>
5:28 pm - Sunday October 10, 1582

አለማየሁ-እሸቴ  ከዘመኑ የቀደመው አቀንቃኝ  (ተመስገን ባዲሶ)

አለማየሁ-እሸቴ  ከዘመኑ የቀደመው አቀንቃኝ 

ተመስገን ባዲሶ

 

 * የመልካም ትዳር ተምሳሌት ….
ድንቅ ከያኒ አስገራሚ የህይወት ውጣውረዶችን በጽናት ታግሎ ያለፈ አንጋፋ አርቲስታችን…
………ከወራት በፊት የድምፃዊ አለማየሁ-እሸቴን የሕይወት እና የሙያ እውነታዎች ለመፃፍ ፈልጌ አንዲቷን የገጠመኝ ክፍል ብቻ ነካክቼ ነበር የተውኩት። አንዳንድ ስልቹ አንባቢያን የፅሁፌን መርዘም…. ፈልጌ እና ጊዜ ተርፎኝ የቸከቸኩት እየመሰላቸው እንደ-ቅሬታም፤ እንደ-ወዳጃዊ አስተያየትም በማድረግ <•አሳጥረው!•> ይሉኛል። በእርግጥ የሰውን ሁሉ ፍላጎት ብሞላ ደስታዬ ወደር የለውም። ግን አንዳንድ ታሪኮች አሳጥሬ ልፃፋቸው ቢባልም በጄ የሚሉ አይደሉም። በተለይ ባዮግራፊ ሲሆን፤  ግለሰቡ የኖረውን እና ያለፈበትን የህይወት ውጣ-ውረድ… ምኑን-ከምኑ ቆራርጦ ማሳጠር እንደሚቻል ጭንቅ ይላል። ምክንያቱም እንደ-አለማየሁ እሸቴ እና በቀደመው ዘመን የኖሩ ስመ-ጥር አርቲስቶችን ታሪክ በውስን ቦታ ከመገደብ ይልቅ የአባይ-ወንዝን መገደብ ይቀላል። እያንዳንዱ ያለፉበት… የሙያም ሆነ የግል ህይወታቸው ተቆርጦ የሚጣል ሽንፍላ የለውም። ችሎ ላነበባቸው…. ሁሉም መሳጭ፤ አስገራሚ፤ አስተማሪ እና ለሀገር የሚተርፍ ታሪኮችን በውስጣቸው ስላዘሉ የቱን ቆርጦ መጣል ይቻላል? ስለዚህ የአንዳንድ ፅሁፎቼ እርዝማኔን ለምን እንደረዘሙ በርዝመት ተረዱኝ። oky ma friend’s…!?  ደሞ አሁን ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ? ረጋ ብሎ መኮምኮም ነው። አለም ሁሉ እስር ቤት እኛም ታማኝ እስረኞች ሆነን አይደል? እኛስ ርቀት ጠብቀን ወጣ ብለን ጉሊት ደርሰን መምጣት እንችላለን። አማሪካ፤ አውሮፓ እና ሚድልኢስት ግን መውጣት ኢንጂሩ። ስለዚህ ማንበብ ነው። 24 ሰአት በምን ይገፋል? በተሜዋ ጽሁፍ ነዋ።
•…… አለማየሁ እሸቴ ብዙ ታሪክ ያለው ድንቅ ከያኒ እና አስገራሚ የህይወት እውነታዎችን አልፎ የመጣ አንጋፋ አርቲስታችን ነው። እንኳን ህይወቱ ይቅርና እጅግ የሚያመራምሩት የዘፈኑ ግጥሞችን ተንትነን እንፍታቸው ብንል ጊዜ አይበቃንም። በዚያ ላይ እነ-አሌክስ የኖሩበት ዘመኑ በራሱ….. የታሪክ-ምህዳሩ ሰፊ እና የብዙ ሰዎችን ህይወት አዋቅሮ የገነባ በመሆኑ የግለሰብ ሳይሆን የማህበረሰብ ታሪክ ነው ማለት ይቻላል።
