>

ወገኔ ሆይ ስማ (በዘምሳሌ)

ወገኔ ሆይ ስማ

በዘምሳሌ 


ይቅር መነጣጠል
በኢትዮጵያ ክፍል
ዘርን እየለዩ ዘር በዘር መቋሰል ።
መጤ እያላችሁ ሰውን በሀገሩ እያባረራቸሁ
ደሜን ከደማችሁ እየነጠላችሁ
የሰው ስብዕናን ክብር የነካችሁ
ልዩ ነን አትበሉ ልዩነት ናፍቋችሁ
ያልነበረን ታሪክ እየፈጠራችሁ
መጤ ነህ አትበሉ እናንተ መጥታችሁ
ወገንን ከምድር እያፈናቀላችሁ
ስላማዊ ህዝብን ሽብርም ነዝታችሁ
ሰዉን እርስበርስ በቁም አባላችሁ።
ለግማሽ ምእትም ዘርን ሰትሰሩ
ብሶት ስትፈጥሩ ብሶት ሰትዘሩ
ግፍ እየኖራችሁ ግፍን ስትጨምሩ
ጥላቻን ስትዘሩ ዘርን ስታከሩ
የሌላውን ሰው ዘር ጉድጓድ ስትቆፍሩ።
በብሔር አውድማ
በተረኝነት ገድል ስንቱ ቆስሎ ደማ
ህይወቱም ተቀጥፎ በመንገድ ገለማ
በግልፅ ጥቅመኝነት በከንቱ አላማ
በዘር አመካኝተው ሆነው እንዳልሰማ
ግፍን ሲጨምሩ ሆነው በከተማ
ቤት ንብረት ሲያነዱ ሆነው እንዳልሰማ።
በጎሳ ክፍፍል የሰውልጅ ሲገደል
ዘር እየተለየ ዘሩ ሲመነገል
ባገር ሲገለል በእምነቱ ሲቆስል
ሲታረድ ሲቆረጥ ሲጨምር ከገደል።
አመታት ነጎዱ ግማሽ ምእት ሆነ
የዘረኝነት ምክር ባገር ከሰፈነ
በአጥፊዎች ደጃፍ ይኼው ከገነነ
የዜጎችን ህይዎት በከንቱ እያጎነ።
ወገኔ ተው ንቃ ዘረኝነት ይቅር
ሞትን ሙቶ መኖር
በኢትዮጵያ ምድር
ስትኖርን መኖር
ራስ ወገንህን መግደልና መቅበር።
የበቀል ምልክት በልብ ሰንቀው
ሕግ እያራቀቁ ሕጋቸውን ንቀው
በማንአለብኝነት ስብዕናን ገፈው
አረዱት ፈረጁት በሀሰት ብያኔ
እቆማለሁ ባለ እርሱም ለወገኔ
የሀገሬ ሕዝብ ሆይ እህህ እስከመቼ
በሚያማልሉ ቃል ፊትህ እየዋሹ
በስውር ደባቸው ህዝብ ሲያንገሸግሹ
ጊዜ በደላቸው በያዙት መሳርያ
ወጣቱን አሰፈጁት ሊያውም በገበያ።
እምባህን ሳትጠርግ ግፍ እየጨመሩ
የህግ ያለህ እንድትል በህግ የገተሩ
ተቋሞ እንድትገልፅ እያስደነበሩ
ተወስነህ እንድትቀር አንገት ሊያሰብሩ
ወህኒ ሊያኖሩህ ጠንክረው ሲሰሩ።
ታጅለህ እንድትቀርብ እንዳልሆንክ ዜጋ
በኖርክበት ምድር አሳጥተው ዋጋ
ውጣ ልቀቅ አሉ ዘርህን ፍለጋ።
  ወገኔ ሆይ ስማኝ
እንዲህ በል በላቸው
እምቢ ለሃገሬ
ለተሳሰረባት ደሜን ከደማችሁ
አጥንቴም ከምድር በላይ ካጥንታችሁ
እትብቴ ተቀብሮ ከኖርንበት ምድር
እኔን ነጥላችሁ
ውጣ ማለታችሁ
ከቶውንም ለምን እንዴት ታሰባችሁ
መጤ እያላችሁ ሰው ማሳደዳችሁ
ያልነበረን ታሪክ በትርክት ፈጥራችሁ
