>

ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፡- እየተፋቀሩም፣ እየተናቆሩም! (እውነት ሚድያ አገልግሎት)

ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፡- እየተፋቀሩም፣ እየተናቆሩም!
እውነት ሚድያ አገልግሎት

 

✍️ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› የሚለው መርህ ተግባራዊ አፈጻጸሙ አጠያያቂ ነው፤ ሁለቱም በተመሳሳይ ሕዝብ ላይ ስለሚያተኩሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‹‹መነካካታቸው›› አይቀሬ ነውና፡፡
 
✍️ የኦርቶዶክስን ‹‹ብሔራዊ ሃይማኖት›› ሆኖ መቆየት እንደ ታሪካዊ ስህተት፣ የድህነታችን መንሥኤ እና ኋላቀርነት የሚያዩ ሰዎች አሉ፤ ዛሬም ድረስ ብሔራዊ ሃይማኖት ኖሮአቸው በምጣኔም፣ በሥልጣኔም እጥፍ የሚበልጡን ሀገራት እንዳሉ ግን መረሳት የለበትም! 
 
✍️ በሀገራዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር መተባበር በየትኛውም አኳኋን ‹‹ፖለቲከኛ›› ሊያሰኝ አይገባም፤ ለሃይማኖቱም ምድራዊ ሕልውና የሀገር ሰላምና ልማት ያስፈልጋልና፡፡
 
✍️ ‹‹ሁለቱም ተጋቢዎች›› ለረጅም ጊዜያት ክፉውንም፣ ደጉንም አብረው ሲቋደሱ እንደመኖራቸው፣ ዛሬም በብዙ ነግሮች መፈላለጋቸው ስለማይቀር ጋብቻው ጸንቶ መኖሩ አያጠያይቅም፤ በትዳር ወግ እየተፋቀሩም፣ እየተናቆሩም ይኖራሉ!
 ““““““““
መንግሥትና ሃይማኖት በመርህ ደረጃ በዓላማም በአካሄድም የተለያዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የሁለቱም ሕልውና የተመሠረተው በሕዝቡ ላይ በመሆኑ ትኩረት (Target Group) ያመሳስላቸዋል ብቻ ሳይሆን ወደየራሳቸው ፍልስፍና በመሳብ ሂደት ውስጥ ያነታርካቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ‹‹በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት›› ናት፤ ምድራዊው መንግሥትም በሕዝብ ተመሥርቶ፣ ለሕዝብ የሚሠራ፣ ሕዝባዊ ነው፡፡ እናም ሁለቱም ያለ ሕዝብ (ሰዎች) ኀልዎታቸው ሊነገር አይችልም፡፡
1.    ታሪካዊው ጋብቻና ገጽታው
ግንኙነቱ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት ትስስር በዓለምም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የነበረ፣ ዛሬም ድረስ የሚስተዋል ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሁለቱ ‹‹ጋብቻ›› ፍልስፍና ከተጠቀሱት ሁለቱ መሠረቶች (መጽሐፍ ቅዱስና የዓለም ታሪክ) የተቀዳ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም!
በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፤ የረጅም ጊዜ ቁርኝት ነበራቸውና፡፡ በብሉይ ኪዳን በንግሥት ሳባ የተጀመረው ግንኙነት (1ነገ.10፡1)፤ በኋላ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በ34ዓ.ም በዘመኑ የአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር (ጃንደረባው ባኮስ) አማካይነት ክርስትናን ስትቀበል (የሐዋ.8፡26-42) የበለጠ ተጠናከረ፡፡ ይህ ክስተት ከተለመደው የግሪኮ-ሮማን ዘመን የክርስትና ታሪክ (ክርስትና በተራ ሕዝቦች ተጀምራ ወደ ነገሥታቱ የምታመራበት ሁኔታ) ጋር ተቃራኒ ነበር፤ በተገላቢጦሹ በኢትዮጵያ ክርስትናን ለሕዝቡ የሰበከው የቤተ መንግሥቱ ጃንደረባ ነውና፡፡
በተለይ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ከሆነበት ከ4ኛው መ/ዓ (አብርሃ ወአጽብሐ ዘ/መ) ጀምሮ እስከ 17ኛው ምዕተ ዓመት ፍጻሜ (ዘመነ መሳፍንት)፣ ከዚያም ከዐጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ መከራውንም ደስታውንም አብረው ሲቋደሱ ለዘመናት ዘልቀዋል፡፡ አንዱ በሌላው ውስጥ ጣልቃ ከመግባትም ባለፈ አንዱ ለአንዱ ‹‹የመሾም›› ሚናም ነበራቸው፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ የነገሥታት (ቤተ መንግሥት) እና የክርስትና (ቤተ ክህነት) ትስስር ምንኛ ከሥር መሠረቱ እንደነበር የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ቤተ ክህነት ነገሥታቱን ቀብታ በማንገሥ (በየመሃሉ ከነበሩ የንግሥና ሽግግር ችግሮች በስተቀር)፣ ሕዝቡም ለእነርሱ እንዲገዛ ባላት ተሰሚነት በማሳመን፣ ለሕዝቡ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ ግንባር ቀደም ሚናን ተጫውታለች፡፡ ነገሥታቱም አንድም ሃይማኖተኞች ስለነበሩ፣ በሌላም መልኩ ደግሞ ለፖለቲካዊ አስተዳደራቸው እጅግ ስለምታስፈልጋቸው (የመንግሥታቸው ሕልውና የሚለካው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት መጠን ስለነበር) ቤተ ክርስቲያኒቱን የሙጥኝ ብለዋት አልፈዋል፤ በአንድ መልኩ ሲደግፏትና እየጠቀሟት፣ በሌላ ጊዜም ሲገፏትና ሲጠቀሙባት፡፡
በተለይ አንድ በሚያደርጓቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ አብረው ሲመክሩ፣ ወራሪ ጠላትን በጋራ ሲከላከሉ፣ የሕዝቡን ነጻነትና አንድነት ሲጠብቁ ኑረዋል፡፡ ልዩነቱ፡- ቤተ ክህነት ለነገሥታቱ ታደርጋቸው የነበረችው ተግባራት ሁሉ ‹‹የሚጠበቅባት፣ ግዴታዋ›› ሲሆን (ለምሳሌ፡- ‹‹አልቀባም›› የማለት አቅሙ ነበራት ለማለት ስለማያስደፍር) ነገሥታቱ ለቤተ ክርስቲያን የሚያደርጉት ግን በመልካም ፈቃደኝነታቸው ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህ የተጽዕኖ ፈጣሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ቦታቸውን በግልጽ ያሳያል፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ‹‹እግዚአብሔር አባታችን፣ ቤተ ክርስቲያን እናታችን፣ ኢትዮጵያ ሀገራችን›› እያለ ባለመነጣጠል ሲጠራ፤ ‹‹ንጉሡን ከክብሩ፣ ካህኑን ከደብሩ፣ ታቦቱን ከመንበሩ አይለይብን›› እያለ ሲጸልይ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
2.    ትስስሩ ‹‹ስህተት›› ነበርን?
ስለ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ግንኙነት ስናነሳ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ሲኖርባቸው የተጣመሩበት ክስተት ስህተት ነበር ወይ?›› የሚለውን መጠየቅና መመለስ የግድ ይላል፡፡
አስቀድሞም እንደተገለጸው በአገራችን ውስጥ በተለይም እስከ አጼ ኃ/ሥላሴ በነበረው የአስተዳደር ዘይቤ መንግሥትና ሃይማኖት ብዙም የተለያዩ አልነበሩም፡፡ አንዱ በሌላው ውስጥ ጣልቃ ከመግባትም ባለፈ አንዱ ለአንዱ ‹‹የመሾም›› ሚናም ነበራቸው፡፡ ይህ ክስተት ‹‹እውነትም የሆነ ነገር ነበር›› ብሎ ማመንና ‹‹የሆነው ግን ስህተት ነበር›› ብሎ መቀበል ግን ልዩነት አላቸው፡፡