አሌክስ በእናት እና አባት የጋራ እቅፍ ውስጥ ያደገ ልጅ አይደለም። ከተወለደ በኋላ በእናት እና አባቱ መሃል ስምምነት ስላልነበረ ወላጆቹ ምርጫቸው ያደረጉት መለያየትን ነበር። ለአባቱ ብቸኛ ልጅ የሆነው አሌክስን ለማሳደግ እና  ከእናትየው ጉያ ለመንጠቅ ወላጅ አባቱ እስከማስፈራራት የደረሰ እና ኃይልን የተጠቀመ እርምጃ በመውሰድ በመጨረሻ በእጃቸው ያስገቡት ሲሆን፤ በወቅቱ የሁለት አመት ጨቅላ ስለነበር በወላጆቹ መሃል የተፈጠረውን ቅራኔ አያውቅም ነበር። እናም በእንጀራ እናት እጅ ለማደግ ተገደደ። አሌክስ በሙዚቃው የእንጀራ እናትን በደል እና ብሶት ያዘሉ ዘፈኖችን በማቀንቀኑም ከእውነተኛ ህይወቱ ጋር አያይዘው ፍቺ ለመስጠት የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩም፤ አሌክስ ግን አጋጣሚ እንጂ…. <•በፍፁም የእንጀራ-እናቴን ለመንካት ሆን ብዬ ያዜምኩት ዘፈን አይደለም•> ይላል። ስለ-እንጀራ እናት የዘፈነው ግጥም በጊዜው የነበረውን የማህበረሰብ ስሜት ያንፀባርቃል በሚል ግጥም እና ዜማውን የደረሱት ኮ/ል ግርማ-ኃይሌ ሲሆኑ፤ ከነበሩት የጊዜው ድምፃዊያን መሃል አሌክስ እንዲዘፍነው ሲደረግ በአጋጣሚ ከራሱ ህይወት ጋር ልክክ አለ። የሚገርመው የእንጀራ እናቱ <•ዘፈኑን የዘፈንከው ለእኔ ነው!•> ብለው በህይወት እስከነበሩበት 1990ዎቹ ድረስ ለአንድም ቀን አናግረውት አያውቁም ነበር።
…….የአሌክስ የልጅነት ህይወት ያለፈው አባኮራን ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሲሆን፤ ይሄ አካባቢ በርካታ የወሎ ተወላጆች የሰፈሩበት መንደር ነው። ሰፈሩ ታላቁ አንዋር መስኪድ ወይም ወደ ሀብተጊዮርጊስ መሄጃ በስተግራ መገንጠያ ላይ ይገኛል። በ1949 አመተ-ምህረት ትምህርቱን ይከታተል የነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን፤ በጊዜው ት/ቤቱ ይገኝ የነበረው በቅሎ ቤት አካባቢ አሁን ኮንኮርድ ሆቴል ከሚገኝበት በስተጀርባ ነበር። ትምህርት ቤቱ ክርስቲያን ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት /CTI/ ይባል የነበረ ሲሆን፤ የተማሪዎቹ ውሎና-አዳራቸው እዚያው ሆኖ በወር አንድ ጊዜ እረፍት ይሰጣቸው ነበር። ታዲያ በአንደኛው የእረፍት ቀን አሌክስ  አባኮራን ወደሚገኘው ቤታቸው ይመጣል። ቤት ውስጥ ብዙ ሰው ተሰብስቧል። አሌክስ እንደገባ አባቱን፤ የእንጀራ እናቱን፤ ሠራተኛቸውን በየተራ ከሳማቸው በኋላ፤ በቤቱ የነበሩትን አንዲት እንግዳ ሴትዮ በመሀል ዘሏቸው ወንበር ላይ ተቀመጠ። አባትየው ወደ አሌክስ እያዩ…..<•ምነው እሷን ተውካት…ሳማት እንጂ!!•> አሉት። አሌክስ በአባቱ ትህዛዝ መሰረት እንግዳዋን ሴት ሳማቸው። አባት አስከትለውም…..<•ታውቃታለህ!?•> ብለው ጠየቁት። አሌክስ እየተቅለሰለሰ እና ግራ በመጋባት ስሜት ተውጦ…..<•እረ እኔ አላውቃቸውም!•> ሲል…..እንግዳዋ ሴትዮ በቅፅበት ተነስተው ቢላዋ በማንሳት አባትየውን ለመውጋት ተንደረደሩ። በንዴት እና በብስጭት ቢላዋ ያነሱት ሴትዮዋ በገላጋይ እና በስንት-እግዚኦታ ካበረዷቸው በኋላ….. ሳግ እየተናነቃቸው ብድግ በማለትም አሌክስን እቅፍ አድርገው……<•ለካስ ከልጄ ጋር አቆራርጠኽኝ ነው የኖርከው!