የናንተን አመጣጥ ማንስ ይንገራችሁ
መጤ ነህ አትበሉኝ እናንተ መጥታችሁ
በ ባዕዳን ምክር ሰው እያስፈጃችሁ
ያልነበረን ወንጀል በድርሰት ፈጥራችሁ
በዘር በሃይማኖት ኢትዮጵያን ከፍላችሁ
በልቦለድ ውሸት ሀውልት አቁማችሁ
በሀገሬ ምድር ግፍ እየዘራችሁ
ማጨዳችሁ ላይቀር ይህን ክፋታችሁ
ቀን እነደሁ ይመጣል በቁም ሊፈርዳችሁ
ለምትሰሩት ግፍ ቁና ሊሰፍራችሁ።
ወገኔ ተው ስማ
አይጠቅምም ዝምታ
ታስረህ በይሉንታ
በውሸት ትርክት
በቀጣፊው ቅጥፈትና ድርሰት
ስግብግብ አላማ የማንነት ህይወት
አርቆ ሳይቀበርህ ባታላዩ ስብከት።
ከገባህበትም የእንቅልፍ አለም ኑሮ
ተው ንቃ ይሻላል ሳያንቅህ አሲሮ
በካድሬዎች ስብከት ጩኸት ግር አይበልኽ
ወገን አይበደል አይገደል ደጅኽ
ታግለህ መጣል ስትችል ወንጀለኞች በጅኽ።
ለኢትዮጵያ ስትል ተራዳ በፍቅር
ባብሮነት ለመኖር ወጥቶ ከጎጥ መንደር
ከእንግዲህ እንዲበቃ ሞትን ሙቶ መኖር
እያነቡ እስክስታን በገዳዮች መንደር
በተፈጠርክባት ባደግክባት ሀገር
ይቂም ይብቃ እንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር
አትሁን መልእክተኛ የበቀል ዛር ፍጡር
መለኮተ ፍጅት የወገን የቁም ፃር።
      ወገኔ ሆይ ስማ
እነርሱም ሲያሻቸው በቁም ሲባንኑ
በዘር ጠልነታቸው ወንጀል ሲከውኑ
የበደልን ውጥን ይዘው ሲዘውሩ
የኢትዮጵያወያን ደም አንጫልጠው ሲያቀሩ
ሽብርን ፈብርከው ደምህን ሲዘሩ፣ ሲያዘሩ።
በገዛ ምድርህ ላይ ልቀቅ ተጓዝ ሲሉ
በሀሰት ስያሜ መሬትን ሲያድሉ
ደጋፊ ለማብዛት ሌላውን ሲነቅሉ
የኖረውን ዜጋ አንጋጠው ሲገሉ
አዛዦችም ሆነው ፍርድ ሲገመድሉ
በጊዜያዊ አልቅና ሰውን ሲበድሉ
በየስፍራው ወጥተው ባንተ ሲፎልሉ።
       ወገኔ ሆይ ስማ
አይሆንም በላቸው
ለዋሾነታቸው፣
ያልነበረን እውነት ሲነግሩህ ባፋቸው
ቅሬትሲያከማቹ ለ ልጅ ልጆቻቸው።
ይብቃና ይበቃል የሁለት ቃሎች ጥምር
ሲነግሩት ሚቀል ሲያደርጉት የሚመር
የተገፊዎች ኪዳን የብርቱዎች ምክር
በላቸው ይበቃል ሀሞትህም ይምረር።
ወገኔ ይበቃል የወገን ሰቆቃ የንጉርጉሮ ኑሮ
በጥቅም ታጅሎ በገንዘብ ታውሮ
ህልውናህ ጠፍቶ የሰቀቀን ኑሮ
አጥፊው እያደባ
ሲገል የአዞ እንባ
ማስገደል መግደልን ወንጀሉን ባንቀልባ
መሸከም እንዲቀር ፍትህ እንዲጠባ
ፊለፊት ታገለው ወደትግሉ ግባ
አጥፋ ከኢትዮጵያ ላይ የዘረኛን ደባ።
        ወገኔ ሆይ ስማ
በቃላትና አማሎ ስሜትህን ገሎ
