ድግስ እና ግብዣ የሚዘወተርበት ወር ነው። ለዚህም ነው – በግዕዝ ጥሁር፤ በአማርኛ ጥሩ ወይም ጥር የሚል ስያሜ ይዞ የቀረው። በሌላ በኩል ደግሞ – ለምሳሌ በጥንታዊው ደቡብ አረቢያ “ፀረረ” እና በጉራጊኛ – የጥር ወርን “ጥርር” በሚል ስያሜ ይጠሩታል። የዚህም መነሻ – በዚህ ወር ያለው ጠራራ ጸሃይ ሊሆን ይችላል። የጸሃይዋ መጥረር ወይም ማቃጠል አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል – “ጥር” የሚለውን ስያሜ ያስገኘልን።
የካቲት – በግዕዝ ከቲት ወይም ይከትት ማለት፤ መክተት ከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር አቻ ናቸው። በገበሬው ዘንድ እህል ተሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚከተትበት ወር ነው። በመሆኑም የመክተቻ ወር መሆኑን ለማመልከት – የካቲት ተባለ። ከቲት ማለት ከታች ማለት ሲሆን፤ የካቲት ደግሞ የመክተቻ ጊዜ እንደማለት ነው።
መጋቢት – የመጋቢት ወር ፍቺ ግልጽ ነው። በግዕዙም ቢሆን… ምግብ የሚመግበውን መጋቢ፤ አንስታይ ጾታ ወይም ሴት ከሆነች ደሞ መጋቢት ይለዋል። ጥቅምት ጠቃሚ ወር በመሆኑ፤ ጠቃሚቷ ወር ጥቅምት ተብላለች። አሁን ደግሞ ምግብ ሰጪ እና መጋቢ የሆነውን ወር – መጋቢት ያሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህ የበልግ ወር እህል እና ጥራጥሬ ብቻ ሳይሆን፤ ወፍ ዘራሽ እና የጫካ ፍራፍሬዎች ጭምር በየስፍራው ያድጋሉ። እንሰሳት እና አእዋፋትም እንደልባቸውና እንደሆዳቸው መጠን የሚመገቡበት ወር ስለሆነ፤ ይህን የምግብ እና የጥጋብ ወር መጋቢ ወይም መጋቢት ብለው ጠሩት።
ሚያዝያ – በአረብኛ – ማዛ ማለት መልካም ወይም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ሚያዝያን ከመልካም ሽታ ጋር ያያይዙታል። እውነታው ግን ወዲህ ነው። ሚያዝያ የሚለው ቃል የሚወለደው፤ “መሐዘ” ከሚለው የግዕዝ ቃል ነው። መሐዘ ማለት፤ ጎለመሰ ወይም ሚስት ለመያዝ በቃ ማለት ነው። እንደልማድ ሆኖ ከግንቦት ወር ጀምሮ ሰርግ አይደረግም። ስለዚህ የጎለመሰ ወይም የመሐዘ ሰው፤ ሚዜ አደራጅቶ ሚስት የሚያገባው ከግንቦት ወር ቀድሞ በሚገኘው ወር ነው። በዚህ ምክንያት ወሩም… ትዳር መያዣ ወይም መሐዘ – መሐዘያ – መያዥያ ሲባል ቆይቶ፤ አማርኛው ሚያዝያ ብሎ ቃሉን ወረሰው።
ግንቦት – ትርጉም እና አመጣጡ አማርኛ ነው። በዚህ ወር መሰረት ተቆፍሮ ግንባታ የሚጀመርበት ነው። ለምሳሌ ፈለገ የሚለው ቃል ፍላጎት እንደሚባለው፤ ሰረቀ ብሎ ስርቆት እንደሚባለው፤ ገነባ ብሎ ግንቦት ይላል። በአገራችንም በዚህ ወር በርካታ የግንባታ ስራዎች ይከናወናሉ። የአባይ ግድብ ጭምር የተጀመረው በግንቦት ወር ነው።