ይህ ትስስር ‹‹ስህተት ነበር›› ብለው በግንባር ቀደምትነት የሚተቹት ጽንፈኛ የኦሮሞ ልኂቃን ናቸው፡፡ በመሠረቱ ግን ይህ የሃይማኖትና መንግሥታዊ አስተዳደር ትስስር እነርሱ ጠንቅቀን እናውቀዋለን በሚሉት ማኅበረሰብ የገዳ ሥርዐት ውስጥም ቢሆን የተለመደ ነው፡፡ ‹‹ምንም እንኳ… ሃይማኖት ከፖለቲካ ግልጽ ባለ መልኩ የተነጣጠለ ቢሆንም የቃሉ ተቋም በፖለቲካም ረገድ ትልቅ ተሰሚነት አለው፡፡…‹ቃሉ› በመንፈሳዊውም ሆነ በፖለቲካው መስክ መንታ ተግባሮችን ያከናውናል›› እንዲል (በኃሮ ቢያንሳ፤ ኦሮምያ፤ 1985፡31)፡፡ እንዲያውም በገዳው ሥርዓት ማንኛውም ሰው አባ ገዳ ለመሆን ዋነኛ ቅድመ ሁኔታው የዋቄፋና እምነት ተከታይ መሆን ሲሆን ከዚያም አልፎ በሉባነት (ካህንነት) ለማገልገል ደግሞ በሃይማኖት መሪው ቃሉ (አባ ሙዳ) መቀባት፣ ከእርሱም ቡራኬና ምርቃት ማግኘት የግድ ነው (ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006:246)፡፡ ከሀገራችንም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በንጉሣዊ ሥርዓት በሚተዳደሩት ሀገራት ሁሉ ተመሳሳይ ክዋኔዎች አሉ፡፡ ስለዚህም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ሙሉ በሙሉ መነጠል የሚቻል አይመስልም፤ ‹‹ስህተት›› ብለን የምንይዘውም ‹‹መነካካታቸውን›› ሣይሆን ‹‹መጨቀያየታቸውን›› ቢሆን የተሻለ ይመስላል፡፡
በመሠረቱ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› የሚለው መርሕ በሕገ መንግሥታችንም ደረጃ አንቀጽ-11 ላይ በግልጽ የተቀመጠ እውነታ ነው፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ ግን የዚህ መርሕ ‹‹ትክክለኛ አፈጻጸሙ›› ጥያቄ ሲያስነሣ ይኖራል፤ ሁለቱም ‹‹አንድ ሕዝብ›› ላይ እስከሚሠሩ ድረስ በዓላማቸው ደረጃ እንጂ በአሠራራቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‹‹መነካካታቸው›› አይቀሬ ነውና፡፡ ደግሞም በሀገሪቱ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ውስጥ የማይተካ ሚና የነበራትን (ምናልባትም ዋና ቀራጺ የነበረችውን) ቤተ ክርስቲያን ወደ ጎን ትቶ ኢትዮጵያን መምራት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ማንም (ሕግ አውጪዎቹን ጨምሮ) የሚገነዘበው ነው፡፡
3.    ‹‹የኋላቀርነታችን ምልክት፣ የድህነታችን ምክንያት›› ያሰኛል?
የኦርቶዶክስን ‹‹የመንግሥት ሃይማኖት›› መሆን እንደ ታሪካዊ ስህተት፣ የድህነታችን መንሥኤ እና ኋላቀርነት የሚያዩ ሰዎች አሉ፤ ይህ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ለምን ቢባል እስከ ዛሬም ድረስ ‹‹ብሔራዊ ሃይማኖት›› ያለባቸው አገሮች መኖራቸው አንዱ እውነታ ሲሆን እነዚህ ሁሉ ደግሞ በእድገትም ሆነ በሥልጣኔም ደረጃ ከእኛ ለመሻላቸው ዓለምአቀፋዊ ምስክርነቶች አሉና፡፡
በዋናነት ካቶሊክ ብሔራዊ (የመንግሥት) ሃይማኖት የሆነባቸውን የአውሮፓ አገሮችን መጥቀስ እንችላለን፡- ዛሬ የዓለም ሥልጣኔ ቁንጮ የሚባሉት፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ያላቸው፣ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የበለጠ ዲሞክራሲያው ነጻነት ያላቸው /ይልቁንም የስካንደነቪያን ሀገራት ፓሊስ እንኳን የሌላቸው እንዳሉ መረሳት የለበትም/ ሰንደቅ ዓላማቸው ጭምር የመስቀል ምልክት ያላቸው ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በኢስላማዊ መንግሥት የሚተዳደሩ የመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ አንዳንድ ሀገራት ‹‹Islamic State›› ብለው በይፋ ከማወጃቸውም በላይ በባንዲራዎቻቸው ላይ የግማሽ ጨረቃ ምልክት ያለባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በሥልጣኔም፣ በምጣኔ ሀብትም ከሌሎች የተሻሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
4.    ‹‹ሃይማኖትና ፖለቲካ ተቀላቀሉ›› ይባል ይሆን? 
አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ሆነ ማለት ከዓለማዊ ሥራዎች ለመለየትና ለነፍሱ ለማደር መወሰኑን ያመላክት እንደሁ እንጂ ሙሉ በሙሉ (በአካልም ጭምር) ከምንኖርባት ዓለም መለየት ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይልቁንም የሃይማኖት ተግባራትን ጭምር ለማካሄድ የሚቻለው ሀገር ስትኖር፣ ሰላሟም ሲረጋገጥ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፡- ‹‹ለማበድ እንኳን ሀገር ያስፈልጋል›› ሲሉ እንደተናገሩት፡፡
እናም የሃይማኖት ሰዎች ሀገራቸውን ከልብ መውደድ፣ ስለ ሰላሟም ጠንክረው መጸለይ ግዴታ አለባቸው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ስላሉ ‹‹ሁሉም›› ብለን ለመጠቅለል ባንደፍርም በአንዳንድ ኢ-ኦርቶዶክሳውያን ቤተ እምነቶች ለሀገራዊ ስሜት በቂ ትኩረት ሲሰጥ አይታይም፡፡ ምናልባትም በአንድ በኩል ስለ ሀገር ማሰብና መቆርቆር ማለት ‹‹ፖለቲከኝነት›› አድርገው ስለሚቆጥሩ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ አንዳንድ መምህራን ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ (ፊልጵ.3፡20) ያለ ቦታው ጠቅሰው ስላደናገሯቸው እንደሆነ ይታሰባል፡፡
ክርስትናም ሆነ እስልምና መነሻቸውን መካከለኛው ምሥራቅን ቢያደርጉም ለዘመናት የኖሩት ግን ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ሆነው እንጂ ‹‹እስራኤላዊ›› አልያም ‹‹አረባዊ›› ሆነው አይደለም፡፡ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክርስትናን በመቀበል ከግብጽ ብትቀድምም የሐዲስ ኪዳን ክህነቷን ያመጣችው ግን ከመንበረ ማርቆስ ነው፡፡ በሌላ መልኩ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የግብጽ ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በግብጻውያን ቢደሰቱ ሊገርመን አይገባም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ኦርቶዶክሳውያንም ሆኑ ሙስሊሞች ግን በዓባይ ግድብ ጉዳይ (ለምሳሌ ያህል) የኢትዮጵያን አቋም ያራምዳሉ እንጂ ‹‹ግብጻዊ መሥመር ላይ›› ሊቆሙ አይችሉም፤ እምነትና የሀገር ጉዳይ በየዘርፋቸው መስተናገድ አለባቸውና፡፡
የፕሮቴስታንቱ እንቅስቃሴም ቢሆን መነሻው አውሮፓዊ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያውያን ወግና ባህል ተቃኝቶ መጓዙ የታወቀ ነው፡፡ መነሻው ከአውሮፓ ስለሆነና ምናልባት ዛሬም ድረስ በምዕራባውያን የሚደገፉ እንቅስቃሴዎችም ቢኖሩት ‹‹ውለታ ለመመለስ ሲባል›› ሀገርን በሌላ የሚተካ፣ ጠላቶቿ በሀገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለሚያራምዷቸው የሤራ ፖለቲካዎችም በማሳለጫ መሣርያነት የሚያገለግል አካሄድ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ሲጠቃለል በሀገራዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር መተባበር በየትኛውም አኳኋን ‹‹ፖለቲከኛ›› ሊያሰኝ አይገባም፤ ለሃይማኖቱም ምድራዊ ሕልውና የሀገር ሰላምና ልማት ያስፈልጋልና፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም በታሪክ አጋጣሚ ከሀገር መሪዎች ጋር መሥራቷ፣ ሀገራዊ ስሜትን መያዟ፣ ከሀገር ጋር ተያይዘው የመጡትን መልካም ጸጋዎችንም ሆነ መጥፎ ክስተቶችን መጋራቷ ሊያስነቅፋት የሚገባ አይሆንም፡፡
5.    ዛሬስ ለምን አይፋቱም?