•> በማለት ምርር ብለው አለቀሱ። ያኔ ዕድሜው 13 አመት የሞላው አሌክስ ነፍስ ካወቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ትክክለኛ እናቱን በአካል ያያቸው። ያንን ቀን ዛሬም ድረስ ሲያስታውሰው እንባ አይኖቹን ይሞላዋል። በእናቱ እጅ የማደግ ዕድሉን ያላገኘው አሌክስ ከእናቱ ከወረሰው ነገር ዋንኛው ሉጫ-ፀጉሩን ሲሆን፤ ይሄው ፀጉሩ በኋላ ለገባበት የሙዚቃ ህይወቱ እና ኤልቪስ-ፕሪስሊን መስሎ ለቀረበበት ስታይሉ ትልቅ እገዛ አድርጎለታል። ያላሳደጉት እናቱን ጸጉር የወረሰው እና ገና በታዳጊነት ዕድሜው በሙዚቃ ፍቅር የተለከፈው አሌክስ….. በባህር ማዶ ሙዚቃዎች ጨርቁን የጣለ እብድ ስለነበር የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን ሲያቀነቅን ተስተካካይ አልነበረውም። በወቅቱ ስመ-ገናና ከነበሩት የምዕራቡ አለም አቀንቃኞች መሃል ለኤልቪስ-ፕሪስሊ ሁሉ ነገሩን የሰጠ ነበር። አሌክስ መሆኑን እና የተፈጠረበትን የማንነት ህልውናውን እስኪያጣ ድረስ ኤልቪስ በአሌክስ ማንነት ውስጥ የተወሰኑ አመታት በቅሎ ኖሯል። ሁሉ ነገሩን ለማስመሰል ከጠዋት እስከ ማታ ኤልቪስን መስሎ ከቤት እስከ ከተማ ሲዳክር ውሎ፤ ሲለፋ ያነጋል። ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ አፍቃሪ የሆነው አሌክስ አሜሪካዊው የሮል ኤንድ ሮል አቀንቃኝ በነበረው በኤልቪስ ፕሪስሊ ሁለንተናዊ ነገሩ ተለክፎዋልና…. በወቅቱ በድፍን አለሙ ገናና ስም የነበረው  እና ወርቃማ-ጊዜው የእሱ ነው በሚባልበት ጊዜ አሌክስም የሙዚቃው አድማጭ እና አድናቂ ብቻ ሳይሆን፤ ኤልቪስን ለመምሰል የማያደርገው ነገር አልነበረም….እናም ኤልቪስን ሲያይ…. የአዘፋፈን ስልቱ፤ የዳንስ እንቅስቃሴው፤ የአለባበስ ስታይሉ፤ መድረክ ላይ ድንገት የሚያሳየው የአይን አክሽኑ፤ እንደ-ሙሴ በትር ፀጉሩን ለሁለት የሚከፍልበት አበጣጠሩ እና ጎርነን ያለ ንግግሩ ሳይቀር አሌክስን ማርኮ ጥሎታል። በሕልሙም ሆነ በውኑ ኤልቪስ ከአዕምሮው ሳይመጣ የዋለበት እና ያደረበት ቀን የለም። ሲበላም፤ሲጠጣም፤ ሲጫወትም ትዝ የሚለው እሱ ነው። በዚያ ላይ አፍላ ጉርምስናውም አለ…እናም እሱን የመምሰል፣ እሱን የመሆን አባዜ በጥልቀት ተጠናወተው። አሌክስ ኤልቪስን ከስታይሉ ውጪ በብዙ ነገሩ ያደንቀው ነበር፤ ሲዘፍን ከሌላ ፕላኔት የመጣ ልዩ ፍጥረት ይመስለዋል። መድረክ ላይ ወጥቶ ሲያቀነቅን እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሉን ከሪትሙ እና ከሙዚቃው ጋር ሲያዋህደው፤ የሚያደርገው ጥበባዊ ንቅንቄ ሁሉ የአሌክስን ሰውነት ንዝር ያደርገዋል፤…< ንግግሩ ጭምር ሙዚቃ ነው!> የሚለው አሌክስ ልክ-የእሱን ድምፅ አስመስሎ ጭምር ይናገር ነበር። አሌክስን ወደ ሙዚቃው አለም ሙሉ በሙሉ የጎተተው ከሀገራችን ቀደምት ዘፋኞች በላይ ከውቅያኖስ ማዶ ያለው ኤልቪስ ፕሪስሊ ነበር ማለት ይቻላል።