የህገ አራዊትን ህጌ ነውም ብሎ
የኢትዮጵያወያን ትግል በዳር አንገዋሎ
በስሟ ሲገዘት በብዙሃን ምሎ
ዝም ያልነው ላገር ነው
ብለኽም ንገረው
በጊዜያዊ ስብከት ታውረን እንዳይመስለው።
ጀግናው መች ጠፋና ብርቱ ተቆርቋሪ
ለኢትዮጵያ የሚሆን ላገር ታሪክ ሰሪ
ለዘሩ ያልወገነ ላገሪቱ መሪ ብሎም ፊት
አውራሪ።
ነግ በኔ ማለቱን ተረዳ ከወገን
በዘር ተሸብበህ ትተህ ማዳላቱን
በስልጣን መከታ ትተህ መዘባነ ን
እንደሚችል አውቀህ ህዝብ የሰቀለውን
መልሶ እንደሚያወረድ ቃል ያልጠበቀውን
የሟቾቹ ሲቃ ይሰማህ ያ ሀዘን
ተጎጂንም ታደግ ዝም አትበል ትተህ መጎፋነን
ስምህ እንዲጠራ አትደር ባንድወገን
ቀደሞ ስለሚያንቅህ ያ የገባኸው ቃል።
 ወገኔ ሆይ ስማ
ጊዜ የሰጠውንግዜም ያንሰዋል
በጨበጥካት መንበር ስንቶቹ አልፈዋል
ለታሪክ ቅድድም ብዙ ብታቅድም
በእድገት በለውጥ ስራ ራስን ብትሰጥም
ፍቅር በኢትዮጵያ እንዴትስ ሊታለም
ፈፅሞ ካልቆመ የሚፈሰውም ደም።
በዙሪያው ያጠርከው የጎሰኝነት ለምድ
ለሃገር የማይጠቅም የዜጎች መሳደ ድ
ከለላ እየሆነ በግላጭም በፍርድ
ከቀድሞ የባሰ የሰውልጆች ፍዳ
መከራና ውሎ የመታሰር እዳ
በጎሳ ተከፍሎ በ ብሔር መቋሰል
በኢትዮጵያችን ላይ ግፍንም መቆለ ል
በቋንቋ ገድቦ ራስን መደልደል
በተገፋ ህዝብም ላይ ፍርድንም ማጓደል ።
ኢትዮጵያ አትፈርስም
ትሰማ እንደሁ ስማ
በምኞት ምንደኞች ዘውጌዎች አላማ።
አትፈርስም ኢትዮጵያ አፍራሿ ይፈርሳል
በህዝቦቿ አንድነት ባንድ ይደመሰሳል።
ወገኔ ሆይ ስማ
ኢትዮጵያዊ ማለት
የሀበሾች ድምቀት
የሰው ልጅ ስብጥር ሕብረአበርነት
ያረንጓዴ ቢጫ የቀዩ ቀለማት
ያባቶች ጀግንነት ደም የፈሰሰበት
ጠላትን መክተው ያቆዩትነፃነት
ኢትዮጵያዊ ማለት
የአንድነት ስሬት በዘር ያልነወረ የሁሉ መሠረት
የሀበሾች ምድር የአፍሪካ ነፃነት
ገኖ የወጣበት፣
ኢትዮጵያዊ ማለት
በሄክበት ምድር አንገት ማትደፋበት
የጥቁር ዕንቁ ህይወት
አላማና ኩራት
የባርነትም ጠር
ነፃነት ቀዳጅ ፈር።
ኢትዮጵያዊ ማለት
የዜጎች የደም ስር
ጥንታዊቷ ሀገር
የአባይ ስጦታ መገኛ የሰው ዘር
የድንቅነሽ ሚስጥር
የክርስትና በር
የሙስሊሞች አምባ ዋስ ጠበቃ ድንበር
የሙሴ እንቁ ፅላት ማደሪያ ልዩ ሀገር
ደጋግመህ ጩኽላት እምቢ በል ላገሬ
ለተፈጠርኩበት ለኖርኩባት ክብሬ
ወገኔ ሆይ ስማ
ያባቶቸን ኪዳን በውስጥኽ ያኖርከው
ወንድም ከወንድሙ ተመርጦ ሲገደል
በታሪክ ያልሆነ የዝቅዝቅ ሲሠቀል