ሰኔ – የቃሉ ምንጭ ትግረ ትግርኛ ነው። በትግረ ሰነየ ማለት መልካም ሆነ፤ ሰናይ ሆነ፤ አማረ ማለት ነው። ይህ ወር በአርጎብኛም ጭምር ሰነይ ይባላል። አማርኛው በሂደት ቃሉን… ከሰነይ ወደ ሰኔ ቀየረና የዚህ ወር መጠሪያ አድርጎታል።
ሐምሌ – በሐምሌ ወር ክረምት ይገባና ልምላሜ ይጀምራል።  የለመለመ ነገር ደግሞ ሐመልማል ይባላል። ሐመለ ማለት አበባ አፈራ ማለት አይደለም፤ አበበ ወይም ለመለመ ማለት ነው። ሐምለይ ማለት ደግሞ ለምለም ማለት ነው። በስነ ቃል ብዜት… ሐመለ፣ ሐምለይ እያለ ይበዛል። ደቡብ አርጎባም ቢሆን፤ እንዳማርኛ ወሩን ሐምሌ ነው የሚለው። የሆኖ ሆኖ… ሐምለይም በጊዜ ሂደት ወደአማርኛው አጠራር ሐምሌ ተባለ። በትግርኛ ሐምለ፤ ጉራጌ አገር ደግሞ ክስተን፣ ስልጢ፣ ወለኔ፣ ሙኸር ሐምሌን አምሌ ይሉታል።
ነሃሴ – የነሃሴ ወርን አመጣጥ ከአረብ አገር የሚያደርጉ አሉ። በእርግጥ ግብጽ እና አረቦች የጳጉሜን ወር “ናሴ” ብለው ይጠራሉ። ሆኖም 12ኛ ወር ማለትም ነሐሴን ከአረቦች ወሰድን የሚለውን አልስማማበትም። በግዕዝ ነሐሰ ማለት መስራት እና መገንባት ነው። በአገራችን በነሐሴ ወር የሚገነባ ነገር ብዙም ስለሌለ፤ ከግዕዙ መጣ ለማለት ያስቸግራል። የነሃሴ ትክክለኛ አመጣጥ ሊሆን የሚችለው፤ በዚህ ወር በሰማይ ላይ የምናያቸው ነሃሳማ ቀለማት ናቸው። እዚህ ላይ ስለነሃስ ለማያውቁ ሰዎች ጥቂት ማብራሪያ እንስጥ።
ነሃስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለረዥም ጊዜ ይታወቃል። የቤተክርስቲያን ደቀል፣ መስቀል እና ጸናጽል ጭምር በነሃስ ይሰራል። ነሃስ ደግሞ በባህሪው እየቆየ ሲመጣ ቀለሙ ወደግራጫነት ይቀየራል። እጅግ ከበዙት የአለማችን ሃውልቶች መካከል የኒውዮርኳን Liberty of Statue መጥቀስ ይቻላል። በነጭነት እና በግራጫነት መካከል የሚገኝ ቀለም አላት። የነሃሴን ሰማይ ብንመለት፤ እንደአህያ ሆድ ነጭ፣ ግራጫ እና ጠቆር ብሎ እናየዋለን። እናም በኢትዮጵያ የነሃሴ ወር ሰማይ ነሃስ የመሰለ፤ ነሃሰይ የሆነ ነው። ነሃሰይ ማለት ደግሞ ነሃስማ ቀለም ማለት ሲሆን፤ አማርኛው ደግሞ ልክ ሰነይን ሰኔ፤ ሐምለይን ሐምሌ እንዳለው፤ ነሃሰይን ነሃሴ ብሎታል።
ጳጉሜ – እነዚህ 12 ወራት ወይም 360 ቀናት ካለቁ በኋላ፤ ሽርፍራፊና ቀሪ 5 ቀናት ይኖራሉ። እነዚህ ትርፍራፊ ቀናት በእንግሊዘኛው  epagomenal ኤፓጎሜናል ይባላሉ። በግሪክ ደግሞ ፓጉሜን ይሉታል፤ የግሪክ አቻ ትርጉም “የተረሱ ቀናት” ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ… እነዚህ አምስት ቀናት ያሉበትን የቀናት ጥርቅም አንድ ላይ አድርገው፤ 13ኛ ወር አድርገውታል። ቃሉንም ከግሪክ በመዋስ፤ ፓጉሜን ጳጉሜ ብለነዋል።
Filed in: Amharic