•……።አሌክስ አንድ ወቅት ላይ ለኤልቪስ የአድናቆት ደብዳቤ ጭምር ሊልክለት ጀምሮ ትቶታል። መፃፉን ለምን እንደተወ አሌክስ ምክንያቱን በአንድ ወቅት ሲናገር…..<እኔ ወደ ሙዚቃው እና ወደ እውቅናው ብቅ ባልኩበት ሰአት ኤልቪስ ከሙዚቃው አለም እያፈገፈገ የመጣበት፤ ሰውነቱ ያለ-ቅጥ የወፈረበት እና ድራግ ውስጥ ጭምር የተዘፈቀበት ስለነበር በዚህ የመደበቂያ ዋሻ ውስጥ ሆኖ እንዴት የእኔን ደብዳቤ አንብቦ፤ በቁምነገር የአፀፋ መልስ ሊሰጠኝ ይችላል? የሚለውን ሳስብ ደብዳቤው መንገድ ከሚቀር ብዬ ጅምሩን ራሴ ጋር አስቀረውት!> ይላል። ግን ዛሬም ድረስ ኤልቪስን ለውጦ በአሌክስ ልብ ቀዳሚ ስፍራ ያገኘ ዘፋኝ የለም። ዛሬም ዘፈኖቹ የጆሮው ቀለቦቹ ሆነው የዘለቁ ሲሆን፤ በዚህ ዕድሜው እንኳን መድረክ ላይ ሲያቀነቅን የኤልቪስ አሻራዎች ይታዩበታል። አሌክስ ገና በአፍላ ዕድሜው በፍላፃው ወግቶ የጣለው ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ሲኒማው ጭምር ነበር።
•……አሌክስ ለኪነ-ጥበብ በነበረው ፍቅር የተነሳ የምዕራባዊያን ፊልሞች አፍቃሪ እና ሱሰኛም በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ገናና ስም ከነበራቸው ውስጥ ልክ በሙዚቃው ኤልቪስን እንደሚያደንቀው….በሲኒማውም <እነ-ጆን ዌይ፤ በርት ላንክስተር፤ ኪርክ ዳግላስ፤ እና ጃክ ፖላንስ> የመሳሰሉት የዘመኑ አክተሮች የትወና ችሎታ ይመስጠው ነበር። አብዛኛውን ትምህርቱን እየፎረፈ ውሎው ሲኒማ ቤት ነበር። እናም ፊልሙ እና የአክተሮቹ ትወና በፈጠረበት መደመም የተነሳ እኔስ እንደእነሱ ለመሆን ምን ይሳነኛል?….የሚለው ሃሳብ በውስጡ ተቀረፀ። ይሄን ለማድረግ ደግሞ በቁም ከመቃዠት እና በምናብ ከማለም ውጪ በተግባር መንቀሳቀስ እንዳለበት ራሱን አሳመነ። ዓሳውን ለማጥመድ ግዴታ ወደ ዓሳው መገኛ ሓይቅ መውረድ አለበት። ፊልሙን ለመስራት ደግሞ የትወና ሜዳው ከሚገኝበት ሆሊውድ ማምራት አለበት። ታዲያ ጉዞው ከየት መጀመር አለበት? የመውጪያው መንገዱስ በየት በኩል ነው? መቼም መላእክቶች አንሳፈው በክንፋቸው ሆሊውድ ደጃፍ አይጥሉት!…..ስለዚህ ህልም የሚሞላው አንድ እርምጃ ወደሚፈልጉት ግብ በመንቀሳቀስ ነውና አሌክስ ቀጥታ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ የባህር በር ከሆነችው ምፅዋ ለማምራት ቆራጥ ውሳኔ ላይ ደረሰ። ስደት ለብቻ መውጣት ከባድ ነው፤ ለክፉም ለደጉም ሁለት ሆኖ መሰደዱ መልካም መሆኑን ያመነው አሌክስ በወቅቱ ከነበሩት ጓደኞቹ ብርቱ መንፈስ ያለውን መኮንን የተባለውን ጓደኛው አጭቶ እና አሳምኖ ምፅዋ ገቡ።