ብዙዎች ዛሬ ላይ የሚስተዋለውን የቤተ ክህነት እና የቤተመንግሥት ንክኪ እንደ ተዓምራዊ ሁኔታ ይመለከቱታል፤ የሰሞነኛዋን ‹‹ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው›› ዐዋጅ ብቻ መነሻ በማድረግ ይመስላል፡፡ ጉዳዩ ግን እንዲህ ቀላልና የሰሞንኛ ክስተት ብቻ አልነበረም፤ ‹‹ጋብቻ›› እስከመባል የደረሰ አብሮነት እንጂ፡፡ ስለዚህም ‹‹ለምን ጨርሰው አይፋቱም?›› ብሎ ሊጠይቅ የሚወድ ቢኖር ሙሉ መልስ ሊያገኝ የሚችለው ከፍቺው በመጀመር ሳይሆን በመጀመርያ እንዴት እንደተጋቡና በትዳራቸው ዘመናት ምን ዓይነት መልካምና ፈታኝ ገጽታዎችን አብረው እንዳሳለፉ ሲያጤን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኋላ ታሪክን ጠንቅቆ ማጥናት ይጠይቃል፡፡
ሃይማኖትን ብቻ ሣይሆን ሀገርን ከነዳር ድንበሯ፣ ሙሉ ነጻነቷና ክብሯ ጠብቃ ለትውልድ ያስተላለፈችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከየትኛውም ቤተ እምነት በተሻለ ለሀገሪቱ መስዋዕትነትን ከፍላለች፤ የጳጳሳቷንና መነኮሳቷን ሕይወት እስከመሠዋት ድረስ፡፡ እናም በጸሎቷም ሆነ በአገልግሎቷ ተልእኮዎች ሁሉ የሀገርን ሰላምና የዜጎችን አንድነት ማእከል አድርጋ መንቀሳቀሷ እሙን ነው፤ ‹‹መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናል›› እንዲል መጽሐፉ (ማቴ.6፡21፤ ሉቃ.12፡34)፡፡ እናም የዜጎቿን ፓለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቡናዊ ማሕቀፎችን በመቅረጽ ረገድ ደማቅ አሻራ ካሳረፈች ቤተ ክርስቲያን ተፋትቶ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን መምራት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡
‹‹ባለትዳሮቹ›› ለበርካታ ሺህ ዓመታት (ከብሉዩ ጀምሮ እስከ ደርግ ሥርዓት ዋዜማ ድረስ) የተቆራኙበትን እትብት በአንድ ጀምበር ቆርጦ መጣል ወረቀት ላይ የመጻፍና ሚዲያ ላይ የመናገር ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ አንዱ በሌላኛው ጣልቃ አይገባም›› የሚለውን ሕግ ያረቀቁት መንግሥታት እንኳን በአፈጻጸም ደረጃ ሲታዩ ‹‹አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው›› እንደሆነባቸው እንገነዘባለን፡፡
ለምሳሌ፡- ኢህአዴግ የበረሃ ትግሉን አጠናቅቆ የሥልጣን መንበሩን እንደተቆናጠጠ የመጀመርያ ሥራው ያደረገው ‹‹ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ እንዳይሾም›› የሚደነግገውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና ጥሶ፣ ያልፈለጋቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪ (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን) አውርዶ ይሆኑኛል ያላቸው ሌላ መሪ (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ) እንዲሾሙ ግፊት ማድረጉ ነበር፡፡
እናም ሲጠቃለል፡- ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ፈጽሞ የማይቀደድ ‹‹ሰማንያ›› ተፈራርመው መጋባት ባይኖርባቸውም እንኳን ጨርሰው ሊፋቱ ግን እንደማይችሉ ከዓለም አቀፋዊም ሆነ ከሀገራዊ ታሪኮች ሂደት ተሞክሮ ቀስሞ በወጉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ሕዝቦች ታሪክ፣ ባሕል፣ ሥልጣኔና ቅርስ እንዲሁም የዕለት ተዕለት የማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብር ውስጥ ካላት/ከነበራትም ሰፊ ድርሻና አሻራ የተነሣ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መንገድ የመሳሳቡ ነገር መጠኑ ይቀንስ ይሆናል እንጂ ፈጽሞ ሊጠፋ ይችላል ለማለት ይከብዳልና፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በምንገነዘበው ሐቅም ነገሥታቱ ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን በማግለል በነጻነት ያራመዱት ፖለቲካ አለመሳካቱን/መጨረሻው አለማማሩን ነው፡፡ መንግሥት ሕዝቡን ለመያዝ ሲል የግድ ተሰሚነት ባላቸው (የሃይማኖት ተቋማት) አማካይነት ይሠራል፤ ይህ በዙፋን ለመጽናትም ለመንሸራተትም ወሳኝ መሥመር ነው ብሎ ያስባልና፡፡