ከበው ሚያስተውሉ ይህን አገዳደል
ምስኪኑን ሲደፉ ሲሰክሩ በደም ጠል
አይነጋም መስሏቸው
ፀሐይ የማትወጣ
ፍዳን ሲጨምሩ በሀጢያት ላይ ቁጣ
ፍርድ እንደሁ አይቀርም ለጊዜው ባይመጣ
የግፍ ፅዋ ሞልቶ መፍሠሱ ማይቀር ነው
በሠፈሩት ቁና መሰፈር ያለ ነው።
በማንአለኝነት በክፋት ዳኝነት
ህዝብን ቢያሰቃዩ
ትውልድ ቢለያዩ
ዘርን እያሳዩ በጎጥ እየለዩ
ስልጣን ቢጨብጡ ዜጎች እየዳጡ
በሃሰት ኮርቻ ታሪክን ቢሸጡ
በዘረፉት ዶላር በውስኪ ቢራጩ ሃብትን ቢከምሩ፣
መንግሥት ቢዘውሩ።
ለሆዱ ያደረ ደጋፊ አከማችተው
በነጋ በጠባ ቢሉ አሰረሽ ምችው
በዙሪያቸው ቢያዙም አይሞላ ስስቱ
የደም ጥማታቸው፣
ሰው የሚቀሉበት ቢላ ገጀራቸው።
ወገኔ ሆይ ስማ
እንደግሪሳ ወፍ ግር ብለው ሲወጡ
አይናቸውም ፈጦ በጥርስ እያገጡ
አውሬዎች ሲወጡ አውሬዎቹ መጡ
የሰው ደም ሊጠ ጡ አጥንቱን ሊግጡ
አርፎ የኖረን ህዝብ በግላጭ ሊድጡ።
ወገኔ ግን ስማ
ይሄ ሁሉ ሲሆን አይቶእንዳላየ
ሰምቶ እንዳልሰማ ዋንኛው ታበየ
ግና መች ሆነ ና ግብረ መለኮቱ
ለህዝቦች የቆመ ቢሆን ማንነቱ
ባልታበየ ነበር በዘር ተጠፍሮ ልምራችሁ ማለቱ።
ጆሮ አይሰማው የለ ባዲስ ዜማ ጉዞ
በይስሙላ ይቅርታ፣
ለበደሉት ካሳ ሳይሰጥ ወሮታ
ምንድነው ይቅርታ
ከልብ ያልመነጨ
የዜጎችን ህይወት ሀብትን እያስፈጨ
በበደል ላይ በደል በሰው ልጅ ወዮታ
ካልተስተካከለ የዜጎች እውነታ
በእኩል ያልቆመ የበደል ከፍታ
እንዴት ይታሰባል በቀላሉ ይቅርታ
ሕዝብ እያፋጁ በደል እያወጁ
የተገፋውን ሰው በደሉን ሳይዋጁ
ቀላል ነው ለነርሱ ይቅርታን ማወጁ
በቁሙ ሲሰቃይ ሁሉ በየደጁ
ወገኔ ግን ስማ
አይሆንልኝም በል ይኽ ዋሾነታቸው
ያንገት በላይ ምፀት ይቅር ማለታቸው
እንኳን የቅርብ በደል
ያልተፈፀመውን የሗለኛ ዘመን
ያልሆነውን ታሪክ ተፈፀመ ብለው ሁልጊዜም ሲሠብኩ
ጣዖት መሳይ ሀውልት አኖሌን ገትረው
ሕዝቦችን ሲያስፈጁ
ጦርነት ሲያውጁ
ሃምሳ አመታት ሞላ ቆመው ሲያንጎላጁ
ወገኔ ሆይ ስማ
ለሀገርህ ብለህ ቁም በአንድ አላማ
ውጣ ለነፃነት ለኢትዮጵያ ግርማ
ይፍረስ የዘር አጥር
የአንድነቱን ፀር
የግፍ ህይወት ቀንበር
ከሀበሾች ጫንቃ ይነጠል ይሰበር
ለዘላለም ኮርታ ኢትዮጵያ እንድትኖር
ታፍራና ተከብራ ባለም ህዝቦች መሀል
ይቁም የዘር በደል በገንዘብ መደለል
ህዝብ እየነጠሉ መገደል ማንገዋለል
በየስፍራው ሁሉ በኢትዮጵያ ክፍል።
ወገኔ ሆይ ስማ።።

 

Filed in: Amharic