    •   አሌክስ እና መኮንን ምፅዋ እንደገቡ በግራ መጋባት ስሜት፤ የአካባቢውን ጂኦግራፊያዊ ሁኔታ በማጥናት እና የባህር ዳርቻውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመቃኘት ከሶስት ቀን በላይ ምፅዋ ላይ ውለው፤ አነጉ።…..ከሶስት ቀን በኋላ ከባህር ዳርቻ የቆመች መርከብ ላይ እነ-አሌክስ የአይናቸውን መልዕቅ ጣሉባት። መርከቧ ለጉዞ ጣጣዋን የጨረሰች አይነት ናት። ስሟ…<ሳሂካ> ሲሆን፤ ንብረትነቷ የግብጾች ነው። የጫነችው ቆዳ ሲሆን፤ የጉዞ ኮምፓሷ የተቃኘው ወደ ሎስ-አንጀለስ ከተማ ነው። ይሄ እነ-አሌክስ ምፅዋ በገቡበት ጊዜ የተፈጠረ አጋጣሚ እንጂ ከአዲስ-አበባ ሲነሱ <ሳሂካ> ትኖራለች ብለው ፕላን አድርገው አይደለም። ግን በባህሩ ላይ እግር የጣላት ብቸኛ መርከብ በወቅቱ እርሷ ብቻ ናት። ሌሎች መርከቦች እስኪመጡ መጠበቅ ምፅዋ ውስጥ ተቸግረው መሰንበታቸው ነው። ስለዚህ እዚህች መርከብ ላይ አንድ ነገር መሞከር አለብን ብለው የወሰኑት አሌክስ እና መኮንን የልባቸውን በልባቸው ይዘው ያን ቀን ምሽት ወደ ናይት ክለብ አመሩ። በወቅቱ ምፅዋ ውስጥ <ቶሪኖ> የተባለው ይሄ ክለብ ታዋቂ እና መርከበኞች የሚዝናኑበት ነው። እነ-አሌክስ ከመጠጡ የሉበትም፤ ገና ልጆች በመሆናቸው ወደ ቶሪኖ ያመሩት ሙዚቃና-ዳንሱን ብቻ ፈልገው ነው። የሙዚቃ ፍቅር ውስጡን የሚያተራምሰው አሌክስ ሙዚቃ ሲሰማ እንዴት ያስችለው? ወጣና ዳንሱን ሸከሸከው። እየደነሰ ከሙዚቃው በላይ እየጮህ ዘፈኑንም በድምፁ እኩል ያስነካው ጀመር። ኤልቪስ በወቅቱ የትም ቦታ የሚከፈት የዘመኑ ቁጥር አንድ ተመራጭ አቀንቃኝ ስለነበር ምፅዋም አየሯ በእሱ ሙዚቃ የተጥለቀለቀ ነበር። በወቅቱ አሌክስ ፀጉሩ ረዥም እና ሉጫ ስለነበር… ልክ እንደ-ኤልቪስ ፀጉር ለሁለት ከፍሎ በማስተኛት ስታይሉ ተመልካችን ይስብ ነበር።  በቶሪኖ ክለብ ደጋግሞ የተከፈተው የኤልቪስ ሙዚቃ የተመቸው አሌክስ…ሙዚቃውን እኩል እየዘፈነ፤ በእንቅስቃሴ ሲያዛምደው ኤልቪስ ከየትኛው ሰማይ ወረደ ያስብል ነበር። ሳያቋርጥ ይደንስ እና ይዘፍን የነበረው የአሌክስ መሳጭ ትዕይንት ከሁሉም አይን ውስጥ የገባው በቤቱ ይዝናኑ በነበሩ የውጪ ዜጎች ሲሆን፤ እነዚህ ቶሪኖ ክለብ እግር የጣላቸው ደግሞ የ<ሳሂካ-መርከብ> ባልደረቦች ናቸው። በሙሉ ወጣቶች ሲሆኑ፤ አሌክስን በአድናቆት ጠርተው መተዋወቃቸው አልቀረም።…..ከየት እንደመጣ፤ ወዴት መሄድ እንዳሰበ፤ ወደፊት ምን መሆን እንደፈለገ እና ከአዲስ አበባ ምፅዋ ጠፍቶ የመጣበትን ምክንያት አንድም ሳይሸሽግ ለመርከበኞቹ ነገራቸው። በተኮላተፈ እንግሊዘኛውም ቢሆን የሳሂካ-መርከብ ባልደረቦች ስለተረዱት…….< በቃ ሎስአንጀለስ እኛ ይዘንህ እንሄዳለን!