በወረቀት ገንዘቦች ላይ የተደረገው ለውጥ
ከይኄይስ እውነቱ
ወራሪዎችን፣ አፈናቃዮችና ነፍሰ ገዳዮችን በማሠማራትና በማስተባበር የሙሉ ጊዜ ሥራው ያደረገውና ራሱን ‹‹ብልጽግና›› ብሎ የሚጠራው የኦሕዴድ አገዛዝ አገርንና ሕዝብን በማወክ፣ በማስጨነቅና ዕረፍት በማሳጣት፣ አገዛዝ ሠራሽ ከሆነው ከዚህ መአት ብቸኛ ታዳጊያችሁ እኔ ስለሆንኩ ለእኔ አርፋችሁ ተገዙ በማለት ከፈጣሪው ከወያኔ የቀሰመውን ሰይጣናዊ ልምድ ያዋጣኛል ብሎ ከተያያዘው ሰንበትበት ብሏል፡፡
ያልበላውን ማከክ ልማዱ የሆነው ይህ አገዛዝ ሰሞኑን ደግሞ አንድ ማናጠቢያ ጉዳይ ወርውሮልናል፡፡ 20 የሚጠጉ ባንኮችን ያዘረፈና ሕግ ፊት አቅርቦ ያልጠየቀና ያላስመለሰ፣ ብሔራዊ ምልክታችን የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌቦችን አሠማርቶ ባዶውን ያስቀረ፣ አንጋፋውን የቤቶችና ቁጠባ (ሞርጌጅ) ባንክን ያከሰመ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልማትን ወይም ኢንቨስትመንትን ለማገዝ ያቋቋሙትን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወያኔ ቀረ የተባለውን ጥፋት በመፈጸም ግብአተ መሬቱን ለመፈጸም እየሠራ ያለ፣ ውሱን የሆነ የውጭ ምንዛሬን በሕገወጥ መንገድ ለተረኞች ወይም በጥቅም ለተሳሰሩ ድርጅቶቸና ግለሰቦች ያደለ የወራሪዎችና ዘራፊዎች ስብስብ በማንአለብኝነት ሥራ ላይ ያለውን የወረቀት ገንዘብ ቀይሯል፡፡ ለውጡ ፖለቲካዊ ምክንያት ይኑረው ለግል ዝና ጊዜው ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህንን ለማድረግ ሥልጣን (ማንዴት) አለው ወይ? ብሎ መጠየቁም ትርጕም ያለው አይመስለኝም፡፡ ለምን አሁን? ጠቀሜታውስ? የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ሙያዊ ማብራሪያ መሻቱም ለዕውቀት ካልሆነ በቀር መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚቀይረው አይመስለኝም፡፡
እውነት በዝርፊያ የተሰበሰበው ገንዘብም ሆነ ሕገ ወጡ የውጭ ምንዛሬ ማን ጋ ነው ያለው? አገራችን እውነተኛ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት መ/ቤትና ባለሙያዎች ቢኖራት በዚሁ በመዲናችን እንኳን እንደ እህል በየመጋዘኑ የተከማቸውን ጥሬ ገንዘብ ዐቢይና የግል ‹ፀጥታ› መ/ቤታቸው አጥተዉት ነው?
እኔን እንደ አንድ ዜጋ ያሳሰበኝ የወረቀት ገንዘቡ ለውጥ ባገራችን ላይ ያስከተለው አላስፈላጊ የሕትመት ወጪ እና ጥሮ ግሮ የሚያድረው ተራው ዜጋ ለሕይወቱና ንብረቱ ዋስትና በሌለበትና እምነቱን የማይጥልበት አገዛዝ ጋር ያለችውን ትንሽ ጥሪት በአደራ እንዲያስቀምጥ በጉልበት መገደዱ ነው፡፡ ላገር ለወገን የሚያስብ የሚሠራ መንግሥት ባለበት ሕዝብ የቁጠባ ባህል እንዲያዳብር ማስተማር በተግባርም እንዲቆጥብ ማድረግ ላገር ኢኮኖሚ ዕድገት ታላቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የኢኮኖሚ ጠበብትነትን አይጠይቅም፡፡ የአሁኑ የዐቢይ የግል ርምጃ ግን የአገር ሀብት በዝርፊያ ወደ ውጭ ያሸሹትን፣ ሕገ ወጥ ገንዘብ በ‹ሕጋዊ› ድርጅቶች ሽፋን ያዘዋወሩትን፣ በወንጀል ገንዘብ ልጆቻቸውን ባሕር ማዶ የሚያቀማጥሉትን፣ ኢሕአዴግ በተባለው የወንጀል ድርጅት ውስጥ የሚገኙ የ4ቱን ድርጅቶች ዘራፊ አመራሮች ለማስመለስ፣ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ በአገር ሀብት የተፈጸመውን ንቅዘት እና በቀጣይም እየተፈጸመ ያለውን ሥርዓት ለማስያዝና ሌቦችንም ለፍርድ ለማቅረብ የታለመ አይደለም፡፡ ማን ንጹሕ ሆኖ (መቐለ የሸሸው የሽብርተኞች ስብስብም ሆነ አሁን አገር የሚያምሰው ኦሕዴድና ማኅበሩ) ጣቱን በሌላው ላይ የመቀሰር የሞራል ብቃት አለው? የ27 ዓመታቱ የወያኔ የአገር ጥፋትና ውድመት ሬከርድ በዚህ የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በዐቢይና ዘረኞች ዘመዶቹ የጥፋት ‹ማራቶን› አልተሰበረም? በአገዛዙ አመራሮች የሚታየው ቅጥ ያጣ የትእቢት፣ የንቀትና የማንአለብኝነት መንፈስ አብጦ ሊፈነዳ የተቃረበ ይመስላል፡፡ የሕዝብም ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነትም ፍጻሜው እየቀረበ ይመስላል፡፡ የ‹ሰውየው› አገዛዝ ቀናትም እየተቈጠሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኀ ሠራዊቱ፡፡ ወያርብኅኒ ኢድኅነ በብዝኀ ኃይሉ፡፡ እንዳለ ንጉሥ ዳዊት (በመዝሙር 32÷16) ያ ቀን ሲመጣ መሸሸጊያ ጥግ አይገኝም፡፡