እጅግ የሚገርመው ግን በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ውስጥ መንግሥት ጣልቃ የሚገባው ራሱ ፈልጎ ብቻ አለመሆኑን ስናስብ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቤተ ክህነት ራሷ ለአዎንታዊም ይሁን ለአሉታዊ የመንግሥት ጣልቃ ገብነቶች በሯ ክፍት ነው፤ አዎንታዊው ተቋማዊ አቋም ሲሆን አሉታዊው ግን ብዙውን ጊዜ የግለሰቦች ፍላጎትና ግፊት ያለበት ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ዱላው የሚያርፈው ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ መሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ጣልቃገብነቱ ብዙውን ጊዜ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ‹‹ጋባዥነት›› የሚፈጸም ነው፤ በተለይ አንድ የማይፈለግን ግለሰብ/ማኅበር ለማስመታት ሲባል በፖለቲካ መክሰስ፡፡ በመጽሐፉም፡- ‹‹ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር›› እንደተባለው (ሉቃስ 23፥2)። በአገራችን ታሪክም ነገር ሰሪዎች በየዘመኑ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን ከነገሥታቱ ጋር በማጋጨት ያስቀጡበት/በእስር እንዲማቅቁ ያደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል፡- ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲጋዝ፣ የደብረ ሊባኖሱ እጬጌ ጻድቁ አባ ፊሊጶስ በአደባባይ ራቁቱን እንዲገረፍ የተደረገው በመሰል ሤራዎች ነበር፡፡
በቅብዐ ነገሥት መንግሥትን ለሀገር ትሾም የነበረች ቤተ ክርስቲያን በግልባጩ መንግሥት ለእርሷ ‹‹ካህናትን›› የሚሾምበት ሁኔታም አስተናግደናል፤ ይህ የሆነው ደግሞ በራሷ ክፍተትና ጋባዥነትም ጭምር ነበር፡፡ ይግባኝ አልባው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና ሉዐላዊ ሥልጣኑ በግለሰቦች የተንሻፈፈ አረዳድና ስውር ዓላማ ምክንያት ከሕገ መንግሥት ጋር እንዲላተም የተደረገባቸው ሙከራዎችም ነበሩ፡፡ የፍትሐ ብሔር ምንጭና ሰማያዊት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿ ለማንነቷ በማይመጥን ምድራዊ ሕግ ሲከሷትና ሲካሰሱ ማየትም የተለመደ ሆኗል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ድረስ የራሷን ልጆች፣ ያደራጀቻቸውን ማኅበራት፣ ያሰማራቻቸውን አገልጋዮችና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎቿን በብቃት የምትከታተልበት አሠራርና ሥርዓት ባለመኖሩ (ካለም በአግባቡ ባለመተግበሩ) ‹‹በግልባጭ ደብዳቤዎች›› መንግሥትን ስትማጸን ትኖራለች፡፡ መንግሥትም ‹‹ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ›› በሚል አካሄድ በተፈቀደለት መሥመር ገብቶ ፖለቲካዊ ዒላማውን ሲያሳካ፣ ሃይማኖታዊ እሴቶችንም ሲዳፈር ተስተውሏል፡፡ በዚህ መልኩ ‹‹ሁለቱም ተጋቢዎች›› ከተፈላለጉ ደግሞ ጋብቻው ጸንቶ ለመኖሩ አጠያያቂ አይሆንም፤ በትዳር ወግ እየተፋቀሩም፣ እየተናቆሩም መኖር ግድ ይላቸዋልና!
Filed in: Amharic