> አሉት። አሌክስ ግን <እኔ ሎስአንጀለስ አልፈልግም፤ መሄድ የምፈልገው ሆሊውድ ነው!> አላቸው። መርከበኞቹ በአሌክስ ንግግር አንድ ላይ ሳቃቸውን ለቀቁት። ገና ትንሽ ልጅ በመሆኑ ያለማወቁ ያን ያህል አልገረማቸውም። ይልቅ <ሆሊውድ አነስተኛ የፊልም መስሪያ መንደር እንደሆነች እና መገኛዋም ሎስአንጀለስ ከተማ ውስጥ መሆኑን!> እንዲገባው አርገው አስረዱት፤ አሌክስ በሰማው ነገር እና መርከቧ ቀጥታ የምታደርሰው ሆሊውድ መሆኑን ሲረዳ ልቡ በደስታ ትልቅ ብላ ልትወጣ ደረሰች። ፈነጠዘ….መርከበኞቹን በየተራ እያቀፈ ሳማቸው። የመጨረሻውን ደስታም የኤልቪስን ዘፈን እኩል እየዘፈነ እና እየደነሰ መርከበኞቹን በማዝናናት ተቋጨ። ወደየማደሪያቸው ሲያመሩም ስንት ሰአት ወደብ ጋር መድረስ እንዳለባቸው ለአሌክስ እና ለጓደኛው ነገሯቸው። ያ-ሌሊት እንዴት ይንጋ?
………፦ አዲስ አበባ ላይ እነ-አሌክስ የት እንደሄዱ ሚስጥር አፈትልኮ ወጥቶ ቤተሰብ ትርምስ ውስጥ ገብቷል። በመጨረሻ አስመራ ከተማ ከሚገኝ አንድ ሰው ጋር ስልክ ተደውሎ በምፅዋ በኩል አድርጎ…. አሌክስ በመርከብ ወደሌላ ሀገር ለመጥፋት ጓዙን ሸክፎ መሄዱ ሪፖርት የተደረገላቸው ሰው ከአስመራ ወደ ምፅዋ ነጭ-ለባሽ የደህንነት ተከታታዮች ልከው እነ-አሌክስ ታድነው እንዲያዙ አዘዋል። እኝህ ሰው በወቅቱ አስመራ ውስጥ ኮሚሳር የነበሩ ባለስልጣን ናቸው። ደህንነቶቹ በታዘዙት መሰረት ምፅዋ ወደብ ላይ መልዕቋን ከጣለችው <ሳሂካ> ከተሰኘችው ቆዳ-ጫኝ መርከብ በቅርብ ርቀት አድፍጠው ፀጉረ-ልውጥ አፍላዎችን ለመያዝ አይናቸውን ጥለዋል። አሌክስ እና መኮንን ብዙም አልቆዩም። መርከቧን ከርቀት ቆማ ሲያይዋት በቡረቃ እየፈነጠዙ ወደ ውሃ ዳርቻው በሩጫ ሲያመሩ ደህንነቶቹ ግማሽ መንገድ ላይ ተቀበሏቸው። ተፈላጊዎቹ እነሱ እንደሆኑ ባይጠራጠሩም ለማረጋገጥ ያህል ጥቂት ጥያቄዎችን አቀረቡላቸው። እነ-አሌክስም ምንም አይነት ጥርጣሬ ስላልነበራቸው ሳይዋሹ ከየት እንደመጡ እና ማን እንደሆኑ በግልፅ ተናገሩ። በመኪና ጭነው አስመራ በመውሰድ ኮሚሳሩ ቢሮ ሲያስገቧቸው እና አሌክስ ወንበሩ ላይ የተቀመጡትን ባለስልጣን ሲያይ እንደ-ሎጥ ሚስት የጨው አምድ መስሎ ተገተረ……< እሺ ጎረምሳው የባህር ጉዞ የከተማ ሽርሽር መሰለህ!….እንዴት ብለህ ነው በመርከብ አሜሪካ ለመግባት ህልም የሰነቅከው? በእውነት ድፍረትህን ባደንቅልህም ይሄ የማይሆን ቅዥት ነውና…..ቀጥ ብለህ አዲስ አበባ ሄደህ ትምህርትህን ተማር። ተምረህ ጥሩ ደረጃ ስትደርስ ያን ጊዜ በቦሌ የምትወጣበት መንገድ ይመቻችልሃል!….በምፅዋ ግን የአሳ ነባሪ እራት ሆነህ እንድትቀር አልፈልግም!> ብለው ሆሊውድ አላሚውን አሌክስ ወደ ሸገር ሸኙት። እኚህ ሰው አጎቱ ነበሩ።
አለማየሁ እሸቴ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ካደረሱት አንዱ ነው “ኢትዮዽያዊው ጀምስ ብራውን” ወይም
“ሃበሻው ኤልቪስ” የሚባሉ ቅፅል ስሞችም ነበሩት::
“አዲስ አበባ ቤቴ” “የወይን አረጊቱ” “የሰው ቤት የሰው ነው” “ደንዬው ደነባ” “ትማርኪያለሽ” “ወልደሽ ተኪ እናቴ” የሚባሉት ዘፈኖች ከመጀመሪያዎቹ መሃል ናቸው::
ለመጀመርያ ጊዜ በ1955 ዓ, ም በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ የተቀጠረዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በዝያን ጊዜ በብዛት የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃዎች በአማርኛ ደግሞ የጥላሁን ገሰሰን ሙዚቃዎች ያዜም እንደነበር ይናገራል፤ ግን ቀደም ሲል አዲስ አበባ GCA ትምህርት ቤት ሳለ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙሮችን ያዜም ስለነበር ለዚህ ጉዞዉ ፈር ቀዳጅ እደሆኑት ይናገራል። አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎቹን ከአዲሱ ትዉልድ ጋር አስማምቶ የመሥራቱ ሚስጥር ጠንክሮ መሥራት መሆኑን ይገልፃል።
አዲስ አበባ ተወልዶ በህጻንነቱ ቀድሞ ወሎ ክፍለ ሃገር ወደሚባለዉ አካባቢ እንደነበር የሚናገረዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ አባቱ ሙዚቀኛ መሆኑን እንዳልወደዱለት ይናገራል። ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ከኩኩ ሰብስቤ ጋር እንግዳዬነሽ በሚለዉ የቅብብሎሽ ሙዚቃዉ ቢታወቅም ቢወደድም ከሌላ ሙዚቀኛ በጋራ አብሮ የማዜም እጅግ ፍቅርም እንደሌለዉ ተናግሮአል።
ቀደም ሲል “እዬዬ”; “ማሪኝ ብዬሻለሁ” በተሰኙት ዜማዎቹና “ስቀሽ አታስቂኝ”; “ማን ይሆን ትልቅ ሰው”; “እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ” በሚላቸው ዘፈኖቹ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ አርቲስትም ነው። ለሚስቱና ለልጆቹ ማቆላመጫ “ውዷ ባለቤቴ” የምትል ዜማ ተጫውቷል።
አለማየሁ እስካሁን ድረስ ከ92 በላይ ዜማዎቹ በሸክላ ተቀርጸው 15 ሺህ ያህሉ ተሽጠውለታል። ብቻውን እንዲሁም ከማህሙድ አህመድ ጋርም አብረው በመሆን በመላው አለምም እየዞረ ስራዎቹን አቅርቧል:: ከተለያዩ የውጪ ሪኮርዲንግ ካምፓኒዎች ጋርም ስራዎቹን ሪኮርድ አድርጏል::
እረጅም እድሜ ለአንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ እያልኩኝ በውጭው አለም መድረክ ላይ ቀጥታ የተጫወተውን “አዲስ አበባ ቤቴን” ተዝናኑበት ቸር ይግጠመን::
አለማየሁ እሸቴ ኮሌክሽን
Filed in: Amharic